በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ዓለም ውስጥ በሥነ-ግጥም ችሎታቸው አንቱ ተብለው ባለቅኔ ወደመባል ደረጃ ከደረሱ ልሂቃን መካከል አንዱ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለረጅም ዓመታት ከማስተማሩም በላይ የኢትዮጵያን ቋንቋ በተለይም አማርኛን የሥነ-ጽሑፍና የመደበኛ ትምህርት ማካሄጃ ለማድረግ በነበረው እንቅስቃሴ ውስጥ ያበረከተው አስተዋፅኦ በእጅጉ ግዙፍ ነው።
የኢትዮጵያን የሥነ-ጽሑፍ፣ የሥነ-ግጥም እና የቴአትር ጥበብን ታሪክ በማጥናትና በመመራመር ረገድ ለትውልድ አቆይቶት ያለፈው መረጃ ለዘላለም ስሙ እንዲነሳ ያደርገዋል። የአያሌ ታላላቅ ሰብዕናዎች ባለቤት የሆነውን ምሁር ዛሬ በዚህ የባለውለታዎቻችን አምድ ታሪኩን አንስተን ለአበርክቶው ክብር እንሰጣለን። ይህ ሰው መምህር ፣ ገጣሚ፣ ፀሐፌ-ተውኔትና፣ ተመራማሪ ደበበ ሰይፉ ነው።
ደበበ ሰይፉ ሐምሌ 5 ቀን 1942 ዓ.ም ይርጋለም ከተማ ተወለደ። ይርጋለም በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ጥንታዊ ከተሞች መካከል አንዷ ነች። ከሀዋሳ ከተማ በአጭር ርቀት ውስጥ ያለችው ይርጋለም ሲዳማ ውስጥ ዝነኛ ከሆኑ ከተሞች መካከል ግንባር ቀደሟ ናት።
ይርጋለም ጥንታዊት ናት። ከዚያም አልፎ ጥንት የደቡብ ኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና የልዩ ልዩ ሕዝቦች መናኸሪያ ነበረች። ይህች ከተማ በ1940ዎቹ፣ 50ዎቹ እና 60ዎቹ ውስጥ ከልዩ ልዩ የደቡብ ከተሞች ተማሪዎች እየመጡ የመካከለኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚከታተሉባት ማዕከል ሆና ቆይታለች። ይርጋለም ኅብረ ሕዝብ ያለባት የኢትዮጵያ ምሳሌ ነች። እናም በዚህች ከተማ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ደበበ ሰይፉ ለኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ሰፊ ብርሃን ሰጥቶ ያለፈ የኪነት ፀሐይ ነበር።
ደበበ ሰይፉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በኮከበ ጽባሕ ት/ቤት ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ከሚታወቀውና በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ሥነ-ጽሑፍን መማር ጀመረ። ከዚያም በ1965 ዓ.ም ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ማዕረግ ተመረቀ። ቀጥሎም በዚያው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሥነ-ጽሑፍን ማስተማር ጀመረ።
እንደ ደበበ ሰይፉ ያሉ መምህራን በዚህ ትምህርት ክፍል ውስጥ መቀላቀል ሲጀምሩ ዲፓርትመንቱም እያደገና እየተስፋፋ የመጣበት ዘመን እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ምክንያቱም የጥናትና የምርምር ውጤቶች በስፋት መሠራት ጀመሩ።
ለምሳሌ ደበበ ሰይፉ የኢትዮጵያ የሥነ-ግጥም እና የሥነ-ጽሑፍ ታሪክን እና በዚህ ታሪክ ውስጥ ደግሞ ኪነታዊ አስተዋፅኦዋቸው ሰፊ የሆነውን ጉምቱ አበው ፀሐፊያንን ታሪክና የአፃፃፍ ቴክኒካቸውንም ጭምር እያጠና ማቅረብ ጀመረ። ያለፈው የጥበብ ዐሻራ ለመጪው ጥበብ የሚያቀብለውን መረጃ እየወሰደ ትውልድን በጥበብ ማስተሳሰር አንዱ ተግባሩ ነበር።
የአንዲት ሀገር ማንነት ተቀርጾ ከሚኖርባቸው ጉዳዮች ዋነኛው ሥነ-ጽሑፍ ነው። በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ደግሞ ታሪክ አለ፣ ሥነ-ግጥም አለ፣ ቴአትር አለ፣ ፍልስፍና አለ፣ አስተሳሰብ አለ፣ ፖለቲካ አለ፣ ሕዝብ አለ፣ ኧረ ብዙ ብዙ ነገሮች አሉት።
ደበበ ሰይፉ ደግሞ እነዚህን የኢትዮጵያን የማንነት መገለጫዎች ከጥንታዊ ሰነዶች ውስጥ እየፈተሸ በማውጣት ትውልድ እንዲህ ነበር፣ እንዲህም ኖሯል፣ እንዲህም አስቧል …. እያለ የዘመን ርቀታችን እንዳያለያየን ከትውልዶች ጋር ያገናኘን ነበር። ደበበ በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ የትውልድ የመሸጋገሪያ ድልድይ ሆኖ አገልግሏል።
ደበበ ሰይፉ በቀላል አነጋገር ሀያሲ ነበር። ሀያሲ ታሪክ አዋቂ ነው። ያለፈውን ከአሁኑ ጋር እያነፃፀረ የሚያስረዳ፣ የሚተነትን ባለሙያ ነው። የሂስ ጥበብን ደግሞ እንደ ሙያ ከታደሉት ሰዎች መካከል ደበበ ሰይፉ አንዱ ነው። በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሂስ ጥበብ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ሰው ቢኖር አንዱ ደበበ ሰይፉ ነው።
ደበበ ገጣሚ ነው። በአገጣጠም ችሎታው ውብ እና ማራኪነት የተነሳ ብዙዎች ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ እያሉ ይጠሩታል። ይህ በሥነ-ግጥም ዓለም ውስጥ የተሰጠው ፀጋ ከሌሎች ጉዳዮች ሁሉ ገዝፎ የሚነገርለትም ነው። ደበበ ሲነሳ ገጣሚነቱ አብሮ ብቅ የሚልለት የጥበብ ሰው ነው።
እነዚህን የግጥም ትሩፋቶቹን በ1980 ዓ.ም የብርሃን ፍቅር በሚል ርዕስ ሰብስቦ አሳትሟቸዋል። በዚህች የብርሃን ፍቅር በተሰኘችው የሥነ-ግጥም ስብስቡ መጽሐፍ ውስጥ ቀደም ሲል በተማሪነት እና በአስተማሪነት ዘመኑ ሲፅፋቸው የነበሩትን ግጥሞች የምናገኝበት ድንቅ መጽሐፉ ነች።
ከዚህች መጽሐፉ በተጨማሪ በ1992 ዓ.ም በሜጋ አሳታሚ ድርጅት አማካይነት ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ በሚል ርዕስ ሁለተኛዋ የሥነ-ግጥም መጽሐፉ ለንባብ በቃች። ነገር ግን በዚህ ወቅት ደበበ በሕይወት አልነበረም። ሥራዎቹ ዘላለማዊ ናቸውና እርሱ በሕይወት በሌለበት ወቅትም የትውልድ ሀሴት በመሆናቸው ይታተሙለታል። እናም ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ በምትሰኘው መጽሐፉም የደበበን የሥነ-ግጥም ርቀት እና ጥልቀት የምናይበት ሥራ ነው።
ደበበ ሰይፉ በሥነ-ግጥም ተሰጥኦው እና በሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጐልቶ ከሚነሱ ከያኒያን መካከል አንዱ መሆኑን ቀደም ያሉት ሃያሲያን ጽፈውታል።
የደበበ ችሎታ በዚህ ብቻም አያበቃም። ደበበ የቴአትር ጥበብ መምህር ከመሆኑም በላይ በዘርፉ ውስጥ ግዙፍ የሚባል አስተዋፅኦ አበርክቶ አልፏል። ደበበ በመድረክ ላይ የሚሰሩ ቴአትሮችን እና የቴአትር ጽሑፎችን የያዟቸውን ሃሳቦች በመተንተን እና ሂስ በመስጠት ለዘርፉ እድገት የበኩሉን ሚና ተጫውቷል።
ደበበ የቃላት ፈጣሪም ነው። ለምሳሌ በቴአትር ዓለም በአጠቃላይ በሥነ-ጽሑፉ ዓለም ውስጥ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጠሪያ የሆኑ ሙያዊ ቃላትን ወደ አማርኛ በማምጣት አቻ የሆነ የአማርኛ ትርጉም በመስጠት ይታወቃል። በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ መጠሪያ የሆኑትን ለምሳሌ ገፀ-ባህሪ፣ ሴራ፣ መቼት፣ ቃለ-ተውኔት ወዘተ እየተባሉ የሚገለፁትን መጠሪያዎች የፈጠረው ደበበ ሰይፉ ነው።
– Character የሚለውን የእንግሊዝኛ መጠሪያ “ገፀ-ባህሪ” በማለት አቻ ትርጉም ሰጥቶታል፣
– Setting የሚለውን የእንግሊዝኛ መጠሪያ በውስጡ ጊዜ እና ቦታን መያዙን በመረዳት ወደ አማርኛ ቋንቋ ‘መቼት’ ብሎ ደበበ ተረጐመው። መቼት ማለት ‘መች’ እና ‘የት’ ማለት ሲሆን፤ ጊዜንና ቦታን ይገልፃል።
– Dialogue የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ተዋናዮች በትወና ወቅት የሚናገሩት ሲሆን፤ ይህን Dialogue የተሰኘውን ቃል ወደ አማርኛ አምጥቶት ቃለ-ተውኔት በማለት የተረጐመው ደበበ ሰይፉ ነው።
ደበበ እነዚህንና ሌሎችንም ሥነ-ጽሑፋዊ ቃላትን በመፈጠር በትውልዶች አንደበት፣ አእምሮ እና ብዕር ውስጥ ለዘላለም እንዲኖር ያደረገ ጥበበኛ ነው።
ደበበ ሰይፉ ለዚሁ ለቴአትር ትምህርት ዘርፍ ካበረከታቸው አስተዋፅኦዎች መካከል ለትምህርቱ መጐልበት ይረዳ ዘንድ በ1973 ዓ.ም መጽሐፍም አሳትሟል። መጽሐፏ የቴአትር ጥበብ ከፀሐፌ-ተውኔቱ አንፃር የምትሰኝ ርዕስ የያዘች ሲሆን፤ ለሀገራችን የቴአተር ሙያተኞች እንዲበራከቱ እና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሰፊ ድርሻ አበርክታለች።
ደበበ በዚሁ በቴአትር ዘርፍ ውስጥ የተፃፉ የንባብ መጽሐፍት ያለመኖራቸውን ክፍተት ተገንዝቦ ያንን ክፍተት ለመሙላት ሙያዊ ጥሪውን የተወጣ ባለሟል ነው።
ደበበ ሰይፉ ፀሐፌ – ተውኔትም ነው። በርካታ ተውኔቶችን ፅፎ ለመድረክ አብቅቷል። አንዳንዶቹ ደግሞ ለምሳሌ ክፍተት የተሰኘው ተውኔቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለበርካታ ጊዜያት ታይቶለታል። በዚህ ክፍተት በተሰኘው የደበበ የቴሌቭዥን ድራማው ላይ በመተወን ተፈሪ ዓለሙ፣ አለማየሁ ታደሰ እና ሙሉአለም ታደሰ ድንቅ የሆነ ብቃታቸውን አሳይተውበታል።
ደበበ ሰይፉ ከፃፋቸውና ከተረጐማቸው ተውኔቶች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡-
ከባህር የወጣ ዓሣ
እናትና ልጆቹ
እነሱ እነሷ
ሳይቋጠር ሲተረተር
የህፃን ሽማግሌ
ማክቤዝ እና
ጋሊሊዮ ጋሊሊ ይገኙበታል።
ከእነዚህ ሌላም በ1973 ዓ.ም ማርክሲዝምና የቋንቋ ችግሮቹ የሚል መጽሐፍ ከማሳተሙም በላይ በ1960 ዓ.ም ያዘጋጃት የሦስት አጫጭር ልቦለዶች መድብል የሆነችው ድርሳኑ ትጠቀሳለች።
ደበበ ሰይፉ ከእነዚህ ከረቀቁ እና ከመጠቁ ምሁራዊ አስተዋፅኦው በተጨማሪ በበርካታ ኪነ-ጥበባዊ ጉዳዮች ላይም ዐሻራውን ያሳረፈ ነው። ለምሳሌ በቀድሞው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ መስፋፋት እገዛው ሰፊ ሆኖ ኖሯል። በኢትዮጵያ ሬዲዮ ውስጥም የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ውስጥ ያሉትን ፕሮግራሞች አማካሪ ሆኖ ሰርቷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የቋንቋዎች ተቋም ጆርናል አሳታሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኖ አገልግሏል። ደበበ ሰይፉ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆኖ ሰፊ ድርሻ አበርክቷል። ደበበ ሰይፉ በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ዓለም ውስጥ ትልቅ ድርሻውን አበርክቶ ያለፈ የትውልድ ምሳሌ ነው።
ግን ሁሉም ነገር እንዳማረበት እስከ መጨረሻው አይሄድምና ደበበ ህመም ገጠመው። መናገርም አቆመ። ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ በአጠቃላይ ለኪነ-ጥበቧ እድገት የአንበሳውን ድርሻ ያበረከተው ደበበ ሰይፉ ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። እኛም ይህንን የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ባለውለታ ነፍስ ይመር ለማለት እንወዳለን።
ለዚህ ጽሑፍ በምንጭነት የተለያዩ ድረ ገጾችን ተጠቅመናል!
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም