ምህረት ሞገስ
የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በሆነችዋ አዲስ አበባ ዋነኛ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ዋነኛው አጀንዳ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖር ሰው በሙሉ ስለቤት ሲነሳ ጆሮውን የማያቆም ቢኖር ጥቂት ሰው ነው። ቤት ሲባል ሁሉም አቤት ይላል። ምክንያቱም በአዲስ አበባ እጅግ ውድና ብርቅ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ቤት ነው።
ቤት ያለው እጅግ ሀብታም እና የሀብታም ሀብታም ነው። ምክንያቱም በየወሩ የሚጨመር የቤት ኪራይ ወጪ የለበትም። በየሁለት ወሩ እና በየሦስት ወሩ ቤት እየለቀቀ ኮተቱን እየጫነ አይንከራተትም። ላለመንከራተት ከታች ድሃ ከሚባለው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ድርጅት እስከ መንግሥት አመራር ድረስ ሁሉም በየትኛውም መንገድ ቤት ይፈልጋል። ለብዙ የከተማዋ ነዋሪዎች ቤት የቀን ቅዠት የሌሊት ህልም ነው።
በጣም አስገራሚው
ነገር፤ ቤት ህልሙ
የሆነው የከተማ ነዋሪ
ቤት የሌለው ብቻ
አይደለም። ቤት ያለውም
ተጨማሪ ቤት ይፈልጋል።
ምክንያቱም ቤት ማለት
ዋነኛው የገንዘብ ምንጭ
ሆኗል። እያገላበጠ እየሸጠ
በየዓመቱ እያተረፈ በቤት
ሽያጭ ብቻ የሚኖረውን
ቤቱ ይቁጠረው። ግማሹ
ሁለትና ሦስት የግል
ቤት ሲኖረው፤ ሌላኛው
የቀበሌ ቤትና የግል
ቤት ይዞ ይኖራል።
በሌላ በኩል ቤት
ቀርቶ መጠለያ የሌለው
አለ። ቤት የሚለውን
መስፈርት የማያሟላ እንደው
በዓለም አቀፍ ደረጃ
ከወጣውና ከሚታወቀው በቤቱ
ውስጥ ምቹ መኝታ
እና ማረፊያን እንዲሁም
ምግብ ማብሰያን የያዘ
ቤት ቀርቶ አንዲት
ክፍል መጠለያ የሌለው
ሰው ቁጥር ቀላል
አይደለም። በየጎዳናው ሸራና
ላስቲክ ወጥሮ ከሚያድረው
ባሻገር በቀበሌ ቤት
ከሰዎች ጋር በጥገኝነት
የሚኖሩም የከተማዋ ሰዎች
ብዛታቸው ቀላል አይደለም።
እነኚህ ሰዎች ማግኘት ካለባቸው በታች በሸራ ቤት የሚኖሩት መጠለያ የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑንና ለአንዳንዶቹም የቀበሌ ቤቶች እየተሰጣቸው እንደሚገኝ ዜናዎች መደመጥ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። እንደሚገለፀው ቤቶቹ በሕገወጥ መልኩ የቀበሌ ቤትን ከያዙ ሰዎች ላይ በመንጠቅ የሚሰጡ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ በብዛት የቀበሌ ቤቶችን የማስለቀቅና የማሸግ ተግባር በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በተለይም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ተበራክቷል የሚል አቤቱታ ቀርቧል። እኛም ባለፈው ሳምንት ዕትማችን ‹‹የተዘጋው የቀበሌ ቤት›› በሚል ርዕስ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 በቤት ቁጥር 286 የምትኖር ግለሰብ ለ30ዓመታት ከኖርኩበት ቤት አላግባብ ተባረርኩ በሚል ያቀረበችውን ቅሬታ እና በቅሬታው ላይም ከወረዳ 2 አስተዳደር የተሰጠውን ምላሽም በማከል አንባቢ ፍርዱን እንዲሰጥ ለንባብ ማብቃታችን ይታወሳል። ለዛሬም የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ የሰጠውን ምላሽ በማከል ይዘን ቀርበናል። በተለይም ከቀበሌ ቤት ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት ወደ አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በርካታ ጥያቄዎች እየቀረቡ ስለሆነ ዛሬ የምናቀርበው መረጃ ለብዙዎች ምላሽ ሊሆን እንደሚችል እምነታችን ነው።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስተዳደርና የክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር የሰጡትን ምላሽ ከማቅረባችን በፊት ቅሬታ አቅራቢዋ ደረሰብኝ ስለሚሉት በደል በቅድሚያ በተወሰነ መልኩ ልናስነብባችሁ ወደድን።
ትዕግስት ታደሰ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 የቤት ቁጥር 286 ከ35 ዓመታት በላይ እንደኖረች ትናገራለች። እንደትዕግስት ገለፃ፤ የአቶ ታደሰ ባለቤት ወይዘሮ እማዋይሽ ሃብቴ እና አቶ ታደሰ ከእናቷ ከፍቅርተ አደፍርስ ተረክበው እሷን ማሳደግ የጀመሩት ክርስትና ከመነሳቷ ማለትም ከተወለደች 80 ቀን ሳይሞላት ነበር። ትዕግስት የልጅነት ጊዜዋን ሁለቱም ወላጅ እናትና አባቷ እንደሆኑ በማመን አሳለፈች። አቶ ታደሰ እና ወይዘሮ እማዋይሽ አሁን ትዕግስት ትኖርበት በነበረው ቤት ውስጥ እየኖሩ ትዕግስትን ተንከባክበው እያስተማሩ አሳደጓት።
ትዕግስት አባቷ ማን እንደሆነ አታውቅም። የምትጠራው በአቶ ታደሰ ስም ነው። የትዕግስት አሳዳጊ ወይዘሮ እማዋይሽም ልጅ የሌላቸው በመሆኑ ትዕግስትን እንደልጅ እየተንከባከቡ አሳደጓት። ነገር ግን በእናትነት ሲያሳድጉ የነበሩት ወይዘሮ እማዋይሽ ሕይወታቸው አለፈ። በአባትነት ያሳደጓት አቶ ታደሰ የወይዘሮ እማዋይሽን ሞት ተከትሎ፤ የእርሷ እናት እማዋይሽ አለመሆኗን እናቷ ፍቅርተ የተባለች የአቶ ታደሰ የራሳቸው እህት መሆኗን ነገሯት።
አቶ ታደሰ የሚስታቸው መሞት ጎዳቸው፤ ኑሯቸውን በብቸኝነት ለመግፋት አልፈለጉም፤ ሌላ ውሃ አጣጭ ሻቱ። ሆኖም ከባለቤታቸው ከወይዘሮ እማዋይሽ ህልፈት በኋላ ሚስት ማግባትን ቢያስቡም ከወይዘሮ እማዋይሽ ጋር ይኖሩበት በነበረበት ቤት መኖር አልፈለጉም። ምክንያቱም ምንም እንኳ ወይዘሮ እማዋይሽ ሆኖላቸው ልጅ ባይወልዱም ትዕግስትን ጨምሮ ሌሎች ልጆችንም አሳድገዋልና የቀበሌ ቤቱን ትዕግስት እንድትኖርበት ሌሎቹም እነርሱ ያሳደጓቸው ወንዶች እንዲያድሩበት ትተውላቸው ከ14 ዓመት በፊት ትዕግስትን ካሳደጉበት ቤት ፊለፊት ቤት ገዝተው ከአዲሷ ሚስታቸው ጋር ልጆች አፍርተው መኖር ጀምሩ።
ትዕግስት አሳዳጊዋ አቶ ታደሰ ተለይተዋት መኖር ሲጀምሩ እርሷ ደግሞ ከወይዘሮ እማዋይሽ ሞት በኋላ ትምህርቷን ለመቀጠል አልጓጓችምና ከ10ኛ ክፍል በኋላ ትምህርቷን አቁማ፤ የውጭውን ዓለም ተጋፍጣ ሕይወቷን ለመቀየር ወደ አረብ አገር አቀናች። ሁለት ዓመታትን ካሳለፈች በኋላ አዕምሮዋ ሲታወከ ወደ አገሯ ብትመለስም በቀላሉ አልዳነችም። በህክምናውም በፀበልም ስትል ቆይታ፤ እየተሻላት ጤናዋ ላይም ለውጥ እየታየ ሲመጣ በተለምዶ የአርከበ ሱቅ ተብሎ የሚጠራውን ሱቅ ተከራይታ ፀጉር ሹሩባ እየሰራች በምታገኘው ገቢ መኖር ጀመረች። ሲያማት ቤተክርስቲያን ሲሻላት ሥራዋን እያለች ኑሮዋን በዚያው በቀበሌ ቤት ውስጥ ዓመታትን አሳለፈች።
ከአንድ ዓመት በፊት አቶ ታደሰ አረፉ። ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ አሁን ላይ በአቶ ታደሰ ስም የተመዘገበው የቀበሌ ቤት ትዕግስት ለ35 ዓመታት ብትኖርበትም መልቀቅ አለብሽ ተባለች። በአቶ ታደሰ የተገዛው የግል ቤት ከአዲሷ ሚስታቸው የወለዷቸው ልጆችና ባለቤታቸው መኖራቸውን ቀጥለዋል። ትዕግስት የሚረዳት የለም። ከልጅነቷ ጀምሮ አብረዋት ከኖሩት ጎረቤቶቿ ጋር በምታገኘው ገቢ ያላትን እየተቃመሰች የሕይወት ጉዞዋን ብትቀጥልም፤ አሁን ላይ የዚያ ቤት እህል ውሃሽ አብቅቷል ተባለች።
በዚህ የቀበሌ ቤት ስትኖር የመኖሪያ ቤት ኪራይ በአሳዳጊዋ በአቶ ታደሰ ስም እየከፈለች ቆይታለች። በቀበሌው ነዋሪ በመሆኗም በቤት ቁጥሩ ቅፅ ውስጥ ስሟ የተካተተ ከመሆን አልፎ፤ በቤት ቁጥሩ መታወቂያ አውጥታ እንደማንኛውም የቀበሌ ነዋሪ የሚሰጠውን አገልግሎት በሙሉ በማግኘት ላይ ትገኛለች። ታኅሣሥ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ግን ከወረዳ እርሷን ከቤቷ ለማስወጣት የተዘጋጀ ግብረ ኃይል ቤቱን ሊያሽገው መሆኑን ገልፆ፤ ዕቃዋን እንድታወጣ አስጠንቅቋታል።
ትዕግስት እንደምትለው አማራጭ ያልነበራት በመሆኑ ንብረቴ የምትለውን ዕቃ በሙሉ ከጎረቤቶቿ ጋር ተጋግዛ አውጥታ ደጃፉ ላይ አስቀመጠች። በግብረኃይሉ ቤቱ ታሸገ። በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ሄዳ አቤት አለች። ምላሽ የሰጣት አልነበረም። መልሱ ወደ ፊት ይታይልሻል የሚል ብቻ ነበር። ቤቱም ለማንም ሳይሰጥ ቀናትን ብቻ ሳይሆን ሳምንታትን እያለ ወራትን እያሳለፈ ለእርሷም ለሌላም ሳይሰጥ እነሆ ዛሬ ላይ ደረሰ። ሦስተኛው ወር አልፎ አራተኛ ወሩን ያዘ።
ትዕግስት አሁን ጎዳና ላይ ወጥታለች። በቤቱ ደጃፍ ላይ ምንጣፍና ሸራ ወጥራ ዕቃዋን ሸፍና ታድራለች። አርከበ ሱቅ ተከራይታ ሹርባ ሰርታ ስትተዳደር፤ ኑሮዋ ከእጅ ወደ አፍ ነው። ሱቅም ተከራይታ ቤትም ተከራይታ በሹሩባ ሥራ በልታ ማደር የሚታሰብ አይደለም። አንዳንዴ ሥራም እየቀረች ሲጨንቃትና ህመሙ ሲብስባት ፀበል ትሄዳለች። ኑሮ እንዲህ ለከበደባት ትዕግስት ቤት የተነጠቀችው ምን ያህል ከእርሷ የባሰበት ተገኝቶ ነው በማለት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 አስተዳዳሪዋን ማረግነሽ ደምሴን ጠይቀናል።
የወረዳው አስተዳዳሪዋ እንደተናገሩት፤ በወረዳው በጣም ብዙ የቤት ጥያቄዎች አሉ። የድህነት መጠኑ በጣም የሰፋ እና ካሉት ክፍለከተሞች ውስጥ የማህበረሰቡ አኗኗር እጅግ በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ በመሆኑ በጣም እገዛ የሚያስፈልገው ወረዳ ነው። ስለዚህ የቤት ጥያቄዎችን ለመመለስ በተቻለ አቅም በሕገወጥ መንገድ የተያዙ ብዙ ቤቶች እየተለቀቁ የድሃ ድሃ ለሆኑ ሰዎች እየተሰጡ ነው። በእርግጥ ቤቱን ከማስለቀቁ ጋር ተያይዞ ብዙ ቅሬታዎች እየቀረቡ ናቸው። በተለይ ድሃ ሆነው ያለአግባብ የያዙ ሰዎች ‹‹ለምን እንድንለቅ ተገደድን›› የሚል ቅሬታ አላቸው። ለምሳሌ ጥገኛ ሆነው ሲኖሩ ቆይተው የቤቱ ተከራዮቹ ሲሞቱ ወይም የጋራ መኖሪያ ቤት ሲደርሳቸው እንዲሁም በተለያየ አጋጣሚ ሲለቁ ጥገኛ ሆነው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች፤ የቀበሌ ቤቱን በስማቸው ኪራይ ሲከፍሉበት የነበሩ ሰዎች ዘመዶች ወይም ባዳ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ቤቱን እንደያዙ ይቀመጣሉ። ይህ ሕገወጥ ነው። እነርሱ እንዲለቁ ይደረጋል። አሁንም በዚያው መልኩ እየተደረገ ነው።
እንደአስተዳዳሪዋ ገለፃ፤ መጀመሪያ ሕግ መከበር አለበት። ሰዎች ሊገዙ የሚገባው በሕግና በአሠራር ነው። መመሪያ ካልተጠበቀ ሕገወጥነቱ ይሰፋል። ጉልበተኛው ብቻ እየኖረ ይቀጥላል። ስለዚህ ለረዥም ጊዜ ውል ያላደሱ፤ የቤት ኪራይ ከፋዮቹ የጋራ መኖሪያ ቤት የደረሳቸው ሆነው ከተቀመጡ፤ ለረዥም ጊዜ በቤቱ ያልኖሩ እና በጥገኞች የተያዙ እንዲለቁ እየተደረገ ነው።
ነገር ግን በወረዳ 02 ብቻ ሳይሆን በክፍለከተማ ደረጃ በ10ሩም ወረዳዎች ሕጋዊም ሳይሆኑ ቀርተው በጣም በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሕጋዊ ባይሆኑም የሚታዩበት ሁኔታ ቢኖር መልካም ነው በሚል በክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ በኩል አቅጣጫ ወርዷል። ስለዚህ ወደ ሕጋዊነት የሚመጡበት ሁኔታ እየተጀመረ ነው።
በተመሳሳይ መልኩ አቤቱታ አቅራቢዋ ትዕግስት ታደሰም የሚታይላት በዚሁ መልኩ መሆኑን በመጠቆም፤ ነገር ግን በማለት ከትዕግስት ሕይወት ጋር ተያይዞ የቤቱን ሁኔታ በሚመለከት ከመመሪያ ውጪ የተፈፀመ አንድም ድርጊት አለመኖሩን ያብራራሉ። አንድ የቀበሌ ቤት ተከራይቶ የሚኖር አባወራ እና እማወራ በራሱ ስም የጋራ መኖሪያ ቤት ከደረሰው ወይም መኖሪያ ቤት ከገዛ የግድ ቤቱን ለመንግሥት ማስረከብ እንዳለበት ያዛል። ይህ መመሪያ ብቻ ስለሆነ ሳይሆን ሃሳቡም ትክክል ነው። ምክንያቱም ብዙ በባሰ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የቀበሌ ቤት ጥያቄ አቅርበው ወረፋ እየጠበቁ ባሉበትና የቤት ችግር ጣራ በነካበት በዚህ ጊዜ፤ የትዕግስት አባት አቶ ታደሰ ቤት መግዛታቸው እየታወቀ ለእነርሱ ቤተሰብም ሆነ ለቤተሰባቸው ቤት መሰጠቱ ፍፁም ፍትሃዊነት የጎደለው ነው ይላሉ።
ትዕግስት ትኖርበት የነበረው ቤት የተያዘው በአቶ ታደሰ ስም ነው። አቶ ታደሰ ደግሞ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ካርታ ያለው ቤት ገዝተዋል። እርሳቸው ከተከራዩት የቀበሌ ቤት ወጥተዋል በማለት የወረዳው አስተዳዳሪ ይናገራሉ።
እዚህ ላይ ተበዳይነኝ ባይ ትዕግስት እንደምታስረዳው፤ በትክክል አቶ ታደሰ አባቷ አለመሆኑን ከፍርድ ቤት አስመስክራ ለወረዳው ማስረጃ ሰጥታለች። በተጨማሪ አቶ ታደሰ ቤት ከገዙ በኋላም ለ14 ዓመታት ትዕግስት በዛ ቤት ኖራለች።
አስተዳዳሪዋ እንደሚስረዱት፤ ትዕግስትም ሆነች ከእርሷ ጋር ተመሳሳይ ጉዳይ ያላቸው ሰዎች ጥያቄያቸው ምላሽ የሚገኘው በመመሪያ እና በአሠራር ብቻ ነው። ሁሉም በየደረጃው በልኩ የሚታይ ይሆናል።
በመመሪያ ላይ አንድ የቀበሌ ቤት ተከራይቶ የሚኖር አባወራ እና እማወራ በራሱ/ሷ ስም የጋራ መኖሪያ ቤት ከደረሳቸው ወይም መኖሪያ ቤት ከገዙ የግድ ቤቱን ለመንግሥት ማስረከብ እንዳለባቸው ያዛል። የቀበሌ ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ሰዎች ሲለቁ ቤቱን ሲያስረክቡ ጥገኞቹም አብረው ይለቃሉ። ጥገኞችም ሆኑ የቤት ተከራዮቹ ልጆች ተወልደው አድገው እዛው ስለኖሩ ብቻ ሳይሆን፤ ምንም ዓይነት የሚተዳደሩበት ገቢ የሌላቸውና ቤተሰባቸው የተሻለ ገቢ የሌላቸው ከሆነ ቤቱም የተለቀቀው በአስቸጋሪ ሁኔታ ማለትም ለምሳሌ ተከራዩ ከሞተ እና የእርሱ ልጆች የሚኖሩበት ከሌላቸው እንዲወጡ የማይገደዱበት ሁኔታ መኖሩን ያስረዳሉ።
እንደአስተዳዳሪዋ ገለፃ፤ የትዕግስት ጉዳይ ሲታይ ግን አቶ ታደሰ ማለት ገንዘብ ያላቸው በመሃል ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሰባተኛ አካባቢ ውድ የሆነ የመሬት ግዢን መፈፀም የቻሉ ሰው ናቸው። እርሳቸው የቀበሌ ቤት እንዲይዙ አይበረታታም። ነገር ግን ትዕግስትም በእርግጥ የቀበሌ ቤት ተመዝግቦ እየጠበቀ ካለው ሰው በላይ ችግር አለባት ወይ የሚለው የሚታይ ይሆናል ይላሉ።
እዚህ ላይ አቤቱታ አቅራቢዋ ትዕግስት አሳዳጊዋ አቶ ታደሰ ቤቱን መግዛታቸው እሙን ቢሆንም፤ የሞቱት ሕፃናት ልጆችን ትተው ነው። አቶ ታደሰ በገዙት ቤት ውስጥ የሚኖሩት የእርሳቸው ባለቤትም ልጆቹን እያሳደጉ ያሉት እንጀራ ጋግረው በመሸጥ መሆኑን በመጥቀስ፤ አስተዳዳሪዋ የአቶ ታደሰን ሀብት እና አኗኗር የገለፁበት ሁኔታ የተሳሳተ መሆኑን ታስረዳለች።
አስተዳዳሪዋ ግን ይቀጥላሉ፤ በእርግጥ መመሪያውን ለማስፈፀም ወደ ታች ሲወረድ የሚያጋጥሙ ብዙ ነገሮች አሉ። ወረዳው በተቻለው መጠን ችግሩን ለመፍታት ጥረት ያደርጋል። ስለዚህ ትዕግስትም ሆነች ሌሎች ሰዎች ያሉበት ሁኔታ እየታየ እየተፈተሽ ማስተካከያ ሊደረግላቸው የሚገቡ ካሉ በተቻለ አቅም ጥረት ከማድረግ ወደ ኋላ የማይባል መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደአስተዳዳሪዋ ገለፃ፤ መመሪያዎች በጣም እየተሻሻሉ ነው። ነገር ግን መመሪያ ቢያግድም ደግሞ ከከተማ አስተዳደሩ የሚላኩ ማሻሻያዎች (ሰርኩላሮች) አሉ። መመሪያው ቢልም ከከተማዋ ነዋሪዎች ችግሮች አንፃር ታይተው የተገናዘቡ ሁኔታዎችን እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም መሠረት በማድረግ እየተሰራ ነው። በተለይ ግን የቀበሌ ቤት ተወልደው አድገው በቤተሰባቸው ቤት ራሳቸውም ጋብቻ ፈፅመው ልጆች ወልደው የሚኖሩ ሰዎች እየታየላቸው ነው።
አስተዳዳሪዋ በወረዳው በኩል የኅብረተሰቡን ጥቅም በማስከበር ሰዎች በደል እንዳይደርስባቸው ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፀው፤ የትዕግስት ችግርም በልኩ ታይቶ ውሳኔ የሚሰጥበት መሆኑን ነግረውናል። ነገር ግን ከእርሳቸው ጋር ቃለመጠይቅ ባደረግን ማግስት ማለትም መጋቢት 28 ቀን 2013 ጠዋት ትዕግስት ሸራ ወጥራ በፊት ትኖርበት ከነበረው ከቤቱ ደጃፍ በግብረ ኃይል እንድትነሳ የማስገደድ ተግባር መፈፀሙን እና ዕቃውም ተጭኖ ሊሄድ ሲል የአካባቢው ኅብረተሰብ ተቃውሞ በማሰማቱ እና ተበዳይ ነኝ ባይዋ ትዕግስት ከዕቃው ጋር እኔም እጫናለሁ ብላ እያለቀሰች በመጮኋ ሳይነሳ መቅረቱን ለማወቅ ችለናል። አሁንም ድረስ ትዕግስት በቤቷ ደጃፍ በጎዳናው ላይ ሸራ ወጥራ በመኖር ላይ መሆኗን ስንረዳ ደግሞ ጉዳዩን ይዘን ወደ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አመራን።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ውቢት ዲንቃ እንደገለፁት፤ በሦስተኛ ወገን በሕገወጥ የተያዙ ቤቶችን የማስለቀቅ ሥራ እየተሰራ ነው። የግል ቤት ሰርተውም ሆነ በተለያየ መልኩ ቤት አግኝተው እነርሱ ግን በሕጉ መሠረት የቀበሌ ቤቱን ለመንግሥት ከማስረከብ ይልቅ አከራይተው የሚኖሩ ሰዎች አሉ። እንደዚህ ዓይነት ሕገወጥ ሰዎች ቤቱን እንዲለቁ በማድረግ በከንቲባዋ አማካኝነት 201 ቤቶች ለሚገባው ለድሃ እንዲሰጥ ተደርጓል። እንደዚህ ዓይነት ሕገወጦች በእርግጥም እንዲለቁ እየተደረገ ነው።
ትዕግስት ታደሰ ወደ ክፍለከተማ በመምጣት እርሳቸው ጋር አለማመልከቷንና ጉዳዩን እንደማያውቁት በመግለፅ፤ ነገር ግን 14 ዓመት በቤቱ ውስጥ ከኖረች በ2011 በወጣው የቀበሌ ቤት መመሪያ መሠረት ለአምስት ዓመታት በቤቱ ውስጥ የኖረ ሰው በዚያ ውስጥ ተካቶ በቤቱ የመጠቀም መብት ይኖረዋል ስለሚል በዚያ ውስጥ መካተት እንደምትችል ይናገራሉ። የጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ እንደሚገልፁት፤ ነገር ግን ይህን ያህል ሲቆዩ የቤቱን ኪራይ ክፍያ መፈፀም ያለባቸው በራሳቸው ስም መሆን አለበት። በሌላ ሰው ስም ከሆነ የሚታወቀው በስሙ ኪራይ እየተከፈለበት ያለው ግለሰብ በመሆኑ ግለሰቧ የማግኘት መብት የሌላቸው መሆኑን ያብራራሉ። ነገር ግን ምንም ገቢ ከሌላት በአደረጃጀት ተተችተው በሕዝብ ታይቶ የሚስተናገዱበት ሁኔታ እንደሚኖር ያብራራሉ።
በሌላ በኩል በቤቱ ውስጥ ልጅ ወይም እንደልጅ ያደገ ግለሰብ የወራሽነት ማረጋገጫ ካመጣ ቤቱን የሚገኝበት ዕድል መኖሩን በማስታወስ፤ ትዕግስት ወይም የወራሽነት ማረጋገጫ ካመጣች የሚታይበት ሁኔታ መኖሩን እና ነገር ግን ትዕግስት የወራሽነት ማረጋገጫም ሆነ የይገባኛል ጥያቄን ይዛ ወደ ከፍለ ከተማው አለመምጣቷን ጠቁመዋል። መዘንጋት የሌለበት ግን አሰራሩ በሙሉ መመሪያን መሠረት ያደረገ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።
የወረዳ 2 አስተዳዳሪ ያነሱትን ሃሳብ በማስታወስ፤ በእርግጥ ቤቶቹ የሚለቀቁት ለድሃዎች ለመስጠት ነው። ነገር ግን የባሰ ድሃም ጎዳና ላይ ይውደቅ የሚል አቋም የለም። ስለዚህ ያለችበት ሁኔታ ታይቶ ችግሩ የሚፈተሽበት ሁኔታ አለ። ነዋሪ ከሆነች፣ የአካባቢው ነዋሪና አደረጃጀቶች ካወቋት፤ ምንም ገቢ እንደሌላት ከተረጋገጠ ተተችታ የወረዳው ካቢኔ አፅድቆ ከላከ የክፍለከተማው ፕሮሰስ ካውንስል አፅድቆ ምላሽ የሚሰጣት ይሆናል ይላሉ።
በመመሪያ 5/2011 መሰረት ቤት ውስጥ የቤቱ ተከራይ የጋራ መኖሪያ ቤት ደርሶት ወይም ቤት ሰርቶ ከሄደ፤ ነገር ግን ከቤት ተከራዩ ጋር አብሮ ቤተሰብ መስርቶ የሚኖር ሰው ካለ ምንም ገቢ ከሌለው በአደረጃጀት ተተችቶ ችግሩ ሊታይለት እንደሚችል ተቀምጧል። ነገር ግን በዚህ መልኩ ለማለፍም ተበደልን ባዮቹ ከወረዳውም ሆነ ከክፍለ ከተማው ጋር መገናኘት አለባቸው።
‹‹በቤቱ ውስጥ ተወልዶ አድጎ ቤተሰብ ያፈራና ልጅ የወለደ እንዲሁም ገቢ የሌለው ነው።›› ብሎ የቀጠና አደረጃጀት ሃሳብ ከሰጠበት በኋላ የወረዳው ካቢኔ አይቶ ለክፍለከተማው ይልካል። ክፍለ ከተማው ደግሞ በፕሮሰስ ካውንስል አስፀድቆ መልሶ ለወረዳው በመላክ ግለሰቡ ቤት የሚያገኝበት ሁኔታ የሚፈጠር መሆኑንም ነው የጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ የሚናገሩት።
እንደኃላፊዋ ገለፃ በዚያው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ውስጥ ሚስት የሞተችበትን አንድ ግለሰብ ምንም እንኳ በሕገወጥ መልኩ ቤት የያዘ ቢሆንም፤ ግለሰቡ በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆኑ ተረጋግጦ መፍትሔ እንዲሰጠው ተወስኗል። ስለዚህ አሁንም በመመሪያው መሠረት ትዕግስት ታደሰም የምትታይበት ሁኔታ እንደሚኖር ይገልፃሉ።
በእርግጥ መረሳት የሌለበት የተሻለ ገቢ እና ቤት እያላቸው ቤቱን አንለቅም ብለው የሚያስቸግሩ መኖራቸውን በመጠቆም፤ ሰዎች ቤት አጥተው ጎዳና ላይ በላስቲክ ቤት ውስጥ የሚያድሩትን ማሰብ እንደሚኖርባቸው በመግለፅ፤ በእነርሱ በኩል አሁን እየተሰራ ያለው ፍትሃዊነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው ብለዋል። በተለይ ወረዳ 9 ላይ በዝናብ ቤት አጥተው ጎዳና ላይ ወድቀው በብርድ የሚሰቃዩትን ሰዎች የመታደግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ።
የጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ በመጨረሻም ክረምት ላይ በዝናብ ቤት አጥተው እየተሰቃዩ ያሉ ሰዎች ቤት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑንና ይህንንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ያመለከቱት።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም