አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የጤና መስፈርቶችን በማሟላት በተለይም በድንገተኛ አደጋ ዝግጁነት ፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ አቅም ላይ ትልቅ ለውጥ ማሳየቷን የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
በዓለም የጤና ድርጅትና በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ዓለም አቀፍ የድንገተኛ አደጋ ሥራዎች ሥልጠና (GEOCX 2024) በትናትናው ዕለት መሰጠት ጀምሯል፡፡
ጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የጤና መስፈርቶችን በማሟላት በተለይም በድንገተኛ አደጋ ዝግጁነት ፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ አቅም ትልቅ ለውጥ አሳይታለች።
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያላት አቅምም ሀገራዊ የህብረተሰብ ጤና ጂኖሚክ ላብራቶሪ እና በመላ ሀገሪቱ የተስፋፋ የላብራቶሪ ንብረቶችን ያጠቃልላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ይህን ዓለም አቀፍ ሥልጠና ማዘጋጀቷ ያላትን አቅም ለመገምገም፣ ያሉትን ክፍተቶች ለማሻሻል እንዲሁም የምላሽ ስልቶችን የማጥራት እድል ይሰጣል ያሉት ሚኒስትሯ፤ እንደዚህ አይነት ሥልጠናዎች በጤናው ዘርፍ ያሉ ትብብሮችን እንደሚጨምሩ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም በጋራ በመሥራት የዓለም አቀፍ የጤና ስጋቶች መከላከል እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡
እንደ ዶክተር መቅደስ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ አገልግሎት ፣ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም እንዲሁም የቤተሰብ ጤናን በማጠናከር ለገጠሩ ማህበረሰብ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ተችሏል። ሆኖም እንደ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ሊከሰቱ የሚችሉ ሌሎች ድንገተኛ የጤና አደጋዎችን ለመቆጣጠር ጠንካራ የጤና ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ የጤና ጥበቃን ለማጠናከር ያላት ቁርጠኝነት የበሽታ ክትትልን በዲጂታል እስከ ማድረግ ድረስ ይዘልቃል፡፡ ይህም የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን በበለጠ ፍጥነት እና ትክክለኛ ምላሽ እንድንሰጥ ያስችለናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር)፤ እነዚህ የመሰሉ ዓለም አቀፍ ሥልጠናዎች ለወደፊት የህብረተሰብ ጤና ስጋቶች ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት የጋራ አቅምን የሚያጠናክሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም ለህብረተሰብ ጤና ደህንነት ያላትን ቁርጠኝነት በትብብር፣ በሥልጠና እና የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት እያሳየች ትገኛለች ብለዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ኖንህላንህላ ድላሚኒ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፣ ኢትዮጵያ የዚህ ሥልጠና አዘጋጅ እንደመሆኗ መጠን የምትጫወተው ሚና ለዓለም አቀፍ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመመከት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል። የ GEOCX 2024 ሥልጠና ለአባላት ሀገራት የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት እና የምላሽ ሥርዓቶቻቸውን እንዲያጠናክሩ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም