አሕጉርን የተሻገረ የአዕምሮ ፈጠራ

ወጣትነት የትኩስነት መገለጫ ነው። ይህ ዕድሜ እንደ ባለቤቱ ማንነት ይወሰናል። ወጣትነትን በወግ በአግባቡ የተጠቀመው ቢኖር የሥራውን ፍሬ ለማየት አይዘገይም። ‹‹ወጣት የነብር ጣት›› ይሉትን ምሳሌ ተግብሮ ስለነገው ይሮጣል። ከቁምነገር ተኳርፎ፣ ከጊዜ ተቀያይሞ በዋዛ ፈዛዛ የሚያሳልፈው ካለ ደግሞ ያለአንዳች የሕይወት ዐሻራ ከዕድሜው ማምሻ ይደርሳል።

ሃሳባቸውን በወጉ ከሚተገብሩ ወገኖች መደብ ይመዘናል። ለእሱ ወጣትነት ማለት ዕድሜ ብቻ አይደለም። ሄኖክ አማኑኤል ገና አፍላ ወጣት ነው። ጊዜያቸውን በአግባቡ ከሚጠቀሙ ወጣቶች አንዱ ነው፣ ለሄኖክ እያንዳንዷ ሰከንድና ደቂቃ ከሥራ ጋር ታልፋለች፣ አዕምሮው ብሩህና ፈጣን በመሆኑ ችግሮችን ለመለየትና መፍትሔ ለመፍጠር ቅርብ ነው፡፡

ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማ ለዚህ ወጣት ማንነት ድርሻው የጎላ ነው። ተወልዶ አድጎበታልና ዕለት በዕለት የሚያስተውላቸው ችግሮች አዕምሮውን ለመፍትሔ አዘጋጅተዋል። ሄኖክ ሁሌም የሚያስተውላቸውን ችግሮችን አይቶ ማለፍ፣ ሰምቶ መቀመጥ አልወደደም። አንዳንዴ እናቱ እንጀራ መጋገር ሲጀምሩ መብራት ሲጠፋባቸው ያያል፣ በምድጃ ምግብ ሲያበስሉም እንዲሁ።

ይህ እውነት ለወጣቱ ሄኖክና ለሌሎች ስሜቱ እኩል አይደለም። አብዛኞች መብራቱ ተመልሶ እስኪመጣ ይጠብቃሉ። ሌሎች ደግሞ በእንጨትና በከሰል መጠቀምን ይመርጣሉ። በብዙ ቦታዎች መብራት ሲጠፋ ሥራ ይቋረጣል። ችግሩ አሳሳቢና የሰፋ ነው። ሄኖክ ግን ይህ አጋጣሚ ሲደጋገም ማየትን አልወደደም። ለእናቱ ብቻ ሳይሆን ለብዙኃን የሚበጅ መፍትሔ ለመፍጠር አዕምሮውን ተጠቀመበት፡፡

ሄኖክ የትውልድ አካባቢውን ጨምሮ ዙሪያ ገጠሩ በቂ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንደማያገኝ ያውቃል። ከሰሐራ በታች ያሉ ሀገራትም የዚህ ኃይል እኩል ተጠቃሚዎች አይደሉም። ይህ አይነቱ ሐቅ ሁሌም ውስጡን ሲጠይቀው ኖሯል። በአንድ ወቅት ግን ለጥያቄዎቹ ምላሽ ይሆን ዘንድ ራሱን አዘጋጅቶ ተነሳ። አዕምሮውን ከእጆቹ ጥበብ አዛምዶም ሙከራውን ተገበረው።

የሄኖክ የትምህርት መስክ ከኤሌክትሪክ ሙያ ጋር ይገናኛል። ለቴክኒክ ሥራ ቅርብ መሆኑም በተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተመራጭ ሲያደርገው ቆይቷል። ቀደም ሲል በተወዳደረባቸው ሰባት አይነት የቴክኖሎጂ ሥራዎች በሃገር አቀፍና በአሕጉረ አፍሪካ የአንደኝነት ደረጃን አግኝቶ ነበር፡፡

ሄኖክ በወቅቱ 61 ሀገራት በተወዳደሩበት የዓለም አቀፍ ዞን ዘጠነኛ በመውጣት ተመዝግቧል። ይህ ውድድር በዳኞች እይታ ብቻ የሚወሰን እንዳልሆነ ይታወቃል። በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ጭምር ታግዞ ውጤቱ የሚለይበት ነበር፡፡

ሄኖክ ከአፍሪካ ቀዳሚውን አሸናፊነት ያስመዘገበው ኢትዮጵያን ወክሎ በተገኘበት የሀገረ ቻይና ውድድር ላይ ነበር። በወቅቱ በተጎናፀፈው ድልም በሀገሪቱ መንግሥት ነፃ የትምህርት ዕድል ተሰጥቶታል። የዚህ ወጣት ብርታትና ጥረት ታዲያ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዓይኖች ለመግባት አልዘገየም። እሱን ጨምሮ መሰል የአዕምሮ ፈጠራ ያላቸው ወጣቶችን የሚያጣምር አጋጣሚ ተፈጠረለት፡፡

የሙያ እርሾው በከንቱ ያልባከነበት ሄኖክ እሱን ከሚመስሉት ወጣቶች ጋር በተገኘ ጊዜ በአዕምሮው አኑሮት የቆየውን የፈጠራ ሙያ ለመተግበር ዕድሉን አገኘ። ሄኖክ በመብራት መጥፋትና መቆራረጥ የሚቸገረውን የገጠርና ከተማ ነዋሪ ሕይወት አልዘነጋም። ጓደኞቹም ቢሆኑ ቴክኖሎጂውን ቀዳሚ ለማድረግ የአዕምሮ ጥበባቸውን ሲያዋጡ ከልባቸው ሆነ። ጥምር ዕውቀታቸውን በአንድ ገምደው ጄኔሬተር ለመሥራት ወሰኑ። ይህ መፍትሔ ሰጪ የመብራት ጄኔሬተር ፍጹም ድምፅ አልባ ነው። እንደተለመደው ዓይነትም አካባቢን በጭስ መርዝ አይበክልም፡፡

ሄኖክ እንደሚለው ጄኔሬተሩ ለገጠርና ከተማ አገልግሎት ይውላል። የገጠር ነዋሪዎች በ2ሺህ 500 ኪሎዋት ቻርጅ አድርገው እንዳሻቸው ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ለከተሜዎቹም መብራት በጠፋባቸው አራት ማይክሮ ሰከንድ ውስጥ ጄኔሬተሩ ፈጥኖ ይተካላቸዋል። መብራት በመጣ ግዜም ያለአንዳች የድምፅ ጩኸት ተመልሶ ይዘጋል፡፡

ራሱን በራሱ ኃይል የመሙላት ሂደት ያለው ይህ ጄኔሬተር በአውቶማቲክ ቴክኖሎጂ የተዋቀረ ነው። የሚያወጣውን ኃይል ሳይቀር መልሶ የመሰብሰብ አቅምን ጭምር ተችሯል። ለቤትና ለቢሮ አገልግሎት የተፈለገውን ያህል ጠቀሜታ ለመስጠትም ጉልበቱን አይሰስትም፡፡

ሄኖክና ሁለት ጓደኞቹ ይህ የቴክኖሎጂ ጅማሬ ቀጣይ ዕቅዳቸውን ለማስፋት መነሻቸው ነው። ወደፊት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀስ መኪናን ለመሥራት ውጥን ቋጥረዋል፡፡

ጓደኛሞቹ በእጃቸው ያለውን የቴክኖሎጂ ውጤት በማስፋት በብዛት የማምረት ዕቅድ አላቸው። ለዚህም አስቀድመው ንድፉን በማስቀመጥ በቀን ከ50 በላይ መኪኖችን ማምረት የሚያስችላቸውን አቅምና ቴክኖሎጂ ወጥነዋል። ሄኖክ ይህን ቀጣይ ዕቅድ የሚናገረው በእርግጠኝነት ነው። መንግሥት ድጋፍ ሆኖ ቢያግዛቸው ደግሞ ወደ ምርት ለመግባት መንገዱ ቀላል እንደሚሆን ያምናል፡፡

ወጣቱ የቴክኖሎጂ ፈጣሪ የእሱና የጓደኞቹ ዕቅድ በሀገር ቤት ብቻ የተወሰነ አለመሆኑን ይናገራል። የአዕምሯቸውን ውጤት ለአፍሪካውያን ጭምር የማድረስ ዓላማ አላቸው፡፡

ሄኖክ የተወዳደረባቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች በትምህርት በመታገዝ ዕድሉን ያሰፉለታል። ለዚህም የተሰጠው ዓለም አቀፍ የእውቅና ሰርተፊኬትና ትምህርቱን ሲያጠናቀቅ በቻይና እንዲማር የተፈቀደለት የሁለተኛ ዲግሪ ዝግጅት አስተዋፅዖ የጎላ እንደሚሆን ዕምነቱ ነው፡፡

ሄኖክ ዛሬ ለደረሰበት የቴክኖሎጂ እመርታ ቤተሰቦቹ ሰፊ ድርሻ አላቸው። ሀሳቡን በመደገፍ፣ ሥራውን በማበረታታት ለፍሬያማነቱ ጠጠር ጥለዋል። እነሱ ገና በጠዋቱ ላስተዋሉበት ልዩ ክህሎት ፊታቸውን አላዞሩም። ሥራው የሚፈልገውን ሁሉ እያቀረቡ እጁን ይዘው አራምደውታል፡፡

ወጣቱ ሄኖክ ስለነገ የሰነቀው ሕልም ታላቅና ሰፊ ነው። እሱና ጓደኞቹ በራሳቸው አቅም ካምፓኒ አቋቁመው ቴክኖሎጂውን ለማስፋትና አዲስ አቅም ለመጨመር ዕቅድ ይዘዋል። ከውጭ ሀገራት በውድ ዋጋ የሚገዙ ግብዓቶችን በራስ አቅም በመተካትም ታሪክ የመቀየር ዓላማ አላቸው፡፡

እነሄኖክ ማኅበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም ባደረጉት ጥናት የእነሱን ቴክኖሎጂዎች የሚፈልጉ ከሦስት ሺህ አምስት መቶ በላይ ግለሰቦችና ተቋማት ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው አረጋግጠዋል፡፡

የእነሱን ፍላጎት ጨምሮ ለሌሎች ወገኖች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ያላቸው ሄኖክና ባልንጀሮቹ በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ ውደ ውጭ ሀገራት ጭምር ቴክኖሎጂውን ለማድረስና ለመሸጥ ተዘጋጅተዋል፡፡

ሄኖክ ለአንድ ቴክኖሎጂ መፈጠር ምክንያቱ ከችግሮች መነሳት መሆኑን የራሱን ተሞክሮ ዋቢ አድርጎ ይጠቅሳል። ለእሱ ጄኔሬተር መፈጠር የመብራት መጥፋትና የብዙኃን ችግሮች ቁጭት ፈጥሮ ከውጤት አድርሶታል። እሱን መሰል ወጣቶች ማንኛውም የቴክኖሎጂ ሀሳቦች ቢኖራቸው በዝምታና በቸልተኝነት እንዳያልፉት የሚመክረው በተለየ አትኩሮት ነው። ወጣት ሄኖክ ባለ ድንቅ አዕምሮ፤ አሕጉር ተሻጋሪው ተሸላሚ ፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

 አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You