ኢትዮጵያ በማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ያላት ተሞክሮ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ያደርጋታል

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ያላት ተሞክሮ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት እንደሚያደርጋት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ፡፡

የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች የተካተቱበት ልዑክ በሃዋሳ ከተማ እና በድሬዳዋ አስተዳደር በመገኘት የማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች በኢትዮጵያ ያላቸውን ተሞክሮ ተመልክቷል፡፡

በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ያላት ተሞክሮ እንደ ጥሩ ትምህርት ተወስዶ ለሌላ ሀገር ማካፈላችን፣ ሀገራችን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የምትሆን ሀገር መሆኗን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራም ረጅም ዕድሜ ያለው ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ በኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ መንግሥት ለችግር የታጋለጡ ወገኖችን ለመርዳት የራሱን ፕሮግራም ቀርጾ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ በ2007 ዓ.ም. የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ መውጣቱን ተከትሎ ስትራቴጂ ወጥቶለት ፕሮግራሞቹ በተደራጀ መንገድ እንዲከናወኑ ሲደረግ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

በሴፍቲኔት ፕሮግራም ደግሞ ሰዎች የገንዘብና የምግብ ርዳታ የሚያገኙበት ብቻ ሳይሆን ሰዎች ሠርተው መለወጥ የሚችሉበት ፕሮግራም መሆን አለበት ተብሎ ሰዎች ባገኙት ትንሽ ድጋፍ የራሳቸውን ሥራ ሠርተው ከተረጅነት እንዲወጡ ምርታማ ፕሮግራም መቀረጹንም ገልጸዋል፡፡

ፕሮግራሙ ሲጀምር በገጠር ያሉ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍ እንደነበር ጠቁመው፤ በገጠሩ ላይ የተመዘገበውን ውጤት በማየት ከግብርና ሚኒስቴር እና ከከተማ መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የከተማ የሴፍቲኔት ፕሮግራም መጀመሩን አመላክተዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ከሌሎች የምንማረው ነገር እንዲሁም ለሌሎችም የምንሰጣቸው ነገር አለ ያሉት ኤርጎጌ (ዶ/ር)፤ ማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን እና የመንግሥት ለመንግስት ግንኙነትን ያጠናክራሉ ብለን እናምናለን፡፡ ከወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በጅቡቲ የጀመርነው ሥራ አለ፡፡ አንዱ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የምንሰጠው የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎት ነው። ይህን ሥራ ወደ ደቡብ ሱዳን እና ወደ ሌሎች ጎረቤት ሀገራትም የምንወስደው ይሆናል ብለዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን ጀንደር፣ ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አያ ቤንጃሚን በበኩላቸው፤ ልዑካቸው የማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች በኢትዮጵያ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆኑ በመመልከት ደቡብ ሱዳን ከተሞክሮው ልምድ መውሰድ የምትችልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ቆይታ ማድረጉን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው ወደ ጎዳና የሚወጡ ዜጎችን አንስቶ በማገገሚያ ማዕከላት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ መደበኛ ሕይወትን እንዲቀላቀሉ የሚደረግበት ሂደት እንዳስደነቃቸውና ሀገራቸው ከዚህ ተሞክሮ ትምህርት እንደምትወስድ ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን መንግሥት በማህበራዊ ጥበቃዎች ላይ በጀት በመመደብ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ባለመኖሩ እንደ ዓለም ባንክ ባሉ አጋሮች በሚመድቡት በጀት እንደሚሠራ ጠቁመው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በራሱ አቅም ለዜጎች የሚያደርገው አስተዋጽኦ መኖሩ ትልቅ ተሞክሮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጤንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ከሌለ አምራች ማህበረሰብ አይኖርም ያሉት ሚኒስትሯ፤ በደቡብ ሱዳን የጤና መድህን ዋስትትና ፕሮግራም እንደሌለ እና በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የማህበረሰብ ጤና ኢንሹራንስ ብዙ ጥቅም እንደሚሰጥ ተገንዝበናል ነው ያሉት።

ተስፋ ፈሩ

 አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም

Recommended For You