እሥራኤል እና ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነት አደረጉ

እሥራኤል እና የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ለ13 ወራት የዘለቀውን ውጊያ ለመቋጨት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አረጋገጡ። “በሊባኖስ እና በእሥራኤል ድንበር ላይ እየተደረገ ያለው ፍልሚያ ይቋጫል” ሲሉ ባይደን ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን የተኩስ አቁሙ ግጭትን በዘላቂነት ወደ ማቆም ስምምነት ለመድረስ ያለመ እንደሆነ አመልክተዋል። ሄዝቦላህ ስምምነቱን ከጣሰ እስራኤል ጥቃት ከመሰንዘር ወደኋላ እንደማትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተናግረዋል። በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ በስምምነቱ ላይ እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።

እስራኤል ከአየር ጥቃት በተጨማሪ ሊባኖስ ላይ ወረራ በመፈጸም የተቀናጀ ጥቃቷን አጠናክራ መቆየቷ ይታወሳል። በሊባኖስ ውስጥ በአስርተ ዓመታት ውስጥ ከታዩ የከፋ በተባለው በዚህ ጦርነት ከ3 ሺህ 823 በላይ ነዋሪዎች መገደላቸውን የሃገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንደታቀደው ትናንት ረቡዕ፣ ኅዳር 18 ቀን 2017 ዓ.ም. እንደተጀመረ ተገልጿል። በአሜሪካ አደራዳሪነት የተደረሰው ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤል በሚቀጥሉት 60 ቀናት ከሊባኖስ ደቡባዊ ክፍል ቀስ በቀስ ወታደሮቿን ታስወጣለች። በምትኩም የሊባኖስ መንግሥት ወታደሮች ስፍራውን የሚቆጣጠሩት ይሆናል።

ስምምነቱ በሄዝቦላህ እና በእሥራኤል መካከል በአውሮፓውያኑ 2006 የተከሰተውን ጦርነት የተቋጨው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 1701 በተሰኘው ውሳኔ የተመሠረተውን ድንበር መሠረት ያደረገ እንደሆነ ተገልጿል። ይህም እሥራኤል እና ሊባኖስ ከሚዋሰኑበት ሊታኒ ከተሰኘው ደቡባዊ ሊባኖስ ስፍራ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች እንዲርቁ ማድረግን ያካተተ ነው ተብሏል።

“ይህ ስምምነት በስፍራው ዘላቂ መረጋጋትን ለማምጣት እና በሁለቱም ሃገራት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በሠላም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎችን ይፈጥራል” ሲል የስምምነቱን አፈጻጸም በጋራ ይከታተላሉ የተባሉት አሜሪካ እና ፈረንሳይ ገልጸዋል።

እስራኤል፣ ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ከጣሰ ወታደራዊ እርምጃ የመውሰድ መብት እንዳላት የገለጸች ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ባይደንም ራሷን የመከላከል መብት አላት” ብለዋል።

“ሄዝቦላህ ስምምነቱን ከጣሰ እና ራሱን የሚያስታጥቅ ከሆነ ጥቃት እንፈጽማለን። በድንበር አካባቢ የሽብር መሠረተ ልማቶችን ከገነባ ጥቃት እንፈጽማለን” ሲሉ ኔታንያሁ አስጠንቅቀዋል። ከሄዝቦላህ ጋር ያለው ጦርነት መጠናቀቅ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት “በኢራን ስጋት” ላይ እንዲያተኩር እንደሚያስችለው ኔታንያሁ ተናግረዋል።

ሔዝቦላህ በጋዛ የሚገኘው ሐማስን በመደገፍ በእስራኤል ላይ ሮኬቶችን በመተኮሱ ፍጥጫው የጀመረው ባለፈው ዓመት እኤአ መስከረም 27 እንደነበር ይታወሳል።

 

አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You