ያዘው..ሌባ ሌባ..

አርብ ከሰአት የተቋሙ ጸሀፊ የሆነች ሴት ደውላ ፈተናውን በአንደኝነት አልፈሀል ሰኞ ለቃለመጠይቅ ትፈለጋለህ ካለችኝ ሰአት ጀምሮ ምድር ጠባኝ ነው የሰነበትኩት፡፡ ቅዳሜና እሁድ እንደ ዝንተዓለም በላዬ ላይ ሲያልፉ ደህና ግቡ ከሚል ምርቃት ጋር ነበር፡፡ ጊዜም እንደመንገደኛ ስንቅ ቋጥሮ ወደሩቅ ሀገር የሚሄድ የሚመስልበት አንዳንድ ኩነት አለ… ቅዳሜና እሁድ ከነጓዛቸው ወደሰኞና ማክሰኞ ወደድሮም ሲያዘግሙ እንዲያ ነበር የመሰሉኝ፡፡

ሰኞ ጠዋት ከዚህ በፊት እንዳሳለፍኳቸው ማለዳዎች አልመስልህ ብሎኝ ነበር፡፡ በፍኖ ቶሎዛ ያንቀላፋው ያዕቆብ እንኳን የኔን አይነት የተዋበ ሌሊት ስለማሳለፉ እጠራጠራለሁ። የሚረፍድብኝ መስሎኝ ቁርሴን ዘልዬ ነጭ ሸሚዝ ከጥቁር የጨርቅ ሱሪ ጋር ለብሼ ከቤት ወጣሁ፡፡

..ቤታችን ለባቡር ጣቢያ አቅራቢያ ነው፡፡ በግምት ሀያ ሰላሳ ርምጃዎች፡፡ ትኬት ቆርጦ ባቡር የመሳፈርን ያክል የሚቀለኝ የለም፡፡ ሰአቴን አየሁ..ታክሲ በማጣት ሩብ ደቂቃዎች አልፈዋል። እስከቅንድቡ የተሞላ ባቡር አጠገቤ መጥቶ ቆመ፡፡ ምን ላይ ሊቆም እንደሆነ ባላውቅም ሰው እየተሯሯጠ ይሄዳል፡፡ እዚህስ አልገባም ስል አሳለፍኩት፡፡ ከዛ በኋላ የሞሉ ሶስት ታክሲዎች አለፉኝ፡፡ አስር ደቂቃዎች ተቆጠሩ..ልቤ ከቅድሙ ሩብ ጋር ደባለቃቸው፡፡ ከርቀት የባቡር ድምጽ ተሰማኝ ምንም ይሁን በዚህ መሄድ አለብኝ እያልኩ ሳስብ ከቅድሙ በባሰ ሞልቶ አጠገቤ በሩን ከፈተ፡፡ ላልሄድበት በማልኩት ባቡር ልሄድ ግድ ሆነብኝ። የጋለ ትኩስ ትንፋሽ ከሆነ አይነት ጠረን ጋር እንኳን ደህና መጣህ አለኝ። እግሬ ስፍራ አግኝቶ ስለመቆሙ እጠራጠራለሁ። ትፍፍጉ፣ ጥግግቱ ክፉ መከራን ያስንቃል፡፡ ሲኦል የገባሁ ነበር የመሰለኝ፡፡ ድህነት ሲኦል አይደል? ያለው ብሆን ኖሮ በኮንትራት ታክሲ ከጉዳዬ ደርሼ ነበር፣ ውስጤን በብሶት እንዲህ አመስኩ፡፡

የሆነ ፌርማታ ላይ አንድ ሴት ልትወርድ የቡጢ ያህል ወገቤን ደቁሳኝ ወደበሩ ተሸጋገረች፡፡ ብዙ ቦታ ይዛ አጠገቤ የቆመች እንደሆነ የገባኝ ከአጠገቤ ስትሸሽ ነበር፡፡ አርበ ሰፊ ናት..ለብቻዋ የያዘችው ቦታ የእኔን ያህል ሃምሳ ያቆማል ስል በውስጤ ቀለድኩ፡፡ የእሷን መውረድ ተከትሎ አጠገቤ የሆነ እሪታ ተሰማ፡፡

‹ሀብሌን..ሀብሌን..ዘረፈኝ!

‹ዘረፈኝ..ዘረፈኝ..እሱ ነው ያዙት› ስትል ያለሁበትን ፈነቃቅላ ውጪ ወደሚታዩት ፖሊሶች ጮኸች፡፡

ሁሉም በየግሉ የራሱን አጉተመተመ፡፡

‹ማን ይሆን የፈረደበት? አለ ውስጤ፡፡ በዚህ ሌባ አማካኝነት ከጉዳዬ ላረፍድ እንደሆነ ሳውቅ ሌባ በተባለው ቀማኛ ላይ አንድ ሁለት ቡጢ ማዋጣት እንዳለብኝ ተሰማኝ፡፡ የጅህን ይስጥህ..ወዴት እየሄድኩ እንደሆነ ሳታውቅ እንዴት በዚ ሰአት ትዘርፋለህ..? የእኔን መሳይ በእድሜ ለአንድ ጊዜ የሚመጣ እድል ይዘው ወደጉዳያቸው እየሄዱ ያሉ ሰዎች እንዳሉ ብታውቅ በስራህ ታፍር ነበር ስል ጥርሴን ነከስኩበት፡፡

ተሰረቀብኝ ያለችው ሴት በጩኸትና በለቅሶ ከባቡሩ ወርዳ ወደእኔ እያመላከተች ‹ያዙት..እሱ ነው ሌባው..ያዙት› ስትል ጮኸች፡፡ ሌላ ሰው ማለቷ ነው ብዬ ሰው ፍለጋ ወደ ኋላዬ ስገላመጥ..ምን ትገላመጣለህ..? ያዙት..ሰርቆኛል› ስትል እሪ አለች። ምን እያሰብኩ እንደሆነ ሳላውቅ ሁለት ወጠምሻ ፖሊሶች ግራና ቀኝ በሀይል ጎትተው ከባቡሩ አወጡኝ፡፡ ጉተታቸውን መቋቋም ስላልቻልኩ መሬት ላይ በሀይል ወደኩ፡፡

በሁለቱ ፖሊሶች ግራና ቀኝ ተይዤ ወደፖሊስ ጣቢያ ተወሰድኩ፡፡ ሲሰርቅ እጅ ከፍንጅ የተያዘ ሌባ ነው ሲሉ ለመርማሪ ፖሊስ አስረከቡኝ፡፡ አልቃሿ ሴት ‹ሀብሌን ከአንገቴ ላይ…› ሳትጨርሰው ለቅሶዋ አስቆማት፡፡ በአልቃሿ እዬዬ መሀል በአራት እና በአምስት ፖሊሶች ተከብቤ ተብጠለጠልኩ፡፡

መርማሪው ፖሊስ ‹ና ወደዚህ! ሲል አንድ ጊዜ ፊቴ ላይ በጥፊ ደረገመብኝ፡፡ ‹ሰርተህ አትበላም ከምትዘርፍ?

ዝም አልኩ..አንድ እውነት ሲኖራችሁ በከሳሾቻችሁ ፊት ዝምታ ነው መልሳችሁ፡፡ እየሱስ በፍርድ አደባባይ፣ በጲላጦስ ፊት ለምን ዝም እንዳለ፣ ስቀለው.. ስቀለው በሚሉ የክፋት ድምጾች ፊት ለምን እንዳቀረቀረ አሁን ገባኝ፡፡ እስካልደረሱብን ድረስ ሌሎች ላይ አይተናቸው የሚገቡን ነገሮች ጥቂቶች ናቸው፡፡

‹የታል ሀብሉ? መርማሪው ፖሊስ በጎላ ድምጽ ጠየቀኝ፡፡

‹እኔ ምንም አልሰረኩም..›

ሁለተኛውን ጥፊ አስከተለ፡፡ ተንገዳገድኩ..ለረጅም ሰአት አዞረኝ፡፡ ገጼ ላይ የመዳፉ ሰንበር የአምስት ጣቶቹን ታርጋ ይዞ ይታኛል፡፡ እስከዛሬ እንዲህ ተመትቼ አላውቅም፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ሲባልም ይሄን እንደሚመስልም አላውቅም ነበር፡፡ እኔ የተማርኩት አንድ ሰው ወንጀል ቢሰራ እንኳን በህግ እንደሚዳኝ እና ማንም በአካሉ ላይ ጥቃት እንደማያደርስበት ነው፡፡ እኔ የማውቀው አይደለም ያልሰረቀ ሲሰርቅ የተያዘም ቢሆን በህገመንግስቱ መሰረት ተጠያቂ እንደሚሆን ነው፡፡

‹ልብሱን አውልቃችሁ ፈትሹት..› አለ

ልብሴን አውልቀው ፈተሹኝ፡፡ ሀብሉን ያስቀምጥበታል ብለው ያሰቡበትን ሁሉ እርግጠኛ በሆነ መንገድ ፈተሹት፡፡ ምንም አላገኙም፡፡

‹ዝም ያለው ምናልባት አፉ ውስጥ አድርጎት ሊሆን ይችላል..ከማለቱ አንዱ ፖሊስ ‹እስኪ አፍህን ክፈት? ሲል ተጠጋኝ፡፡ አፍ ይሄን ያክል ሰፊ ነው? የሆነ ጓዳ ጎድጓዳ ያለው ይመስል ለረጅም ሰአት ሲያስተውለው ነበር፡፡

‹የት ነው ያደረከው ሀብሉን? እውነቱን ብትናገር ይሻልሀል ያለዛ? አለኝ ሁለት ጥፊ ያላሰኝ መርማሪ፡፡

‹የሌባ ነገር ምንድነው እሱ..? አምጣው! አለኝ በካኪ ወደተሸፈነው ዶክመንቴ እያየ፡፡ እስክሰጠው ሳይጠብቅ ከእጄ ላይ መንጭቆ ዶክመንቴን ከመሬት ዘረገፈው፡፡ ‹እሄኔ ገንዘብ መስሎት ከአንዱ ከርታታ ላይ ቀምቶት ነው› አለ ይዘውኝ ከመጡት ፖሊሶች አንዱ፡፡ እንደተራ ነገር ቆሻሻ ላይ እያንደባለሉ አገላበጡት፡፡ ከስምንተኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያሉ የትምህርት ማስረጃዎች ለአንድ ኢትዮጵያዊ ምን ማለት እንደሆኑ ላልገባው የህግ አስከባሪ ሊቅነት ምን ይሰራል? የነፍሴ ጥያቄ ነበር፡፡

መሬት ከወደቁ የትምህርት ማስረጃዎቼ መሀል ስትሬት ፎር ያመጣሁበት የአስረኛ ክፍል የማትሪክ ውጤቴና ሜዳሊያ የተሸለምኩበት የዩኒቨርሲቲ ወረቀቴ ደረታቸውን ገልጠው አይኔ ውስጥ ተማገዱ፡፡ ለምን እንደሆነ በማላውቀው ሁኔታ አይኖቼ እንባ አቀረሩ፡፡

ከወረቀቱ ጋር አብሮ የወደቀ ሀብል እንደሌለ ሲያውቅ ‹ቆሻሻህን አንሳ› ሲል ገላመጠኝ፡፡ ቆሻሻ እንዳይደለ ልነገርው ባልፈልግም አለመንገር ግን አልሆነልኝም ‹ቆሻሻ ነፍስ ያለው የብርሀንን ውበት ሊረዳ አይችልም› ስል ለሶስተኛ ጥፊ የዳረገኝን ንግግር አደረኩ፡፡ ሶስተኛው ጥፊ ፊቴ ላይ ሲያርፍ ከደም ጋር ነበር፡፡ እንደጦስ ዶሮ አንደፋድፎኝ፡፡ ብቻውን የመታኝ አልመሰለኝም..የወዳጆቹን መዳፍ አስተባብሮ ያሳረፈብኝ እንጂ፡፡ የአንድ ሰው መዳፍ ይሄን ያህል ሰማይ ከምድር ያዞራል?

በሆነ የዛለ አቅም ሜዳ የተበተነ ወረቀቴን ላነሳ ጎንበስ ባልኩበት ቅጽበት በመካከላቸው አብሯቸው ሆኖ ሲናገር ያላየሁት አንድ ፖሊስ ወደወረቀቴ ጎንበስ ብሎ ኖሮ ቀድሞኝ የዩኒቨርሲቲ ውጤቴን በእጁ አስገባው፡፡ ያመጣሁት ውጤት ፊቱ ላይ አንዳች ስሜትን ሲጭር እያየሁ ነበር፡፡ ቀና ብሎ አስተዋለኝ..በወፋፍራም ጥፊዎች ዝዬ ደክሜበት ነበር፡፡ እኔጋም እሱጋም ያሉትን ወረቀቶች አስተካክሎ ካኪው ውስጥ አስገብቶ አቀበለኝ፡፡

ተሰረቀብኝ ያለችው ሴት ካላባራ ለቅሶ ጋር ከአሁን አሁን ፍርዴን በመጠባበቅ ቆማለች፡፡ ጉንጮቿ በእንባ ቦይ ሰንበር አበጅተዋል…፡፡ ከበዋት የቆሙትም ፖሊሶች ምን ማድረግ እንዳለባቸው እርስ በርስ በመጠያየቅ ይታዩኛል፡፡ አይኔን ወደእጅ ሰአቴ ሰደድኩ..ስድስት ሰአት ከነግርማው አላገጠብኝ። ከእለታት ውስጥ የበቀለ ህልሜ በህልም እልም ሰወረኝ፡፡ ይሄን ነው በህይወት ማርፈድ የምለው፡፡ ይሄ እኮ ነው ትንሳዔና ሞት በአንድ ገጽ ላይ፡፡ ከዚህ ለማምለጥ እኮ ነው ሞቴን አሳምርልኝ የምንለው። ለዚህ እኮ ነው በሰላም አውለኝ የሚጠቅመው፡፡

ጥሩ የመሰለኝ ፖሊስ ወደሴትዮዋ እያየ ‹እርግጠኛ ነሽ እሱ ነው የሰረቀሽ?

‹አዎ እሱ ነው የሰረቀኝ..ሲነካካኝ፣ ሲላፋኝ ከአንዴም ሁለት ጊዜ አይቼዋለሁ› አለች በእርግጠኝነት፡፡

‹ምናልባት ወልቆ አሊያም ተበጥሶ ወደጉያሽ ገብቶ ሊሆን ይችላል..ግፊያ ካለ እንደዛ አይነት ነገር ይከሰታል› አለ፡፡

‹እረ በፍጹም እሱ ነው የወሰደው..› በማለት እየተናገረች እጇን ወደጉያዋ ሰደደች..እጇን ስታወጣው ግን ከሀብሏ ጋር ነበር።

‹ክው አለች.. ሁሉም ፖሊሶች ስሜቷን ተጋሯት፡፡ አንዴ ሀብሉን አንዴ ፖሊሶቹን እያየች ደርቃ ቀረች፡፡ ምንም ያለ ማንም አልነበረም፡፡ ነጻ መውጣቴን ሳውቅ ትቻቸው ወጣሁ..ከኋላዬ አንድ ኮቴ ይሰማኛል..አልዞርኩም…ማንም ቢሆን ግድ አልነበረኝም፡፡ እየፈጠንኩ ነው..ወዴትና ለምን እንደምፈጥን አላውቅም፡፡ ግን ከህይወት፣ ከሰውነት መራቅ አምሮኛል..የምደርስበት ሌላ ዓለም ናፍቆኛል፡፡

‹ፍሰሀ› አለኝ የሆነ ድምጽ

ወደ ኋላዬ ዞርኩ..ሲተባበረኝ የነበረው ፖሊስ ‹መታወቂያ ጥለሀል› ሲል ወደቆምኩበት ተረማምዶ አቀበለኝ፡፡ ትቼው ሄድኩ። ቆሞ እያየኝ እንደሆነ ያወኩት በኮቴው ነው..በማይሰማ ኮቴው፡፡

ከየት እንደቀረሁ..ከየት እንደዘገየሁ…ምን እንደቀረብኝ..ከምን እንዳስመለጡኝ ማንም አያውቅም፡፡ ወዴት እየሄድን እንደሆነ..ለምን እየሄድን እንደሆነ አያውቁም፡፡ አንዳንዶች በአሁን ውስጥ ዘላለምን ይነጥቁናል፡፡ በቅጽበት ውስጥ ሁልጊዜን ያሳጡናል..በዛሬ ነገን ይቀሙናል፡፡ ደስ ከሚል አሁን ደስ ወደማይል በኋላ እንደገፈተሩኝ ቢያውቁ ተመኘሁ..ባያውቁም ግድ የለም፡፡

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You