ከታዳጊነት እስከ ጉልምስና በሙዚቃ ዝና

እንደብዙዎቹ የሀገራችን ቀደምት ድምፃውያን ለሙዚቃ ስትል ከቤተሰብ አልተጣላችም። ሙዚቃ አሠሩኝ ብላ የበርካቶችን ደጅ አልጠናችም። ሙዚቃ እራሷ ፈልጋት መንገድ ያበጀችላት ይመስላል። ውልደትና እድገቷ የጥበብ መናኸሪያ በሆነችው ሽሮሜዳ ነው። በመኖሪያ ቤታቸው ማንኛውንም ሥራ ስትሠራ ሙዚቃ እየሰማች አብራ ታንጎራጉራለች። በተለይ የብዙነሽ በቀለ፣ የንዋይ ደበበና የሐመልማል አባተ ሥራዎችን አብዝታ ትዘፍናለች። መጀመሪያ አካባቢ ቤት ውስጥ ስታዜም “እባክሽ አትረብሽን” የሚሉ ድምፆች ይሰሙ እንጂ ተቃውሞም ይሁን ማበረታቻዎች አልነበሩም።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በተከታተለችበት የአመሐ ደስታ የሙዚቃ ቡድን ቢኖርም ለመቀላቀል አላሰበችም። ግን ደግሞ የቅርብ ጓደኞቿ ስትዘፍን ድምጿን ሰምተው ተደንቀዋል። አንዲት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ መዝፈን ትችላለች የሚል ወሬ ቡድን መሪው ጋር ደርሷል። በኃይለኝነቱ የሚታወቀው ይህ ዩኒት መሪ ወደዚች ተማሪ ክፍል ገብቶ የምትዘፍነው የትኛዋ እንደሆነች ጠየቀ። ያኔ ‹‹ጥፋቴ ምን ይሆን?›› አለች፤ ተንቀጠቀጠች። ዩኒት መሪውም ከክፍል ጓደኞቿ ነጥሎ ወደ መምህራን ቢሮ ወሰዳት።

ቢሮ ሲደርሱ ‹‹መዝፈን ትችላለች ሲባል ሰምቻለሁና እስቲ ዝፈኚ›› አላት። ፒያኖ የሚጫወቱ መምህር እያጀቧት ዘፈነች። በድምጿ የተደነቁት ሁለቱም መምህራን እንዴት እስከዛሬ ሳናውቅ በሚል ተገርመው የትምህርት ቤቱን የሙዚቃ ቡድን እንድትቀላቀል አደረጉ። የትምህርት ቤቱ የሙዚቃ ቡድን አባላት ቀድሞም ልምምድ ሲያደርጉ የቆዩና በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ሥራቸውን ሲያቀርቡ የነበሩ በመሆናቸው ለትንሽ ጊዜ ከነሱ ጋር መዋሓድ ከብዷት ነበር። ነገር ግን ተፈጥሮዋ ለሙዚቃ የተሠራ ነውና ብዙም ሳትቆይ ተዋሓደች፤ለመደች።

አመሐ ደስታ ትምህርት ቤት አርባኛ ዓመቱን ሲያከብር ከትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ በተጨማሪ በርካታ የአካባቢው ነዋሪ የተሳተፉበት የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት አዘጋጅቶ ነበር። በዚህ ዝግጅት ላይ የአሰፉ ደባልቄን “እንደው ክብረት ዓለም” እና የሐመልማል አባተን “የትዳሬ ማገር” የተሰኘውን ሙዚቃ በመጫወት ድንቅ ብቃቷን አሳያች። በብቃቷ የተደነቁ ተማሪዎች በርካታ ሳንቲም በመሸለማቸው የሱሪዋ ኪስ በሳንቲም ተሞልቶ ከብዶት ኖሮ ወደታች ካልወለኩ እያለ አስቸግሯትም ነበር። ያኔ በሰፈሩ ዝናዋ ሲናኝ ከትምህርት ቤት አልፎ ራሷን በትልቅ መድረክ ለማየት ማለም ጀመረች፡- የያኔዋ ታዳጊ የአሁኗ ዝነኛ ድምፃዊ ኅብስት ጥሩነህ።

የኅብስት ጥሩነህን የመድረክ ብቃት ያዩ ቤተሰቦቿ የሷ ድምፅ የተለየ መሆኑን ለማወቅ ጊዜ አልፈጀባቸውም። ለዚህም ይመስላል ቤተሰቦቿ በኩራት ስለኅብስት ብቃት በየሄዱበት መናገር የጀመሩት። ታላቅ ወንድሟ ከጓደኛው ጋር በጨዋታ መሐል ታናሽ እህቱ የሚገርም ድምፅ እንዳላት ይነግረዋል። ይህን የሰማው ጓደኛው የታንጎ ሙዚቃ ቤት ባለቤት የሆነው ዓሊ አብደላ ኬፋን (ዓሊ ታንጎ) እንደሚያውቀውና እሱ ጋር ቢወስዷት ጥሩ እንደሆነ ይነግረዋል። ወንድሟ በሀሳቡ በመስማማቱ ወደ ታንጎ ሙዚቃ ቤት ያቀናሉ። ዓሊ ታንጎም ካሴት ማውጣት ከፈለገች ደፋር ዘፋኝ መሆን እንዳለባት ይናገራል።

ከእድሜዋ ትንሽነት አንጻር ዘፋኝ ትሆናለች ብለው ያላመኑት አቶ ዓሊ ‹‹እስቲ ዝፈኚ›› አሉ። ያኔ በዛው በታንጎ ሙዚቃ ቤት ከወጣ ቅርብ ጊዜ የሆነውን የንዋይ ደበበን “የጥቅምት አበባን “ዘፈነች፤ የሐመልማል አባተን በድንቅ ብቃት ደገመች። ያኔ ዝፈኚ ስትባል ያለፍርሃት ሰዎች ባሉበት ዘፍናለችና “የምታድግ ልጅ ናት” ሲሉ ዓሊ ታንጎ ካሴት ሊያወጡላት ተስማሙ። እናም ከገጣሚያንና ዜማ ደራሲያን ጋር መገናኘት ጀመረች። የሙዚቃ ቤቱ ባለቤት ያኔ ብቸኛ ለነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚገርም ድምፅ ያላት ትንሽ ልጅ አለችና ብትመለከቷት ሲሉ ጥቆማ ሰጡ። ጥቆማውን ተቀብለው የተመለከቷት የቴሌቪዥን ጣቢያው ሰዎች በብቃቷ ስለተማመኑ የብዙነሽ በቀለን “የሚያስለቅስ ፍቅር” እያዜመች የ120 መዝናኛ ፕሮግራም ላይ ቀረበች።

አፍሮ ፀጉር ቡኒ ሹራብ የሚያሳሳ የልጅነት መልክ ይዛ የምታዜመው ታዳጊ የብዙዎች ትውስታ ናት። በ1985 ዓ.ም ከማትሪክ ፈተናዋ ተቀራራቢ ጊዜ ውስጥ ‹‹በርቺ በሉኝ›› የተሰኘ የመጀመሪያ አልበሟ በታንጎ ሙዚቃ ቤት አማካኝነት ገበያ ላይ ዋለ።

እምቡጥ ነኝ ለሚያየኝ

እምቡጥ ነኝ ጽጌረዳ

ለሁሉም አዲስ ነኝ

ጀማሪ ነኝ እንግዳ

ምኑንም የማላውቅ……

በርቺ በሉኝ

አይዞሽ በሉኝ

ጀማሪ ነኝና በርቺ በሉኝ

በዚህ ዘፈን አስራ አምስት ዓመቴ ነው ብላ በመናገሯ በተለያዩ መድረኮች ላይ እድሜዋን መደበቅ የማትችል አርቲስት ይሏታል። በወቅቱ አባቷ የትምህርት ሚኒስቴር ጸሐፊና የቤተክርስቲያን አገልጋይ በመሆናቸው ከተወሰኑ ሰዎች “ልጅህ ስትዘፍን እንዴት ዝም ትላለህ?” የሚል አስተያየት ቀርቦላቸው ነበር። አባቷ ፈጣሪ የሰጣት ፀጋ ነው በማለት ለሙዚቃ ሥራዋ ድጋፍ እንደቸሯት በተለያየ ጊዜ ከሚዲያዎች ጋር በነበራት ቆይታ ገልጻለች። ያኔ እውነትም የአስራ አምስት ዓመት ታዳጊ ናትና ትኩረቷ ሥራዋ ላይ ነበር። እድሜዋ ለሙዚቃ ሥራ የደረሰ ባለመሆኑ እሷን ወክሎ የሚፈርመውም ሆነ ክፍያዎችን የሚቀበሉት አባቷ ነበሩ።

ሙዚቃ ቤቱ አልበሙን ለመሥራት በሦስት ሺ ብር ክፍያ የተስማሙ ቢሆንም ስኬታማ በመሆኑ ተጨማሪ ክፍያ ተሰጥቷታል። ምንም እንኳን ከልጅነቷ የተነሳ በልኳ ባይገኝም ለቪድዮ መቀረጫ የሚሆኑ ልብስና ጌጣጌጦችንም የሙዚቃ ቤቱ ባለቤት ናቸው ያሟሉላት። በዛ ወቅት ‹‹ከእነሱ ጋር መሥራቴ ዕድለኛ ነኝ›› ከምትላቸው ሮሃ ባንድ አባላት ጋር የመሥራት ዕድሉም ገጥሟታል። ከ‹‹በርቺ በሉኝ›› ሙዚቃ በተጨማሪ በየአልበሞቿ የተካተቱትን አምስት የኦሮምኛ ዘፈኖቿን ግጥምና ዜማ ከደረሱት ጋሽ አየለ ማሞ ጋር ሠርታለች።

በመጀመሪያው አልበሟ የተካተቱት እናቴን አደራ፣ ሸጋው ባንተ ላይና ምን ይሻላል የሚሉት የሙዚቃ ሥራዎቿ አሁንም ድረስ ዘመን ተሻግረው ይደመጣሉ። በዚሁ አልበም ሥራ የተካተተውና ‹‹ሸጋው ባንተ ላይ›› የተሰኘው ሥራ ብቸኛው የፍቅር ዘፈን ነበርና እንዴት በዚህ እድሜዋ የፍቅር ዘፈን ትዘፍናለች ተብላ ተቃውሞ ደርሶባታል። “እናቴን አደራ” የተሰኘ ዘፈኗ ደግሞ የእናትን ፍቅር ኃያልነት ያጎላና አሁንም ድረስ በርካቶች ሲሰሙት የሚያነቡለት ተወዳጅ ሥራዋ ነው። ያኔም አሁንም ወደፊትም ዘመኑን የሚመጥን የእናትን ውለታ የልጅን ብድር ለመክፈል ያለ ጉጉት የሚተርክም ነው።

አደራን አደራ

እምዬን አደራ

ጠብቃት አደራ

አምላክ አትግደለኝ

ቁምነገር ሳልሠራ

እምዬን አደራ

ሲታጠፍ አንጀቷ

እምዬን እናቴን

የሰው ቤት ሲደምቅ ዓውዳመቱ

ሲጫወት ሲስቅ ጎረቤቱ

ስታዝን እምዬ እየከፋት

መቆሚያ መሄጃ እየጠፋት

እንደሰው ሳትስቅ አንድ ቀን ሳይደላት

እባክህ ጌታዬ ሳያልፍ አትግደላት

የኅብስት ጥሩነህ አልበም በከተማው በሚገኙ ሙዚቃ ቤቶች ተለጥፎ ዝናዋ ቢናኝም ከሙዚቃ ሥራዋ ጎን ለጎን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷ ቀጥላለች። አልበሟ ሽፋን ላይ ያለው ፎቶ በየሙዚቃ ቤቱ ደጃፍ ከመሰቀሉ በላይ በርካታ ሙዚቃዎቿ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተቀርጸው ይተላለፉ ነበር። በዚህ የተነሳም የምትማርበት ክፍል ስትገባና ስትወጣ እሷን ሊያይ የሚመጣ ተማሪ ቁጥር ቀላል አልነበረም። እሷን የሚፈልግ ተማሪ በመብዛቱ ከተማሪዎች ዘግይታ ለመግባትና መውጣት ተገዳለች። ያኔ የመኖሪያ ጊቢያቸው አጥር የእንጨት ሆኖ በየመሐሉ ክፍተት ነበረው። ከእህቶቿ ጋር ስትጫወት ኅብስት ሲባል ሊያያት የሚፈልገው አልፎ ሂያጅ አጥራቸው ላይ ቢበረክት፤ የሰውን ትኩረት ለመቀነስ ሲባል ወላጆቿ ሐና የሚል ሌላ የቤት ስም እስከማውጣትም ደርሰዋል።

ከታንጎ ሙዚቃ ቤት ጋር ሁለተኛ አልበሟን ብትጀምርም የሙዚቃ ቤቱ ባለቤት ከሀገር ሊወጡ በማሰባቸው ከኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ጋር አገናኟት። የመጀመሪያውን ሁለት አልበሞች በሀገሪቱ ዝናቸው ጣራ ከነካው ሮሃ ባንድ ጋር ሠርታለች። ሦስተኛውን አልበም ከሠርጉዓለም ተገኝና ዳዊት መለሰ ጋር በመጣመር ለአድማጭ አቅርበዋል። ኤክስፕረስ ባንድ የጥምረቱ አካል ነበር። ሦስት አልበሞችን ካወጣች በኋላ ኑሯዋን አሜሪካ አደረገች። ሆኖም በርካታ የጥበብ ሰዎች ይዛ የጠፋችው አሜሪካ እሷን ልታጠፋት አልቻለችም።

ከአሜሪካ ወደ ሀገር ቤት በመመላለስ ግጥምና ዜማ በመውሰድ “ይቅርታ” አልበምን ሠራች። አሜሪካን ሆና የሠራችው “ይቅርታ” አልበምን በወቅቱ እዛው ይኖር የነበረው እውቁ አቀናባሪ አበጋዝ ክብረወርቅ አቀናብሮላታል። የአልበሙ ቅንብር በሦስት ሳምንት መጠናቀቁን ተናገራለች። ለዚህም ግጥምና ዜማውን ለማብላላት ጊዜ መውሰዷና፤ ዝግጁ ስትሆን ስቱዲዮ እንደምትገባ ገልፃለች። አምስተኛ አልበሟን “ተጣልተናል ወይ”፤ የሙዚቃ አቀናባሪው አበጋዝ ክብረወርቅ መኖሪያውን ወደኢትዮጵያ ከቀየረ ወዲህ ወደ እርሷም ኢትዮጵያ መጥታ አቀናብሮላታል።

ከአምስተኛ አልበሟ “ታገሰኝ” ለተሰኘው በሀገረ አሜሪካ ቪድዮ ክሊፕ ተሠርቶለታል። “ሲመሽ መጣ” የተሰኘው ዘፈን ለማስታወቂያ ሥራ ወደ ኢትዮጵያ በመጣችበት ወቅት የቪዲዮ ክሊፑን በቢሾፍቱ ሠርታለታለች። በተለይ በሐይቅ የተሠራው ክፍል ላይ እሷ ያለችበት አነስተኛ ጀልባ ቀዳዳ ያለውና ውሃ የሚያስገባ በመሆኑ ሌሎች ሰዎች በትልቅ ጀልባ ሆነው ውሃ በባልዲ እየተቀዳ ቀረጻው ተካሂዷል። በሰዓቱ ባልፈራም ቀረጻው ከተጠናቀቀ በኋላ እንዲህ ቢሆንስ በማለት ሊደርሱ ይችሉ የነበሩ አደጋዎችን ሳስብ ፈርቻለሁ ትላለች።

መሐሙድ አሕመድ፣ በዛወርቅ አስፋው፣ ትዕግስት አፈወርቅ እና ሌሎችም በርካታ አርቲስቶች በተካተቱበት የትዝታዎች ትዝታ ላይ “ወራሽ ያጣ ፍቅር” የተሰኘ የትዝታ ሥራዋ ተካቷል። ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ “እናምራለን”፣ “እጠብቅሀለሁ”እና “ቀረ እንዴ” የተሰኙ ነጠላ ዘፈኖችን ለአድማጭ ተመልካች ምስልን ከድምፅ አዋሕዳ አቅርባለች።

የመጀመሪያ አልበሟ መውጣትን ተከትሎ ቪድዮ ልትቀረጽበት ከሄደችበት የወቅቱ ዝነኛ የምሽት ክለብ ሁለት ነገር አትርፋለች። በድምጿ የተማረኩት የቤቱ ባለቤት በቤቱ እንድትዘፍን ሥራ ሰጧት። በሂደት የቤቱ ባለቤት ልጅ ከሆነው ባለቤቷ አቶ ግርማ ሞገስ ጋር መገናኘቷ ሌላው ትርፏ ነው። ያኔ የተጀመረው የፍቅር ጥንስስ 20 ዓመታትን ተሻግሮና በአንድ ሴት ልጅና ወንድ ልጅ ተባርኮ አሁንም በፍቅር ይኖራሉ። መኖሪያዋን በአሜሪካ አድርጋ በርካታ ሥራዎችን ለመሥራቷ አንዱ ምስጢር የባለቤቷ ድጋፍ መሆኑን ትናገራለች።

“ዘፈኖቼን ስሰማ ደስ ይለኛል” የምትለው ኅብስት በአንድ ወቅት በመሰንበቻ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ በነበራት ቆይታ “ጎበዝ ኅብስትዬ እያልኩ እሰማለሁ።” ብላለች። የኅብስት ተክለሰውነት ተስተካክሎ ዘመናትን ተሻግሯል። የዚህ ምስጢርም ስፖርትና የምትበላውን የምግብ አይነትና መጠን መቆጣጠር መሆኑን ትናገራለች። እናቴን አደራ፣ ሸጋው ባንተ ላይ፣ ቆይ ብቻ፣ አረ አስጥሉኝ፣ በፈጠረህ፣ ሁሉን ነገር ትቼ፣ ወፍ ሳይንጫጫ እና ተጣልተናል ወይ ከሥራዎቿ መሐል በብዙዎች የሚታወሱ ናቸው። አሁንም ቢሆን ተጨማሪ ተወዳጅና ጥዑም ዜማዎችን ለአድማጭ ጆሮ ጀባ እንደምትል ይጠበቃል!!

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ህዳር 1/ 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You