ማዳበሪያን በተፈጥሯዊ መንገድ የሚተካ ቴክኖሎጂ 

የግብርናው ዘርፍ ከኋላቀርነት ተላቅቆ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ከማድረግ ባሻገር ምርትና ምርታማነት መጨመር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ማዘመን ለነገ በይደር የሚተው ጉዳይ አይደለም። ይልቁንም ያለውን ሀገራዊ አቅም አሟጥጦ በመጠቀም ግብርናውን ሊያዘመኑ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን እንዲፈጠሩ፣ እንዲስፋፉና ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያደርጉ ሥራዎችን በመሥራት ምቹ ሥነምህዳር መፍጠርን ይጠይቃል።

የግብርናው ዘርፍ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶት ከሚሠራቸው የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል አንዱ ነው። በመሆኑም ከኋላቀርነት ተላቅቆ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር በማድረግ ረገድ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። ግብርና ቀድሞም የነበረ፤ አሁን ያለው ወደፊት የሚቀጥል ዘርፍ እንደመሆኑ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሱ የፈጠራ ሃሳቦች ማበረታታትና መደገፍ ያስፈልጋል። በተለይ ወጣቱ ሃሳብ በማመንጨት የአርሶ አደሩን ድካም ሊያቃልሉ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲያፈልቁ ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር፣ መደገፍና ማበረታታት ከመንግሥት ብቻ የሚጠበቅ ሳይሆን የግሉን ዘርፍና የሁሉንም ተሳትፎና ርብርብ የሚጠይቅ ነው።

የግብርና ዘርፍ ወደ ትራንስፎርሜሽን እንዲመጣ ከሚሠሩ ዓለምአቀፍ ተቋማት መካከል አንዱ ሀይፈን ኢንተርናሽናል፤ ግብርናው የሚያዘመኑ ሃሳቦች በመደገፍና በማበረታታት በሚሠራቸው ሥራዎቹ ይታወቃል።

ሀይፈን ኢንተርናሽናል የሁሉንም የአፍሪካውያን አርሶ አደር አጀንዳ ይዞ አዩቴ አፍሪካ ቻሌንጅ ኢትዮጵያ 2025 የተሰኘው ውድድር በማዘጋጀት ግብርናው የሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎችን በማወዳደር ይሸልማል። በእዚህም በተለይ ግብርናውን የሚያዘመኑ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች በማሳተፍ እየደገፈና እያበረታታ ይገኛል። የውድድሩ ዋና ዓላማ ግብርና የሚያዘመኑ የፈጠራ ሃሳቦች ከመደገፍ ባሻገር በወጣቶች መካከል የእውቀት ሽግግር እንዲኖርና ለውጦች እንዲመጡ የሚያስችሉ ሥራዎች መሥራት ነው።

በመሆኑም ድርጅቱ በየዓመቱ ውድድሮች በማዘጋጀት ድጋፍና ማበረታቻ ሲሰጥ ቆይቷል። አዩቴ አፍሪካ ኢትዮጵያ 2025 ውድድር ወጣቱ ያለውን አቅም ተጠቅሞ በግብርና ዘርፍ ላይ አዳጊ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ በማድረግ ግብርናውን የሚያዘመኑና አርሶ አደሩን ሕይወት የሚያቀሉ ቴክኖሎጂዎች እንዲያቀርቡ ያበረታታል። ከዚህ ባሻገር ለአሸናፊዎች በቀጣይ ሃሳባቸው ወደ ተግባር እንዲቀይሩ የሚያስችላቸው ስልጠናና የድጋፍ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል።

አዩቴ አፍሪካ ቻሌንጅ ኢትዮጵያ 2025 ውድድር በኢትዮጵያ መካሄዱ መጪው ትውልድ የግብርናው ዘርፍ ላይ ለውጥ እንዲያመጣ እንደሚያደርገው ተመላክቷል። ይህ ውድድር ከተጀመረ የዘንድሮው ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፤ ባለፉት ሦስት ዙር 1 ሺህ 500 የኢኖቬሽን ሃሳቦችን ማወዳደር ተችሏል። ከእነዚያ መካከል ዘጠኙ መሸለሙ ተገልጿል። በተለይ በባለፈው ዓመት ከተሸለሙት መካከል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ሃሳብ ይዞ የቀረበው ኢትዮጵያው ከኢትዮጵያ አልፎ በሩዋንዳ በኪጋሊ በተካሄደው ‹በአፍሪካ ኔክስት ጀኔሬሽን ቻሌንጅ› አሸናፊ መሆን ችሏል። ይህም ለኢትዮጵያውያን ኩራት ብቻ ሳይሆን አዲስ ምዕራፍ ከፋች እንደሆነም ተገልጿል።

እንዲህ እንዲህ እያለ በዘንድሮ ዓመትም 319 ያህል ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል። ይህም ከመላው ሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ሃሳብ ያላቸው ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል። እነዚህ ያላቸውን ሃሳብ ይዘው በውድድሩ የቀረቡ ተወዳዳሪዎች ሃሳብ ኖራቸው የፋይናንስ ድጋፍ ያጡ በርካታ ወጣቶች እንዳሉ ማሳያ ነው።

በአዩቴ ውድድር የወጣቶቹን የፈጠረ ሀሃሳብ በማወዳደር የተመረጡ አስር ተወዳዳሪዎች የተለያዩ ስልጠዎች እንዲያገኙ ተደርጓል። ይህ ውድድር እንደመሆኑ የግድ የተሻለ ሃሳብ ያላቸውን መምረጡ አይቀሬ በመሆኑ፤ ከእነዚህ መካከል የተሻለ ሃሳብ ይዘው የቀረቡ አምስቱ የገንዘብ ሽልማትና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።

በዘንድሮ አዩቴ አፍሪካ ቻሌንጅ ኢትዮጵያ 2025 ውድድር ከተመረጡት አምስት ተወዳዳሪዎች መካከል መምህር አማረ አዲስ የተባለው ተወዳዳሪ የተሻለ ሃሳብ ይዞ በመቅረብ አንደኛ ሆኖ ተመርጧል። 15ሺህ ዶላር ሽልማት ማግኘት ችሏል። መምህሩ በውድድር አንደኛ እንዲወጣ ያደረገው የምርምር ሃሳብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ / ኦርጋኒክ ፈርቲላይዘር/ ነው።

መምህር አማረ ሁለተኛ ዲግሪውን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተማረ ሲሆን፤ አሁን ላይ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ምህድስና ትምህርት ክፍል በመምህርነት እየሠራ ይገኛል። ‹‹ናኔክስ ባዩቸር ሶልዩሽን›› የተሰኘ ድርጅት መስራች ነው። ድርጅቱ የተፈጥሮ ማዳበሪያ /ኦርጋኒክ ፈርቲላይዘር/ የሚያመርት ሲሆን፤ ከተመሠረተ አንድ ዓመት አስቆጥሯል። በዚህ አንድ ዓመት ጊዜ በምርምር የተገኘውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።

አማረ ሁለተኛ ዲግሪውን በተማረበት ወቅት ለመመረቅ የሚያበቃው ጥናታዊ ጽሑፍ ሲሠራ፤ ያገኘው የምርምር ውጤት ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ሥራ እንዲገባ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለት ይናገራል። የዕፅዋት እና የእንስሳት አካላት ብስባሽ ባሕሪያት መለየት ላይ ትኩረት አድርጎ በሠራው የምርምር ሥራ በላብራቶሪ ፍተሻ አደረገ። በዚህም ለማዳበሪያነት የሚሆኑ ንጥረ ነገሮችን ማግኘት የሚቻልበትን ሁኔታ ተረዳ። ቀጥሎም ይህንን ሃሳቡን ለማዳበር የሚያስችሉትን የተለያዩ ጥናቶች ሲያካሂድ፤ ወደ የተፈጥሮ ማዳበሪያ /ኦርጋኒክ ፈርቲላይዘር/ የሚቀየሩ ንጥረ ነገሮች ማግኘቱን ያስረዳል።

አርሶ አደሩ ኬሚካል ማዳበሪያ በመጠቀም የሚያጋጥሙትን ችግሮች በሚገባ ስለተረዳ፤ ችግሩን ከሥር መሠረቱ ለመቅረፍ የሚችል ምርምርና ጥናት የማድረግ ጥረት አጠናክሮ ቀጠለ። የኬሚካል ማዳበሪያ ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላ የመቀንጨር በሽታና ተያያዥ አረሞች እንዲበዙና እንዲበራከቱ ምክንያት መሆኑን ይናገራል።

በሀገሪቱ የኬሚካል ማዳበሪያ ከገባ ጀምሮ የመሬቱ ለምነት በአሲድ እየተጠቃ እንደሚገኝ ጠቅሶ፤ ለጎርፍና ለሌሎችም የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭነት እየጨመረ መምጣቱን ተናግሯል።

ኬሚካል ማዳበሪያ ሀገር ውስጥ ሳይገባ በፊት አርሶ አደሮች ምን እንደሚጠቀሙ ማጥናቱን ይናገራል። በጥናቱ ሀገር በቀል በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጁ የሚጠቀሟቸው በጣም ብዙ ዘዴዎች እንዳሉ መረዳት መቻሉን ይገልጻል። ‹‹እነዚህን ሀገር በቀል እውቀቶች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማምጣት የግድ ይላል። በመሆኑም እኔም ይህን ተሞክሮ በመውሰድ ሳይንሳዊ አሠራሮችን በመጠቀም እሴት በመጨመር ወደ ምርት አመጣሁት።›› ይላል።

አማረ ‹‹የሚጣሉና የማንጠቀምባቸው ወደ 19 የሚሆኑ አትክልቶችን በአንድ ላይ በማቀናጀት ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመቀየር ስሞክር ትልቅ ለውጥ ማግኘት ቻልኩ። ሙከራዬ ላይ ምርታማነት በእጅጉ የጨመረ ነበር። ይህ ውጤታማ ስለመሆኑ በተለያዩ መልኩ አረጋግጠናል።›› ይላል።

አሁን በሀገሪቱ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የኬሚካል ማዳበሪያ አሲዳማነት ቶሎ ሳይለቅ እንዲቆይ የሚያደርግ ነው የሚለው መምህር አማረ፤ የአሁኑ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ግኝት ግን ከኬሚካል ማዳበሪያ በብዙ መልኩ እንደሚለያይ ይገልጻል።

መምህሩ እንዳብራራው፤ በአማራ ክልል ጎጃም ጮቄ የሚባል የድንች ምርት በብዛት በሚመረትበት አካባቢ ተግባራዊ ተደርጓል። ናሙና በመውሰድ ካለምንም የኬሚካል ማዳበሪያ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተደርጎ ሲሞከር ከ20 እስከ 40 በመቶ ያህል የምርት ጭማሪ አሳይቷል። በላብራቶሪ በደንብ ቢሠራበትና የተለያዩ አየር ንብረቶች ላይ ጥናት በማድረግ ቢሞከር የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለሁሉም አካባቢዎች የሚስማማ ሆኖ የተሻለ ውጤት ማግኘት ያስችላል። በተለይ የተለያዩ ንጥረ ነገር ያላቸውን በአንድ ላይ በማቀናጀት መሥራት ቢቻል የተሻለ ውጤት ለማምጣት ይቻላል።

ጥቅም ላይ የማይውሉ የሚወገዱ የቡና ቅጠላ ቅጠሎችና የስንዴ አገዳን ጨምሮ አንድ ላይ በማቀናጀት ሙከራ ማድረጋቸውን ጠቅሶ፤ የተዘራው ሰብል ምርታማነቱ እየጨመረና እየተሻለ ውጤት ማስገኘቱን ያመላክታል።

አሁን ላይ በምርምር ያገኛቸውን ወደ 19 የሚጠጉ ሀገር በቀል እጽዋቶችን አንድ ላይ በማቀናጀት ወደ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ በመቀየር ጥቅም ላይ እንዲውሉ እያደረገ መሆኑን ይገልጻል። የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን አንዱን ኪሎ ግራም በ16 ብር እያቀረበ መሆኑን አስታውቋል።

‹‹እኔ የአርሶ አደር ልጅ በመሆኔ በአካባቢዬ ያለውን የማዳበሪያ አቅርቦትም ሆነ የግዢ ሁኔታ በሚገባ አውቃለሁ። አሁን ላይ አርሶ አደሩ አንዱን ኩንታል ማዳበሪያ ስምንት ሺህ ብር በማውጣት እየገዛ ይገኛል።›› የሚለው መምህር አማረ፤ ይህ ማለት አርሶ አደሩ አንድ ኩንታል ማዳበሪያ ቢዘራ በስምንት ሺህ ብር ጤፍ ወይም ስንዴ ያመርታል ማለት ነው። ስለዚህ የአርሶ አደሩ ትርፍ ገለባው ብቻ ይሆናል ማለት ነው። ይህንን የተፈጥሮ ማዳበሪያ /ኦርጋኒክ ፈርቲላይዘር/ እንደዚህ አይነቱን ችግር በመቅረፍ ምርትና ምርታማነት ለመጨመር የሚረዳ ነው ሲል ያስረዳል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያውን ለመሥራት 19ኙም ንጥረ ነገሮች አንድ ላይ መቀናጀትን ይጠይቃል፤ አንዱ ከውስጡ ከጎደለ ምርታማነት አይጨምርም የሚለው መምህሩ፤ ከእነዚህ ስምንቱ የሚወገዱ ናቸው። 11 ዱ ደግሞ የአትክልት ወይም የእንሰሳት ተረፈ ምርቶች ሊሆን እንደሚችሉ ያመላክታል። እነዚህን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት ለመቀየር ለእያንዳንዱ የሚያስፈልገው የሙቀት መጠን የተለያየ ስለሚሆን በሚፈልገው ሙቀት መጠን ልክ ተስተካክሎ ወደሚፈለገው ይዘት እንዲቀየር ይደረጋል ብሏል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያው በተለያዩ ቦታዎች ሙከራ የተደረገ ሲሆን፤ ከአጋር አካላት ጋር በሲዳማ ክልል ቤንሳ አካባቢ ተሞክሮ እንደነበር ይገልጻል። በአካባቢው የተፈጥሮ ማዳበሪያውን በመጠቀም ዘሩ ካለ ኬሚካል ማዳበሪያ እንዲዘራ ተደርጎ የተሞከረ መሆኑን ጠቅሶ፤ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ችሏል ሲል ያብራራል።

በሀገሪቱ ለተፈጥሮ ማዳበሪያነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ንጥረ ነገሮች /ባዮማስ/ በዓመት 20 ሚሊዮን ቶን ማንም ስለማይፈልጋቸው እንዲወገድ የሚደረግ መሆኑን ይገልጻል። እነዚህ ጥቅም ላይ የማይውሉትን በመሰብሰብ አንድ ላይ በማቀናጀት የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንደሚሠራ ይናገራል። ጥቅም ላይ የሚውሉት ጥሬ እቃዎች አካባቢው ላይ በቅርበት ስለሚገኙ ለአርሶ አደሩ የሚቀርቡበት ዋጋ ተመጣጣኝ የሆነና የአርሶ አደሩን የመግዛት አቅም ያገናዘበ መሆን አመላክቷል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያን ልክ የኬሚካል ማዳበሪያ በፓኬጅ ታሽጎ እንደሚከፋፈል ሁሉ ይህም መከፋፈል እንደሚችል በመጠቆም፤ አንድ ፋብሪካ ከተገነባ በኋላ ፓኬጅ ተዘጋጀተው ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የሚደረግ ይሆናል ሲል አስረድቷል።

መምህሩ እንዳብራራው፤ ድርጅቱ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ብቸኛ የካርበን ሻጭ ድርጅት ነው። የካርበን ልቀት በመከላከሉ የአሜሪካ ባዩ ኢንተርናሽናል ኢንቬቲቭ 340 ሺህ የኢትዮጵያ ብር እየከፈለው ይገኛል። በቀጣይም ድርጅቱ ከ54 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን ተደራሽ ለማድረግ አቅዶ ይሠራል። አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ ክልል ቅርንጫፎችን በመክፈት ማሽኖችን በመትከል ልክ እንደኬሚካል ማዳበሪያ ታሽጎ ተደራሽ ይደረጋል።

እንደዚህ አይነት ውድድሮች መምጣታቸው ለጀማሪ ስታርትአፖች መልካም አጋጣሚ መሆኑን የሚናገረው መምህሩ፤ የስታርትአፕ ሥነ-ምህዳሩን ብዙ ተግዳሮቶችና ተጽእኖዎች እንዳሉበት ይናገራል። በመሆኑም ውጤት ላይ ለመድረስ መታለፍ ያለባቸው ተግዳሮቶች በራስ ጥረት ማለፍ እንደሚገባ ጠቅሶ፤ ይህንን ሥራ ተግባራዊ እንዲሆን ለመፈተሽ ገንዘብ ከኪሱ እያወጣ ሲያከናውን እንደነበር ይናገራል። በተለይ ስታርትአፖች ባይሳካላቸው የሚያጡት ነገር ቢኖርም መሞከራቸውን ማቆም የለባቸውም ሲል ይመክራል።

አሸናፊ በመሆኑ ያገኘውን የገንዘብ ሽልማት ለታለመለት ዓላማ በማዋል የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማስፋፋት አርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን የማድረግ እቅድ እንዳለው የሚገልጸው መምህሩ፤ በቀጣይም በአፍሪካ ደረጃ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የሚያመርት ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማቋቋም ማቀዱን ተናግሯል።

የሀይፈን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ አየለ እንደተናገሩት፤ ረሃብና ድህነት ለማጥፋት ትናንትና የነበረውን መሣሪያ ከመጠቀም ይልቅ፤ ከዘመኑ ጋር አብሮ ሊጓዝ የሚችል ቴክኖሎጂን መፍጠር እና መጠቀም ያስፈልጋል። ለዚህም በግብርናው ዘርፍ ግብርናውን ለማዘመን የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን የሚፈጥሩ ሥራ ፈጣሪዎችን ማበረታታትና ማብቃት አስፈላጊ ነው።

ወጣቱ ግብርናን በሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሠራ እንደሚገባው አመልክተው፤ አዩቴ ኢትዮጵያ 2025 ተወዳዳሪዎች የአርሶ አደሩን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ የፈጠራ ሃሳቦችን ይዘው ማምጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል። የፈጠራ ሃሳብ አንድ ጊዜ ብቻ ተፈጥሮ የሚቀር ሳይሆን፤ በየጊዜው እየተሻሻለና እየዳበረ የሚሄድ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

አዩቴ ሃሳብን ፈንድ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው አቅም ለመፍጠር ይሠራል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ግብርናን የሚያዘምን የቴክኖሎጂ ሃሳቦች የሚያመነጩ ወጣቶችን መደገፍ ግብርናን በመለወጥ ምርትና ምርታማነት መጨመር የገበያ ተደራሽነትን ማስፋት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You