
ለስታርትአፖች ምቹ ሥነ ምህዳር እየተፈጠረ መሆኑ፤ የስታርትአፖች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል። እንዲሁም አቅማቸው እንዲጎለብትና ነጥረው እንዲወጡ እያገዛቸው ይገኛል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በቅርብ ጊዜ ይፋ በተደረገው የኢትዮጵያ ግሎባል ሥነ ምህዳር ሥርዓት /ሲስተም/ 490 በላይ ስታርትአፖች ገብተዋል። ይህ የስታርትአፖች አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበት መምጣቱን ያሳያል።
ስታርትአፖች አቅማቸውን እያሳደጉና እያጎለበቱ ትልቅ አቅም እየፈጠሩ ነጥረው በመውጣት ላይ መሆናቸውን በተያዘው በጀት ዓመት በግንቦት ወር መጀመሪያ በኢትዮጵያ በተዘጋጀው ከምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ መመልከት መቻሉ ተገልጧል። በተለይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲደግፋቸው ከነበሩ ስታርትአፖች መካከል የተመረጡ 30 ያህሉ እንዲሳተፉ የተደረገበት እንደነበር ተገልጧል።
በዛሬ ‹‹ሳይንስና ቴክኖሎጂ›› አምዳችን ምቹ ሥነምህዳር መፈጠር ስታርትአፖች በምን መልኩ እያገዘ ነው? ስታርትአፖች ከምን ተነስተው የት ደረሱ? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ልናስቃኛችሁ ወደደን።
ወጣት ሮቤል ፍቅር ይባላል። ‹‹ያስፈልጋል ኢትዮጵያ›› መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው። ‹‹ያስፈልጋል ኢትዮጵያ›› የተሰኘው ድርጅት እ.ኤ.አ 2019 መጨረሻ አካባቢ የተመሰረተ ሲሆን፤ በልዩነት ተፈጥሮአዊ (ኦርጋኒክ) የሆኑ ምርቶችን በየትኛውም ጊዜ የትኛውም ቦታ ላይ ያለገደብ ለማግኘት የሚያስችል መድረክ (ፕላትፎርም) ነው። ፕላትፎርሙን ከሌሎች የሚለየው ተፈጥሮአዊ (ኦርጋኒክ) ነገሮች የሚገኙበት ብቻ ሳይሆን፤ አሰራሩ /ሲስተሙ/ በራሱ ለየት ያለ ነው የሚለው ሮቤል፤ በኦንላይን የታዘዙ ምርቶች ወደ ተጠቃሚው የሚደርሱበት ዘዴዎቹም አሁን ላይ ከሚታወቀው በተለየ መልኩ አገልግሎት የሚሰጥበት መሆኑን ያብራራል።
ትዕዛዝን ለማድረስ የሚጠቀምባቸው የትራንስፖርት መንገዶችን ጨምሮ አካባቢው አሉታዊ ተጽዕኖ የማያስከትሉ እንዲሆኑ አድርጓል። ለዚህም በኤሌክትሪክ በሚሰሩ ሞተር ሳይክል በመጠቀም ትዕዛዞች ያደርሳል፤ ድርጅቱ ምርቶቹን ለማሸግ የሚጠቀምባቸው ቁሳቁሶችም እንዲሁ የተመረጡና ከፕላሰቲክ ነጻ የሆኑ አካባቢ ላይ ብክለት የማያስከትሉ እንዲሆኑ አድርጓል። ጥራታቸውን የጠበቁ ስለመሆናቸው የተመሰከረላቸው መሆናቸው ተረጋግጦ ጥቅም ላይ ይውላሉ ይላል።
በተጨማሪ በጎ ፈቃደኞችን የሚያበረታታ የልዩ ቅናሽ አሰራር ያለው ነው ሲል የሚናገረው ሮቤል፤ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና በሌሎች አካባቢዎች በጎ ፈቃደኛ ሆኖ የሚሠራ ሰው ልዩ ቅናሽ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው የሚለው ሮቤል፤ ልዩ ቅናሽ ማድረጉ በጎ ፈቃደኞች ለማበረታታትና በጎ ሥራ በተሻለ መልኩ እንዲሰፋ ለማድረግ ታስቦ እየተሠራ መሆኑን ይገልጻል።
ፕላትፎርሙ ቢዝነስ ከቢዝነስ ወይም ቢዝነስን ከደንበኛ ጋር በአንድ ያስተሳሰረ መሆኑንም ጠቅሶ፤ አማዞንን ጨምሮ ባሉት ሌሎች ፕላትፎርሞች ቢዝነስ ከቢዝነስ አልያም ቢዝነስን ከደንበኛ ለማገናኘት ሲፈለግ ሲስተሙ የግድ ከአንዱ ወደ አንዱ መቀየርን ይጠይቃል። ‹‹ያስፈልጋል ኢትዮጵያ›› ግን ሁለቱንም በአንድ ያጣመረ በመሆኑ በኦንላይን ግብይት እየተካሄደ በቀጥታ እንደደንበኛም እንደ ድርጅት መሥራት ይቻላል ብሏል።
በሀገሪቱ ቀደም ሲል ድርጅት ሆኖ እንኳ ኢኮሜርስ መጠቀም ያስቸግር እንደነበር አንስቶ፤ ከሀገሪቱ የፋይናንስ ሕግ ጋር አብሮ መሄድ የሚያስችል አሰራር እንዲኖር በማድረግ ሁሉም ነገር በሲስተሙ እንዲያልቅ የተደረገ መሆኑን ይገልጻል። በሌላ በኩል ፋይዳ መታወቂያ ጋር ሳይቀር ለማስተሳሰር የተቻለ እንደሆነ ያመላክታል።
አንድ ሰው ለስጦታ የሚሰጠው እቃ እንዲገዛ በማድረግ አብሮነት ለማበረታት የተደረገ ጥረት መሆኑን ጠቅሶ፤ በተጨማሪ አብሮነትን የሚያበረታታና አሳታፊ የሆነ አሰራር እንዲኖር የሚያደርግ ነው። በተመሳሳይ ከድርጅቱ ፕላትፎርሙን ተጠቅሞ እቃ የሚገዛ አንድ ደንበኛ ለሚፈልገው የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ ማዕድ ማጋራት እና የመሳሳሉ እንዲሰጥለት የሚፈልገው ያህል ገንዘብ መስጠት የሚችልበት አሰራር የተዘረጋለት ነው ሲል አስረድቷል።
አንደ ሮቤል ገለፃ፤ በተለየ መልኩ የወር ደመወዝተኞች ደመወዝ እስኪደርስ የሚፈልጉት አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያደርግ አሰራርም ያለው ነው ። ደመወዝ ለመድረስ ሰባት ቀናት ሲቀሩት አንድ እቃ ለመግዛት የሚፈል ደሞዝተኛ ቢኖር ከድርጅቱ ጋር በሚያደርገው የሰባት ቀናት ስምምነት የሚፈልገው በብድር መልኩ ሊወሰድ ይችላል። ደንበኝነቱ እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ እንደሚከፍል ገልፆ መውሰድ የሚችልበት አሰራር ተዘርግቷል።
ፕላትፎርሙ የብድር አሰራር/ክሬዲት ሲስተም/ የራሱ አሰራር ያለው ሲሆን፤ ደንበኛ ስለመሆኑ የሚጠይቀው የብድር እቃ ከታየ በኋላ ከዚህ ቀደም ደንበኛ መሆኑንና የምን ያህል እቃ ወሰዶ ነበር? የሚለው በሲስተሙ መመልከት ያስችላል። ያንን መሰረት በማድረግ አሁን ለሚወሰደው ብድር የሚወሰን ይሆናል። ለአብነት ቀደም ሲል የአስር ሺ ብር እቃ የወሰደ አንድ ደንበኛ ብድር መውሰድ ቢፈልግ የአስር ሺ ብሩን ሁለት በመቶ ግምት ያለው እቃ ያለምንም መያዥ ሊወሰድ ይችላል። ሆኖም በብድር የወሰደውን እቃ ገንዘብ በተቀመጠው ጊዜ ገድብ መመለስ አለበት። የሚከፍልበት ቀን ገደብ የሚያሳልፍ ከሆነ ደግሞ ወለድ እንዲከፍል የሚደረግበት አሰራር እንዳለ አመላክቷል።
ፕላትፎርሙ የተለያዩ የክፍያ አማራጮች ያቀረበ ሲሆን፤ ሲቢኢ ሞባይል ባንኪንግ፣ ቴሌ ብር እና በትዕዛዙ በደረሰ ሰዓት ወዲያው ገንዘቡን መክፈል የሚቻልበት ነው።
በተጨማሪ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አብረውን እንዲኖሩ ተደርጓል፤ የፕላትፎርሙ ተጠቃሚዎች ተቋማትንም ሆነ ሰዎች ለመርዳት ሲፈልጉ በቀጥታ በማስተር ካርድና በቪዛ ካርድ መርዳት የሚችሉበት ሲስተም አለው ሲል ተናግረዋል።
ድርጅቱ ከተመሰረተ አምስት ዓመታት የሆነው ስታርትአፕ ድርጅት ቢሆንም ቀደም ሲል ከነበሩት ተግዳሮቶች የተነሳ በተፈለገው ፍጥነት መጓዝ እንዳልቻለ የሚገልጸው ሮቤል፤ የስታርትአፕ ሥነ ምህዳሩ እየሰፋ በመምጣቱ ድርጅቱ በየጊዜው አሰራሮች እያሻሸለ እንዲሄድ ምቹ እድል እንደፈጠረለት ይገልጻል።
አሁኑ ወቅት ለስታርትአፖች የተፈጠረው ምቹ ሥነምህዳር ድርጅቱ የተመሰረተበት ዓላማ ከግብ እንዲደርስና ነጥሮ እንዲወጣ እያደረገ መሆኑን ጠቅሶ፤ በቀጣይ ከዚህ በላይ በመሥራት ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ጥረት እያደረገ መሆኑን አመላክቷል።
ሌላኛው ወጣት ጌትነት ዘመነ ይባላል። የእፎይ ፕላስ ሀውሲንግ ሶሉሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው። ስታርትአፑ እ.ኤ.አ በ2020 የተመሰረተ ሲሆን፤ ድርጅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አጠቃላይ መኖሪያ ቤቶችን የሚያስተሳስር ዘመናዊ የሕብረተሰብ አስተዳደር ሥርዓት/ስማርት ኮሚኒቲ ማኔጅመንት ሲስተም / ለመፍጠር አልሞ ይሠራል።
ጌትነት መተግበሪያ ለመሥራት ስላነሳሳው ምክንያት ሲናገር፤ አብዛኛውን ጊዜ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ባሉ ነዋሪዎችና ማኅበራት መካከል ከፍተኛ የግልጸኝነት ችግር አለ። ይህንን የግልፅነት ችግር መፍታት የሚቻለው አሰራሩን በቴክኖሎጂ በመታገዝ መፍታት ሲቻል እንደሆነ ስለገባው ወደዚህ ሥራ ለመግባት አስቧል።
በአዲስ አበባ ከተማ አፖርትመንቶችን ጨምሮ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና ኮምፓውንድ የሆኑ የመኖሪያ ግቢዎች እየተበራከቱ መጥተዋል። በመሆኑም አሰራሩን /ሲስተሙን/ በማዘመን ከዘመናዊ ከተማ/ ስማርት ሲቲ/ ጋር የተገናኘ ፕላትፎርም መዘርጋት አስፈላጊ ነው።
በዚህ ፕላትፎርም ነዋሪ የሆነውንና ያልሆነውን፤ የአከራይ እና ተከራይ መኪናዎችን፣ መዋጮችንና መረጃ በአንድ ቋት እንዲያገኙና ያለባቸው መዋጮዎች የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፍሉ ያስችላል። መተግበሪያው በሞባይልና በድረገጽ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፤ ማኅበሩ አሰራሩን በማዘመን ዘመናዊ አሰራር መዘርጋት ነዋሪዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቅበታል ብሏል።
አሰራሩ ከተዘረጋ ነዋሪዎቹ የግድ ማኅበሩ ቢሮ ድረስ መሄድ ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ሆነው የሚጠበቅባቸው የተለያዩ ክፍያዎችንና ወራዊ መዋጫን ሳይቀር በቴሌ ብር በመሳሳሉት የክፍያ ሥርዓቶች ለመፈጸም የሚያስችል መሆኑን ተናግሯል።
ጌትነት የፕላትፎርሙ መኖር ጠቀሜታን በተመለከተ እንዳብራራው፤ ማኅበራቱን የሚያስተዳደሩት ኮሚቴዎች ግቢውን የሚያስተዳደሩት ከነዋሪዎች በተሰበሰበ መዋጮ ነው። መዋጮ በመሰብሰብ ለግቢው ልማትና ለተለያዩ ሥራዎች እንዲውሉ ቢያደርጉም ብዙ ጊዜ ነዋሪዎች ተባባሪ ባለመሆናቸው ልማቶቹ በሚፈለገው መንገድ አይሄዱም ። በዚህ የተነሳ የሚፈለገው ሥራ ሳይሰራ ይቀራል። ይህን ተከትሎ በማኅበራቱና በነዋሪዎች መካከል ቅራኔ ይፈጠራል።
ቴክኖሎጂው አጠቃላይ አሰራሩ መረጃ አያያዙም ሆነ ክፍያ አፈፃፀሙ ዘመናዊ እና በኦንላይን እንዲሆን ማድረግ ያስችላል። አሰራሩ መዘመኑ ደግሞ መረጃዎች በዘመናዊ መልኩ እንዲያዙ፣ ክፍያዎች በኦንላይን እንዲሆኑና ሪፖርት በቀላሉ እንዲያኙ፣ አጭር መልዕክቶች በአፋጣኝ እንዲያገኙ ያደርጋል። ይህም በነዋሪዎቹና በማኅበራቱ መካከል መተማመን እንዲፈጠር ያግዛል።
ከዚህ በተጨማሪ ሌላ አሰራሩ ዘመናዊ መሆኑ መንግሥትም ከነዋሪውና ከማኅበረሰቡ ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ዘመናዊ እንዲሆን ያስችላል ። ምርትና አገልግሎቶችን በቅናሽ ለነዋሪዎች ማቅረብ የሚፈልጉ አምራቾችም ሆኑ ነጋዴዎች መጠቀም የሚችሉበት በመሆኑ፤ ነዋሪው ትኩስ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል።
‹‹ይህንን ፕላትፎርም አዘጋጅተን ሥራ ስንጀምር የማኅበራቱ ኮሚቴዎች አሰራራቸውን ወደ ዘመናዊ አሰራር የመቀየር ቁርጠኝነት የሌላቸው እና በተለመደ መልኩ የሚሰሩ መሆናቸው ችግር ፈጥሮብናል።›› የሚለው ጌትነት፤ ማኅበራቱን የሚመሩ አስተዳደሮች ያለምንም ክፍያ በትርፍ ጊዜያቸው የሚሰሩ በመሆናቸው እነርሱን ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ያመላክታል። ምሽት ጠብቀው አግኝተው ያሳመኖቸው ደግሞ እነርሱ ተገናኝተው ተወያይተው ውሳኔ እስከሚያስተላልፉ ረጅም ጊዜ እንደሚፈጅባቸው ይገልጻል። በመሆኑም ማኅበራቱ አሰራራቸውን ለማዘመን ካሰቡ በቀጥታ ድርጅቱ አነጋግረውን ሊያሰሩ የሚችሉበት አሰራር እንዳመቻቹ አመላክተዋል።
ወደ ድርጅቱ ፕላትፎርም ለመግባት የሚፈልግ ማኅበር ሊያሟላ የሚገባው መስፈርት በሕግ የተቋቋመ ሕጋዊ እውቅና ፈቃድ ያለው፤ የራሱ የመተዳደሪያ ደንብ ያለውና በነዋሪው የተመረጠ ለመሆኑ ማረጋገጫ ያስፈልጋል። በተጨማሪም ከድርጅቱ ጋር ለመስራትና ዘመናዊ አሰራር ለመግባት የሚያስፈልጋቸው ኮምፒዩተር፣ ዋይፋይ እና የሰው ኃይል አሟልተው ከተገኙ ሲስተሙን ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ክፍያ እንደሚያገኝ አስታውቋል።
ድርጅቱ ይህንን ፕላትፎርም ለመስራት የሚያገኘው ጠቀሜታ የሕብረተሰቡ ግልጸኝነትና እርካታ ነው የሚለው ጌትነት፤ ከዚህ ጎን ለጎን አብረው ሊሄዱ የሚችሉ የቢዝነስ ሞዴሎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ትላልቅ ኮርፖሬት ድርጅቶች ከድርጅቱ ጋር አብረው እየሰሩ በመሆኑ ማስታወቂያዎች በመስጠት ስለሚያግዙ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይናገራል።
የስታርትአፕ ምህዳሩ እያደገ መምጣቱ ለስታርትአፖች ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው የሚለው ጌትነት፤ ድርጅቱ ገና ስታርትአፕ ቢሆንም ከትንሽ ተነስቶ እያደገ ከመምጣቱ ባሻገር ከሌሎች ስታርትአፖች ተወዳድሮ በማሸነፉ በዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ላይ ሳይቀር መሳተፍ መቻሉን ይገልጻል። በአሁን ወቅት መንግሥት ለስታርትአፖች የተለየ ትኩረት መስጠቱን ገልጾ፤ የተለያዩ ድጋፎች ሲደረግላቸው እንደነበርና አሁንም ድጋፉ እንደቀጠለ መሆኑን አስገንዝቧል።
ፕላትፎርሙ ብዙ ችግሮች የሚያቀልና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፤ የማኅበራቱና የነዋሪዎችን ችግር የሚፈታ ነው። ከዚህ ባሻገር አሰራሮችን በማዘመን ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን በማድረግ ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል ሲል ተናግሯል።
በከተማው ውስጥ ያሉ ሁሉም ማኅበራት ይህንን አሰራር ተከትለው አሰራራቸውን ቢያዘመኑና ግልፅነት ከማስፈን ባሻገር በብዙ መንገድ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበት ነው የሚለው ጌትነት፤ ማኅበራቱ ወደዚህ ሲስተም እንዲመጡ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ይጠይቃል።
ጌትነት እንዳብራራው፤ ቴክኖሎጂው ገና እየተለመደ ቢሆንም አሁን ላይ ከ120 በላይ ማኅበራት በፕላትፎርሙ እየተጠቀሙ ይገኛሉ። 200 የሚሆኑት ማኅበራት ሀሳቡን ተቀብለው ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በቀጣይ በአዲስ አበባ ከ3ሺህ 500 በላይ ማኅበራት ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል። ሌሎች የክልል ከተሞች ላይም ለመስራት የሚያስችሉ ሥራዎች ተጀምረዋል። በቀጣይ ድርጅቱ በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ አባወራና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ10ሚሊዮን በላይ ነዋሪ በዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ አቅዶ እየሠራ ነው።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም