የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የበለጸጉ ሀገራት በቁርጠኝነት ሊሠሩ ይገባል!

የአየር ንብረት ለውጥ የዓለማችንን ተፈጥሯዊ አካባቢን በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑ ካሉ ችግሮች በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው። የችግሩ ቀዳሚ ባለቤቶች የበለጸጉት/ ያደጉት ሀገራት ቢሆኑም ፤ ጫናው ግን ከፍ ያለ ዋጋ እያስከፈላቸው ያሉት ድሃዎቹን የዓለም ሀገራት እንደሆነ መረጃዎች በስፋት ያትታሉ።

አሁን ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ የበለጸጉት ሀገራት ኃላፊነት በማይሰማው መልኩ ወደ አየር ከሚለቋቸው በካይ ጋዞች ጋር በተያያዘ የዓለማችን የተፈጥሮ አካባቢ በብዙ መልኩ እየጎዳ ነው፤ የከባቢ አየር ሙቀት መጨመርም ሆነ ፤ እሱን ተከትሎ እየተፈጠረ ላለው የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው።

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚስተዋሉት የአየር ንብረት ለውጦች ፤ ጎርፍ ፣ አውሎ ንፋስ ፣ የበረሃማነት መስፋፋት ፣ የውቅያኖስ የውሃ መጠን መጨመር ፣ የመሬት መንሸራተት ..ወዘተ ከዚሁ ችግር ጋር በቀጥታ ተያይዞ ፣ፈጣን ዓለም አቀፍ ምላሽ ካላገኘ ወደ ከፋ ደረጃ ሊሻገር እንደሚችል ይታመናል።

በሽታ አማጭ ቫይረሶች መድሃኒቶችን መልመድ ፣ አዳዲስ የበሽታ ዓይነቶች መከሰት ፤ የሰዎች በሽታን የመቋቋም አቅም እየቀነሰ መምጣት ፤ በመሬት ላይም ሆነ በባህር ውስጥ በሚኖሩ ፍጥረታት ላይ እየደረሰ ያለው ጥፋት ፤ የተፈጥሮ ሚዛንን በማዛባት ሊያስከትል የሚችለው አደጋም አስጊ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው።

አደጋው በተለይም ችግሩን በመፍጠር ሂደት ይህ ነው የሚባል አስተዋጽኦ ለሌላቸው ድሃ እና ኋላቀር ሀገራት “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” በመሆን ፤ የዜጎቻቸውን የለት ተዕለት ሕይወት የበለጠ እያወሳሰበው ፤ ኑሯቸውን እያከበደው፤ ተስፋ የሚያደርጓቸውን ነገዎች እያደበዘዘባቸው ይገኛል።

የችግሩን አሳሳቢነት በተመለከተ አንቱታ ያተረፉ በዘርፉ ምርምር የሚያካሂዱ ተመራማሪዎች ፣ በመስኩ የተሠማሩ ባለሙያዎች እና የችግሩ ሰለባ እየሆኑ ያሉ ሀገራት መንግሥታት መግለጫዎች እና ማሳሰቢያዎች ቢያወጡም ፤ የችግሩ ዋነኛ ባለቤት ከሆኑት የበለጸጉት ሀገራት ተገቢውን ምላሽ ሊያገኙ አልቻሉም።

ሀገራቱ ለችግሩ የሚጠበቅባቸውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ፤ አዘናጊ ምክንያቶችን በመስጠት ችግሩ ከትናንት ዛሬ ለመላው ዓለም የበለጠ ስጋት ወደ ሚሆንበት ደረጃ እንዲሻገር አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠሩ ነው። በዚህም የድሃ እና የኋላቀር ሀገራት ሕዝቦችን ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ እያስገደዷቸው ነው።

ስለፍትሃዊነት ብዙ በሚዜምበት አሁነኛው ዓለም ፤ የበለጸገው ዓለም በብልጽግና ላይ ብልጽግና እየደረበ ፤ እርሱ ለሚፈጥራቸው ችግሮች ዓለም ያልተገባ ዋጋ ሊከፍል አይገባም ፤ ይህ ከራስ ወዳድነት በላይ የሆነ ፤ ከዓለም አቀፍም ሆነ ከሞራል ሕግ አኳያ ፣ አጠቃላይ በሆነው የተፈጥሮ አካባቢና የሰው ልጅ ላይ የሚደረግ ወንጀል ነው።

የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የእያንዳንዱን ቤት እያንኳኳ ላለው ለዚህ ችግር የበለጸጉት ሀገራት “ጆሮ ዳባ ልበስ“ ማለታቸው፤ በየጊዜው ከችግሩ ጋር በተያያዘ የመፍትሄው አካል ለመሆን ለሚገቧቸው ቃላት ተፈጻሚነት ደንታ ቢስ መሆናቸው ፣ ነገ ላይ የታሪክ ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ነው።

ሀገራቱ ዛሬ ለችግሩ የመፍትሄ አካል መሆን እየቻሉ ባልተገባ መንገድ ፈጥኖ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ዓለም ዋጋ እየከፈለች ነው ፣ ችግሩ በተለይም በታዳጊ ሀገራት የሚኖሩ የዓለማችን ሕዝቦች ከድህነት እና ከኋላቀርነት ለመውጣት የሚያደርጉትን ትግል ክፉኛ እየተፈታተነው ነው።

የተፈጥሮ አካባቢን መንከባከብ እና መጠበቅ ከሁሉም በላይ የሰው ልጅ ኃላፊነት ነው ። ይህን ኃላፊነት ለመወጣት በተለይም የችግሩ ዋነኛ ባለቤት የሆኑት የበለጸጉት ሀገራት የማይተገበር ቃል ከመግባት ወጥተው ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት የሚጠበቅባቸውን ፈጥነው መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ነገን መጠበቅ ሳይሆን ዛሬ ላይ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል!

 አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You