ካሳማ ከተማ ለአዲስ አበባ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ድጋፍ አበረከተ

የጃፓኗ ከተማ ካሳማ ለአዲስ አበባ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ የቅርጫት ኳሶች ድጋፍ አበረከተች። የጃፓን ኤምባሲ በኢትዮጵያ ከትናንት በስቲያ ከካሳማ ከተማ የተበረከቱትን የዊልቼር ቅርጫት ኳሶች ተረክቦ ለአዲስ አበባ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ማስረከቡን ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ አሳውቋል።

የካሳማ ከተማ ከንቲባ ሚስተር ያማጉቺ ሺንጁ ባለፈው የካቲት ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስቴድየም የተለያዩ የፓራሊምፒክ ስፖርተኞችን አግኝተው ነበር። በዚህም ከንቲባው ስፖርተኞቹን በማበረታታት ከአካል ጉዳተኝነት ጋር ያሉትን ፈተናዎች ተጋፍጠው ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉና ለሌሎችም አርአያ እንዲሆኑ መክረው ነበር። በዚያው አጋጣሚ ከንቲባው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ለፓራሊምፒክ ስፖርተኞቹ ስፖርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር። በዚህም መሠረት በካሳማ ከተማ ስም የዊልቼር ቅርጫት ኳሶችን ለአዲስ አበባ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ መላካቸው ታውቋል።

ከከተማዋ የተበረከተውን የቅርጫት ኳሶች ድጋፍ የጃፓን ኤምባሲ በኢትዮጵያ ተወካይ ሚስተር ኔትሱ ሹንታሮ ለአዲስ አበባ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ በቀለ ጎንፋ ያስረከቡ ሲሆን፣ በሥነሥርዓቱም ላይ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ መኪዩ መሐመድ መገኘታቸው ተጠቁሟል።

ሚስተር ኔትሱ ሹንታሮ በሥነሥርዓቱ ላይ እንደገለፁት፣ ከካሳማ ከተማ የተበረከቱት የቅርጫት ኳስ ድጋፎች በኢትዮጵያ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ቡድኖች የተሻለ የልምምድ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው እገዛ ያደርጋሉ ብለዋል። አክለውም ኢትዮጵያና ጃፓን የስፖርት ዘርፋቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በበርካታ ጉዳዮች በትብብር እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የካሳማ ከንቲባው ሚስተር ያማጉቺ ቀደም ብሎ በተቀረፀ ተንቀሳቃሽ ምስል ባስተላለፉት መልዕክት፣ “ኢትዮጵያን በጎበኘሁበት ወቅት በፓራሊምፒክ ስፖርቶች እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሰዎችን የማግኘት እድል ነበረኝ፣ በጉብኝቴ ወቅት የዊልቼር ቅርጫት ኳስ በኢትዮጵያ በስፋት እንደሚዘወተር ሰምቻለሁ፣ ስለዚህ ከእኛ የካሳማ ከተማ የ3በ3 ፕሮፌሽናል የቅርጫት ኳስ ቡድኖችና ሌሎች በቅርጫት ኳስ ዙሪያ ካሉ ሰዎች ጋር በመተባበር በጃፓን ኤምባሲ በኩል የቅርጫት ኳሶችን ድጋፍ ለማድረግ ወስነናል፣ እነኚህ የቅርጫት ኳስ ድጋፎች በኢትዮጵያ የዊልቼር ቅርጫት ኳስን ለማስፋፋት አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

በተመሳሳይ ሚስተር ያማጉቺ ባለፈው ዓመት ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተለያዩ የስፖርት ቁሳቁሶች ድጋፍ በካሳማ ከተማ ስም ያበረከቱ ሲሆን፣ ካሳማ ከተማ ባለፉት ስድስት ዓመታት የጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰቢያ የሆነ የግማሽ ማራቶን ዓለም አቀፍ ውድድር በማዘጋጀት እንደምትታወቅ ኤምባሲው በላከው መግለጫ አስታውሷል።

በጃፓን ኢባራኪ ግዛት ካሳማ ከተማ በየዓመቱ የሚካሄደው የጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ መታሰቢያ ግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የዓለማችን አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን፣ መሰል ወድድሮች ረጅም ዘመናት ያስቆጠረውን የሁለቱን ሀገራት ዘርፈ ብዙ ግንኙነቱ ይበልጥ አጠናክሮና አስተሳስሮ ለማስቀጠል ትልቅ ሚና እንዳለው በቅርቡ በተካሄደው ውድድር ወቅት የከተማው ከንቲባ መግለፃቸው ይታወሳል። ከተማው ከበጃፓን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር እየሠራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባው መናገራቸውንም በጃፓን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You