ታምራት ተስፋዬ
በደብረ ብርሃን ከተማ በኤሌክትሪክ የምትሰራ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ በግል ኢንተርፕራይዝ ተሰርታለች። የተሸከርካሪዋ አምራች መቅድም ለሁለገብ አገልግሎት የሚውሉ ማሽነሪዎች መፈብረኪያ ድርጅት ባለቤት አቶ መቅድም ኃይሉ መሆናቸው ታውቋል።
ግለሰቡ ቀደም ሲል በደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኝ መምህር የነበሩ ሲሆን በኮሌጁ በማስተማር ላይ እያሉ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ሰርተዋል። በአሁን ወቅትም በግላቸው የብረታ ብረት ወርክሾፕ ከፍተው እየሰሩ ናቸው።
የፈጠራ ስራዎቻቸውን በሚመለከት አቶ መቅድም እንደገለፁት፣ ቀደም ሲል የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽን፣ የብሎኬት ማምረቻ ማሽን፣ የወተት ስትራላይዜሽን ማሽንና ሞተር ሳይክልን ወደ ባጃጅ የመቀየር ስራን ሰርተዋል።
‹‹ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ስራዎችን ስሰራ ነው የቆየሁት›› የሚሉት አቶ መቅድም፣ በተለይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ለመስራት አቅደው ወደስራ በመግባት በአሁን ወቅት ላይ ባለሦስት እግር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መስራታቸውን ተናግረዋል።
በአብዛኛውን ቴክኖሎጂዎች በአገር ውስጥ ምርት ለመስራት ጥረት እንደሚያደርጉ የሚያስረዱት አቶ መቅድም ‹‹ባለሶስት እግር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዋንም ስሰራ በአብዛኛው የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም ነው›› ሲሉ ተናግረዋል።
‹‹ባለሶስት እግር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በማንኛውም የኤሌክትሪክ ቻርጀር ለ3 ሰዕታት ቻርጅ ተደርጋ በሰዓት እስከ 40 ኪሎ ሜትር መብረር ትችላለች›› ያሉት አቶ መቅድም፣ ተሽከርካሪዋ ከሾፌሩ ጋር 4 ሰዎችን የመጫን አቅም እንዳላትም አስረድተዋል።
ተሽከርካሪዋን መጠቀም የሚቻለው ለከተማ ውስጥ የታክሲ አገልግሎት ሲሆን ይሑንና ጠጠር መንገድ ውስጥም ገብታ ያለምንም ችግር መስራት እንደምትችል የጠቆሙት የፈጠራ ባለሙያው፣ ከነባሮቹ ባጃጆች በተለየ መልኩ ጎማዋን ከፍ አድርገው መስራታቸውን ገልፀዋል። ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዋ በአሁኑ ሰዓት ለገበያ ብትቀርብ 160 ሺህ ብር ልትሸጥ እንደምትችል ነው ያስታወቁት።
በአሁን ወቅት በስራ ላይ የሚገኙ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በአገልግሎት ዘመናቸው ወጪያቸው ከፍተኛ መሆኑን ያስረዱት አቶ መቅድም፣ እሳቸው ያመረቷት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በአንፃሩ በማንኛውም የኤሌክትሪክ ቻርጀር ሶስት ሰዓት ቻርጅ ተደርጋ በስራ ሂደት ውስጥ ያለን ከፍተኛ ወጭ በእጅጉ እንደምትቀንስ አብራርተዋል። ይሕም የተሽከርካሪዎን ትልቅ ጥቅም የሚያሳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ከዚህ በፊት የሰራቸው ብዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ድጋፍ አግኝተው ለሀገር በሚጠቅም መልኩ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ አለመደረጋቸውን ያስታወሱት የፈጠራ ባለሙያው፣ በቀጣይ ግን የሰሯቸውን ስራዎች በማስፋት ለማህበረሳቡ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ለማድረግ እንደሚተጉ እና ለዚህም ወርክሾፓቸውን አስፍተው ከመንግስት ጋርም ሆነ ከሌሎች ደጋፊ አካላት ጋር በመተባበር እና ምሩቃንን በማሳተፍ ውጤታማ ስራን ለመስራት ራዕይ እንዳላቸው ተናግረዋል። መረጃውን ያገኘነው ከደብረ ብርሃን ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2013