ተገኝ ብሩ
አገር በትውልድ ቅብብሎሽ የምትሻገር፤ በልጆችዋ ጥረት የምትፀና ናት፡፡ የበለፀገችና ለዜጎች ምቹ የሆነች አገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ዋንኛ ጉዳይ የዜጎች በጎ አመለካከት ግንባታ ነው፡፡ የዜጎች ምክንያታዊ አመለካከትና ለአገራቸው ያላቸው ፍቅር የለውጦች ሁሉ መሰረት ነው፡፡
ወጥ የሆነ አገራዊ መግባባት ላይ የደረሰ፣ ጉዳዩን በጥልቀት የሚመለከት፣ በውይይት የሚያምንና ጠንካራ የሥራ ባህል ያለው ዜጋ የአገሩን ብልጽግና ማረጋገጥ ይችላል፡ ፡ ለዚህም ነው ሰብዓዊ ልማት ላይ መሥራት ወሳኝ ነው የሚባለው፡፡ ከሁሉ ነገር ቀድሞ የሰዎች አመለካከት ላይ መሥራት ዘርፈ ብዙ አገራዊ ችግር መፍታት የሚያስችል ቁልፍ በእጅ እንደ መያዝ ይቆጠራል፡፡
በምክንያት የሚያምንና አስተሳሰቡ የተገራ ትውልድ አገርን በመገንባት ሂደት ውስጥ ታላቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ ሰላም ማረጋገጥና መጠበቅ፣ የዴሞክራሲን ባህል ማጎልበት፣ አገራዊ አንድነትን ማጠናከርና ማስቀጠል፣ ኢኮኖሚን በጠንካራ መሰረት ላይ ማኖር፣ ፍትህን ማረጋገጥና አገራዊ ክብርን መቀዳጀት የሚቻለው ቀድሞ እነዚህ ሁሉ የሚመሩትን ሰዎች መግራት ሲቻል ነው፡፡
የበለፀገች አገር ለመገንባት አዕምሮው የበለፀገ ዜጋ ቀድሞ ማዘጋጀት ግድ ይላል፡፡ አገር የቱንም ያህል ብትለማ መሰረተ ልማት ቢሟላላትና ልዩ ልዩ ግብዓቶችን ብታሟላ እነዚህን ተጠቃሚ የሆነው ህብረተሰብ ካልተለወጠ ጥቅሙን ሊረዳው ስለማይችል አልያም ደግሞ የራሴ የሚለው ስሜት ውስጡ ስለማያድር የለማው በአያያዝና በግንዛቤ እጥረት በአመለካከት ችግር መበላሸቱና መፍረሱ አይቀርም፡፡ ስለ ዘላቂ ልማት ማሰብም አይቻልም፡፡
አገራት የመጨረሻ ግባቸውና አልመው መድረስ የሚፈልጉበት ዋንኛ መዳረሻ ራዕያቸው ብልጽግናና ዕድገት ነው፡፡ ብልጽግናቸው ፅኑ እንዲሆን ልማታቸው አስተማማኝነቱ እንዲቀጥል ደግሞ ሰብዓዊ ልማት ላይ ትኩረት ሰጥተው ይሠራሉ፡፡ ለዚህም አውሮፓዊትዋ አገር ጀርመንና የመካከለኛው ምሥራቋን እሥራኤልን መጥቀስ ይቻላል፡፡
እነዚህ አገራት ቀዳሚው ተግባር ቀድመው ለይተው ከሁሉ አስቀድመው ዜጎቻቸውን በአመለካከት ለውጠው ለዘላቂ ለውጥና ልማታቸው ፅኑ መሰረት ጥለዋል፡፡ በጊዜ ሂደትም አገራቱ ያስመዘገቡት ታላቅ ስኬት በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በልማት ቀዳሚ የሆኑ በዓለም ከፍ ብለው በተለያየ መልክ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ አገራት መንገድም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው፡፡
አገራዊ ብልጽግና ላይ ለመድረስ መንገዶቹ ሰላምና ዲሞክራሲ መሆናቸው እሙን ነው፡፡ መሰረታዊ የሆነ የአመለካከት ለውጥ ባላመጣ ማህበረሰብና ባልበለፀገና ደካማ መሰረት ባለው ኢኮኖሚ ውስጥ ዘላቂነት ያለው ሰላምና ዲሞክራሲ ማስፈን ያዳግታል፡፡ ለዚህም ነው በፅኑ መሰረት ላይ የቆመ የማይዋዥቅና ቀጣይነት ያለው ለብልጽግና የሚያዳርስ ዜጋን ማፍራትና በዚያም ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት የሚያስፈልገው፡፡
ድህነት እጅን ይጠመዝዛል፤ መቸገር የነገን ራዕይ በሰፊው ከማለም ያሰናክላል፡፡ እኛ አትዮጵያውያን በቂ የተፈጥሮ ሀብት ተችሮን፣ ምርታማና የሰጡትን የሚያበቅል ለም መሬት ይዘን፣ ማልማት የሚችል ለውጥን ማቀጣጠልና በአጭር ጊዜ ጥሩ እምርታን ማስመዝገብ የሚችል የሰው ሃይል እያለን አገራዊ የሆኑ ሀብቶችን ለይቶ ባግባቡ መጠቀም ተስኖን ቆይቷል፡፡
የአለንን የሰው ሀብት አመለካከቱን ቀይረን በተገቢው ሁኔታ አሰልጥነንና ለአገራዊ ልማቱ በትክክል መጠቀም ስላልቻልን ሰፊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲደራረቡብን አድርጓል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ደግሞ ሰፋፊ ሥራዎች ያሰፈልጉናል፡፡ ስለዚህ ሀገራዊ አንድነት ማጠናከር፣ ሰላማችን ማረጋገጥ፣ የማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ማሻሻልና የሀገሪቱን ዕድገት ማፋጠን ልናሳድረው የማይገባ የቤት ሥራችን ነው፡፡
ከምክንያት በመራቃችን በሚያለያዩን ጉዳዮች ላይ የመወያየት ባህል እንብዛም ስላላዳበርን በርካታ ፈተናዎች ገጥመውናል፡፡ በእርግጥ ታዳጊ አገር ነንና በዕድገት ወቅት የሚገጥም ፈተና ሁሌም ይጠበቃል፤ ለተሻለ ስኬት ፈተናዎቹን ተቋቁሞ ማለፍ ግን ይገባል፡፡ ለውጥ ሁሌም አልጋ ባልጋ ሆኖ ሊመጣ አይችልም፤ ይልቁንም በሩጫችን መደናቀፋችን በሂደታችን መሰናከላችን አይቀሬና የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡
የማይናወጥና ፅኑ መሰረት ያለው ለውጥ ማስመዝገብ ይቻል ዘንድ ደግሞ ለዚህ ለውጥ ዋንኛ መሰረት የሆነውን ሰውን መለወጥ ቀዳሚ ተግባራችን መሆን ይገባዋል፡፡ በዚህም የህዝባችንን መለወጥና የአገራችንን ዕድገት ለማረጋገጥ ያላትን ተፈጥሯዊ ሀብት በትክክል መጠቀም ይቻላል፡፡ ሰብዓዊ ልማትን ማረጋገጥ ወሳኝ የሚሆነውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
ከአስተሳሰብ ልዕልና ላይ ያልደረሰ ህዝብ መሰረታዊ ዕድገት ማስመዝገብ ካልቻለ በኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ለፈረጠሙ አገራት እጅ መስጠቱ አይቀርም፡፡ ድህነት ነፃነትን ይነሳል፡፡ አቅም ማጣት እጅ ያዘረጋል፡፡ የተዘረጋ እጅ የሚያይ ደግሞ ያንተን ነገር ጣልና የኔን አንሳ ማለትን ያስከትላል፡፡
የተዘረጋ እጅ ደግሞ ችግር ነውና ያዘረጋው ሳይወድ የራሱን አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ድህነት የሚነሳው አይነተ ብዙ ነፃነትን ነው፡፡ ለዚያውም ቀጥ ለጥ የሚስብል እንደፈለጉ ሳይሆን እንዳስፈለጋቸው ሁኑ ሲሉ የሚሆኑበት የነፃነት እጦት፡፡
ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ አቅም ዳብሮ በራስ መቆም ሲጀመር እንኳን ለቤት ለሌላም ይተረፋል፡፡ ሀገራዊ ጥቅምን ለማስከበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነትና ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን እንዲቻል ብልጽግና ላይ መድረስና ብርቱ መሆን ያሻል፡፡ ድህነት ነፃነትን የሚያሳጣውን ያህል አገራዊ ዕድገትና ብልጽግና መብት ያጎናጽፋል፡፡ አገራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ደግሞ አገራዊ ዕድገት ወሳኝ ነው፡፡ ለአገራዊ ዕድገት መሰረት የሚሆነው አመለካከት መግራት ቀዳሚው ነው፡፡
ዓለምን አንደፈለግን እናሹር በፈለግነው መልኩ እንቅረፅ የሚሉት አገራት የኢኮኖሚ አቅማቸው መሰረቱ ኢኮኖሚው የገነባው ዜጋ ነው፡፡ ዜጎቻቸውን አሰልጥነውና ገርተው ብሎም አመለካከታቸውን ለውጠው ለልማትና ለውጣቸው በሚሆን መልኩ በወጉ ተጠቅመዋል፡፡
በዚህም ዛሬ ዕድገታቸውን አረጋግጠው ዓለምን ከፊት መምራቱን ቀጥለዋል፡፡ እነዚህ አገራት ያላደጉና የእርነሱን ድጋፍ ፍለጋ በራቸውን በሚያንኳኩ የሦስተኛው ዓለም አገራት ላይ ፖለቲካዊ አቋማቸውን በመጫን የፖሊሲ ለውጥና ትግበራም ጭምር እንዲለውጡ በማድረግ እንዳሻቸው ያሾሩዋቸዋል፡፡ በመሆኑም ከምንም በፊት ለሰብአዊ ልማት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል፡፡
ሰዎችን በመለወጥ ሰላም የተረጋገጠባት፣ የዲሞክራሲ ባህል የዳበረባት፣ የዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት የተቀየረባትና ሁለንተናዊ ለውጥ ያረጋገጠች አገር መገንባት ያስችላል፡፡ እንደ አገር በራስ መቆም፤ በሁለንተናዊ መስክ ነፃነትን ያጎናጽፋል፡፡ ያን ለማምጣት ደግሞ በእጅ ያለን ሰፊ የሰው ሀብት በትክክል መጠቀም መቻል ግድ ይላል፡፡ አበቃሁ ቸር ይግጠመን፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 5/2013