ጀርመን በየዓመቱ 288 ሺህ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጓት ተገለጸ

ጀርመን በቀጣዮቹ 15 ዓመታት በየዓመቱ 288 ሺህ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጓት ተገልጿል፡፡ በአውሮፓ ቁጥር አንድ ሀብታም ሀገር በሆነችው ጀርመን የሠለጠኑ ሠራተኞች እጥረት ማጋጠሙ ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎ ሀገሪቱ የገጠማትን ሠራተኞች እጥረት ለመፍታት የስደተኞች ፖሊሲዋን ከአንድ ዓመት በፊት አሻሽላለች፡፡

የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ወይም ዶቼቪሌ የበርቴልስማን ፋውንዴሽን ጥናትን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ሀገሪቱ እስከ እኤአ 2040 ድረስ በየዓመቱ 228 ሺህ ሠራተኞች ያስፈልጓታል፡፡ ሀገሪቱ አሁን ላይ መሥራት የሚችሉት ዜጎቿ ቁጥር 46 ሚሊዮን ሲሆን በ2040 ይህ ቁጥር ወደ 42 ሚሊዮን ዝቅ ይላልም ተብሏል፡፡

እንዲሁም ከሀገሪቱ ጠቅላላ ሕዝብ መካከል መሥራት የሚችሉት ቁጥር በእኤአ 2060 ወደ 35 ሚሊዮን ዝቅ እንደሚልም ተገምቷል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ በየዓመቱ የሚወለዱ ሕጻናት ቁጥር እየቀነሰ የሚሄድ በመሆኑ እንደሆነም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡

ጀርመን ከ500 ሺህ በላይ የሠራተኞች እጥረት እንዳለባት አስታወቀች፡፡ ጀርመን የገጠማትን የሠራተኞች እጥረት ለመፍታት ከአንድ ዓመት በፊት ባሻሻለችው ሕግ ላይ የመኖሪያ ፈቃድ፣ የሥራ ፈቃድ እና የዜግነት አሠጣጥን ሁኔታ የሚያቀሉ አሠራሮችን በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡

ይሁንና የሀገሪቱ የሠራተኞች እጥረት አሁንም ችግር ላይ ነው የተባለ ሲሆን በተለይም የጤና፣ ግንባታ እና ተያያዥ ሥራዎች እጥረቱ ከፍተኛ መሆኑን አል ዐይን ዘግቧል፡፡

አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You