ታምራት ተስፋዬ
የኖቭል ኮሮና ቫይረስ /ኮቪድ 19/ ወረርሽኝ ደሀ ሀብታም፣ አዋቂና ታዋቂ፣ መሪና ተመሪን ዘርንና የቆዳ ቀለምን ሳይለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሚሊየኖችን በማጥቃትና ሚሊየኖችን ሕይወት በመቅጠፍ ጨካኝ መሆኑን ማስመስከሩ ቀጥሏል።
አገራት የተቃጣባቸውን የቫይረስ ወረራ ለመመከት እና ጉዳቱን ለመቀነስ በርካታ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎችን ከመከወን አልቦዘኑም። ቫይረሱ በትንፋሽና በንክኪ በቀላሉ መተላለፉም ድካማቸውን መና በማስቀረት በሁሉ ረገድ ከባድ ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል።
የቫይረሱን መራባት ለመግታት መፍትሄ ይሆናል ተብሎ ይፋ የሆነው ክትባትም በመላ ዓለም በቂ በሆነ መልኩ ተደራሽ መሆን አልቻለም። ምንም እንኳን ክትባቶች በአይነትም ሆነ በመጠን እየጎለበተ ቢመጡም በዓለም አቀፍ ደረጃ በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙና ህይወታቸውን የሚነጠቁ ሰዎች ቁጥር ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልተስተዋልም።
አገራትም ዜጎቻቸውን ከአስከፊው ቫይረስ ለመታደግ በተሻለ አደረጃጀትና የቴክኖሎጂ ብቃት የኮቪድ ምርመራን በስፋት በማካሄድ ላይ ተጠምደዋል። ይህም የመከላከል እና የመቆጣጠር ጥረትን በማገዝ የቫይረሱን መራባት በመግታት የዜጎችን ህይወት በማዳን ረገድ ጉልህ ሚና እያበረከተ ይገኛል።
ይሁንና የኮቪድ ምርመራ የሚያደርጉ ሰዎችም ከአፍም ሆነ ከአፍንጫ ናሙና በሚወሰድበት ጊዜ ምቾት የማይሰጡ ሁኔታዎች እንዳሉ ሲገልፁ ይደመጣል። የጤና ምሁራንም፣ በሂደቱ መካከል የሚሰጡ ግብረ መልሶች ናሙናው በትክክል እንዳይወሰድ ተግዳሮት መሆኑን ይጠቁማሉ።
ከቀናት በፊት ታዲያ ‹‹ይህን ችግር በእጅጉ ያቃልላል፣ ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ ከዋሉት የተሻለ ነው›› የተባለለት የኮቪድ ምርመራ ናሙናን ከአፍንጫ ለመውሰድ የሚያስችል ፈጠራ ይፋ ሆኗል። አዲሱ ፈጠራ ያስተዋወቀውም ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ ለተለያዩ የጤና ተቋማት ለኮቪድ 19 ምርመራ ናሙና መውሰጃ የሚያገለግሉ ምርቶችን ሲያቀርብ የቆየው ኦፒቲ የተባለ ኩባንያ መሆኑ ታውቃል።
ኩባንያው ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ አዲስ በቀላል መንገድ ከአፍንጫ ለመውሰድ የሚያስችል የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እና ናሙና መስጫ መንገድ ለማስተዋወቅ የተለያዩ የህክምና ተቋማት ምርምሮች ማድረጉም ታውቋል።
አዲስ ከአፍንጫ ናሙና መውሰጃም‹‹ በጣም ስስ እና ፀጉር መሰል ቅርጽ ያላቸው ርጥበት ሰብሳቢ ቁሶች ያሉት፣ ከነባሩ በተሻለም በርካታ ናሞናዎችን ሸብሽቦ ማስቀረት የሚቻል ነው›› ተብሏል። ፈጠራውም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ በሆስፒታሎች አካባቢ የሚስተዋሉ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እና ናሙና መስጫ እጥረቶች በማቃለል ረገድ ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር ታምኖበታል።
እስካሁን ባለው ሂደትም ከ 800,ሺህ በላይ ናሙና መውሰጃዎችን ለጤና ተቋማትና የቤት ለቤት ምርመራ ለሚሰሩ ተቋማት በማከፋፈል የግብአት እጥረቱን ለማገዝ መሞከሩም ታውቋል። በዚህም ቫይረሱን በመከላከል እና በመቆጣጠር የሚከናወኑ ጥረቶች በማገዝ ረገድ ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን ተመስክሮለታል።
ኩባንያው በአሁን ወቅትም በቀን ከ80 ሺህ በላይ ናሙና መቀበያዎችን የሚያመርት መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በቀጣይም ከጤና ተቋማት እና ድርጅቶች ጋር በመደመር የማምረት አቅሙን እና የምርት ተደራሽነቱን ለመጨመር እንደሚተጋ ታውቋል። መረጃው ኤም አይቲ ኒውስ ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 5/2013