የገቢ ወጪ ንግዱ ሥነ ልክ፣ አክሪዲቴሽን፣ ቴክኖሎጂ፣ ደረጃና ተስማሚነት አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ደረጃዎችን እንዲቀዳጅ የሚያደርግ ከ5 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ውጭ የተደረገበት የጥራት መንደር መመሥረቱ ዘርፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው። ጥራታቸው የተረጋገጡ ምርቶች ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግሩ ሞተር ከመሆናቸው ባሻገር ዜጎች ወይም ሸማቾች ጥራታቸው የተጠበቀ ምርትና አገልግሎት በመገብየት ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ ስለሚሆኑ የሀገራችንን ተወዳዳሪነት ያሳድገዋል። በዚህም ኢኮኖሚው ያድጋል። የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ጫፍ ላይ ለደረሰች፤ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣናን ተግባራዊ ለማድረግ ደፋ ቀና እያለች ላለች ሀገር የጥራት መንደሩ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑ አያጠያይቅም።
የጥራት መንደሩ የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅትን ያካተተ ነው:: የጥራት መንደሩ የተቀናጀና ደረጃውን የጠበቀ የጥራት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው፤ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት በብዛት የማይገኙ የሴራሚክ፣ የባትሪ እና የሶላር ኃይል ማመንጫ መፈተኛ መሳሪያዎችን ለመፈተሽ የሚያስችሉ ላብራቶሪዎችን ጭምር የያዘ ነው::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ፤ የጥራት መሠረተ ልማት ለዘላቂ ዕድገት መሠረት መሆኑን፤ በተለይ ጥራት ያለው ምርትን ወደ ውጭ በመላክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚያስችል ፤ ጥራት ከዜጎቻችን የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር የተሳሰረ፤ የጥራት መንደሩም ደረጃቸውን የጠበቁና ጤናማ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል። የጥራት መንደሩ እጅግ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠውና በኢትዮጵያ ምርቶች ወጪ ንግድ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ፤ በዚህም የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን ጅማሮ ያበሰረ መሠረተ ልማት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል::
መንደሩ በፊዚክስ እና ተያያዥ የጥናት ዘርፎች ዝንባሌ ያላቸው ታዳጊዎችን ለማፍራትም ተጨማሪ ዕድል ይዞ መምጣቱን ፤ ከዚህ አኳያ ወላጆች ልጆቻቸው የጥራት መንደሩን እንዲጎበኙ በማድረግ ታዳጊዎች ከወዲሁ ፊዚክስ እንዲሁም የቴክኖሎጂና የምርምር ዝንባሌ ይዘው እንዲያድጉ ማድረግ እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል::
በአብነት ከእነዚህ ውስጥ የኢንቨስትመንትና የተስማሚነት ምዘና ምንነት እንመልከት። አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ወደ ተጠቃሚ ከመድረሱ በፊት ጥራትና ደህንነቱ በተስማሚነት ምዘና ሥርዓት ማለፍ የግድ ይላል:: ይህም መዋዕለ ነዋዩን ለሚያፈስ አካል ወጪን ያላግባብ እንዳያወጣ የሚረዳው ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ወጪ በምን ያህል ጊዜ የሚለውንም ይመልሳል::
የምርቶችን የጥራት ደረጃ የማረጋገጥ ተግባራት የሚከውኑ የተስማሚነት ምዘና ድርጅቶች በመንግሥትም ሆነ በግል የሚከናወን ተግባር ሆኖ የዚህን ውጤታማነት የሚያረጋግጡ አካላትም ይኖራሉ:: ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ መዋዕለ ነዋይ ለማፍሰስ ደግሞ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትና ዕውቅና ያለው የተስማሚነት ምዘና አገልግሎቶችን መጠቀም ወሳኝ ነው::
ይህም ጉዳይ የድርጅቱን ህልውና የሚወስን ይሆናል:: አምራቾች ምርቱን በሚያመርቱበት ፋብሪካ የጥራት ክትትልና ቁጥጥር ቡድን ቢኖራቸውም 3ኛ ወገን የጥራት ማረጋገጫን መያዝ ለድንበር ተሻጋሪ የንግድ መድረክ ምትክ የሌለው ሚናን ይጫወታል:: ይህንንም ማረጋገጫ መጠቀም ከወጪና ትርፍ አኳያ ሲታይ በጥቂት ወጪ ብዙ ማትረፍ ያስችላል::
ሸማቹ አካል ደግሞ በተስማሚነት ምዘና ጥራቱ የተረጋገጠና ያልተረጋገጠን ምርት ለመለየት የጥራት ማረጋገጫ ሠርተፊኬቶችን ስለሚጠቀም አምራቹ የምርቱን ጥራት በራሱ አቅም ከመፈተሹ ጐን ለጐን በነፃና ገለልተኛ 3ኛ ወገን ማስፈተሹ አሳማኝ ምስክሩ ብቻ ሳይሆን ከአላስፈላጊ ወጪና ኪሳራም ይታደጋል::
የሚያስገኘውም ጥቅም ዘርፈ ብዙ ሲሆን በዋነኛነት ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳና የምርት ጥራትን ካለመጠበቅ ከሚከሰቱ የማህበረሰብ ጤናና የአካባቢ ደህንነት ችግሮች መታደግ መቻሉ ነው:: ከዚሁ ጎን ለጎን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለው የተስማሚነት ምዘና ሥራዎችን የሚተገብሩ ተቋማትን ለይቶ አብሮ መሥራት ከሀገር ውስጥ የንግድ መድረክ ባለፈ ለዓለም አቀፉ ንግድ እንደ ድልድይ ያገለግላል:: ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ስለ ኢተምድ አንዳንድ መረጃዎችን እናንሳ።
የኢትዮጵያ ተሰማሚነት ምዝና ድርጅት /ኢተምድ/በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 6,823 አገልግሎቶችን በላብራቶሪ ፍተሻ፣ በውጪና ሀገር ውስጥ ምርት ኢንስፔክሽን፣ በሠርተፊኬሽን እንዲሁም በጂቡቲ ወደብ በኩል ለ445,651.65 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ እና ለ7,193,952.00 የምግብ ዘይት ኢንስፔክሽን አገልግሎት ሰጥቷል::
ኢተምድ ዋና መ/ቤቱን አዲስ አበባ በማድረግ በ9 የተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ቅርንጫፍ በመክፈት እንዲሁም በውጭ ሀገር በጅቡቲ ወደብና በኬንያ ላሙ ወደብ የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎቶችን በመስጠት ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገቶች አስተማማኝ መሠረት እንዲኖራቸው እና ቀጣይነታቸውን በማረጋገጥ ሀገራዊ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት በሚደረገው ርብርብ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል::
ለተቋማት አስፈላጊውን ግምገማ ካደረገ በኋላ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት የተስማሚነት ደረጃ የምስክር ወረቀት መስጠት ሌላው ተግባሩ ነው። የምስክር ወረቀት ከሰጣቸው ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ይገኝበታል። የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO 9001፡2015) ሰርተፊኬት ከኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ተቀብሏል።
ዩኒቨርሲቲው በጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ደረጃ የISO 9001:2015 ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን ማሟላቱን በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ተገምግሞ እና ኦዲት ተደርጎ ነው የምስክር ወረቀቱን ያገኘው። ብዙም ስላልተነገረለት የጥራት ፖሊሲ አስፈላጊነት እናንሳ።
የዘመነ ግሎባላይዜሽን የንግድ ማሕቀፍ ምርትና አገልግሎቶች በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ እንዲቆራኙ ምቹ ከባቢን ፈጥሯል። ኢትዮጵያም በዚህ ዓለም አቀፋዊ የንግድ ትስስር ዕድገት ተጠቃሚ በመሆን በማህበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፍ ልማትን ማረጋገጥ፣ ድህነትን መቀነስና በአካባቢ ላይ የሚደርስ ተጽዕኖን መቋቋም ይኖርበታል:: በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት የምርትና አገልግሎት ጥራትና ደህንነትን ማረጋገጥ የፖሊሲ አውጪዎች ትኩረትን በከፍተኛ ሁኔታ በማግኘት ላይ ይገኛል::
የኢትዮጵያ አምራቾች፣ ላኪዎች ወይም አቅራቢዎች በዚህ ዓለም አቀፋዊ የንግድ ትስስር ሲገቡ የሚያጋጥማቸውን ፈታኝ ሁኔታ በመረዳት መፍትሔ ማስቀመጥ ተገቢ ነው። ለዚህ ምክንያት የሚሆነው በዓለም አቀፉ ገበያ በተለይም በወጪ ምርቶች መዳረሻ ሀገራት የሚገኘው ሸማች በመረጃ የዳበረና ንቃተ ህሊናው ከፍ ያለ ከመሆኑም ባሻገር በምርትና አገልግሎቶች ጥራትና ደህንነት ቁጥጥር የሚያደርጉ ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥጥራቸውን እያጠበቁ ስለሚገኙ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በአንድ ወገን የወጪ ምርት መዳረሻ ገበያዎች በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ብዛት ያላቸውን ሀገራት በማሳተፍ፣ አገልግሎቶችና ግብዓቶች ጥራታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ በአነስተኛ ዋጋ፣ በተፈላጊ መጠን፣ በአስተማማኝ ሁኔታና በዘላቂነት እንዲቀርቡላቸው ይፈልጋሉ። በሌላ በኩል ላኪ ሀገራት ለተመሳሳይ የምርት መዳረሻ ገበያ ተመሳሳይ፣ ጥራቱና ደህንነቱ የተረጋገጠ ብሎም የተቆጣጣሪ አካላትን መስፈርት ያሟላ ምርት፣ አገልግሎት ወይም ግብዓት በማቅረብ በሂደቱ ብቸኛ ተጠቃሚ ለመሆን ውድድሩን አጠናክረውታል።
በአንጻሩ አብዛኛው የኢትዮጵያ ምርትና አገልግሎቶች ለብክነትና ብክለት የተጋለጡ፣ ጥራትና ደህንነታቸው ያልተጠበቀና ዋጋቸውም ከፍተኛ በመሆኑ ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን በሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር ላይ ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል:: በተጨማሪም በስፋት ገበያ ውስጥ የተሰራጩና ጥቅም ላይ የዋሉ ምርትና አገልግሎቶች የምርት ዱካቸው በትክክል የማይታወቅ ወይም በከፍተኛ ሁኔታ የጥራትና ደህንነት ችግር ያለባቸው ናቸው::
በዚህም የተነሳ ለህብረተሰቡ ጤንነትና ደህንነት ጉልህ የሥጋትና አደጋ መንስኤ ከመሆናቸውም በላይ በሀገራዊ ምርትና አገልግሎቶች ተወዳዳሪነት ላይ እንቅፋት መሆናቸው እሙን ነው:: ስለሆነም አምራቹና አገልግሎት ሰጪውም ሆነ አቅራቢው ቀጣይነቱ የተረጋገጠ፣ ፍላጎት መራሽ፣ ደንበኛ ተኮር፣ ምሉዕ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በመቋቋም አገልግሎቱን ማስቀጠል የሚችል፤ የመደገፍ፣ የማብቃትና ቁጥጥር ተልዕኮን ያነገበ እና የተሰናሰለ የጥራት መሠረተ ልማት ምህዳር ተግባራዊና ተደራሽ ማድረግ ዋነኛ የፖሊሲ ስልት ነው::
ይህ ማሕቀፍ ከተናበበ መዋቅራዊ አሰራርና የቴክኒክ ደንብ አፈፃፀም ጀምሮ፣ የደረጃ ዝግጅትና ትግበራ፣ ሥነ ልክ፣ አክሪዲቴሽን፣ ተስማሚነት ምዘና፣ የገበያ ክትትል፣ የአቅም ግንባታ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የተግባቦት፣ የሥልጠና እና ትምህርት ሥራዎችን በማቀናጀት የጥራት ባሕል ግንባታ እንዲያካትት ማድረግ ተገቢ ነው::
ይህንን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታን በቅጡ በመረዳት የኢትዮጵያ መንግሥት የጥራት መሠረተ ልማት ስትራቴጂ ቀርፆ ወደ ተግባር የገባ ሲሆን አገልግሎቱን የሚሰጡ አካላት ማለትም የደረጃ፣ ሥነ ልክ፣ አክሪዲቴሽን እና ተስማሚነት ምዘና ተቋማትን ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶ እያጠናከራቸው ይገኛል::
ከዚህ በተጨማሪም የገቢና ወጪ ምርትን ጨምሮ ክትትሉንና ቁጥጥሩን ለማጠናከር ሴክተር ተኮር ተቆጣጣሪ አካላት በአዲስ መልክ ተጠናክረው ከመቋቋማቸውም በላይ ሴክተሮችን የሚደግፉ የአቅም ግንባታና የምርምር ኢንስቲትዩቶች ከግሉ ሴክተር ጋር ተደጋግፈው ውጤታማ የሚሆኑበት ምህዳር ፈጥሯል።
ይህ አስቻይ ሁኔታ የተናበበ እና የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ ወደ ውጤታማነት በመቀየርና ሀገራዊ ልማቱንና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ሀገራዊ ጥረቶችን የሚያስተሳስር የጥራት ፖሊሲ መኖሩ ታምኖበታል። በዚህም የተነሳ መንግሥት የጥራት መሠረተ ልማት ሥርዓትን በጥብቅ መሠረት ላይ እንዲቆም ካለው ቁርጠኝነት በመነሳት የጥራት ፖሊሲ አዘጋጅቷል::
ፖሊሲው ሀገራዊ የልማት ግቦችን እና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሞችን ከግባቸው እንዲደርሱ ውጤታማ፣ ቀልጣፋና የተሳለጠ የጥራት መሠረተ ልማት ሥርዓትን በማስፈን በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በአቅም ግንባታ እና በቁጥጥር ላይ የተግባር ድግግሞሽን ያስቀራል::
በአጠቃላይ ተጠያቂና ተገማች አሠራርን በቀጣይነት በማሻሻል ፍትሃዊ የንግድ ውድድር እንዲሰፍን በማድረግ፣ ሀገራዊ ምርትና ምርታማነትን በዓይነት፣ በጥራት፣ በመጠን በማሳደግና እሴት በመጨመር የገቢ ምርቶችን መተካት እንዲሁም የወጪ ምርትና አገልግሎት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማስቻል ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጥራት ፖሊሲ ተዘጋጅቷል::
የፖሊሲ ሰነዱ በዋናነት የፖሊሲ አስፈላጊነት፣ የፖሊሲ ዓላማዎችን፣ የፖሊሲ ጉዳዮችንና ዝርዝር አቅጣጫዎችን እንዲሁም የፖሊሲ ትግበራ ስልቶችን ይዟል። የፖሊሲው ጠቀሜታና አስፈላጊነት ኢትዮጵያ በ2022 የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት የመሆን ራዕይን ለማሳካት የሚያስችል የ10 ዓመት የልማት እቅድ አስቀምጣለች::
ይኸውም በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በአይሲቲ፣ በቱሪዝም እና በግብርና ምርታማነትን በማሳደግ እና እሴት በመጨመር የምርት መዳረሻ ገበያን ማበራከት ታሳቢ ያደርጋል:: ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያልተጠናከረና የምርቶቹም ጥራት ዝቅተኛ መሆን በኢኮኖሚውም የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ማበርከት አልቻለም:: ወጪ ምርቶቻችን የመዳረሻ ሀገራትን/የተቀባይ ሀገራትን መስፈርቶች ማሟላት አለመቻላቸው ምርቱን ለማስወገድ የሚኖረውን ተጨማሪ ወጪ ጨምሮ ሀገራዊ ገፅታን በማጠልሸት ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል::
የኢትዮጵያ የጥራት መሠረተ ልማት እስከ አሁን ድረስ ሥራዎችን በሚገባ ለማከናወን የሚያስችል ተገቢ አቅም በመገንባት ላይ ሲሆኑ ከተቆጣጣሪና አስፈጻሚ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት አልተቻለም:: በዚህም ምክንያት ለተገልጋዮቻቸው የሚሰጡት አገልግሎት ውጤታማ አይደለም::
ከዚህ በተጨማሪም የተቆጣጣሪ አካላት ተግባራት ለጥቅም ግጭት የተጋለጡ መሆንና የኃላፊነት መደበላለቅ ለብልሹ አሠራር ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል:: በሌላ በኩል ጥራትና ደህንነቱ ያልተረጋገጠ ምርትና አገልግሎት ይዞ ወደ ገበያ ለመግባት የሚፈልገውን አመለካከቱ የተዛነፈ አምራችና አገልግሎት ሰጭ ላይ ተገቢውን ህጋዊና አስተዳደራዊ ርምጃ በመውሰድ ውድድሩ ጥራት ላይ የተመሠረተ ማድረግ አልተቻለም::
በመሆኑም የምርት ዱካቸው የማይታወቅ ወይም ኃላፊነት የሚወስድ አካል የሌላቸው ጥራትና ደህንነታቸውን ስለማሟላታቸው ማረጋገጫ የማይቀርብባቸው ምርትና አገልግሎቶች በስፋት እንዲሰራጩ ምክንያት ሆኗል:: በዚህም የተነሳ የግሉ ዘርፍ ወደማምረት ክፍለ ኢኮኖሚ በስፋት እንዳይገባና የደንበኞች ፍላጎትን የሚያረካ ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት ላይ እንዳያተኩር ከፍተኛ ጫና አሳድሯል::
ይህንን ተግዳሮት ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይሮ ፈጣን ዕድገት ለማስመዝግብና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ሀገራዊ ምርታማነትን በማሳደግ ለውጭ ገበያም ሆነ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚቀርቡት ምርትና አገልግሎቶች ጥራትና ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆን ይገባቸዋል:: መንግሥት ይህንን እውን ለማድረግ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማትን በማጠናከር፣ ተቆጣጣሪ አካላትን እንደገና በአዲስ መልክ ማዋቀር ይጠበቅበታል።
የትምህርት ተደራሽነትን በማሳደግ፣ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት እና የዘርፍ ድጋፍ ሰጪ የምርምር ኢንስቲትዩቶች በተለይም ለጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራዞች በደረጃዎች የተገለፁ የቴክኒክ መስፈርቶችንና መልካም አሠራሮችን እንዲተገብሩ ተግባራዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተልዕኮ በመስጠት ጥረት እያደረገ ቢሆንም ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን ለመገንባት ተቀናጅቶ ከመሥራት አኳያ ብዙ ይቀራል::
ከዚህ አንፃር የጥራት ፖሊሲው መኖር የልማት እንቅስቃሴዎች በሚከናወኑበት አውድ ውስጥ የሚሳተፉ አካላትን እንዲተሳሰሩና እንዲቀናጁ ምቹ መደላድልን ይፈጥራል:: ፖሊሲው በጥራት መሠረተ ልማት ሥርዓት ውስጥ የሚኖር ተግባርና ኃላፊነት የማስተሳሰሪያ ሁነኛ መሳሪያ ነው:: በሥርዓቱ ውስጥ በቴክኒክ ደንብ ማሕቀፍ የሚካተቱ ሕጋዊና አስተዳደራዊ የአፈፃፀም አሠራሮችን ከጥቅም ግጭት የነፃ እንዲሆን፣ የጥራት አገልግሎት አሰጣጥ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኘ፣ ደንበኛ ተኮርና ተደራሽ በመሆን የተግባር ድግግሞሽን በማስቀረት ውስን ሀብትን በቁጠባ ለመጠቀም የማይተካ ሚና ይኖረዋል::
ከዚህ በተጨማሪም የጥራት ፖሊሲው የቴክኒክ ደንብ ዝግጅትና ትግበራው ብሎም የማረጋገጫ ሂደቱ ለንግድ ዕንቅፋት እንዳይሆኑ አሠራር እንዲዘረጋ ያደርጋል:: የጥራት ፖሊሲ ተጠያቂነትንና ተገማች የሆነ መንግሥታዊ አሠራርን በማስፈን እና በቀጣይነት የሚሻሻል መልካም አሠራርን እውን በማድረግ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ወሳኝ ስልት ነው:: በዚህም የተነሳ የጥራት መሠረተ ልማት አገልግሎት ፍላጎት ስለሚጨምር የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ይጋብዛል::
በመሆኑም የጥራት ፖሊሲው ትግበራ የጥራት ባሕልን በመገንባት በተግባር እንዲገለፅና ልማድ እንዲሆን ስለሚያደርግ ተደራጅቶ ግዴታውን የሚወጣና ጥቅሙን የሚያስጠብቅ ሞጋች ዜጋ ወይም ሸማች ማህበረሰብን በመፍጠር ፍትሃዊ የንግድ ውድድር ያሰፍናል፣ ሀገራዊ ምርታማነት ያሳድጋል፣ ኢኖቬሽንን ያበረታታል::
በዚህም የተነሳ የምርትና አገልግሎቶች የገበያ መዳረሻዎች ይበራከታሉ፣ ኢኮኖሚያዊ አቅምን በውጤታማነት በመምራት ቀጣይነቱ የተረጋገጠ የሥራ እድል በመፍጠር ድህነትን ይቀነሳል:: ስለሆነም የጥራት ፖሊሲ ትግበራ የስኬቱ መገለጫ ሀገሪቷን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ቁልፍ ሚና የሚጫወት ፍቱን መሳሪያ ይሆናል::
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም