ፀገነት አክሊሉ
የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለሥልጣን በአገሪቱ የጨረራ አመንጪዎችን አጠቃቀምና ተያያዥነት ያላቸው ተግባራትን እንዲቆጣጠር እና እንዲከታተል በአዋጅ 1025/2009 ዓ.ም በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ከጨረራ ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ በርካታ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከልም ስለጨረራ ምንነት፣ በተለያየ ዘርፎች የሚሰጠውን ጥቅም እንዲሁም በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋሉ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጉዳት እና መከላከያቸውን በተመለከተ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራት ይገኝበታል፡፡
እኛም ከተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ከአቶ ሰለሞን ጌታቸው ጋር የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለሥልጣን ተግባርና ሃላፊነት እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለሥልጣን በሕግ የተሰጠው ሥልጣንና ሃላፊነት ምንድን ነው?
አቶ ሰለሞን፦ ባለሥልጣኑ ከዋነኛው ሥራው ብንጀምር የጨረራ የራዲየሽንና የኒውክለር ቴክኖሎጂን በአገራችን ላይ በጤናው፣ በግብርናውና በኢንዱስትሪው ላይ ያሉ ችግርችን ለመፍታት የሚያስችል፤ አንዳንድ ጊዜም በብቸኝነት የሚመረጥ ቴክኖሎጂ ነው።
ይህ ቴክኖሎጂ እነዚህን ችግሮቻችንን ለመፍታት እንዲያስችለን ስንጠቀምበት በአግባቡ መጠቀም ካልቻልን ከሌሎች ቴክኖሎጂዎች ሁሉ በተለየ ሁኔታ የጎንዮሽ ጉዳቱ በጣም የከፋ ነው። በሌላ በኩልም ቴክኖሎጂው ወደ አገር ከገባበት ጊዜ ጀምሮ አገልግሎቱን ጨርሶ እስከሚወገድ ድረስ በቁጥጥር ሥርዓት ውስጥ ማለፍ ስለሚያስፈልገው የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለሥልጣን ይህንን ሥራ በሃላፊነት ይሠራል።
በዚህም መሰረት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ያለው ድርሻ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች አገልግሎት ላይ ሲውሉ በአካባቢውና በህብረተሰብ ላይ አሉታዊ ወይም ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳያሳርፉ የቁጥጥር ሥርዓቱን ዘርግቶ ያንን የመከታተል ሥራ ደግሞ ከተግባራቱ ዋናው ነው።
አዲስ ዘመን፦ ከዚህ አንፃር ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እስከ አሁን ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት ምን መልክ አላቸው?
አቶ ሰለሞን፦ በዋናነት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሚሠራው ሥራ ይህ ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ የማስገቢያ ፍቃድ መስጠት፤ ወደ አገር ከገባም በኋላ ደግሞ የተግባር ፍቃድ መስጠት ነው። እነዚህ ፍቃዶች ሲሰጡ አስገቢዎች ሊያሟሏቸው ግድ የሚሆኑ መስፈርቶች አሉ፡፡ እነሱን አሟልቶ የተገኘ ደግሞ ፍቃድ ይሰጠዋል።
ካስገባ በኋላም የተግባር ፍቃድ የምንለውን እንዲያገኝ ሥራውን ለመሥራት የሚያስችለው ብቁ የሆነ ባለሙያ መኖሩን አረጋግጠንና ሌሎች መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ዝግጅቶች ተመልክተን የሥራ ፍቃድ እንሰጣለን። ይህንን እየሠራ እያለ ደግሞ በተሰጠው ፍቃድ መሰረት አገልግሎቱን እየሰጠ መሆኑን የማረጋገጥ የቁጥጥር ሥራ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይሠራል። በተለይም የቁጥጥር ሥራ ክፍሉ እየተዘዋወረ ቁጥጥር የሚያደርግ ሲሆን በተሰጠው ፍቃድ መሰረት ሠርቷል አልሠራም የሚለው ይታያል፤ ከተፈቀደለት ውጭ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሕግን ወደ ማስፈፀም ሥራ ይገባል።
የሕግ ማስፈፀም ሥራው ሂደት ውስጥ ተጠያቂ የማድረግ ሂደቶች ያሉ ሲሆን በዚህም በጣም ቀላል ከሆኑ እርማቶች እስከ መጨረሻው ፍቃድን እስከ መንጠቅ ድረስ የሚሄድ ነው። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይህንን ተግባር ለመፈፀም የአምስት ዓመት ዕቅድ ይኖረዋል፤ ከዛ ተነስቶ ደግሞ በየዓመቱ የሚታቀዱ ሥራዎችም አሉት፤ በመሆኑም በዓመት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለምን ያህል ፍቃድ ጠያቂዎች ፍቃድ ይሰጣል? የሰጠውንስ በምን ያህል መጠን ይቆጣጠራል? እና የሕግ ማስከበር እርምጃን ይወስዳል? የሚለውን በዕቅድ አውጥቶ ነው የሚንቀሳቀሰው።
ይህንን የቁጥጥር ሥራ ለማዘመን የሚያስችል የምርምርና የጥናት ክፍል ስላለ ሥራውን ዘመናዊና ቀልጣፋ አድርጎ ለመሥራት እየተሞከረ ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ ለቁጥጥር ሥራ የሚኬድባቸው ቦታዎች ወይ የህክምና መስጫ ናቸው አልያም ኢንደስትሪዎች ናቸው። ለምሳሌ የህክምና ዘርፉን ብናይ በየተቋማቱ ውስጥ ያሉ ሲቲ ስካን፣ ራዲዮግራፊ፣ ራጅ፣ ማሞግራፊና ሌሎችም መሣሪያዎች ጨረራን የሚጠቀሙ በመሆኑ እነዚህን መሣርያዎች ተጠቅሞ አገልግሎት የሚሰጠውም ሰው ሆነ ህመምተኛን የሚያመጣው አስታማሚ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ስለሚያስፈለግ ተቋማቱ ሥራቸውን ከዚህ አንፃር እየሠሩ ስለመሆናቸው በቁጥጥር ሥራችን እናያለን።
አዲስ ዘመን፦ እዚህ ላይ የቁጥጥር ሥራችሁን በምን ዓይነት ሁኔታና በምን መልኩ ነው የምታከናውኑት?
አቶ ሰለሞን፦ እንግዲህ አንዳንድ መሣሪያዎችን በየዓመቱ የምናይበት ሁኔታ ሲኖር ሌሎቹ ደግሞ በሁለት አልያም በአራት ዓመት ሊታዩ የሚገባቸውም አሉ። ይህ አይነቱ ምደባ ደግሞ ዓለም አቀፍ አሰራር ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ መሣሪያዎቹ የሚያመነጩት ጨረር የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በሆኑት ላይ የቁጥጥር ሥራው ከፍ ያለ ሲሆን ቶሎ ቶሎም ይታያሉ፤ የጉዳት መጠናቸው ዝቅተኛ በሆኑት ላይ ደግሞ እንደዛው የቁጥጥር ሥራው ራቅ ባለ ጊዜ ሊሆን ይችላል።
አዲስ ዘመን፦ የቁጥጥር ሥርዓቱም ዓለም አቀፍ መርሆዎችን የተከተለ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ግን ደግሞ እነዚህ መሣሪያዎች የሚያመነጩት ጨረር እስከሆነ ድረስ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ ወይም ዝቅተኛ ብለን የምንለው በምን መስፈርት ነው?
አቶ ሰለሞን፦ ለምሳሌ የጥርስ ህክምና ራጅን ብንወስድ ይህ መሣሪያ የሚጠቀመው ጨረር በጣም ትንሽ ነው፤ በዚህ ምክንያትም መሣሪያው ፍተሻ የሚደረግበት በየአራት ዓመቱ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የካንሰር ህክምና መስጫው ጨረር ደግሞ አደገኝነቱ በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ በመሆኑ ይህንን መሣሪያ በአግባቡ ካልተጠቀምን ብሎም በየዓመቱ ፍተሻ ካላደረግንበት ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። ሌሎችም በየሁለት ዓመቱ የሚደረጉም አሉ፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ ሲባልና ዝቅተኛ ሲባል የሚለዩት በዚህ ሁኔታ ነው ።
አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ በሚያደርገው የቁጥጥር ሥራ ላይ የተገኙ ችግሮች አሉ? እንዲሁም በጥንቃቄ ጉድለት የደረሱ ጉዳቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ሰለሞን፦ ለምሳሌ እነዚህ የጨረራ መሣሪያዎች ባሉበት ቦታ ላይ በሮች አካባቢ እንዲቀመጡ የሚገደዱ ዓለም አቀፍ ሰምምነቶችም የሚያስገድዳቸው ምልክቶች አሉ፤ እነዚህ ምልክቶች በተለጠፉባቸው በሮች አካባቢ ደግሞ የጨረራ ቁስ አለ ማለት መሆኑ መታወቅ አለበት። በመሆኑም ሁሉም ሰው ከዚህ ጨረር መጠበቅ ስለሚኖርበነት ፍቃድ ሳያገኙ ዝም ብሎ ወደ ክፍሎቹ መግባት ራስን ለአደጋ ማጋለጥ መሆኑም መታወቅ አለበት። በመሆኑም አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማት በሙሉ ይህንን ምልክት እንዲለጥፉ ይገደዳሉ። አንዳንዶች ግን በግዴለሽነት ሳይለጥፉ የመቅረት ሁኔታዎች ይታያል።
በሌላ በኩል ደግሞ የክፍሉ ሠራተኛ የሆነው ባለሙያ በደረቱ ላይ ሊለጥፋት የሚገባ ባጅ አለች፤ እሷን ማድረግ ይጠበቅበታል። ከማድረግም ባለፈ በየወቅቱ ማስነበብም መቻል አለበት። ይህ የሚሆነው ደግሞ ባለሙያው በጨረር አመንጪው ቁስ ምን ያህል ተጠቅቷል? የሚለውን ለማየት ሲሆን ረጅም ዓመት በቦታው ላይ በሚሰጠው አገልግሎት ተጠቅቶ ከሆነ ለእርሱ ደህንነት ሲባል ከሥራው እንዲርቅ መደረግ አለበት። በመሆኑም ይህ እየተሰላ ከተቀመጠው ጊዜ በልጧል አልበለጠም የሚለውን የምናውቀው በዛች ካርድ መሰረት ነው። በመሆኑም ይህ ባጅ ለባለሙያው የሥራ ላይ ደህንነት ማረጋገጫ በመሆኑ አንዱ መስፈርት ቢሆንም ባለፈቃዶቹ ገዝተው እንኳን ቢያቀርቡ በባለሙያው በኩል መዘናጋት ይታያል በሌላ በኩል ደግሞ ተቋማቱም ለጉዳዩ ትኩረት በመንፈግ ባጇን ገዝቶ ያለማቅረብና መዘናጋቶች ይታያል።
በቀደመው ጊዜ ለመዘናጋቱ አንዱ ምክንያት የነበረው ባጇን የሚያነብ ባለሙያ በአገር ውስጥ አለመኖሩ ነበር፤ አሁን ግን ይህንን ባጅ በአግባቡ ሊያነብ የሚችል የግልና የመንግሥት ተቋም ተፈጥሯል። በመሆኑም አሁን ላይ ይህንን ባጅ በትክክል ማድረግ ጊዜው ሲደርስም ማስነበብ ለራስ ደህንነት ከፍተኛ የሆነ ጥቅም አለው። ህጉም ያስገድዳል።
ለምሳሌ ምስል የሚያወጣው ራጅ የሚፈልገውን ምስል ካላገኘ ሐኪሙ ለማንበብና ተረድቶም ታማሚው የሚያስፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ ይቸገራል፤ በመሆኑም አልታየኝም ድጋሚ ይነሳ ይላል፤ ግን ደግሞ ድጋሚ ይነሳ ሲባል ታማሚውን ለተጨማሪ ጨረር እያጋለጥነው ነው፤ በመሆኑም መጀመሪያ መሣሪያው በትክክል ምስሉን መውሰድ አለመውሰዱን ማረጋገጥ በየጊዜው ጥገና ማድረግ የሚያስፈልገው ከሆነም ያንን መሥራቱ አስፈላጊ ነው። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም ቁጥጥር የሚያደርገው አንድም ይህንን ነው።
በሌላ በኩልም መሣሪያው የሚተከልበት ቦታ ሊኖረው የሚገባው ስፋት እንደ መስፈርት ተቀምጧል፡፡ በዛ መሰረት ነው መተከልም ያለበት፤ ይህ ብቻ አይደለም፤ መስኮቱ በሮቹ ላይ ጨረር አፈትልኮ ወደውጭ እንዳይወጣ በሚያደርግ መልኩ “በሊድ” መለበድ አለበት። ይህ የማይሆንና በተለይም በርና መስኮቶቹ ትንሽ ክፍተት እንኳን ካላቸው በሽተኛው ጋር በሚፈለገው መጠን ቢወጣም ከዛ ውጭ ያለው ግን በአካባቢው ላይ ያለውን ሰው ይጎዳል። በመሆኑም ለሌላው ማህበረሰብ ደህንነት በሮቻችንን መስኮቶቻችን በሚፈለገው መስፈርት መሰረት መሰራታቸው መረጋገጥ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ በዚህ የቁጥጥር ሥራ ግን ጉድለቶች ሲገኙ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እርምጃ የመውሰድ አቅሙ ምን ያህል ነው? እስከ አሁንስ እርምጃ የወሰደበት አግባብ እንዴት ይገለፃል?
አቶ ሰለሞን፦ የቁጥጥር ሥራችን በዋናነት አስተማሪ እንዲሆን ነው የምንፈልገው፤ ከቁጥጥር ሥራው ጋር ተያይዞ እርምጃ የመውሰድ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እንዲሁም ቅደም ተከተል (ፕሮሲጀር) አለ፤ ይህ እንግዲህ ምን ዓይነት የሕግ ጥሰቶች እየተፈፀሙ ነው ለሚለው በዝርዝር ተቀምጧል፤ በተጨማሪም ቀላሎቹ ከባዶቹ መካከለኞቹ ጥፋቶችስ ምንድን ናቸው? የሚለውም እንደዛው፤ በተጨማሪም ምን ዓይነት ጥፋቶች ወይም መተላለፎች ሲፈጠሩ ምን ዓይነት ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል የሚሉትም በዝርዝር ተቀምጠዋል።
በመሆኑም ተቋማቱ በሚፈተሹበት ወቅት አንዳንድ ጥፋቶች ሲያጋጥሙ የባለስልጣኑ ተቆጣጣሪዎች እዛው በቃል አስጠንቅቀዋቸው ከሚመጡት ጀምሮ ተቋማቱን እስከ ማሸግ የሚደርስ እርምጃ የመውሰድ ሃላፊነት አለበት። በዚህ ሂደት ውስጥ በቃል የምናስጠነቅቃቸው የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የሚሰጣቸው በጣም ብዙ ናቸው፤ ከዚህ ውጭ ግን የማሸግ ሁኔታዎች ላይ ስንመጣ በተለይም በተደጋጋሚ ቀላል ጥፋቶችን እየፈፀሙ ሳይማሩ የሚቀሩ ተቋማት ላይ ስህተቶቹ ተጠራቅመው ወደከባድ ይዞሩና እስከ ማሸግ ድረስ እርምጃ ወስደንባቸው ከ15 እስከ 30 ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ ታርመው ወደ ሥራ የገቡ አሉ።
በሌላው ጎን ደግሞ ማስተካከል አቅቷቸው ጉዳያቸው ወደፍርድ ቤት የሄደም እንደዛው አሉ። ነገር ግን ፍርድ ቤት ላይ ያለው ሂደት መጓተቱና ሌላውም ሌላውም ነገር ገዘፍ ስለሚል ውጤታማነቱ ላይ ትንሽ ክፍተት አለ። በነገራችን ላይ በሥራቸው ውስጥ ክፍተት እያለ መሥራት የለባቸውም ብለን ያሸግናቸው በጣም ብዙ ተቋማት አሉ። አሻሽለው ሲመጡም ሥራውን ይቀላቀላሉ።
በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ህብረተሰቡንም ማሰብ የሚጠይቀን ጊዜ ብዙ ነው፡፡ አንዳንድ ክልሎች ላይ አንድ ሐኪም ቤት ብቻ ይኖርና መስፈርቱን አላሟላም ብለን ብናሽገው የሚመጣው ውጤት ምንድን ነው? ስንል አገልግሎቱን ፈልጎ ከቅርብም ከሩቅም የሚመጣ ታማሚ አገልግሎቱን ያጣል፡፡ ምናልባትም አገልግሎት ባለማግኘቱ እስከ ሞት ሊደርስ ይችላል። በመሆኑም እንደዚህ አይነት ቦታዎች ላይ የምናሳልፋቸው ውሳኔዎች ከፍተኛ ጥንቃቄን ይፈልጋሉ። ግን ደግሞ ይህ ዓይነት ችግር ይከሰታል፤ በማለትም ልቅ አናደርገውም። በመሆኑም ይህንን ሚዛኑን በጠበቀ ሁኔታ እንሠራለን።
አዲስ ዘመን፦ ጤና ተቋማት በዋናነት የጨረር ተጠቃሚ ቢሆኑም ኢንዱስትሪዎችም ቀላል የማይባል ሃይልን የሚጠቀሙ እንዲሁም ለአካባቢም ቅርብ ናቸውና እንደው እነሱንስ በመቆጣጠሩ በኩል ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ ሰለሞን፦ ከኢንዱስትሪ አንፃር የጨረራ ቴክኖሎጂን ቢራ፣ የሲሚንቶ፣ የለስላሳ መጠጥ ፋብሪካዎች እንዲሁም በኮንስትራክሽን ዘርፉ ደግሞ ለምሳሌ የጥቅጥቃት መጠንን የምንለካባቸው መሣሪያዎች፣ ለማዕድን ፍለጋም የሚውሉ መሣሪያዊች በተመሳሳይ የጨረራ ቴክኖሎጂን ይጠቀማሉ። እንግዲህ እነዚህ ኢንደስትሪዎች ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ልክ እንደጤናው ሁሉ ሊያሟሏቸው የሚገቡ መስፈርቶች አሉ።
በመሆኑም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተግባር ፍቃድ ሲሰጥ የተቀመጡ መስፈርቶች ተሟልተው መገኘታቸውን ያረጋግጣል። ኢንዱሰትሪው አካባቢ የሚፈለጉ መስፈርቶች አንዱ የጥንቃቄ አልባሳት ናቸው፡፡ እነዚህ ኖረውም እንኳን በመጠቀም ላይ ደግሞ ክፍተቶች የሚታዩ በመሆኑ ይህንን በማስተካከል ላይ ሥራዎች ይሠራሉ። ከፍ ያሉ ዝንፈቶች ሲከሰቱ የሚያስከትሉት ችግርም ትንሽ ስላልሆነ እነሱን የማስተካከሉ ላይም ሥራዎች ይሠራሉ።
ለምሳሌ ብዙ ጊዜ ለመንገድ ሥራ ጥቅም ላይ የሚውለው መጠቅጠቂያ ተንቀሳቃሽ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ደግሞ አንድ ፕሮጀክት ተሰርቶ ሲያልቅ እቃው ወደሌላ ቦታ ተጓጉዞ አገልግሎት እንዲሰጥ ይሆናል፡፡ በዚህ መካከል ግን መሣሪያውን ሲያጓጉዙ አልያም ሲጠቀሙ አግባብ ባለው ሁኔታ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ነገር ግን እዚህ ላይ ከፍተኛ ችግር የሆነብን ነገር እነዚህን መሣሪያዎች ለመንገድ ሥራው ያመጣው አካል ሥራውን ሲያጠናቅቅ ወደመጣበት አገር ይዞ የመሄድ ግዴታ ቢኖርበትም ተፈፃሚ አያደርገውም። እዚሁ ጥለውት ይሄዳሉ፡፡ ያ ደግሞ ብክለትን ያስከትላል፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ ከመንገዶች ባለስልጣን ጋር ጠበቅ ያለ ውይይትን እያደረግን ነው፤ በዚህም ሥራውን የጀመሩት አካላት አጠናቀው ሲሄዱ መንገዶች ባለስልጣን እንደ መኪናና ሌሎች ንብረቶች ዝም ብሎ መቀበል ሳይሆን መሣሪያው አገልግሎቱን መስጠት አይችልም ማለት ጉዳት አያደርስም ማለት ስላልሆነ እስከመጨረሻው እስኪወገድ ድረስ በጥንቃቄ መያዝ እንዳለበት ተማምነናል። በመሆኑም ይህንን እንዲያደርጉ ከመንገዶች ባለስልጣን ጋር ሥራዎችን በቅንጅት እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፦ ከጨረር ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሥራ የሚያከናውኑ ባለሙያዎች ስለ ዘርፉ እውቀት ይኖራቸዋል ብዬ አስባለሁ፤ ነገር ግን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ስለ ዘርፉ ግንዛቤ አለው ብሎ ማለትስ ይቻላል?
አቶ ሰለሞን፦ ጥሩ ጥያቄ ነው። ሁሌም የምጠየቀው ነው። በዚህ ግንዛቤ ፈጠራ ውስጥ ግን የእናንተም ሚና የጎላ ነው። የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሁሌም መሠራት ያለበት የተለያየ ጉዳዮችን መፍጠርና የህዝብ መገናኛ ብዙሃንን መጽሔቶችንና ሌሎችንም መጠቀም የሚፈለግ ነው እኛም በዛ መልኩ ዘርፉን ለማስተዋወቅ ብዙ ሥራዎችን እየሠራን ነው።
ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ግንዛቤው ተጨብጧል ወይ የሚለውን ስንገመግም ገና ብዙ የሚቀር ነገር እንዳለም ይሰማናል። ብዙ ሥራም መሠራት አለበት። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ራሱንና ሥራውን ለማስተዋወቅ የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማል፡፡ ነገር ግን ህብረተሰባችን ጋር ደርሷል ወይ ስንል ይቀራል፤ የቀረው ደግሞ ሥራው በቂ ሳይሆን ቀርቶ አይደለም፤ ይልቁንም መስማትና ማዳመጥ የተለያዩ ሆነው ነው። ይህም ቢሆን ግን ግንዛቤው በደንብ እስከሚጨበጥ ድረስ መሥራት ሃላፊነታችን ነው ያንንም እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፦ ጨረራ ቴክኖሎጂ ስንነጋገር እንደመጣነው ከጤናው ዘርፍ ጀምሮ ኢንዱስትሪው ላይ የሚኖረው ሚና ትንሽ አይደለም፤ ግን እንደ አገር ይህንን ቴክኖሎጂ አውቀነው መጠቀም ያለብንን ያህልስ መጠቀም ችለናል?
አቶ ሰለሞን፦ ተጠቅመናል ለማለት እንኳን አያስደፍርም፤ በጣም ገና ነን። ሥራው በጣም ሊሰፋ ይገባል። ለምሳሌ የካንሰር ማከሚያ ማዕከል በብቸኝነት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ነው ያለው፤ አገልግሎቱን ማግኘት የሚፈልግ ህምተኛ ግን በጣም ብዙ ከመሆኑም በላይ ወረፋቸው ሲደርስ አብዛኞቹ ሰዎች ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ይህ የሚያሳየው አገልግሎቱን አለማስፋታችንን ነው ።
መንግሥት ይህንን ችግር በመረዳት አገልግሎቱን ወደስድስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሆስፒታሎች ለማስፋት ፕሮጀክት ተቀርፆ አሁን ላይ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በተጨማሪ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ ጎንደር፣ መቀሌና ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ላይ እንዲኖር የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። በዚህ ደግሞ አንድ የነበረን ወደአምስት ሲሰፋ አገልግሎቱ በትንሹም ቢሆን ተደራሽ ሊሆን ይችላል ማለት ነው። አሁንም ቢሆን ግን ይህ በቂ አይደለም።
ይህ አገልግሎት ከአንድ ወደአምስት ማደጉ አስደሳች ነው እንጂ ካለን የህዝብ ብዛት አንፃር የሚፈለገው ከመቶ በላይ ነው። ይህም ይቅርና አሁን የጀመርነውንም ወደ አስራ አምስትና ሃያ እያሳደግን ብንመጣ ብዙ ችግሮቻችን ይቃለላሉ።
ይህ ቴክኖሎጂ ለህክምናው ብቻ አይደለም፤ በሌሎች ዘርፎችም ተፈላጊ ነው። ለምሳሌ በግብርናው መስክ ላይ በተለይም ወደውጭ የምንልካቸውን የምግብ አይነቶች መጀመሪያ በጨረራ ካከምናቸው መደርደሪያ ላይ ተቀምጠው ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ ይቆያሉ።
አዲስ ዘመን፦ ይህንን ስናደርግ ግን በጥራታቸው ላይ የሚመጣ ችግር አይኖርም?
አቶ ሰለሞን፦ በጥራቱ ላይ በጣም ተመራጭ የሚሆነው ቴክኖሎጂ ይህ ነው። እንደውም ሌላ አይነት ቴክኖሎጂን ብንጠቀም የንጥረ ነገር ይዘቱ ሊቀንስ ይችላል። ይህ ቴክኖሎጂ ግን ጥራቱን ጠብቆ የመቆያ ጊዜውን በማራዘም በኩል ተመራጭ የሆነው ነው። ግን ይህንን ቴክኖሎጂ በአገራችን አልጀመርንም፤ ነገር ግን በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች አለ። ማምጣትስ አይቻልም ወይ ብትይኝ በደንብ ይቻላል። ግን በደንብ መሥራትን ይጠይቃል።
ከላይ ስናነሳ የነበረው የካንሰር ማከሚያ አሁን ላይ አምስት አድርሰናል፡፡ ነገር ግን መመርመሪያ ደግሞ አለ፤ እነዚህንም የሚመረትበትን ተቋም ከማቋቋም አንፃር ምንም የሠራነው ሥራ የለም፤ እነዚህ መመርመሪያዎች ከውጭ እንዳናስገባ የአገልግሎት ጊዜያቸው 20 ወይም 30 ደቂቃ በዛ ከተባለ ስድስት ቀን ነው። እነዚህን አመጥተን ለመጠቀም በጉምሩክ ሂደት አልፎ እስኪመጣ ምን ያህሉ ከጥቅም ውጭ እንደሚሆኑ መገመት ቀላል ነው። በመሆኑም ይህንን ማምረት ይገባል።
በሌላ በኩልም በጥናትና ምርምር ዘርፍ ላይ ለምሳሌ አለርት ሆስፒታል ያለው አርመን ሀንሰን በጤናው ዘርፍ የምርመር ማዕከል ተብሏል፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የድንገተኛ ህክምና (ትራውማ ሴንተር) እየተገነባ ነው፤ ከዚህ አንፃር ከፍተኛ አደጋ ሲከሰት የደም አጥረት ያጋጥማል፡፡ ያንን ሊሸፍን የሚችል ደም ያስፈልጋል፡፡ ታማሚው ደግሞ ደም የሚፈልገው በቀይ የደም ሴሉ ነው፤ ነጭ የደም ሴሉ አያስፈልገውም፤ በመሆኑም ነጭ የደም ሴሉን ገሎ አውጥቶ ቀይ የደም ሴሉ ብቻ ደም ቢያገኝ ወዲያው ያገግማል፡፡ በመሆኑም ይህንን ሊያደርግ የሚችል መሣሪያ ደግሞ ጨረር ነው። እንዲህ ዓይነት ሥራዎች ሌላው ዓለም ላይ የተለመዱ ቢሆኑም እኛ ጋር ግን በጣም ገና ናቸው።
ወደሌላ ስንሄድ ደግሞ እስከ አሁን በአገራችን የምንጠቀማቸው የሃይል ምንጮች ውሃን ጨምሮ ንፋስ ጂኦተርማልና ሌሎችም ናቸው። እነዚህ ደግሞ የተስተካከለ የአየር ሁኔታን ይፈልጋሉ። የአየር ሁኔታው ሲዛባ የሚፈጠርብንን ነገር እናውቀዋለን። ነገር ግን የኒውክለር ቴክኖሎጂን እንደ ሃይል አማራጭ ብንጠቀም ከፍተኛ ጥቅም እናገኛለን። የኒውክለር ቴክኖሎጂን የዛሬ 20ና 30 ዓመት ልንጠቀም ይገባል ካልን ዛሬ ላይ ሥራውን መጀመር አለብን።
አዲስ ዘመን፦ ይህንን ቴክኖሎጂ ላለመጠቀማችን ችግሩ ግን የእውቀት ማነስ፣ የአቅም፣ የገንዘብ ወይስ ሌላ ነው ችግሩ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ሰለሞን፦ ድህነት እንዳንል ከእኛ ያነሱ አልያም የእኛ እኩል የሆኑ አገራት ቴክኖሎጂውን ሲጠቀሙ እናያለን። እኔ ግን ያለበን የአስተሳሰብ ድህነት ከሆነ ያስኬዳል። ምክንያቱም አንዳንዶቹ ልንሠራቸው የምንችላቸው ግን ደግሞ ያልሠራናቸው ናቸው። በእርግጥ አንዳንዶቹ የገንዘብ አቅምም የሚጠይቁ ናቸው።
በሌላ በኩል ከምናመርተውና ወደውጭ ከምንልከው ምርት አብዛኛው በመንገድ ላይ ብልሽት እንዳያጋጥመው የጨረር ማቆያ መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ ይህንን አለማድረጋችን የማንም ሳይሆን የእኛ ችግር ነው።
በመሆኑም ምንም ጥያቄ የለውም ለቴክኖሎጂው አለመስፋፋት የእኛ ክፍተት በጣም አለ። በሌላ በኩል ደግሞ ነገን ስናስብ የሰው ሃይላችንን ዛሬ ላይ ማዘጋጀት ይጠይቃልና እሱ ላይም መሥራትና ማጠናከር ላይ ክፍተቶች ስላሉ ወደራሳችን ወስደን በአግባቡ መሥራቱ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያ ጨረራ ባለሥልጣን አሁን ላይ በምን ዓይነት የቴክኖሎጂ አቋም ላይ ይገኛል? የትስ ለመድረስ ነው እየሠራ ያለው?
አቶ ሰለሞን፦ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ቴክኖሎጂዎቹ ወደአገር ሲገቡ ህብረተሰቡን አካባቢን እንዳይበከል ለጉዳት እንዳይዳረጉ ከመጠበቅ አንፃር ትልቅ ሃላፊነት የተሸከመ ነው። ይህ ቴክኖሎጂ ደግሞ በየጊዜው እያደገ የሚመጣ ነው። በዚህም ሁኔታ የተቆጣጣሪው ባለስልጣን የቁጥጥር አቅሙን ከሰው ሃይል ከቴክኖሎጂ ከመሰረተ ልማት አንፃር ማዘመን ይጠበቅበታል።
በመሆኑም ባለሥልጣኑ በተለይም የቁጥጥር ሥራውን ለማዘመን የሚረዳው ክፍል በማቋቋም እየሠራ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የቁጥጥር ሥራው የሚጠይቀው መስፈርቶችን በአግባቡ የማስቀመጥ ሁኔታን ሕግ ደንብና መመሪያ ቼክ ሊስቶችና ሰነዶች በየጊዜው መቃኘትና ቴክኖሎጂው በደረሰበት ልክ መዘጋጀት ስላለባቸው እሱ ይሠራል ባለሙያዎችንም በተመለከተ አቅማቸውን የማሳደግ ሥራ እየተሠራም ነው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ሰለሞን፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም