ቻይና 83 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የወርቅ ክምችት አገኘች

ቻይና 83 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የወርቅ ክምችት አገኘች:: የዓለማችን ቁጥር ሁለት ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው ቻይና አዲስ የወርቅ ማዕድን በሁናን ግዛት አግኝታለች:: እንደ ሽንዋ ዜና አገልግሎት ዘገባ ከሆነ የሁና ጂኦሎጂ ማዕከል ባደረገው የማዕድን ፍለጋ ከ300 በላይ ቶን መጠን ያለው ወርቅ አግኝቷል::

ማዕከሉ ባካሄዳቸው 40 የወርቅ ማእድን ፍለጋ ጣቢያዎች ውስጥ ያደረገው ጥረት ስኬታማ እንደሆነም ተጠቅሷል:: የወርቅ ማዕድኑ በመሬት ውስጥ በ2 ሺህ ሜትር ርቀት ላይ 300 ቶን ወርቅ የተገኘ ሲሆን እስከ 3 ሺህ ሜትር ሲቆፈር ደግሞ የወርቅ ክምችቱ ወደ አንድ ሺህ ቶን ከፍ ሊል እንደሚል በዘገባው ላይ ተጠቅሷል::

አዲስ የተገኘው ወርቅ አሁን ባለው ዋጋ መሠረት ሲሰላ 600 ቢሊዮን ዩዋን ወይም 83 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ነውም ተብሏል:: እኤአ በ2023 ላይ ባለው የዓለም ወርቅ ግብይት መረጃ መሠረት ቻይና ቁጥር አንድ የዓለማችን ወርቅ አምራች ሀገር ነበረች::

በተያዘው ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 741 ሜትሪክ ቶን ወርቅ የተጠቀመች ሲሆን ከዚህ ውስጥ 268 ሜትሪክ ቶን ወርቅ በሀገሯ የተመረተ እንደሆነ ተገልጿል:: የዓለማችን 10 በመቶ ወርቅ አምራች የሆነችው ቻይና በዓለም ገበያ ውስጥ ወርቅ ሸማች ከሆኑ ቀዳሚ ሀገራት መካከልም ዋነኛዋ መሆኗን አል ዓይን ዘግቧል::

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You