- ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነት መካተቷ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያና ሩሲያ ኢኮኖሚያዊ አጋርነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሠሩ ተገለጸ፡፡ በተለያዩ የቢዝነስ መስኮች ላይ ትኩረት ያደረገው የኢትዮ-ሩሲያ ቢዝነስ ፎረም ትናንት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በቢዝነስ ፎረሙ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ሁለቱ ሀገራት ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበራቸውን ጥልቅ ታሪካዊ ግንኙነት እያጠናከሩ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት በሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት ላይ ያላቸውን አቅም በማጉላት ኢኮኖሚያዊ አጋርነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሩሲያ ኢንቨስተሮች ማዕድንና ማኑፋክቸሪንግን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት እያደረጉ እንዳለ አምባሳደር ምስጋኑ አመላክተዋል፡፡
በንግዱ ዘርፍ ኢትዮጵያ እንደ ቡና፣ አትክልት፣ ጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ወደ ሩሲያ ስትልክ፤ በአንጻሩ የግብርና ማሽኖች፣ ብረት፣ ስንዴ፣ የምግብ ዘይትንና ሌሎች ምርቶችን ከሩሲያ እንደምትቀበልና ይህን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግም የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና አባልነትን እና የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን አስመልክቶ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረጓን ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ የተከፈቱትን የቴሌኮም እና የፋይናንስ ዘርፍ እድሎችን ጨምሮ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ሳቢ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዳደረጓትም ተናግረዋል፡፡ በዚህም የሩስያ ኩባንያዎች በተለያዩ የጤና አጠባበቅ፣ ፋርማሲዩቲካል፣ አይሲቲ፣ ግብርና፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳ ውጤቶችና ታዳሽ ኢነርጂ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አምባሳደር ምስጋኑ የሩስያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያሉትን በርካታ እድሎች እንዲጠቀሙ በማበረታታት፤ ፎረሙም አዲስ አጋርነት እንደሚፈጥር እና በኢትዮጵያና በሩሲያ ሕዝቦች መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት እንደሚያጠናክር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ሩሲያ እና ኢትዮጵያ እንደ ብሪክስ ቤተሰብ አባልነታቸው፤ ኢትዮጵያ የሩሲያ የኢንቨስትመንት እና የንግድ መዳረሻ በመሆን ረጅም ጊዜ ያስቆጠረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሩሲያ ፌዴሬሽን አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በተለያዩ ዘርፎች የላቀ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸውና በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለረጅም ዓመታት የቆየው የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እያደገ መምጣቱ ጠንካራ የንግድ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር ከፍተኛ ፍላጎት ማሳደሩን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባላት ምቹ የንግድ ሁኔታ ከፍተኛ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መኖሩን ጠቅሰው፤ የሩሲያ ኩባንያዎችም ካፒታላቸውን በማውጣት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሳተፍ ላይ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም የሩሲያ ኩባንያዎች በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሰፊ የለውጥ ሥራዎችን እየሠራ እንዳለና ይህም ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላት ስትራቴጅካዊ አቋም፤ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እና በብሪክስ አባል መካተቷ አሁን ያለውን ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል ነው ያሉት።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም