የሪል ስቴቱ ውስጣ ውስጥ ሲፈተሽ!

 

ክፍል 3

የሪል እስቴት ዘርፉ ውጤታማነት ለማረጋገጥ – የሙስና መታገያ መንገዶችን ማበጀት

የሪል ስቴት ዘርፍ ዘላቂ ወይም ቋሚ የኢንቨስትመንት ዓይነት ነው። ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ የሚፈስበት፣ በርካታ የሰው ኃይል የሚጠይቅ እና የተለያዩ አካላት የሚያሳተፉበት ነው። በኢትዮጵያ ያለው የሪል ስቴት ዘርፍ እንደ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ማርኬት፣ የብሮድካስት ባለስልጣን፣ የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር፣ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን፣ ባንኮች ፣ የክልሎች እና የከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮዎች እንዲሁም የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮዎች ፣ ደላሎች ፣ የገበያ ባለሙያዎች፣ አማካሪዎች፣ ባለሀብቶች ወዘተ የመሳሰሉ በርካታ ተዋናዮች ያሉበት ነው።

ይሁን እንጂ ዘርፉ ራሱን ችሎ የሚመራው ተቋም ባለመኖሩ ምክንያት ፈርጀ ብዙ ለሆኑ ብልሹ አሰራሮች ተጋላጭ ሆኗል። ለአብነት ለዘርፉ ከሚውለው መሬት ጋር ተያይዞ በርካታ ቅሬታዎች ይነሳሉ። ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ቤት ፈላጊ ግለሰቦች ሪል ስቴት አልሚዎች ነን በሚሉ አካላት ገንዘባቸውን እንደተዘረፉ ሲገልጹ ይሰማል።ሪልስቴት አልሚዎች አንድ ህንጻ ለመገንባት በዋናነት መሬት ያስፈልጋቸዋል።

መሬት ደግሞ ግልጽነት የጎደለው እና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ ስለመሆኑ በርካቶች ይስማሙበታል። መሬት ውስን የሆነ ሀብት ሲሆን ይህን በአግባቡ መምራት፣ ማስተዳደር እና ተገቢው ቦታ ለተገቢው ልማት ማዋል ያስፈልጋል። ለእርሻ የሚሆን መሬት ቤት ለመሥራት ወይም የማዕድን እንቅስቃሴ ያለበትን አካባቢን ለሌላ ተግባር ማዋል መሬት አግባብነት ባለው መንገድ ለመጠቀም ያለውን ሂደት ይጎዳል።

የኢትዮጵያ ጸረ ሙስና ኮሚሽን የኮሚሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሻሜቦ እንዳሉት፤ መሬት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ድህነትን ለማጥፋትና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል ሀብት ነው። በተጨማሪም የመሬት ጉዳይ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው። ታዲያ ይህ ሀብት የተፈጥሮ ስጦታ መጠኑም በተፈጥሮ የተወሰነ በመሆኑ የሰው ልጅ አምርቶ ሊያሳድገው የሚችለው ሀብት አይደለም። ስለሆነም በአግባቡ ማስተዳደር እና መጠቀም ተገቢ ነው።

ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያ በመሬት ላይ ያለ ንብረት መብት እንዴት መደልደል እንዳለበት፤መሬትን የመጠቀም፣ የመቆጣጠር፣ የማስተላለፍ መብቶች እና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ለመወሰን በተለያዩ ወቅቶች የከተማ እና የገጠር መሬት አዋጆችን እያወጣች ተግባራዊ ስታደርግ ቆይታለች።

መሬትን በአግባቡ ለመጠቀም በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 40 (3) እንደተደነገገው፤ “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግስት እና የሕዝብ ብቻ ነው። መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው።” ይህ የህገ-መንግስት አንቀጽ በግልጽ የሚደነግገው መሬት የሕዝብ እና የመንግስት የጋራ ሀብት ነው፤ የማይሸጥ እና የማይለወጥ ፣ የጋራ ንብረት ነው፤ አርሶ አደሩ በነጻ የማግኘት እና ከመሬት ያለመነቀል መብት እንዳለው ፤መንግስት መሬቱን ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውና ሲወስደው ተመጣጣኝ ካሳ እንደሚከፍል ያመላክታል።

እነዚህን በህገ መንግስቱ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ለማስፈጸም ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ በርካታ የህግ ማሕቀፎችም አሉ። ለምሳሌ የከተማ መሬትን በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅ(አዋጅ ቁጥር 721/2004)፣ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ( አዋጅ ቁጥር 456/1997) ፣ ስለከተማ ፕላን የወጣ አዋጅ ( አዋጅ ቁጥር574/2002)፣ የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ አዋጅ( አዋጅ ቁጥር 818/2006)፣ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ አዋጅ ( አዋጅ ቁጥር1161/2011) ጥቂቶቹ ናቸው ።

ነገር ግን ይህ ውስን የሆነ የመሬት ሀብት በአግባቡ መጠቀም ሲገባ በተለያዩ ምክንያቶች ለሙስና እና ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ ሆኖ ይገኛል። በተለይ ደግሞ የሪል እስቴት ዘርፉ ወጥ የሆነ አሠራር እና የሚያስተዳድረው መንግስታዊ ተቋም ባለመኖሩ ለብልሹ አሠራር ተጋላጭ ሆኗል። እንደ የኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ገለጻ ፤ ተቋሙ በመሬት ላይ 1994 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ከሙስና ጋር የተያያዙ ጥናቶችን አስጠንቷልም።

በ1994 ዓ.ም በአጠናው ጥናት እንዳረጋገጠው ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ማህበራዊ የሕዝብ ችግሮች ውስጥ ሙስና በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠ ነበር። ከ10 ዓመት በኋላ ማለትም በ2003 ዓ.ም ባስጠናው ጥናት ደግሞ ሙስና 7ኛ ደረጃ ላይ ነበር። በዚህም ትልቅ መሻሻል ታይቶበት ነበር። አሁንም ከ10 ዓመት በኋላ በ2013 ዓ.ም ባስጠናው ጥናት ደግሞ ችግሩ ተባብሶ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ማኅበራዊ የሕዝብ ችግሮች ውስጥ ሙስና ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።

አቶ ተስፋዬ እንደሚገልጹት፤ ሙስና በሀገራችን ከኑሮ ውድነት እና ስራ አጥነት ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በዚህ ውስጥ ደግሞ መሬት እና ከመሬት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሪል እስቴት ይገኙበታል። ይህ የሚያሳየው እንደሀገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሌብነት እና ሙስና እያደገ መምጣቱን ነው። ይህን ሙስና ለመታገል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ እስከ ማቋቋም ደርሰዋል።፡

እንደ ጽህፈት ቤት ኃላፊው ማብራሪያ ከሆነ፤ እንደ ሀገር በመሬት አስተዳደር ላይ የሁሉም ሰው ፍላጎት ያለበት ከፍተኛ ችግር አለ። ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ ያለአግባብ የመበልጸግ ሂደቶች ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁለት ዓይነት አካላት አሉ። እነዚህም መሬት ሰርቀው በመሸጥ በህገ ወጥ መንገድ ሀብት ለማፍራት የሚፈልጉ እና ሁለተኛው ደግሞ ከመንግስት ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር በሙስና ቁልፍ ቦታዎችን የሚወስዱ እና ግንባታ የሚያከናውኑ ናቸው። መሬት የሚወስዱት ተወዳድረው ሳይሆን ከመንግስት ኃላፊዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ነው። እነዚህ ሰዎች የገነቧቸውን ቤቶች ያከራያሉ ወይም ይሸጣሉ፤ ከፍተኛ ገቢም የሚያገኙ ናቸው።

ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ሴክተሮችን መሰረት አድርጎ እ.አ.አ. በ2012 ዓ.ም (Diagnosing Courruption in Ethiopia: Perception, Relaites and the way forards for key sectors” ብሎ ባጠናው ጥናት “የኮንስትራክሽን ዘርፉ ሙስና የሚስተዋልበት፣ ግልጽነት ያልሰፈነበት፣ ተጠያቂነት የጎደለው ነው” ሲል ይገልጸዋል። በጥናት ላይ “ቶኒ በርነስ እና ካቲ ዳሬምፕል “Land Sector Corruption in Ethiopia” በሚል ጽሁፋቸው እንደጻፉት የመሬት ዘርፉ ለሙስና እና ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጠ ነው።

ለዚህ ደግሞ የመሬት አስተዳደር እርስ በርሳቸው ተመጋጋቢ በሆኑ አሠራሮች መተግበር ይኖርበታል። በተለይ ለዘርፉ የሚሆን ፖሊሲ ማዘጋጀት፣ ፖሊሲውን ወደ መመሪያዎች እና አሠራሮች መተግበር፣ ተቋማትን መፍጠር፣ ፖሊሲን ማስፈፀም የሚያስችል አቅም መገንባት፣ የክትትል እና የግምገማ ሥርዓትን ማበጀት አስፈላጊ ነው።” ሲሉ ያትታሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ/ም የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋምን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ የመሬት ሙሰና በዋልጌ ባለሥልጣናት፣ በፍቅረ ነዋይ የታወሩ ደላሎች እና ባለሀብቶች አንድ ላይ ሲገጥሙ የሚፈጠር ነው። ሕዝቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ከመሬት ጋር በተያያዙ አሠራሮች በሚያጋጥመው ሙስና እየተማረረ ነው። ምክንያቱም ይህን አይነት ሙስና የሚፈጽሙ አካላት ከፍተኛ የገንዘብ ጉልበት ወይም ጡንቻ ያላቸው አካላት በመሆናቸው ነው ሲል ገልጿል።

አቶ ተስፋዬ፤ “ሀገራችን ጠንካራ የመሬት ፖሊሲ የላትም። ህገ መንግስቱ መሬት የሕዝብና የመንግስት መሆኑን ይገልጻል። ነገር ግን ግልጽ እና ወጥ የሆነ፤ ሊያሰራ የሚችል የመሬት መመሪያ የለውም። በተለይም በከተማ አስተዳደሮች አዲስ ከንቲባ በመጣ ቁጥር መመሪያ ይቀያየራል። መመሪያ በየጊዜው የሚቀያየር ከሆነ ለሌብነት ምቹ ይሆናል። አዲስ አመራር እና ከንቲባ በመጣ ቁጥር መመሪያ የሚቀያይር ከሆነ ለሪል እስቴት ሆነ ለሌሎች ልማቶች የሚውሉ መሬቶች ለሌብነት መጋለጣቸው የማይቀር ነው።

አሁን ላይ በሀገራችን የሚታየው ወደ ስልጣን የመጣ አመራር ሁሉ የተወሰነ ነገር ለማግኘት ሲል የፈለገውን ያደርጋል። የከተማ አስተዳደሮችም ጠንካራ የመሬት ፖሊሲ እና መመሪያ ለማውጣት የማይፈልጉት ለመስረቅ እንዲመቻቸው ነው። ቀደም ብሎ የነበረው የመንግስት ባለስልጣን ያወጣውን ህግ አሁን የመጣው ባለስልጣን ሳይሽር ሌላ ተጨማሪ የራሱን ህግ ስለሚያወጣ አሁን ላይ በሀገራችን ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚፈጸመውን ሙስና አባብሶታል ሲሉ ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ ጸረ ሙስና ኮሚሽን በ1997 ዓ.ም ከመሬት ጋር በተያያዘ ባጠናው ጥናት በመጥቀስ አቶ ተስፋዬ ሲያብራሩ፤የመሬት ልማትና አስተዳደር የሚመለከት 30 መመሪያ ነበረው። እነደዚህ አይነት ተለዋዋጭነቶች፣ ለሕገወጥነት በር ይከፍታሉ። መመሪያ ካለ፣ ተጨማሪ ሰርኩላር ለምን አስፈለገ? የሚለውም መጠየቅ አለበት። አንድን መመሪያ በሰርኩላር መጣስም ተገቢ አይደለም።

ለዚህም ምክንያቱ አመራር በተቀያየረ ቁጥር ለራሱ የሚመች የመሬት ህግ ስለሚያወጣ ነው። 30ዎቹ መመሪያዎች ለዝርፊያ ያልተመቸው አመራር በካቢኔ የተወሰነ በሚል በመመሪያዎች ላይ ሰርኩላር (circuralr) ይጨምራል። በዚህ ሰርኩላርም ሊጠቅም የፈለገውን ወገን ይጠቀማል። ወጥ የሆነ ህግ ቢኖር ግን ይህን ማድረግ አይችሉም” ነበር ሲሉ አቶ ተስፋዬ ያስረዳሉ።

“ሪል እስቴት ኢንቨስትመንት አስተዳደር እና ግብይት” በሚል በ2013 ዓ.ም በኢንጂነር ደሳለኝ ከበደ የታተመው መጽሐፍ እንደሚያሳየው “የሪል እስቴት ዘርፍ የተወሳሰበና ብዙ የሙያና የንግድ ዘርፎች በውስጡ የሚያካትት ነው። በተለይም ዘርፉ ከዲዛይን ሥራ፣ ግንባታ፣ ልማት፣ግዥ፣ ሽያጭ፣ ማስተዋወቅ፣ የባንክ ብድር፣ የድለላ (የማሻሻጥ)፣ መሰረተ ልማት እና የመሳሰሉትን የሥራ ዘርፎችና በዘርፎቹ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን ግብዓት ተጠቅሞ የሚከናወን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ነው። እነዚህ ሁሉ ተግባራት የሚከናወኑት ደግሞ መሬት ላይ ነው። መሬት በአግባቡ ማስተዳደር ካልተቻለ ለብልሹ አሠራር በተለይም ለሙስና ተጋላጭ ይሆናል። ይህ ደግሞ በተግባር በሀገራችን በተደጋጋሚ ታይቷል ሲሉ ያብራራሉ።

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ተመራማሪ ዶክተር ዘመንፈስ ገ/እግዚአብሔር በ2011 ዓ.ም በ8ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም “መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልጽግና” በሚል ባሳተሙት ጽሁፍ “የከተማ ቤት ልማት በኢትዮጵያ ስኬት፣ ተግዳሮቶች እና የወደፊት አቅጣጫዎች” ላይ “የሪል እስቴት ዘርፍ እንደ አንድ የቤት አቅርቦት አማራጭ ተደርጎ የተወሰደ ቢሆንም በቂ የለማ መሬት የማይቀርብበት፣ በአስተማማኝ የፋይናንስ አቅርቦት ያልተደገፈ እና የራሱ የሆነ የህግ ማሕቀፍ የሌለው ሆኖ ቀጥሏል።

በተለይም የሪል እስቴት አልሚዎች ለቤት ልማት የሚወስዱትን መሬት ያለ ግንባታ አጥረው ማስቀመጣቸው ወይም በከፍተኛ ትርፍ ለሦስተኛ ወገን በማስተላለፍ ስራ ላይ መጠመዳቸው ይስተዋላል። በአጠቃላይ አሁን ያለው የሪል እስቴት ዘርፍ የመኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ በሽያጭ ወይም በኪራይ ለቤት ፈላጊዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያስተላልፍ ሳይሆን ከቤት ፈላጊዎች ገንዘብ ሰብስበው ቤት የሚገነቡ ተቋራጮች ስብስብ ሆኖ ይታያል። በሌላ በኩል በግለሰቦች የሚከናወነው የመኖሪያ ቤት ገንብቶ የማከራየት (private rental) ሁኔታ ሲታይ የግሉ ዘርፍ በመኖሪያ ቤት አቅርቦት ረገድ እስከ አሁን ያበረከተው አስተዋጽኦ አነስተኛ ነው።”

በጥቅሉ ሙስና በተለይም ከመሬት ጋር የተያያዘው ሙስና ለሀገር ዕድገት ከፍተኛ ችግር ነው። ከመሬት ጋር የሚከናወኑ ሙስናዎች ግጭቶች እንዲፈጠሩ፣ ከተፈጠሩም ቶሎ እንዳይቋጩ እና እንዳይበርዱ የሚያደርጉ ናቸው። ምክንያቱም ኃላፊነት በማይሰማቸው ባለሥልጣናት፣ በፍቅረ ነዋይ የታወሩ ደላሎች እና ባለሀብቶች የሚከናወን በመሆኑ ነው ሲሉ አቶ ተስፋዬ ይናገራሉ።

በመሆኑም መንግስት እና የሚመለከታቸው አካላት የተስተካከለ ቢሮክራሲ፣ የተቀናጀ መዋቅርና ዘመናዊ አሠራር ለሙስና ተጋላጭነትን ስለሚቀንሱ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሊተገብሯቸው ይገባል። ሙስናን ለማጥፋት ከመሬት ጋር ተያይዘው የሚሰጡ አገልግሎቶችን መፈተሽ፣ መዋቅሮችን ማጠናከር፣ አዳዲስ አሠራሮችን መዘርጋት፣ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥራዎችን ማሳለጥ፣ በሙስና ወንጀል የሚሳተፉ አመራሮችንና ሌሎች ተዋንያንን ለሕግ የማቅረብ፣ ሙስና ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ማድረግ ለሪል እስቴት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በመሬት ዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመዝጋት እና የሪል ስቴት ዘርፉ ተወዳዳሪ እና ዜጎችን እንዲጠቅም ማድረግ ያስችላል።

ክፍል አራት

ወደ አግላይነት እየተጓዘ ያለ የሚመስለው የሪል ስቴት ዘርፍ?

ታቅደው እና በፕላን የሚሰሩ ከተሞች በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ሁሉ ያልታቀዱ እና ፈጣን የከተሞች መስፋፋት በአካባቢ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅእኖዎችን ማሳደራቸው የማይቀር ነው ። በተለይም በውሃ አካላት፣ በአገልግሎት፣ በመሰረተ ልማት፣ የተጣበበ ቦታን በመፍጠር፣ እና ፍትሃዊ ያልሆነ አገልግሎት እንዲስፋፋ ያደርጋሉ። ለዚህ ደግሞ በታዳጊ ሀገራት የሚገኙ ከተሞች ተጠቃሽ ናቸው።

የዓለም ባንክ በ2001 ዓ.ም እና WFP 2006 ዓ.ም ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ በታዳጊ ሀገራት ከተሞች መሰረታዊ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች እንደ ውሃ፣ ንፅህና፣ የቆሻሻ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች፣ የዝናብ ውሃ ማፋሰሻ፣ የመንገድ መብራት፣ ጥርጊያ መንገድ እና የአደጋ ጊዜ መዳረሻ መንገዶች ከፍተኛ ተግዳሮቶች ናቸው። ትምህርት ቤቶች እና ክሊኒኮች የሏቸውም፣ ህጻናት የሚጫወቱባቸው ፤ ማኅበረሰቡ የሚገናኝበት ቦታ እጦት አሉባቸው።

አክሊሉ ፍቅረስላሴ፣ ወንድሙ አበጀ እና ሌሎች “Rapid Urbanization in Ethiopia: Lakes as Drivers and Its Implication for the Management of Common Pool Resources” በሚል የምርምር ጽሁፍ ላይ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ጊዜ 55 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ በከተሞች ውስጥ ይኖራል። ይህ አሃዝ እ.አ.አ በ2050 ወደ 60 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። የአፍሪካ የከተማ ህዝብ ቁጥር ዕድገት ከፍተኛ ነው። የአህጉሪቱ የከተማ ሕዝብ እ.አ.አ በ2010 ላይ 395 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን በ2050 1.5 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። በአጠቃላይ፣ የአፍሪካ የከተማ ሕዝብ አሁንም በዓመት በአማካይ በ3 በመቶ ገደማ እንደሚያድግ እና በግምት በ25 ዓመታት ውስጥ በእጥፍ እንደሚጨምር ይጠበቃል።

ይህ ፈጣን የከተማ ዕድገት በኢትዮጵያም እየተመዘገበ ይገኛል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን የከተማ እድገት ከሚያስመዘግቡ ሀገራት ተርታ ነች። የከተማ ልማትና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ለዚህ የምርመራ ቡድን እንደተናገሩት ፤ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ5 በመቶ በላይ ፈጣን እና ተከታታይ የከተሞች ዕድገት እያስመዘገበች ነው። መንግስትም ይህን በሀገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ያለው ከተሜነት እና ከተሞች በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያላቸውን ቀጥተኛ ተጽዕኖ ለመቋቋም የተለያዩ ሥራዎች እየሠራ ነው።

በተለይም የቤት ፍላጎት እና አቅርቦትን ለማመጣጠን የተለያዩ ዓይነት ሥራዎች እየተሠሩ ነው። መንግስት በጋራ የመኖሪያ ቤት ግንባታ እና አቅርቦት፣ በማኅበራት ማደራጀት፣ የመንግስት እና የግል አጋርነት፣ በተገጣጣሚ ቤት ግንባታ፣ በሪል ስቴት ግንባታ እና በመሳሰሉት የቤት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየሠራ ነው። የግሉ ሴክተርም በሪል ስቴት ልማት ውስጥ በስፋት የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። እዚህ ጋር በዋናነት መጠየቅ ያለበት፤ የሪል እስቴት ግንባታ ዘርፉ በእቅድ የተመራ ከተማን እየፈጠረ ነው ወይስ በተቃራኒው በዕቅድ ያልተመራ ከተማ እየፈጠረ ነው? የሚለው እንደሆነም አመልክተዋል።

የምስራቅ ካሮላይና ዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰር ሙላቱ ውብነህ እአአ በ2019 ዓ.ም “የከተማ ተግዳሮቶች እና ዕድሎች በኢትዮጵያ 2050” በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ፤ “በኢትዮጵያ ከፍተኛ የከተሞች መስፋፋት አለ። ይህ መስፋፋት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየተከናወነ ነው። ይህም በታሪክ ኢትዮጵያን በከተሜነት ከሚራመዱ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ አድርጓታል። በተለይም ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የከተሞች መስፋፋት በከፍተኛ ፍጥነት እየተጓዘ ነው። ይህ ፍጥነት በዚህ ከቀጠለ በ2030 ዓ.ም 35 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በከተማ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ በምጣኔ ሀብት እና በአገልግሎት እንዲሁም በመሰረተ ልማት አቅርቦት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ዛሬ በብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች በቤቶች ልማት ዘርፍ ዋና ተዋናይ የሆነው መንግስት እና የከተማ አስተዳደሩ ነው። ለአብነትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጨረታ ሥርዓቱ የመሬት አቅርቦትና የመኖሪያ ቤቶች ግንባታን ጨምሮ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ በቀጥታ ይሳተፋል። በተቃራኒው መፍትሄ ይሰጣል የተባለው የግሉ ሴክተር በግንባታ እና በአጠቃላይ የሪል ስቴት ልማት ውስጥ ያለው ሚና ውስን ነው። የቤት አቅርቦቱም ቢሆን በተወሰነ ቦታ ወይም ከተማ ላይ ያተኮረ ነው ይላሉ።

በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ዴኤታ እና የቤቶችና የከተማ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ሄለን ደበበ በበኩላቸው፤ በዘርፉ በርካታ ቀውሶች ይስተዋላሉ ይላሉ። ከቀውሶቹ መካከል ደግሞ በዋናነት በሪል እስቴት አማካኝነት የሚገነቡ መንደሮች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ቤቶች፣ አፓርታማዎች ወይም ህንጻዎች ሲገነቡ መሬትን እንጂ ያለውን የመሰረተ ልማት ታሳቢ ያደረጉ አይደለም። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮንስትራክሽን ቢሮ በ2010 ዓ.ም. የህንፃ መመሪያ ቢያወጣም ምን ያህል ተግባራዊ ናቸው የሚለው አሁንም ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው።

ለምሳሌ መመሪያው ግንባታ ሲከናወን የውሃ አቅርቦት፣ የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ፣ የጎርፍ ውሃ ወይም የዝናብ ውሃ አወጋገድ፣ የኢንዱስትሪ ዝቃጭ፣ የውሃ አልባ ቆሻሻ ማስወገጃ፣ የእሳት ማጥፊያ ተከላ ፣እና የመሳሰሉትን ቢያስቀምጥም መመሪያው አጠቃላይ እንጂ ለሪል እስቴት ግንባታ ተብሎ የተለየ መስፈርት የለውም።

የኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን ነገዎ በበኩላቸው፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከተቋቀመበት ጊዜ እስከዛሬ በዘርፉ እዚህ ግባ የሚባል ቁጥጥር አድርጎ አያውቅም። ነገር ግን በቀጣይ እንደሀገር በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ አቅደው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የልማትና ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ምክትል ዲን ዶክተር ሂርጶ በሪሶ ፤ በመሬት ላይ የለማ ነገር ሁሉ የሚለው ውስጡ በርካታ ነገሮችን ስለሚያጠቃለል የሪል እስቴት ዘርፍ እጅግ በጣም ሰፊ ነው። ዘርፉ የንግድ፣ የማምረቻ ወይም የኢንዱስትሪ፣ የግብርና፤ የመኖሪያ ቤት እና ቅይጥ እየተባለ ይከፋፈላል። የመኖሪያ ቤት ሪል ስቴትም እንዲሁ አፓርትመንት፤ በመደዳ የተሰሩና የተጠባበቁ ቤቶች እና ለብቻ ግቢ ያላቸው ሆነው ሊሠሩ ይችላሉ።

በአሁኑ ወቅት በሪል ስቴት በሚኖሩ ሰዎች አካባቢ የሚስተዋሉ ክፍተቶች አሉ። በሪል ስቴት አካባቢ የሚኖር ማኅበረሰብ የተገለለ ማኅበረሰብ እየሆነ ነው። የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንደሚኒየምን) ስንመለከት ቤቱ ለባለዕድለኞች የሚከፋፈለው በእጣ ስለሆነ ኅብረተሰቡ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በገቢ እና በመሳሰሉት የተሰባጠረ ነው። ይህ የሚያሳየው አሠራሩ አካታች መሆንኑ ነው።

ነገር ግን ሪል ስቴት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን ስንመለከት በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ፣ የተሻለ ገቢ ያላቸው፣ ሀብታም የሚባሉ ሰዎች የሚኖሩበት ማኅበረሰብ መኖሪያ እየሆነ ነው። ይህ ደግሞ ውሎ አድሮ የሀብታም እና የደሃ መኖሪያ የሚባሉ ሰፈሮችን ይፈጥራል። ለዚህም መንግስት ቶሎ ፖሊሲ አውጥቶ እና የወጣውን በጥብቅ የአፈጻጸም ብቃት በመቆጣጠር ስብጥር ያለው ኅብረተሰብ እንዲፈጠር መሥራት አለበት ይላሉ።

ለምሳሌ በማሌዥያ ተገንብተው የነበሩ ሪል ስቴቶች የደሃ እና የሀብታም በመባል ችግር ይታይባቸው ነበር። ሊክ ዋን የሚባል መሪ ወደ ስልጣን ሲመጣ በወሰደው እርምጃ ቅይጥ እና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያካተተ የሪል ስቴት አሰራር ተዘረጋ ፤ ተከፋፍሎ የነበረው የኅብረተሰብ ክፍል መቀራረብ ቻለ። ይህም ኅብረተሰቡ እንዲግባባ፣ እና በመካከሉ ያለው ልዩነት እንዲጠብ ብሎም ግጭቶች እንዲወገዱ አስችሏል። ማኅበራዊ መስተጋብራቸውም እንዲጨምር አድርጓል ሲል እንደ ምሳሌ ያነሳሉ።

በኢትዮጵያም በሪል ስቴት አካባቢ ያልታቀዱ ነገሮች እንዳይከሰቱ መንግስት አካታች የሆኑ ማለትም ድሀውን፣ ሀብታሙን፣ አቅመ ደከማውን፣ በቀን ሥራ የሚተዳደረውን የሚያካትት አሠራር እንዲኖር መሥራት አለበት። ይህ ካልሆነ ዛሬ ባይሆንም በተራዘመ ጊዜ በሀሳብ እና በኑሮ ዘይቤም ያልተጠበቀ ነገር ይከሰታል።

የእሳቸውን ሃሳብ የሚጋሩት በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሀውሲንግ እና ሪል ፕሮፐርቲ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት እጩ ዶክተር ልሳነወርቅ ስለሺ ናቸው። ሪል ስቴት የቤት አቅርቦት ችግርን በጥራትም በአቅርቦትም እየፈታ ቢሆንም ያልታቀደ ከተማ ሳይሆን ማኅበረሰብ እንዳይፈጥር መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሪል ስቴት የሚገነቡት አቅም ያላቸው ሰዎች እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፤ ግንባታው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጥሪት እንዲኖራቸው እያደረገ ነው። ይህም ሆኖ ፤ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ሪል ስቴት አካባቢ ከሌላው ማኅበረሰብ የተገለለ እና የታጠሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተፈጠሩ ነው። በሰፊ መሬት ላይ የተገነቡ ቤቶች ነገር ግን አንድ መውጫ እና መግቢያ በር ያላቸው ሪል ስቴቶች በርካታ ናቸው። ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ጋርም ተደራሽነታቸው በጣም ዝቅተኛ ነው።

በእነዚህ ሪል ስቴት አማካኝነት የተዘጉ በርካታ የሕዝብ መንገዶች አሉ። ወደ ሌላ ሰፈር ለማለፍ እንኳን መንገዶችን ዘግተው ጥበቃ አስቀምጠው መታወቂያ እና ሌሎች የተለያዩ ነገሮችን ይጠይቃሉ። ይህ ከአሁኑ በትክክለኛ አሠራር መስመር ካልያዘ ውሎ አድሮ በእኛም ሀገር የደሃ እና የሀብታም ሰፈር የሚለው መፈጠሩ አይቀርም ሲሉ ተናግረዋል።

በዘርፉ ባለሙያ እና ሰፊ ልምድ ያካበቱ እንዲሁም በ2013 ዓ.ም “ሪል ስቴት ኢንቨስትመንት አስተዳደር እና ግብይት” የሚል መጽሐፍ ያሳተሙት ኢንጂነር ደሳለኝ ከበደ ፤ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለው የሪል ስቴት ዘርፍ፣ ግንባታ እና ሂደት ያልታቀደ ከተማ እየፈጠረ ነው ይላሉ።

ደሳሳ እና የጭቃ ቤቶች ባሉበት አካባቢ ላይ ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች ወይም አፓርታማዎች ሲገነቡ ማየት አዲስ አይደለም። በአካባቢ ከህንጻዎቹ የሚወጣውን ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የስልክ እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ማስተናገድ የሚችል አቅም ስለሌለ የአካባቢው ማኅበረሰብ እየተጎዳ ይገኛል።

ለምሳሌ በሲኤምሲ አካባቢ በተገነቡ የሪል ስቴት ቤቶች ምክንያት በአንድ መንደር ውስጥ በርካታ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲኖሩ እየተደረገ ነው። ይህ ደግሞ በሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ ከሚያደርሰው ጫና በተጨማሪ የመኪና የመንገድ መጨናነቅ እንዲኖር እያደረገ ነው። በሪል ስቴት የሚኖሩትን የተሻለ አቅም ያላቸውን ብቻ ሳይሆን ሌሎች መንገዱን የሚጠቀሙ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ላይ ጫና እያሳደሩ ነው። ኅብረተሰቡ የመንገድ መዘጋጋትን ለመሸሸ ከለሌቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ከቤቱ መውጣት ጀምሯል።

ሪል ስቴቶች ታቅደው እና የጤና ተቋማትና እና የመሳሰሉ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ታሳቢ አድርገው ስላልተሰሩ አቅም የሌላቸው ግለሰቦች በግል የጤና ተቋማት እንዲገለገሉ ያስገድዳሉ። ይህ ደግሞ ገንዘብ ላለመክፈል ሲል በተመጣጣኝ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማት የመንግስትን ጨምሮ እንዲጨናነቁ እና እንዲጣበቡ እያደረጉ ናቸው።

ሌላው ያለ እቅድ መሰራታቸውን የሚያመለክተው የ“ሐ” ተጽዕኖ የሚባለው ነው። ትላልቅ ህንጻዎች ወይም አፓርታማዎች ተገንብተው በሆነ ቦታ ላይ ይቆማሉ። እነዚህ ቤቶች የከተማ ውበት መሆን አለመቻል ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ኅብረተሰብ መሰረተ ልማት እና የፍሳሽ ማስወገጃዎች በመጠቀም ከፍተኛ ጫና ይፈጥራሉ። ኅብረተሰቡም በዚህ የተነሳ ለተለያዩ ምሬቶች ይጋለጣል ሲሉ አብራርተዋል።

ክፍል አራት ይቀጥላል

(በመልካም አስተዳደርና የምርመራ ዘገባ ቡድን)

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You