የእሳት ዳር ፍሬ

ነገን በተስፋ ርቀት እየተመለከቱ ድንገት ቦግ እልም! ጭልምልም! ያለ ዕለት የከፋ ነው። ያማል። በቁስል የተመታ ልብ ይደማል። ያመኑት ፈረስ ሲከዳ ከፍ ብሎ ዝቅ እንደማለት የሚከብድ ነገርም የለም። የማይባረድ የኑሮ እሳት ወላፈን እየለበለበ ያረረውን ጨለማ ያስመለከተ ዕለት ቀቢጽ ተስፋ ይጠፋል። የወንዝ ዳር ፍሬ ከጅረቱ ልምላሜን የለመደ እንደምንስ ብሎ ከእሳት ዳር ለመኖር ያስችለዋል? በነበልባሉ ወላፈን እየተቃጠሉ፣ ከፊት የሚጠጋውን እሳት ከመመልከት በላይ ሲቃ የለም። ዘር ታቅፋ ዛፍ ለመሆን የምትሻ ፍሬ ለቅሶዋ ለዛፉም ጭምር ነው። ሞቷም የትልቁ የተስፋ ዛፍ ሞት ነው።

ትናንትና ከለምለም መስክ ላይ ያረፈችውን የሕይወት ፍሬውን ተመልክቶ “ስንት አየሁ ሲሳይ” ስለማለት ሲያስብ ሲያሰላስል ነበር። አዱኛውን ሰብስቦ፣ ሲሳዩን ለመቅመስ ፈገግ ብሎ በሀሴት እያጌጠ ነበር። ሕይወት ሙሉ ሙሉ፣ ኑሮም የተድላ ፍስሀ ነበር። እያደር ሁሉም እየቀረ እንደ ፀሐይ ስታሞቀው የነበረችው ሕይወትም እንደ ሀሩር ንዳድ ታነደው ጀመር። በሥራዎቻቸው የምንዘምርላቸው ታላላቅ የጥበብ ልጆች በየእሳት ገደሉ እየሰጠሙ ካለፈ ወዲያ መላቀስ ለኛ አዲስ አይደለም። የወደፊቱን ባናውቅም ከበፊቱም የነበረ ያለ ነው። ወላዷ ጥበብ ደረቷን ስትደቃ መመልከት ለኛ ትርኢት ሆኗል። ግን እስከመቼስ ነው መሽቶ በነጋ ቁጥር ሁሉ ስናላዝን የምንኖረው?

በየኑሮ ኤርታሌው ስለሚወድቁት ከትናንት ጸጸታችን ለመማር እኮ ሁሉም ታጭደው እስኪያልቁ መጠበቅ አይኖርብንም፤ ካቃተን ለዓመት ሁለት ሦስቱ በቂ ነበሩ። የዘንድሮውም ሰሞነኛ የባሰውን አሰማን። ብዙዎች አምቀውና ታምቀው በዚያው ሲቀሩ እርሱ ግን ከሚዲያ አደባባይ ላይ ወጥቶ ድረሱልኝ ማለቱ አስደንጋጭ ነበር። የተዳረስንበትን የመረሳሳት ጥግ የሚያሳይም ጭምር። ጩኸቱ የአንድ የስንታየሁ ሲሳይ ቢመስልም በውስጡ የብዙዎቹን የሚያሳይ መስታወት ነው። ኑሮ የከፋ ዕለት የሀፍረትን ማቅ ለብሶ፣ ይሉኝታን በጣጥሶ አደባባይ እንደመውጣት ያለ ረመጥ የለም። ግን ይሄ የጥበብ ፍሬ አደረገው። ወጣ።

ከዛሬው የእሳት ዳር ጩኸት፣ አስቀድሞ ከነበረበት የወንዝ ዳር ፍሬነት እንጀምረውና የዝነኛውን አጥር ወደኋላ እንዝለለው። ዓይን ሳንነቅል፣ ልብ ተክለን የተመለከትናቸውና ያደመጥናቸውን ምርጥ ምርጥ የሙዚቃ ክሊፖችን ያበረከተልን ስንታየሁ ሲሳይ ሥራውን ለትርፍና ጥቅም ሲል እንዳያሳልጥ ያደረገው ነገር፤ በልጅነት ካደገበት ማህበረሰብ የሕይወት ዘዬ በመቀዳቱ እንደሆን ይናገራል። ጭንቁ ሥራው ነበር። ስንታየሁ የት ተውልዶ ቢያድግ ይሆን ከዚህ ማንነት መቀዳቱ? … ፍቅር እንጂ ጥላቻ፣ ሰው እንጂ ዘር፣ መተሳሰብ እንጂ ጭንቀት፣ መስጠት እንጂ ንፍገት ከማይታወቅባት የልደታ ሰፈር ውስጥ ነበር ተወልዶ ያደገው። “ከጎረቤት በዳንቴል ተሸፍኖ ከሚቀባበል ማህበረሰብ ነው ያደግኩት” ይላል።

ልጅ ሆኖ ወላጅ እናቱ ዳዊት እንዲደግም ቤተክርስቲያን፣ ቁርአን እንዲቀራ መስጊድ አስገብታው እንደነበረ አይዘነጋውም። ወዲህ በቅዳሴ፣ ወዲያ በአዛን ተኮርኩሯል። እንዳደገበት ማህበረሰብ በነበሩ አካባቢዎች ሁሉ ይኼ የብዙዎች ታሪክ ነው። ኢትዮጵያዊነት በአካለ ሰው ተገልጦ የሚታይበት ነበር፤ ነበር ከማለታችን አስቀድሞ። በእነርሱ ውስጥ ራስን ወዶ፣ ከራስ ተፋቅሮ ወርቅ ቁፋሮ አይገባምና እርሱም ጥቅሙን አስልቶ የሚሰራ አልሆነም። “ለገንዘብ ስል ሠርቼ አላውቅም። ስለራሴና ስለቤተሰቤ እንኳን ሳልጨነቅ የወደድኩትን ሥራ ነው የምሠራው። ኢትዮጵያዊነት የሚታይበትና ዛሬ ላይ ልጆቼ ሲያዩት የማያፍሩበትን ሥራ ነበር የምሠራው። እነዚያ ነገሮች ጋር ዋጋ አስከፍለውኛል” ሲል ባንደበቱ ተናግሯል። ባይሆንማ ኖሮ እኚያን ሁሉ የሙዚቃ ክሊፖችን የሠራ፣ በአድናቆት ያጨበጨብንለት ሰው ዛሬ “ለልጆቼ መሆን ተሳነኝ” ሲል ባልሰማን ነበር።

ጎልማሳው ስንታየሁ ሲሳይ ቀደም ሲል የወጣትነቱን ገሚስ ያሳለፈው በጥበብ ሳይሆን በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ነበር። ለኳስ ካደለው ተክለ ሰውነቱና ችሎታው ጋር ነገን ለሀገሩ የሚመኙለት ነበር። ወደ ታችኛው የኦሜዱላ እግር ኳስ ቡድን ተቀላቅሎ በ”ሲ” ቡድን ውስጥ 3 ወራት ያህል ከሰለጠነ በኋላ ወደ “ቢ” ከፍ አለ። ከአሰልጣኙ ንጉሴ ገብሬ ጋር ለኳስ ትዕይንት ሲሰናዳ ድንገት ግን ዋናውን ቡድን ሳይቀላቀል ጥበብ ጠራችው። ከኳስ ሕይወቱ ባሻገር ወደ ጥበብ መንገድ መግቢያውን የቀደደለት ከጥበብ ሥራዎች ጋር የነበረው ቅርበት ነበር። ከመጽሐፍ ሻጭነት ለጉምቱ ደራሲነት የበቁ እንዳሉ ሁሉ ከፊልም አከራይነት ወደ ፊልሙ ኢንዱስትሪ የጠለቁም ብዙ ናቸው። ስንታየሁም ከእነዚህ ቪዲዮ ቤቶች ከወጡት አንዱ ነው። ታዲያ የጀመረው ያኔ ፊልም ብቻ ሳይሆን ፊልም ከነዲቪዲው በሚከራይበት ዘመን ላይ ነበር። ይህን ሲሠራና የሚያከራያቸውን ሁሉ ሲመለከት ከቆየ በኋላ ወደ ፎቶ አንሺነት ገባ። በሙያው በፍጥነት እያደገ መላው ሀገሪቱን የሚያካልል ተጓዥ ሆነ። ከተለያዩ ድርጅቶችና ኤምባሲዎች እንዲሁም የውጭ ዜጎች ጋር ትስስሩን አፈጠነው። አውደ ርእዮችን በማዘጋጀት የፎቶግራፍ ሥራዎችን ለእይታ ማብቃቱን ተያያዘው።

ይህን ጊዜ የተመለከቱትም ወደ ፊልም ጥበብ መግቢያውን አመቻቹለት። በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኬኒያና ዱባይ በመሄድም በፊልም ስክሪፕት አጻጻፍና በዳይሬክቲንግ ብቁ የሚያደርጉትን ሥልጠናዎችን ወሰደ። በአፋር ክልል ውስጥ ከፈረንሳይ ሀገር ከመጡ የፊልም ባለሙያ ልዑካን ጋር በህጻናት ዙሪያ በተሠራው ዶክመንተሪ ፊልም ስንታየሁ ችሎታውን አስመሰከረ። በስክሪፕትና ዳይሬክቲንግ የሠራበት እርሱ ነበር። በ1996ዓ.ም የወጣው “ቀዝቃዛ ወላፈን” ፊልም በኢንዱስትሪው ውስጥ የማስጀመሪያ ፊሽካ ነበር። በተለይ ለስንታየሁ። አቅሙን ከፍ እያደረገና በጉልህ እየታየ የመጣውም ከዚያን በኋላ ነበር። ከሚሊኒየም ሰሞናት ጀምሮ ከምንመለከታቸው ጣፋጭ የሙዚቃ ክሊፖች ውስጥ ስሙ አይጠፋም። ከሕዳሴው ግድብ ሥራዎች ጀምሮ በልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችም ስሙ የሚነሳ ነበር። ዛሬ ያን በጎነት ለራሱ ሽቷል።

ተሰጥኦ ልክ እንደፍሬ ዛፍ ማለት ነው። በአንድ ጀንበር ዛሬ ተክለው፣ ዛሬውኑ ኮትኩተው ፍሬውን ለመብላት የሚያሰናዱት አይደለም። ከልጅነት እስከ ዕውቀት በደም ውስጥ ተሳስሮ ዕለት ዕለት ሲያቆጠቁጥ የሚኖር እንጂ። ገጣሚው ከመግጠሙ በፊት የተገጠመውን እያነበበ ይደርሳል። ፀሐፊውም በጽሑፎች ውስጥ ያልፋል። ተዋናዩም ቢሆን ትወናን ሳያጤን አይመጣም። በእንክብሉ ሁሉም ከራሳቸው ሥራዎች ውጭ የሆነ መነሻ አላቸው። ስንታየሁ ሲሳይ የሙዚቃ ክሊፕ ዳይሬክተር እንደመሆኑ አስቀድሞ በቆንጆ ጥራት የተሠሩ የሙዚቃ ምስሎችን ተመልክቶ ተጠበበ እንዳንል፤ ያደገው ፎቶግራፍ እንኳን ብርቅ በነበረበት ዘመን ላይ ነው። ቢሆንም ግን እሱም ሊያስታውሰው የሚችለው አንድ ነገር አለ፤ እሱም ባለ ነጭና ጥቁር ምስሉ ቦርጫም ቴሌቪዥን ነው። ብቸኛው አንቴና በሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚታዩ የሙዚቃ ክሊፖች ነበሩ። መልካሙ ተበጀ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ ዓለማየሁ እሸቴ፣ ሀመልማል አባተ፣ አስቴር አወቀ… እያለ ከሚመጣው ጀንበር ጋር ከቴሌቪዥኑ መስኮት ላይ እየተፈራረቁ ሲውረገረጉ ተመልክተናል።

ቅሉ ግን የምንመለከታቸው ከአንድ መናፈሻ ውስጥ ካለ ዛፍ ፊት ቆመው፣ ወይ ደግሞ ከአንደኛው መንገድ ዳር ጀምሮ እስኪያልቅ የምንመለከተው አንድ እነርሱኑ ብቻ ነበር። በጥቅሉ ዛሬ በአንድ የሙዚቃ ክሊፕ ውስጥ ወሳኙ ነገር የምንለው “ሎኬሽን” አልነበረውም። ቀጥሎ በነበረው የ90ዎቹ አጋማሽ “ክሊፕ” የምትለዋን ነገር እያወቅንና እየተላመድን ስንመጣ ግን ነገሮች መቀየራቸው አልቀረም። በዚያው ሰሞን ላይ ብቅ ብሎ ሙዚቃን መሳጭ ፊልም ያደረገ አንዱ ስንታየሁ ሲሳይ ነው።

ጥበብና ጥበበኛው አንድ መንገድ ላይ ተገናኙ። ከዚህ ቀደም ብሎ በዶክመንተሪ ፊልሞች ውስጥ የስንታየሁ ስም ከፍ ማለት ጀምሮ ነበር። ግን ትክክለኛው መዳረሻው ሙዚቃው መሆኑን በማመን ወደዚያው ከሚወስደው ባቡር ውስጥ ገብቶ ተሳፈረ። ከመንደሩም ደረሰ። የአንደኛውን ጓደኛውን ትከሻ ተደግፎ የሙዚቃው ግንብ ላይ ወጣ። አጥሩን ዘሎም ወደ ግቢው ገባ። “ባቡሬ” የበኩር የሙዚቃ ሥራው ነበር። ድምጻዊ ታደለ ሮባ ዋና ካፒቴን፣ ጋሽ አበራ ሞላ በረዳትነት ከድሬዳዋ አዲስ አበባ በሚያከንፏት የሙዚቃ ባቡር ስንታየሁ ተጠበበበት። ሙዚቃው በድምጽ ራሱን ችሎ የሚደመጥ ቢሆንም ወደ ክሊፕ መቀየር ግን እስካሁን ከነበረው ሂደት የባሰ ፈታኝ ነው።

ጆሮ ሞኝ ነው በጥቂት አሞኝተው ለመሸወድ ይቻላል፤ ዓይን ግን አድበስብሰው በዋዛ ሊያመልጡት አይቻልም። ለዓይን ሳቢ፣ ለልብ የሚጣፍጥ አድርገው ለመሥራት ካልቻሉ ሙዚቃውን ከነድምጹ ይዞት ገደል ይገባል። በድምጽ ወደናቸው ደጋግመን ስንሰማቸው በክሊፕ ሠራን ተብሎ የጠበቅነውን ውበት በማጣት የሰለቸናቸው ሙዚቃዎች ስለመኖራቸውም ልብ ይሏል። የክሊፕ ባለሙያ ቀድሞ በድምጽ ደረጃ እንደሠራው ባለሙያ እንዳሻው በተመቸው ዓይነት አድርጎ የመሥራት ነፃነት የለውም። ከምስሉ ጋር የሚጣጣም እንዲሆን ድምጹን ወደ ምስሉ ሊያመጣው አይችልም። ያለው አማራጭ ምስሉን ወደ ድምጹ በመውሰድ፣ ለድምጹ የሚሆነውን ምስል መፍጠር ብቻ ነው። ስንታየሁም ይህን ለማምጣት ለ“ባቡሬ” ልክ እንደፊልም ሁሉ ስክሪፕት ጽፎ፣ ከጅምር እስከ ፍጻሜ እያንዳንዷን ቦታ መርጦ፣ አልባሳቱን ጨምሮ እያንዳንዱን ጥቃቅን ሁሉ አሰባጥሮ “ባቡሬ”ን ሠራው። ባቡሩም እየገሰገሰ መጣ። ስንታየሁ ገና በመጀመሪያው ሥራው አድናቆትና ተወዳጅነትን አተረፈ። ሁለተኛውን በምናሉሽ ረታ ሱዳንኛ ቀጠለ።

ከዚህ በኋላማ ምኑ ተነግሮ ያልቅና ባቡር ተፈተለከ። በነፃነት መለሰ “የታል ልጁ የታል” መባል ተጀመረ። አንድ ሰሞን ላይ ሳር ቅጠሉ ሁሉ ሰለል! ኩቡል! ሲሉበት በነበረው በሳሮን ተፈሪ “ሚሶ ነጋያ” ስንታየሁ እጁን ለመሳም በቅቶበታል። የሐመሮችን ውበት ከነሀረጉ መዞ በዓይን የሚበላ፣ በጆሮ የሚመጠጣ ሙዚቃ አድርጎታል። ከትምህርት ቤት እስከ ፍቅርና የትዝታ ዳገት ከወላይታ ባሕል ጋር ቋጭቶ ያቀረበው የጥበቡ ወርቅዬ “ሊጋባ”ን ማን ይረሳል። ሄለን በርሄ በ“ልቤ”፣ ዘለቀ ገሠሠ ደግሞ “ሀገሬን”፣ ኤደን ገ/ሥላሴ “ሰው ዋኖ”ን ጨምሮ እስከ ሀመልማል አባተ፣ ኃይልዬ ታደሰ ኧረ ምኑ ቅጡ። የእርሱ የጥበብ ዓይኖችና እጆች ያልደረሱበት የሙዚቃ ክሊፕ የለም።

ሌት ተቀን፣ ነግቶ ሲመሽ ውሎና አዳሩ ሙዚቃው ላይ ሆነ። ራሱን ዘንግቶ እረፍት አልባ ሆነባቸው። “…እንዲያውም ብዙ ሽበት የመጣው ሥራዎቼ በጣም ያስጨንቁኝ ስለነበረ ነው” በማለት በቀልድ ሳይሆን ምሽት ጭምር እያነጋ ይሠራ እንደነበረ ያወሳል። ሰው ሥራውን ይገልጽ ይሆናል፣ ሥራ ሰውን ሲገልጽ ግን ስንታየሁ ሲሳይን ነው። ስል ቃላትን ለማደማመቅ አይደለም። የእርሱ ሥራዎች የራሳቸው የሆነ ቀለም አላቸው። ጠረናቸው የስንታየሁ መልካቸው ስንታየሁን ነው። የሙዚቃ ክሊፖቹን ምስል ስንመለከት ገና የማን እንደሆኑ ለይተን እናውቃቸዋለን።

እነዚህ ታላላቅ የሙዚቃ ምሰሶዎችን በማቆም ድፍን 20 ዓመታትን ያስቆጠረው ስንታየሁ ሲሳይ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ በኑሮው ሞቆት ባይደላውም፣ ከፍቶት ግን አንገት አልደፋም ነበር። ቢመችም ባይመችም እንደማንም ያለሰቀቀን ኑሮና ቤተሰቡን ሲመራ ቆይቶ ነበር። በመሃል ግን የዛሬ አምስት ዓመታት ገደማ ድንገት ከሙዚቃ እንደወጣ ሳይመለስ ቀረ። አንገቱን ደፍቶ በኑሮ በረሀ ላይ ሲናውዝ፣ የመከራ ሀሩር የቤትና ልጆቹን አናት ሲያነድ “ምነው ወዳጄ?” ባይ አጣ መሰል ሥራው ሳይታይ፣ ድምጹም ሳይሰማ ቀረ። ሥራ ሥራውን ሲል ከጎን ኑሮ ሽመሉን መዘዘለት። ስንታየሁ ያቺን የእሳት ዳር ፍሬ ወደመሆን የገባው ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ነበር።

ፊቷን አዙራ የጠለቀች ጀንበር ጨለማውን እንዳስታቀፈችው ሳትመለስ ቀረች። የሕይወት ግርፋት፣ የኑሮ እሳት ተቀጣጠለ። ከነበረባት የከፍታ አንጓ ላይ ረግፎ፣ ሲምዘገዘግ ቁልቁል ወርዶ ከወላፈኑ ፊት ጠብ! አለ። እነዚያ ዓመታት ለእርሱ የጨለማ ዘመናት ነበሩ። በደህናው ጊዜ ያካበተው ሀብት ንብረት የለምና ዙሪያው ያሉትን ቤተሰቦቹን ለማኖር ሲል ሲሠራባቸው የነበሩትን ቁሳቁሶች አንድ ሁለት እያለ ሸጣቸው። ለረዥም ዓመታት በግል መኪናው መንቀሳቀስን የለመደው ስንታየሁ እሷንም ሸጣትና የታክሲና የባሱን ግፊያ ተቀላቀለ። በዚህ ሁሉ መስዋዕትነት ለልጆቹ ትምህርት ቤት፣ ለቤተሰቡ እያለ ላለመውደቅ ሲፍጨረጨር ቆይቶ በስተመጨረሻ ነበልባሉ ከፋ። እያደር ህመሙ ጠና። ሁሉም ነገር ከፋ። “…የቤት ኪራይ ለመክፈል አቅቶኝ ፖሊስ እስኪከሰኝ፣ ልጆቼ ደጅ ወጥተው እስኪያለቅሱ ድረስ… የልጆቼን የትምህርት ቤት ክፍያ ለመክፈል አቃተኝ። በኔ ልጆች የደረሰ በማንም ልጅ አይድረስ…” ሲል በተሰበረ ልብ፣ እየተንገሸገሸ የመከፋቱን ጥግ ገልጾ ነበር።

ከእሳት ዳር የነበረው ስንታየሁ ሲሳይ ከመሞት መሰንበት ሲል ከሚዲያ አደባባይ ከወጣ በኋላ እንደመረሳቱ በዝምታ አልታለፈም። “አለሁልህ!” ሲል በቻለው ሁሉ ጎኑ የቆመ ቀላል ሰው አይደለም። በየማህበራዊ ሚዲያውና በተለያዩ መንገዶች 3 ሚሊዮን ያህል ብር ተሰበሰበለት። እሳቱ እየረገበና ፍሬውም በተስፋ የለመለመ መሰለ። በዚህ መሃል ጉዳይህ ጉዳዬ ብሎ እየተንቀሳቀስ ያለ አንድ ኮሚቴም ይገኛል። አርቲስት ስለሺ ደምሴ(ጋሽ አበራ ሞላ)፣ አርቲስት ተስፉ ብርሃኔ፣ ፎቶግራፈር አንቶኒዮ፣ ደረጀ ምክሩ እንዲሁም ጋዜጠኛ መሰለ ገብረ ህይወት እና አብረሃም ግዛው የተዋቀሩበት ኮሚቴ ነው። ከሳምንት በፊትም ለጋዜጠኞች ጥሪ አድርገው ነበር። በሰጡት መግለጫ ውስጥም “…እስካሁን የተደረገለት ድጋፍ እንዳለ ሆኖ፤ ወደ ሥራው እንዲመለስ በማድረግ እርሱን በቋሚነት ስለማቋቋም አስበናል…” በማለት ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል። የሠራላቸውን ድምጻውያን በማሰባሰብ ኮንሰርት የማዘጋጀቱን ነገርም እያሰላሰሉበት ነው። ትልቁ ጋሬጣ የሆነበትን የመኖሪያ ቤት ችግሩን ለመቅረፍም ከንቲባው ጽህፈት ቤት ድረስ ገብቶ ለማሳማን እንደሚተጋ ኮሚቴው አሳውቋል። የልጆቹንም የትምህርት ቤት ጉዳይ ቢሆን ትምህርት ቤቱ በኛ ጣለው ብሎታል። ከእንግዲህም የወንዝ ዳር እንጂ የእሳት ዳር ፍሬ እንደማይሆን ተስፋ እናድርግ። ሁሉም መልካም ይሆናል!

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You