ፈተናዎችን በብቃት የተወጡት የድሬዳዋ ኢንቨስተር

የዛሬ የስኬት እንግዳችን በድሬዳዋ ከተማ ተወልደው አድገዋል። ከልጅነታቸው ጀምረው ሙሉ ዘመናቸውን አቅማቸውን አሟጠው ለድሬዳዋ ሠርተዋል። ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱላሂ ይባላሉ። ሰላምታ፣ እርጋታ እና እርዳታ መስጠት መለያቸው ነው። አባታቸው ደግሞ ታዋቂ የድሬዳዋ የእንጨት ሥራዎች ድርጅት ባለቤት እና ባለሙያ ናቸው። አቶ አብዱላሂ መሃመድ የተሰኘ የእንጨት አምራች ድርጅት ከፍተው፤ ለከተማው ሕዝብ የእንጨት ሥራ ውጤት የሆኑ ምርቶችን በማቅረብ ታዋቂነትን አትርፈዋል።

ወይዘሮ ሰዓዳ እንደሚናገሩት፤ ከጣሊያኖች ጋር የእንጨት ሥራ ይሠሩ የነበሩት አቶ አብዱላሂ የትምህርት ጥቅም ምን እንደሆነ የገባቸው ናቸው። ሙስሊም ቢሆኑም፤ በወቅቱ ሉተር ዳም ትምህርት ቤት ሥነሥርዓት ላይ ማተኮሩን እና በከተማዋ ምርጥ ትምህርት ቤት መሆኑን በማመናቸው እየከፈሉ የበኩር ልጃቸው ወይዘሮ ሰዓዳን በካቶሊክ ትምህርት ቤት አስተምረዋቸዋል። በተጨማሪ በቤት ውስጥ መምህር ቀጥረው እንዲያጠኑ ያደርጉ ነበር።

ወይዘሮ ሰዓዳም ትምህርት ቤቱ ሴቶች ብቻ ይማሩበት ስለነበር ትምህርታቸውን በተሻለ ምቾት ሲከታተሉ ቆዩ። ይሁንና ወይዘሮ ሰዓዳ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ከመዘዋወራቸው በፊት ቤተሰቡ ላይ ከባድ ችግር ተፈጠረ። የደርግ መንግሥት አቶ አብዱላሂን ለመግደል እንደሚፈልግ ተሰማ። አባት ወይዘሮ ሰዓዳን ጨምሮ ዘጠኝ ልጆቻቸውን እና የቤት እመቤት የነበሩ ሚስታቸውን እንዲሁም ለዘመናት ሠርተው ያካበቱትን ሀብት ትተው ተሰደዱ።

ወይዘሮ ሰዓዳ የመጀመሪያ ልጅ ሆነው ዘጠኝ ልጆች በተወለዱበት ቤት ሲኖሩ፤ የበኩር ልጅ ናቸውና የቤተሰቡ ሕይወት እንቅፋት ሲያጋጥመው ስምንት ታናናሽ እህቶቻቸውን እና ወንድሞቻቸውን የማሳደግ ግዴታ በእሳቸው እና በእናታቸው ትከሻ ላይ ወደቀ። “ጊዜው ደርግ ሥልጣን ላይ የወጣበት ወቅት ነበር። አባቴ ሀብት ከማፍራት ውጪ ምንም የሠራው ነገር አልነበረም። ሆኖም የእሱ መሰደድ ሳያንስ እኛም በር በተንኳኳ ቁጥር እንደነግጥ ነበር፡፡” ሲሉ ወይዘሮ ሰዓዳ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።

አንዳንዶች የኮብላዩ ልጅ እያሉ ያሳቅቋቸው እንደነበር በመጥቀስ፤ አባት መጀመሪያ ጅቡቲ ቀጥሎ ወደ ሳዑዲ ሄደው ሠርተው ያገኙትን ገንዘብ ሲልኩ፤ የሚቀበሉት ሩቅ ሔደው እንደነበር እና ቤተሰቡ እጅግ በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ማለፉን ያስረዳሉ።

እንደ ወይዘሮ ሰዓዳ ገለጻ፤ ከአባታቸው ጋር መገናኘት እና ስልክ ማውራት አይችሉም ነበር። ሙስሊም በመሆናቸው ተሸፋፍነው ረዥም ጊዜ በቤት ውስጥ ያሳልፉ የነበሩት የወይዘሮ ሰዓዳ እናት፤ ስለውጪው ዓለም ብዙ አያውቁም። በእዛ ላይ የቤተሰቡ ዋነኛ ሀብት የነበረው የእንጨት ሥራ ማምረቻ ሙሉ ለሙሉ በደርግ ተወረሰ። በተወረሰው ድርጅታቸው ምትክ 48 ብር በወር ይከፈላቸው ነበር። ይህም ቤተሰብ ለማስተዳደር በቂ አልነበረም።

አራት እና አምስት የቤት ሠራተኛ የነበረበት ቤት፤ ቤተሰቡ የሚከፍለው ገንዘብ ስላልነበረው አንድም ሠራተኛ የማይገኝበት ሆነ። እቃም ሆነ ቤት ማጠብ፤ አጠቃላይ ቤተሰቡ የሚመገበውን ምግብ መሥራት በእናት እና በወይዘሮ ሰዓዳ ትከሻ ላይ ወደቀ። የወይዘሮ ሰዓዳ እናት፤ ለልጆች የሚበሉትን ከማዘጋጀት አልፈው፤ የተወረሰውን ሀብት ለማስመለስ በየፍርድ ቤት እና በየአስተዳደር ቢሮ ለብቻቸው መመላለስ አልቻሉም።

ወይዘሮ ሰዓዳ እናታቸውን ለማገዝ የቤት ሥራ ከማከናወን በተጨማሪ ከእናታቸው ጋር ወደ ፍርድ ቤት እና አስተዳደር ቦታዎች መመላለስ ጀመሩ። ምክንያቱም እናት ብቻቸውን ጉዳዮችን ማስፈጸም አለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን ያለ ኦሮምኛ ቋንቋ መናገር ስለማይችሉ የሚያስተረጉሙት ወይዘሮ ሰዓዳ ነበሩ።

ሴት አያታቸውም እርሻ ስለነበራቸው ይደግፏቸው ነበር። የአያት ድጋፍ መታከሉ ወይዘሮ ሰዓዳ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ረዳቸው። ይሁንና የወይዘሮ ሰዓዳ አባት ባለመኖራቸው እናታቸው በገንዘብ ክፍያ እንዳይጨነቁ በማሰብ፤ ወይዘሮ ሰዓዳ በራሳቸው ፈቃድ ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት ገቡ።

ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የድሬዳዋ የሁለተኛ እና የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታተሉ። 12ኛ ክፍል የብሔራዊ ማጠቃለያ ከተፈተኑ በኋላ ኮሌጅ ለመግባት አስቀድሞ ለአራት ወር ማስተማር ግዴታ ነበር። ለአራት ወራት ሐረርጌ ጋራ ሙለታ ወደሚባል አካባቢ ገጠር ለማስተማር ሔዱ። በደኖ ሔደው አስተማሩ። ግዴታቸውን ከተወጡ በኋላ፤ የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) ገብተው መማር ቢጀምሩም ከአንድ ዓመት በላይ መቀጠል አልቻሉም።

የወይዘሮ ሰዓዳ እናት ብዙ መከራዎችን እያሳለፉ በየፍርድ ቤቱ ተንከራተው፤ የእንጨት ሥራ ድርጅቱ ተመለሰላቸው። እናት የሥራ ተቋሙ ከተመለሰላቸው በኋላ ሩቅ መንገድ ሄደው እንጨት እስከ ማምጣት የደረሰ የሥራ ጫና መወጣት ጀመሩ። ይሁንና ሌሎች ደግሞ ድርጅቱን አቃጠሉባቸው። የድርጅቱን መቃጠል ተከትሎ የወይዘሮ ሰዓዳ ወንድሞች ከሀገር ወጡ። ወይዘሮ ሰዓዳ ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም፤ የግድ እናታቸውን ለማገዝ ትምህርታቸውን አቋረጡ።

ለሦስት ዓመት ድርጅቱ ላይ ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ፤ እንደገና እንደ አዲስ ድርጅቱ ስኬታማ እየሆነ መጣ። ትርፋማ እየሆኑ አደጉ። ኢህአዴግ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር፤ አባት ከሳዑዲ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። አባት መጥተው ድርጅቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በተጨማሪ ወፍጮ ቤትም መሥራት ጀመሩ። “አባቴ ጠንካራ ነበር። በሌሊት ሁርሶ ሔዶ እርሻውን አስቆፍሮ ተመልሶ መጥቶ ድሬዳዋ የእንጨት ሥራውን ያከናውን ነበር።” ይላሉ።

ወይዘሮ ሰዓዳ እንደአባታቸው ሁሉ እሳቸውም ጠንክረው ለመውጣት የእንጨት ሥራውን ቢወዱትም፤ እንደሚፈልጉት እጅግ ስኬታማ ለመሆን ተቸገሩ። የተለያዩ ዲዛይኖች ለመሥራት እና ለማሠራት ቢፈልጉም ሰዎች ከለመዱት ውጪ ሊቀበሏቸው አልቻሉም። እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ማህበራዊ ድረገጹ ተስፋፍቷል፤ ቲክ ቶክና ፌስቡክን የመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ሰዎች ስለሚጠቀሙ የተለያዩ ዲዛይኖችን ይቀበላሉ። በፊት ግን ሰዎች ሥራ ሲያዙ ሰው ቤት ያለ ዕቃን የሚመስል እንጂ፤ በአዲስ ዲዛይን የተሠራ እቃን ለመግዛት ብዙም ፈቃደኛ አልነበሩም። ቀድመው የተሻለ ነገር ለመሥራት ቢሞክሩም ብዙ አዋጭ ባለመሆኑ በተለመደ መልኩ ሥራቸውን ቀጠሉ።

በሂደት ወይዘሮ ሰዓዳ ትዳር መሠረቱ፤ የትዳር አጋራቸው የግንባታ ሥራ ባለሙያ በመሆናቸው ከእንጨት ሥራ ተላቀው ወደ ግንባታ ሥራ ገቡ። ጅግጅጋ እና ድሬዳዋ ላይ አንደኛ ተቋራጭ ሆነው እየተጫረቱ ትልልቅ ግንባታዎችን መገንባት ጀመሩ። ድሬዳዋ ላይ የኤፍ ኤም ድሬ እና የቴሌቪዥን ጣቢያ ሕንፃ እና ሁለት ባለ ሦስት ወለል የገበያ ማዕከላትን ገነቡ። ሌሎችም የተለያዩ ሕንፃዎችን እንዲሁም ጋራ ላይ ወጥተው ታዎሮችን ሠሩ። የአራት ትምህርት ቤቶች ሕንፃዎችን እና ከተማ ውስጥ የተለያዩ መሥመሮችን የመዘርጋት ሥራንም አከናውነዋል። ወይዘሮ ሰዓዳ በእዚህ ሂደት ሦስት ልጆች አፈሩ። ቀድመው እናታቸው ቀጥሎ አባታቸው አረፉ።

ወይዘሮ ሰዓዳ እንደሚናገሩት፤ ስድስት ወንድም እና እህቶቻቸው አሜሪካ ናቸው። እሳቸውም አሜሪካ የመሔድ ዕድል አግኝተው ነበር። ይሁንና ከጉብኝት በዘለለ ኑሯቸውን አሜሪካ ለማድረግ አልወደዱም። አሜሪካ ብቻ ሳይሆን አውሮፓ እና የኤዢያ ሀገሮችን ጎበኙ። ሕንድ እና ዱባይ እንዲሁም ሌሎችም ሀገሮች እየሄዱ ሲያዩ መንፈሳዊ ቅናት ይሰማቸው ነበር። ይህንን ተከትሎ የሕይወት መስመር አቅጣጫቸው ሌላ መሥመር የሚያዝበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ከኮንስትራክሽን በተጨማሪ ወደ ሆቴል ሥራ ገቡ።

በድሬዳዋ ከተማ በተለምዶ ሰዒዶ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የመሬት ጨረታ ወጣ። እሳቸው ጨረታውን አሸንፈው ካርታ ከተሰጣቸው በኋላ፤ ሌሎች ሰዎች መሬቱን በሕገወጥ መንገድ ተሻሻጡት። አቤቱታ ሲያቀርቡ ከሁለት ዓመት በኋላ ገደላማ ቦታ ላይ “ሆቴል ሥሪ” ተብለው ተለዋጭ ቦታ ተሰጣቸው። ቦታው ገደል ቢሆንም የግንባታ ማሽኖች ስለነበሯቸው ሐዋሳ እና የተለያዩ ከተሞች ላይ እንዳሉት ሪዞርቶች ዓይነት ያማረ ሆቴል ለመገንባት አሰቡ። ለጊዜው በጨረታ እየወሰዱ መገንባታቸውን አቁመው የራሳቸውን ሆቴል መገንባት ላይ ብቻ አተኮሩ። ከሆቴል አንፃር ብዙ ሆቴሎች የሌላቸውን እነርሱ ብቻ ሊኖራቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ሠሩ።

“ከወንድ ጋር ላለመዋኘት የሚፈልጉ ሴቶች ብዙ ጊዜ ይጎዳሉ” የሚሉት ወይዘሮ ሰዓዳ፤ ከአካባቢው ባህል ጋር የተጣጣመ እና ልጆቻቸው ከወንዶች ጋር እንዲዋኙ የማይፈልጉ ብዙ ወላጆችን ታሳቢ በማድረግ የሕጻናት፣ ወንዶች እና ሴቶች በጋራ የሚዋኙበት ብቻ ሳይሆን ለሴቶች ብቻ የመዋኛ ገንዳ ገነቡ። ድሬዳዋ ላይ ሴቶች ለብቻ መዋኛ የሌላቸው በመሆኑ ወላጆች እየመጡ ሴቶች ልጆቻቸው እንዲዋኙ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ፈጠሩላቸው። በድሬዳዋ መሃል ከተማ ተገንብቶ ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረው ይኸው ሆቴል፤ 58 አልጋዎች፤ ስፓ እና ጂም እንዲሁም ፀጉር ቤት አለው።

90 ሠራተኞች አገልግሎት የሚሠጡበት ይኸው የወይዘሮ ሰዓዳ ሆቴል፤ ተጨማሪ ትዕዛዝ አድራሽ (ዴሊቨሪ) የሚሠሩም አሉ። ከግንባታው ጋር ተያይዞም በያጅ፣ ኤሌክትሪሺያን፤ የቧንቧ ሠራተኞች እና ሌሎችንም ጨምሮ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ 110 አካባቢ ሠራተኞች እየተሳተፉ ሲሆኑ፤ በአጠቃላይ በሆቴሉ አካባቢ 200 ሠራተኞች እየተሳተፉ ናቸው።

ሆቴሉ በቀን ከ150 እስከ 200 ሰው አገልግሎት ይሠጣል የሚሉት ወይዘሮ ሰዓዳ፤ ከእዚህ ውጪ ብዙ ሎደሮች፣ ስካቫተር እና የተለያዩ ማሽነሪዎች ቢኖራቸውም ለጊዜው ማሽኖቹን እየተጠቀሙባቸው አይደለም። ምክንያታቸው ደግሞ የጨረታው ሁኔታ ብዙም አያስደስትም የሚል ነበር። አሁን ሌላም ሁለተኛ ሆቴል ለመገንባት ጀምረዋል።

ከድሬዳዋ ባህል አንጻር በሆቴል ሥራ ላይ ተሠማርቶ የድሬዳዋን ሰው ማሠራት ከባድ ነው። በሥራ ሰዓት ከጠዋት እስከ ማታ የመሥራት ልማድ ያለውን ሰው ማግኘት ያዳግታል። ሆኖም የእነሱን ቦታ መሸፈን የሚችሉ የሌላ አካባቢ ሠራተኞች በተጨማሪነት በመቅጠር አቻችለው ሥራውን ለማከናወን ጥረት እንደሚያደርጉ የተናገሩት ወይዘሮ ሰዓዳ፤ ዋናው ጉዳይ ሥራው ላይ አተኩሮ መሥራት ደግሞ የግድ መሆኑን ያስረዳሉ።

“ለመሥራት ራስን ማሳመን እና መድከም ነው። እስከ ምሽት አራት ሰዓት እሠራለሁ። ሌሊት ስምንት ሰዓት ተነስቼም እሠራለሁ። ኮንስትራክሽን ላይ ሌሊት ሳይቀር ውሃ ከሌለ እየተዟዟርኩ እከታተላለሁ፡፡” ሲሉ የተናገሩት ወይዘሮ ሰዓዳ፤ አንድ ከፍተኛ ስቃይ ያዩበት የውሃ ፕሮጀክት መኖሩን እና ዋነኛው ሕልማቸው ከኦሮሚያ ክልል ጀምረው በአማራ ክልል እንዲሁም በትግራይ ክልል ለሴቶች የውሃ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚፈልጉ፤ እንዲሁም የገጠሩን ሕዝብ የመጠጥ ውሃ ችግር ማቃለል ትልቁ እቅዳቸው መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ፍላጎታቸው እንዲሳካ የአካባቢው አስተዳደሮች እንዲተባበሯቸው የሚፈልጉ መሆኑንም አመላክተዋል።

ከማህበራዊ ኃላፊነት አኳያ “በሃይማኖታቸው ቀኝ እጅህ ሲሰጥ ግራ እጅህ እንዳያይ” እንደሚባል በማስታወስ፤ ይህንን እርዳታ አድርጌያለሁ ወይም ይህንን እርዳታ እየሠጠሁ ነው ማለት “ሃራም” ነው ብለዋል። ሆኖም አረጋውያንን እና ሌሎችንም እንደሚያግዙ በአንድ ቀን በአስር ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ለድጋፍ እንደሚያወጡ ይናገራሉ። በተለያዩ አጋጣሚዎችም የተቸገሩትን እንደሚደግፉ በማስ ታወስ፤ የድሬዳዋ ሱቆች ሲቃጠሉ እንዲሁም ትግራይ ላይ ተማሪዎች መሬት ላይ ሆነው ሲማሩ እባብ እየነደፋቸው መሆኑን ሰምተው ትምህርት ቤት ለማሠራት የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

“ሴቶች ከባል እጅ ገንዘብ መጠበቅ የለባቸውም። ሥራ ላይ አእምሯቸውን ካሳረፉ እና ጠንክረው ከሠሩ ተፅዕኖ አይኖርባቸውም” ያሉት ወይዘሮ ሰዓዳ፤ ሴቶች ጠንክረው እንዲሠሩ መክረዋል።

የኦሮሚያ፣ የአማራ እና የትግራይ የገጠሩን ሕዝብ የመጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል የውሃ ፕሮጀክት ላይ በሰፊው ለመሥራት ጥረት እንደሚያደርጉ አመልክተው፤ የአካባቢው አስተዳደሮች እንዲተባበሯቸው የሚፈልጉ መሆኑን በድጋሚ አመላክተዋል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You