የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሚቀጥለው ወር ለሚያካሂደው የፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈጻሚዎች ኮሚቴ ምርጫ ክልሎችንና ከተማ አስተዳደሮችን በመወከል የሚወዳደሩ እጩዎች ይፋ ተደርገዋል:: በፕሬዚዳንትነት ለመመረጥ የቀድሞ አትሌቶችን ጨምሮ፣ ሰባት እጩዎች ሲቀርቡ ለሥራ አስፈጻሚነት 21 እጩዎች ቀርበዋል:: የአትሌቲክሱን ችግር በመረዳትና ትክክለኛውን መፍትሔ ነድፎ ስፖርቱን ማን ወደ ፊት ያራምደዋል የሚለውም የብዙዎች ጥያቄ በፌዴሬሽኑ 28ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል።
ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት እና በሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የነበሩት አመራሮች የሥልጣን ዘመናቸው በመጠናቀቁ፣ ለቀጣይ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን የሚመሩት ፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ በመጪው ታኅሣሥ 12 እና 13 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል:: በዚህም በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አማካኝነት እጩዎችን የማሳወቅ ሂደት ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም የተጠናቀቀ ሲሆን ለሁለቱም የአመራር ቦታዎች የመጨረሻ እጩዎች በፌዴሬሽኑ አማካኝነት ይፋ ሆነው በተገቢነታቸው ላይ የማጣራት ሥራዎች እየተከናወነ እንደሚገኝ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል::
ለቀጣይ አራት ዓመታት በፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ለመምራት ሁለት የቀድሞ ስመጥር አትሌቶችን ጨምሮ፣ 7 እጩዎች የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል:: እጩዎቹ በአትሌቲክስ ውስጥ ባላቸው አበርክቶ ልምድና የአመራር ብቃት ተለይተው ይወዳደራሉ::
የስፖርት ቤተሰቡን ትኩረት ከሳቡትና እጩ ከሆኑት መካከል ሁለቱ የቀድሞ ገናና አትሌቶች ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት የሚያደርጉት ፉክክር አጓጊ ነው:: አትሌት ስለሺ ስህን እና አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ለመያዝ ከሚፎካከሩት እጩዎች ቀዳሚ ናቸው::
አትሌት ስለሺ ስህን ከኦሮሚያ ክልል ውክልና አግኝቶ ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትነት የሚወዳደር ሲሆን፣ አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም ደግሞ ትግራይ ክልልን ወክሎ እንደሚወዳደር ተገልጿል:: ሁለቱም እጩዎች በአትሌትነት ዘመናቸው ኢትዮጵያን በተለያዩ የዓለም መድረኮች ወክለው የተለያዩ ድሎችን ያስመዘገቡ ሲሆን አሁን ደግሞ በአመራርነት ስፖርቱን ለማገልገል ብቅ ብለዋል::
የኦሮሚያ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከቀድሞው የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ስለሺ ስህን በተጨማሪ በሥራ አስፈፃሚ አባልነት እንዲወዳደሩ ወይዘሮ ሣራ ሐሰን እና አቶ ተመስገን ነሜን እጩ አድርጎ አቅርቧል::
የትግራይ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበኩሉ የቀድሞውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያምን ለፕሬዚዳንትነት ከማቅረቡ በተጨማሪ፣ ለሥራ አስፈፃሚነት አቶ ቢንያም ምሩፅ ይፍጠርን እና ወይዘሮ ሸዋነሽ ገዛኸኝን እጩ አድርጎ ማቅረቡ ታውቋል::
በአማራ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል አቶ ያየህ አዲስ ለፕሬዚዳንትነት ፉክክሩ እጩ ሆነው ቀርበዋል:: አቶ ያየህ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል:: ቀደም ሲል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ያገለገሉትና በቅርቡ በጡረታ የተሰናበቱት አቶ ቢልልኝ መቆያ እና ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ ደግሞ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እጩነት ቀርበዋል::
አዲስ አበባ የቀድሞው የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር ሻምበል ዱቤ ጅሎን ለፕሬዚዳንትነት፣ አትሌት መሠረት ደፋርን እና ትዕዛዙ ሞሴን (ዶ/ር) ለሥራ አስፈፃሚነት እጩ በማድረግ አቅርቧል። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለፕሬዚዳንትነት ኢንጂነር ጌቱ ገረመውን መወከሉ ተረጋግጧል:: ኢንጂነር ጌቱ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ የስፖርት ክለቡ የሥራ አመራር ቦርድ አባልና የአትሌቲክስ ክለቡ ቡድን መሪነትና ሌሎች ክለቡን ጠንካራና ተፎካካሪ የሚያደርጉ ሥራዎችን እንዳከናወኑ ይታወቃል::
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኮማንደር ግርማ ዳባን ለፕሬዚዳንት እጩ አድርጎ የወከለ ሲሆን፣ ኮማንደር ግርማ የቀድሞ አትሌት፣ የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የደቡብ ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዳኞች ማኅበር ሥራ አስፈፃሚ አባል ሆነው አገልግለዋል:: ወይዘሮ ፀሐይ በቀለ እና አቶ አማኑኤል አብርሃም ደግሞ በክልሉ ለሥራ አስፈፃሚነት የተወከሉ እጩዎች ናቸው:: ጋምቤላ ክልል ራሳል ኡፒየው ኢሎክን ለፕሬዚዳንትነት እጩ አድርጎ ሲያቀርብ አቶ ቾል ቤየልንና አቶ ጋርዊች ውርን ለሥራ አስፈጻሚ አባልነት እጩ አድርጎ ወክሏል:: ለፕሬዚዳንትነትና ለሥራ አስፈጻሚነት ኮሚቴ ምርጫ እጩዎችን ከላኩት 12 ክልሎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ 7ቱ ለፕሬዚዳንትነት የሚፎካከር እጩ አላኩም::
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም