ወራትን የተሻገረ ሙሽርነት በጋሞ ዱቡሻ  ሶፌ ባሕላዊ ሥርዓት

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀገራት ለሀገር በቀል እውቀት፣ ባሕል፣ እና ማንነት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ለአንድ ሀገር ዘለቄታዊ እድገት እና የተሻለ ሽግግር አዋጪ ሆኖ የተገኘው ከራስ ማንነት እና ልምምድ ላይ የተነሳ፣ እሱንም ያከበረ እና ያካተተ ዘመናዊነት ነው ሲሉ ምሑራን /ለምሳሌ አኬ (1994)፣ ሀውንቶንዲ (2000)/ ያመለክታሉ። በዚህም አግባብ የራስን ማንነት፣ ባሕል እና ሥርዓት በልኩ የተረዳ ትውልድ ይህ እውነታ ነገን ለመሥራት ስንቅ ይሆንለታል የሚል ድምዳሜን ያክላሉ።

በሀገራችን በርካታ ወጎች፣ የአኗኗር ስልቶች፣ የአመራር እና አስተዳደር ልዩ ጥበቦች በአጠቃላይ በርካታ ባሕሎች ከነአስገራሚ ክንውኖቻቸው በኅብር ይኖራሉ። ከእነዚህ ልዩ ማንነቶች ውስጥ የጋሞ ብሔረሰብ ማንነትን የሚገልጹት ባሕሎች ይጠቀሳሉ። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዚህ ብሔረሰብ ስም እኩል በሚባል ደረጃ የሚነሳበት ትልቅ አሻራ ያስቀመጠ ተግባር አለ። ይህም የጋሞ አባቶች ልዩ ግጭትን የማብረድ እና የመፍታት ችሎታ እና ጥበብ ነው።

በመከባበር እና በእውነተኝነት ላይ ጥብቅ አቋም ያለው የጋሞ ባሕል በማኅበረሰቡ ዘንድ ልዩ ቅቡልነት ስላለው በቃል ብቻ እየተላለፈ ዘመናትን ተሻግሮ እስከ ዛሬ የዘለቀ በፍቅር እና በእኩልነት ማኅበረሰቡን እያስተዳደረ የሚገኝ ባሕላዊ ሥርዓት አለው። እኛም በቦታው ተገኝተን ይሄን እና ሌሎች አስገራሚ ኩነቶችን ታድመን አስፈላጊ መረጃዎችንም ሰብስበን እንደየይዘታቸው ከፋፍለን ለአንባቢያን ማድረሳችንን ቀጥለናል። ለዛሬ ልናካፍላችሁ የወደድነው በብሔሩ የመስቀል በዓልን ተከትለው ከሚከወኑ አስደሳች እና ተናፋቂ ድርጊቶች መካከል አንዱ ስለሆነው የሶፌ ሥርዓት ነው።

በጋሞ ብሔረሰብ መስቀል ከሌሎች ሃይማኖታዊ በዓላት በተለየ በልዩ ክብር እና ዝግጅት ከሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች ጋር በአንድነት እና በጉጉት ተናፍቆ የሚከበር በዓል ነው። አስደማሚ ባሕላዊ ክዋኔዎች ቀኑ ከመድረሱ ቀደም ብለው ሲተገበሩ ይቆዩ እና ዝግጅቶች በዋናነት በዋዜማው ማለትም በመስከረም 16 መከወን ይጀምራሉ። ይሄንኑ ኩነት ለመታደም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን በዞኑ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ እየተመራ ባሕሉን ከምንጩ ለማየት በዶርዜ ቀበሌ ተገኝቷል። በዚህ ቀበሌ የተካሄዱትን ባሕላዊ ድርጊቶች እንዳጠናቀቀም የሶፌ ሥርዓት ወደሚካሔድበት ድቡሻ አቅንቷል።

የጋሞ ብሔረሰብ እርቁን፣ እቅዱን፣ መረጃ ልውውጡን በአጠቃላይ ባሕሉን እና ዋና ዋና የማኅበረሰቡን ጉዳዮች የሚከወንበት ቦታ ድቡሻ ይባላል። በዚህ ድቡሻ ላይ ጥንዶች አምረው ተውበው በባሕላዊ አልባሳት ደምቀው በተጠቀሰው ቀን ይወጣሉ፤ እኛም በስፍራው ጥንዶቹን የመመልከት ዕድሉን አግኝተናል። ጥንዶችን ካየን በኋላ ስለጉዳዩ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የአካባቢውን ሽማግሌዎች፣ ምሑራን እና በባሕሉ ላይ ጥናት እና ምርምር እያከናወኑ ያሉ አካላትን አነጋገርን።

በጋሞ ማኅበረሰብ አንድ ሴት ባፈራት ቤተሰብ፣ በመልኳ፣ በግብሯ እና በቁም ነገሯ ተመርጣ ትታጫለች። የ ስምንት ደሬዎች አስተዳዳሪ የሆኑት ካዎ ታደሰ በተለይ ከ ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፤ ለጋብቻ የተመረጠችው ሴት በባሕሉ መሠረት ሽማግሌ ተልኮ ከብዙ ምልልስ በኋላ ፈቃድ ከተገኘ ጋብቻው ይከናወናል።

ጋብቻ በሌላ መልክም ሊፈፀም ይችላል። ካዎ ታደሰ እንዳብራሩት፤ ጠለፋም አንዱ የጋብቻ አይነት ነው። ወንዱ እና ሴቷ ከተስማሙ ሴቷ በፈቃደኝነት እንዲጠልፋት ሁኔታዎችን ታመቻቻለች። ከዛ እሱም ጓደኞቹን እና የጎሳውን ሰዎች አስተባብሮ ይጠልፋታል። በዚህ ሰዓት ቤተሰቦቿ እና ዘመዶቿ ፈጥነው ሳይወስዷት ቀርተው የልጁ ቤተሰቦች ባዘጋጁላት ጫጉላ ቤት ከገባች ቤተሰቦቿ የግድ ለጋብቻው ይስማማሉ።

ከላይ ከተጠቀሱት የጋብቻ አይነቶች በአንዱ ጋብቻው ከተፈፀመ በኋላ ሙሽሪት የምትሄደው የባሏ አባት በጊቢው ውስጥ ወደ ሠራላቸው መኖሪያ ቤት ነው። በዚህ ቤት ውስጥ ሙሽሪት ምንም አይነት የቤት ሥራ እንድትሠራ አይጠበቅም፤ ከቤት እንድትወጣም አይፈቀድም።

የጋሞ ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አዲሱ አዳሙ (ፒ ኤች ዲ) በጉዳዩ ላይ እንደተናገሩትም፤ መስቀል ከመድረሱ በፊት ዓመቱን በሙሉ የተፈፀሙ ጋብቻዎች የሚመረቁት እና እውቅና ከማኅበረሰቡ የሚያገኙት በዳመራ እለት ስለሆነ ያገቡ ሴቶች ከቤታቸው ሳይወጡ በባላቸው እናት እና እህት በምግብና በመሳሰሉት እንክብካቤ እየተደረገላቸው፣ እየተዋቡ፣ በከፍተኛ እንክብካቤ በቤታቸው ይቆያሉ።

ለምሳሌ ባነሳነው ጉዳይ ላይ ሙሽራዋን በመንከባከብ እና በመመገብ ሂደት ውስጥ የባልዬው እናት ትልቅ ሚና አላት። ምግብ አጣፍጣ በልዩ ሁኔታ ታቀርብላታለች። አቶ አዲሱ እንዳብራሩት፤ ምግቡ ውስጥ የሚጨመረውን ጨው እንኳን መቅመስ አይፈቀድላትም። የዚህ አመክንዮ ምግቡ ጣፍጧት እንዳትጓጓ ታስቦ ስልሆነ መቅመስ ጎሜ ነው ተብሎ ይታሰባል።

አቶ አዲሱ አያይዘው እንደገለጹት፤ በጋሞ ባሕል እንደ ኃጢያት ወይም እንደ እርግማን የሚቆጠሩ ድርጊቶች ጎሜ ይባላሉ። ስለዚህ ባሕሉ የማይፈቅደውን መፈፀም ኃጢያት ስለሚሆን ማኅበረሰቡ እነዚህን ኃጢያት የሚያስብሉ ጉዳዮች ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ሥርዓታቸውን ሳያጓድል ይፈፅማል።

የባልዬው እናት ሙሽራዋን ማየትም አይፈቀድላትም። እሳቤው የመጣው የሙሽራዋን ሰውነት አይታ ትገመግማታለች ፤ በዚህም ሙሽራዋ ልትሳቀቅ ትችላለች ተብሎ መሆኑን አቶ አዲሱ ነግረውናል። አማቷ ካየቻት ግን ጎሜ ወይም ኃጢያት ሠራች ይባላል። ስለዚህ ሰውነቷን ሳታይ ምግቡን ብቻ እያጣፈጠች ታቀርባለች።

በዚህ እንክብካቤ ውስጥ ሙሽሪት ከወራት ያለፉ ምቹ ጊዜያትን ታሳልፋለች። በዚህ መካከል ልጅ የምትወልድ ከሆነ ከጫጉላው ትወጣና እንደማንኛውም ሰው ትዳሯን መምራት ትጀምራለች። ያነጋገርናቸው ሽማግሌዎች እንደገለፁት፤ ልጅ ከተወለደ ጋብቻው በራሱ ጊዜ በማኅበረሰቡ እውቅና ያገኛል። ይህም ማለት ወደ አደባባዩ ወይም ድቡሻው መምጣት አያስፈልግም ማለት ነው።

ሶፌ ማለት በዓመቱ ጋብቻ የፈፀሙ ጥንዶች ለእውቅና ወደ ድቡሻ መምጣት ማለት ነው። ይህን የሶፌ ፕሮግራም ለማካሄድ ሲባል ጋብቻዎች ከሚያዚያ ወር በኋላ እንዲፈፅሙ ይመክራሉ። ያ ማለት በሚያዚያ ከተፈፀመ እስከ ዳመራ በዓል ድረስ የሚኖረው ጊዜ አምስት ወር ብቻ ስለሚሆን መውለድ አይኖርም ማለት ነው። ስለዚህ ጥንዶቹ በአደባባዩ እንዲገኙ የሚጠበቀው ልጅ ሳይወልዱ ነወ።

ስለዚህ አምስት ወይም ከዚያ በላይ ለሆኑ ወራት በእንክብካቤ እና በምቾት የቆየችው ሙሽራ በዳመራ እለት እጅግ ተውባ፣ እንደ የቤተሰቡ አቅም እና ደረጃ በአልባሳት ደምቃ ትወጣለች። እዚህ ላይ ከአልባሳቱ በተጨማሪ የሚፈፀም አስገራሚ ጉዳይ አለ። ወደ ድቡሻው የምትወጣው ሙሽራ መጠኑ ከፍ ያለ ምንአልባትም ከአንድ ኪሎ በላይ የሚሆን የፀጉር ቂቤ ጭንቅላቷ ላይ ታስቀምጣለች። ቂቤው ወደላይ በጥንቃቄ ተደራረቦ ከተቀመጠ በኋላ በቀጭን ጨርቅ ወደ ግምባሯ እንዳይፈስ ይታሰራል። ጉዳዩ በዚህ አያበቃም።

በጭንቅላቷ ዳር ለዳር ዙሪያውን የሰጎን ላባ በምትችለው ልክ እንደ ቤተሰቡ ጉብዝና ትሰካለች። የላቫው ብዛት ለሚሰጣት ክብር እና እውቅና ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፉ ምሑራን ነግረውናል።

ትኩረታችንን የሳበውን የቂቤ ብዛት ትርጓሜ ደግሞ ጠየቅን። አቶ አዲሱ ሲመልሱልን፣ የቂቤው ብዛት የባሏን ቤተሰቦች የሀብት መጠን፣ የልግስና ገደብ፣ ደግነታቸውን እና የጎሣቸውንም ደረጃ እና መልካምነት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። የሰጎን ላቫው ብዛትም የቤተሰበችን ጉብዝና ያሳያል፣ ምክንያቱም ሰጎን በቀላሉ ስለማይገኝ ላባው በበዛ ቁጥር ጉብዝናቸውም ከፍ ያለ እንደሆነ ያሳያል ሲሉ አብራሩልን።

ሙሽሮቹ ከተጠቀሱት ነገሮች በላይ የበዙ ጌጣጌጦች እና አለባበሶችንም በተለያየ መልክ ያደረጉ ሲሆን፣ የተወሰኑት ቡሉኮ ለብሰዋል። ቡሉኮ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ እጅግ የተከበረ እና የተወደደ ፍቅርን እና አክብሮትን ለማሳየት የሚጠቀሙበት በብሔረሰቡ የሚሠራ ባሕላዊ ልብስ ነው።

እነዚህ ጥንዶች በቤተሰቦቻቸው፣ በአካባቢው ሰዎች ዳንኪራ እና በከፍተኛ አጀብ ወደ ድቡሻው ይመጣሉ። በዚህ ሰዓት የአካባቢው ሰዎች በተለይ ሙሽራዋን ለማየት የሰውነቷን መመቸት እና መጎሳቆል ለማጣራት እና ለመፍረድ ይሰበሰባሉ። ጥንዶቹ በድቡሻው ውስጥ ከገቡ በኋላ ከፍ ወዳለ ቦታ ይወጣሉ። ይህም እንደ መድረክ ስለሚያገለግል የተሰበሰበው ሕዝብ ጥንዶቹን ለማየት እንደመቸው ታስቦ የሚከወን ባሕል ነው።

ጥንዶቹ በምስሉ ላይ በሚታየው መልክ ይደረደራሉ። እንደ ቁንጅና ውድድርም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ሶፌን ግን ለየት የሚያደርገው ሙሽራዋ በሰውነቷ ምቾት፣ ማማር እና ውፍረትም እንድትመዘን ያዛል። ይሄን ውድድር የሚዳኙ ሽማግሌዎች ተመርጠው ቦታቸውን በመያዝ ዳኝነቱን ይፈፅማሉ። ውጤቱም በሕዝብ ፊት ተገልፆ ውሳኔው ይፀድቃል።

በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ውድድሩን ያሸነፉ ጥንዶች ምርቃት እና እውቅና ይሰጣቸዋል። ከምንም በላይ የአሸናፊ ቤተሰቦች በማኅበረሰቡ ውስጥ ትልቅ አድናቆት፣ ክብር፣ ፍቅር ያላቸው እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ተደርገው ይወሰዳሉ። በውድድሩ ተጎሳቁላ እና ተጎድታ የታየችን ሴት ቤተሰቦች ሕዝቡ አይቶ አዝኖ ይገስፃል። በአጠቃላይ ግን በእለቱ ለሶፌ ፕሮግራም የወጡ ጥንዶች በሕዝቡ ዘንድ እውቅና እና ክብር አግኝተው ተመርቀው ከዚያች ቀን በኋላ በይፋ በነፃነት ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅለው መኖር ይጀምራሉ። እስከዚች ቀን ግን በፍፁም በተለይ ሴቷን ሰው እንዲያያት አይፈቀድም።

ይህን ሥርዓት ካዎ ታደሰ እንደገለፁት፤ እጅግ በጣም አስፈላጊ እና መበረታታት ያለበት ነው። ለባሕሉ ሲባል ሙሽሪቷ በዚያ ልክ የባሏ ቤተሰቦች እንዲንከባከቧት መደረጉ በዋናነት ልጅቷ ከቤተሰቦቿ እንደመምጣቷ ቤቱን እና ኑሮውን እስክትጀምር ጥሩ መለማመጃ ጊዜ ይፈጥርላታል። ከዚህ በተጨማሪ ከባለቤቷ ቤተሰቦች ጋር ለሚኖራት ረጅም ቆይታ ሶፌ ጥሩ መግባቢያ መንገድ ይሆንላታል። የባሏ ቤተሰቦች ሲንከባከቧት ደግነታቸውን፣ ሙያቸውን፣ ሥነሥርዓታቸውን አጠቃላይ ባሕሪያቸውን ትረዳለች። ይህም በቀጣይ ለሚኖራት መልካም ግንኙነት ትልቅ ዐሻራ ያስቀምጣል። የቤተሰብ ሠላም እና መረጋጋት የማኅበረሰብ ግምባታ መሠረት ስለሆነ። ይሄን ቀናነት እና ፍቅር ያገኘች በተግባር የተለማመደች ሴት ነገ የምትፈጥረው ቤተሰብ በዚህ የተገራ ነው ብንል ምክንያታዊ ነው።

በጋሞ ብሔረሰብ ሴት ልጅ ከሙሽርነቷ ጊዜም ባሻገር ግጭትን በመፍታት ሂደት ውስጥም ትልቅ ድርሻ አላት። በእዚህ አካባቢ ያገኘናቸው ሀለቃ እንደተናገሩት፤ ግጭት ሲፈጠር፣ ወጣቶች ወደ አላስፈላጊ መስመር ሲገቡ እንድ እናት ተንበርክካ ከለመነች ግጭቱ ወዲያው ይቆማል። እናት ክብር እናት አዛኝ እናት፤ ልጆቿን አጥብታ የምታሳድግ ስለሆነች በማኅበረሰቡ ዘንድ ትከበራለች። ወጣቶች የእሷን ልመና ትተው ከሄዱ በማኅበረሰቡ ዘንድ ኃጠያት ወይም ጎሜ ይሆናል።

የጋሞ ድቡሻ ሶፌ ሥነ-ሥርዓት በዚህ ጽሑፍ ከተገለፀው በላይ ጥልቅ ትርጓሜ እና ድንቅ ሀገር በቀል እውቀት የታጨቀበት፣ የማኅበረሰቡን አርቆ አሳቢነት፣ ትንበያ፣ ለአብሮነት የሚከፈልን ቀላል የሚመስል ነገር ግን ትልቅ መሠረት የሚጥልን ልምድ እያሳየ ያለ ባሕል ነው ብንል መነሻችን አባባላችንን ይደግፈዋል።

ምንም እንኳን ዞኑ ባሕሉን ለማስተዋወቅ እና ለመጠበቅ እየሠራ መሆኑን ቢጠቅስልንም፣ ባሕሉ ሊሰጥ ከሚችለው ጥቅም እና ፋይዳ አንፃር ይህ ሥራ በተወሰነ ባለድርሻ አካል ብቻ መወሰን አለበት ብለን አናምንም። እንደዚህ ያሉ ሀገር በቀል እውቀቶች እና ልምምዶች እያሉ፣ የተሻለ ነገር የሌላቸው የሌሎች ሀገሮችን ፍልስፍና መከተል አይገባም፤ ይህን በሚገባ በመገንዘብ ወደ ራስ ማንነት መመለስ ለውጤታማነት ያስፈልጋል።

ስለዚህ ሁሉም ዜጋ በኃላፊነት ራሱን ማወቅ እና በማንነቱ መኩራት እንዲሁም መጠበቅ አለበት። ይህን ማንነት ማሻሻል አያስፈልግም፤ በእውቀት ላይ ተመሥርቶ ማድረግ ከቻለ ሀገራችን ያሏት ባሕሎች በቂ የመፍትሔ ቋቶች ናቸው ብለን እናምናለን። እኛም እንደሚዲያ የሚጠበቅብንን የማስተዋወቅ ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን።

በመቅደስ ታዬ (ፒ ኤች ዲ)

አዲስ ዘመን ህዳር 1/ 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You