ሩሲያ ዛሬ ከደቡባዊ ከተማዋ አስትራክሃን አሕጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳኤል (አይሲቢኤም) የተባለውን ረጅም ርቀት ሚሳዔል መተኮሷን የዩክሬን አየር ኃይል አስታወቀ።
አየር ኃይሉ እንዳለው በተለያዩ ዓይነት ሚሳዔሎች በተፈፀመው ጥቃት ዲኒፕሮ ክልል ዒላማ ተደርጋለች።
የክልሉ ኃላፊ በተፈፀመው በዚህ ጥቃት የደረሰው ጉዳት በውል ባይታወቅም ቢያንስ 15 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። ከተጎዱት መካከል የ16 እና የ17 ዓመት ታዳጊዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰው ዘጠኝ ሰዎች በሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ፤ ነገር ግን ስላሉበት ሁኔታ አለመታወቁን የክልሉ ኃላፊ ሴሪይ ሊይሳክ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ሩሲያ ዛሬ ጠዋት ላይ በዲኒፕሮ በፈፀመችው የሚሳኤል ጥቃት የደረሰውን ጉዳት የሚያሳዩ ምሥሎች የደረሱት ቢሆንም ጉዳቱን ያደረሰው የትኛው የሚሳዔል ዓይነት እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
የዩክሬን ድንገተኛ አገልግሎትም በእሳት የተያያዙ የመኖሪያ ሕንጻዎች እና የወደመ የአካል ጉዳተኞች የማገገሚያ ማዕከልን የሚያሳዩ ምሥሎችን አጋርቷል።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዜሌንስኪም ሀገራቸው ‘በአዲስ የሩሲያ ሮኬት’ መጠቃቷን እና ጥቃቱ የተፈፀመበት መሣሪያ አይሲቢኤም የተባለው የባልስቲክ ሚሳዔል ዓይነት ባሕርይ እንዳለው ገልጸዋል።
ሆኖም ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ወደ ዩክሬን የተተኮሰው ሚሳዔል ባሊስቲክ ሚሳዔል እንጂ አሕጉር አቋራጭ ሚሳዔል አይደለም ማለታቸውን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።
ሩሲያ በባልስቲክ ሚሳዔል ጥቃት ፈፅማለች ስለመባሏ የተጠየቁት የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ አስተያየታቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይም ስለጥቃቱ የሰጠው መረጃ የለም።
ሩሲያ ጥቃቱን መፈፀሟ ከተረጋገጠ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈፀመችበት ጊዜ ጀምሮ በአይሲቢኤም ጥቃት ስትፈፅም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም