የካፒታል ገበያ ያለንን ሀብት በማስተባበር ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማፋጠን ያግዛል

አዲስ አበባ፡– የካፒታል ገበያ ወደ ሥራ መግባት ያለንን ሀብትና እውቀት በማስተባበር የተጀመረውን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠን እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጹ፡፡ የመጀመሪያው የካፒታል ገበያ ጉባዔ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ትናንት መካሄድ ጀምሯል፡፡

አቶ ማሞ ምህረቱ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በሁሉም ፈጣን እድገት አስመዝግባለች፡፡ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራም ገብታለች፡፡

የካፒታል ገበያው የተጀመረውን የኢትዮጵያን ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመደገፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራትና በጋራ መሥራት ከተቻለ ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት እንደሚቻል ገልጸዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በፋይናንስ ዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን የሚቀርፉ አዳዲስ አሠራሮችን እየተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።

የካፒታል ገበያ ምህዳሩን በማስፋት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ የግሉን ዘርፍ ጨምሮ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማትን መደገፍ፣ ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠርና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በዘላቂ መሠረት ላይ መገንባት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፈጣን እድገት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በቅርቡ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ደግሞ ይህንን የሚደግፍ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስመንትን ለመሳብና ሰፊ የሥራ እድል በመፍጠር በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡

እንደዚህ አይነት ጉባዔዎችም ልምድን ለመጋራትና ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖር ሊወሰዱ ስለሚገባው ርምጃዎች ትልቀ ግብዓት ለመሰብሰብ የሚያስችሉ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተልህኩ፤ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ የተረጋጋና ዘላቂ ኢኮኖሚን ለመገንባት የካፒታል ገበያ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የካፒታል ገበያ ምህዳሩን አካታች፣ ንቁ፣ ችግሮችን መቋቋም የሚችል ሆኖ ከተገነባ የፋይናንስ ሥርዓቱን ቀላል ማድረግና ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በጉባዔውም ባለሥልጣኑ እስካሁን ያከናወናቸውን ሥራዎች ለሕዝብ ለማስተዋወቅ፣ በሂደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንና መልካም እድሎች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ገልጸው፤ ለኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ጠንካራ መሠረት ለመጣል ሲዘጋጅ የቆየው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ለሕዝብ ሽያጭ ማቅረብና የግብይት መመሪያም ይፋ እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡

ጉባዔው ”ቀጣይነት ያለው መንገድን ማበጀት” በሚል መሪ ቃል እየተከናወነ ሲሆን፣ ለሦስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቀጥል የወጣው መርሃግብር ያስረዳል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

 አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም

Recommended For You