ለአማራጭ ወደብ አማራጭ

የባሕር በር አልባ ሀገራት የሚባሉት በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከባሕር የራቁ ፤የባሕር ጠረፍ የሌላቸው ሀገሮች ናቸው። የገቢ ንግድ እንቅስቃሴዎቻቸውን የሚያሳልጡት ወደብ ባላቸው ጎረቤት ሀገራት ነው። ሀገራቱ ቀጥታ የባሕር ጠረፍ (ውቅያኖስ ወይም ባሕር) ትስስር የሌላቸው ቢሆኑም ነፃና ሉዓላዊ ግዛት ያላቸው ናቸው።

ሀገራችን ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ወደቦቿን በግፍ ካጣች ጀምሮ የጅቡቲን ወደብ ስትጠቀም ኖራለች። ይህም ሆኖ ሀገሪቱ እያስመዘገበች ካለው የኢኮኖሚ እድገት አኳያ ከጅቡቲ ውጪ ሌላ አማራጭ ወደብ እንደሚያስፈልጋት ይታመናል።

ቀጥታ የባሕር በር ያላቸው ሀገሮች ፤ የባሕር በር ከሌላቸው ሀገሮች የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርታቸው በሦስት እጥፍ ይልቃል። በዘመናችን ዋነኛ የኢኮኖሚ ኃያላን የሚባሉት እንደ ቻይና፣ ጀርመን፣ አሜሪካና ሩስያ ሁሉም ቀጥታ የባሕር መዳረሻ ያላቸው ናቸው። ይህም ወደ 90 በመቶው የሚሆነውን ዓለም አቀፍ ንግድ የሚከወነውን በባሕር መንገዶች (maritime routes) በኩል ነው። የባሕር በር የሌላቸው ሀገሮች የወጪ እና ገቢ ንግድ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የግድ ከ20-30 በመቶ ተጨማሪ ሀብት ያወጣሉ።

ከባሕር በር አልባ ሀገሮች መካከል ኪርግዝስታን ከውቅያኖስ በጣም የራቀች በመሆን ቀዳሚ ነች። ከባሕር በር አልባ ሀገራት በዓለም ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላትም ናት። ከአፍሪካ ወደብ አልባ ሀገራት መካከል ከዋና ከተማዎቻቸው እስከ ባሕር በር ድረስ ባላቸው ርቀት በቅደም ተከተል ሲቀመጡ ቻድ በአንድ ሺህ 880 ኪ.ሜ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በአንድ ሺህ 680 ኪ.ሜ እና ዛምቢያ በአንድ ሺህ 600 ኪ.ሜ ርቀት ቀዳሚዎች ናቸው።

የሩሲያና ቻይና ወደቦችን የምትጠቀመው ካዛኪስታን በዓለም ብዙ ወደቦችን በመገልገል ረገድ ቀዳሚ ነች። ከአፍሪካ እንደ ዑጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ዛምቢያ ያሉ ሀገራት፤ የኬንያ፣ ታንዛኒያንና የደቡብ አፍሪካ ሀገራትን ወደቦች በመጠቀም ፊታውራሪዎች ናቸው። በተቃራኒው ኢትዮጵያ ከብዙ ዋና ዋና ወደቦች አቅራቢያ የምትገኝ ሆና በአንድ ወደብ የተገደበች ነች። የጅቡቲ ፣ የኬንያ ላሙ እና የሱዳን ወደብ ለኢትዮጵያ ቅርብ ናቸው። በኢትዮጵያ መንግሥት የወደብ አማራጮችን ለማመቻቸት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

በዘመናችን የባሕር በር ከሌላቸው ሀገሮች መካከል የተወሰኑ ሀገሮች የባሕር መዳረሻ በድጋሚ ለማግኘት ጥረዋል። ቦሊቪያ ከቺሊ ጋር ባካሄደችው የፓሲፊክ ጦርነት (እ.ኤ.አ. 1879-83) ያጣችውን የባሕር ጠረፍ ባደረገችው ዲፕሎማሲዊ ትግል በድጋሚ አግኝታለች። ቺሊ አንቶፋጋስታ እና አሪካ የተባሉ ወደቦችዋን ለቦሊቪያ ለንግድ እንድተጠቀምበት፣ ጥሬ ዕቃዎቿን እና ሸቀጦቿን እንድታስገባና እንድታስወጣ ፈቅዳለች።

ሌሎች ሀገሮች በጋራ በባሕር ጠረፍ የባቡር መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በመዘርጋት የወደብ ፍላጎታቸውን አሳክተዋል። ኡዝቤኪስታን እና አፍጋኒስታን በጋራ የዘረጉትን የባቡር ሐዲድ ከፓኪስታን የውስጥ የባቡር መስመር በማገናኘት በካራቺና እና በግዋዳር ወደቦች መገልገል መቻላቸውን ብሪታኒካ ድረገጽ ያሳያል።

ወደብ አልባ ከሆኑ ሀገሮችም፤ ካናል/ቦይ በመክፈት ከባሕር ጠረፍ ተገናኝተው ወደብ የመሠረቱ ሀገሮችም አሉ። በዚህም ኦስትሪያ ተጠቃሽ ናት። ሀገሪቱ ወደ ባሕር ለመድረስ ቦዮችንና ወንዞችን በመጠቀም ለውሃ ጎዳና በመክፈት ከዓለም አቀፍ ንግድ ለመገናኘት ችላለች። በዚህም ወንዞችዋን ማለትም የርሂብ- ዳኑብ ካናል (ቦይ) በመክፈት ከሰሜን ባሕርና ከጥቁር ባሕር ጠረፍ ተጎራብታ ወደቦች መሥርታለች። በተመሳሳይ ሞልዶቫ የድንበር መስተጋብር በመፍጠር በሰጥቶ መቀበል መርህ በዳኑብ ወንዝ ዋነኛ የዓለም አቀፍ የውሃ መንገድ ለመክፈትና ቀስ በቀስ የጊኡርጊለስቲ ወደብን ማልማት ችላለች።

በተመሳሳይ ሰሞኑን ዘ ሪፖርተር ጋዜጣ ያወጣው መረጃ ይህንኑ የሚያጠናክር ነው። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት ኦስትሪያ፣ ሀንጋሪ፣ ሩሲያ እና ፖላንድ ድንበር በመጋራት በመግባባት ለክፍለ ዘመናት በወደብ ተጠቃሚነት ዘልቀዋል። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በተከሰቱ የግዛት ለውጦች አንዳንድ ሀገሮች የባሕር በር አጥተዋል። ሌሎች ደግሞ ወደቦች አግኝተዋል። ለምሳሌ ኦስትሪያ በጣሊያን በኩል የወደብ መዳረሻ አግኝታ ከጣሊያናውያን ተገልጋዮች እኩል የክፍያ ውሎች ትጠቀማለች ።

ከአፍሪካ ካናል በመክፈት ከባሕር በቀጥታ ለመገናኘት የቻለ ሀገር ባይኖርም ኢትዮጵያ ለወደቦች ቅርብ ስለሆነች ከባሕር ጠረፍ እስከ ድንበሯ ጫፍ ቦይ በመቅደድ እና በመገንባት ወይም ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም የባሕር ጠረፍ የማግኘት እድል እንዳላት አንዳንድ ሰነዶች ያስረዳሉ። ወደብ አልባ ከሆኑት ሀገሮች በሕዝብ ብዛት ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር የለም።

ሀገሪቱ ከቀይ ባሕር በ50 ኪሜ ርቀት ላይ ትገኛለች። ለኢትዮጵያ ቅርብ የሆነው የቀይ ባሕር ክልል በይሉል ይባላል። ቦታው ከአሰብ ወደብ ወደ ሰሜን በኩል ለቀይ ባሕር ዳርቻ ቅርብ የሆነ ሲሆን በአፋር የቡሬ መንደር የሚገኝ ነው። የተጠቀሰውን የ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለውን ቦታ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመስማማት እስከ ቡሬ ኢትዮጵያ የሚደርስ ቦይ መቆፈር መደራደርና በሰጥቶ መቀበል መልክ ሁለቱም ሀገሮች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ወደፊት መስማማት ይጠበቃል።

በቅርቡ ኢትዮጵያ ቀጥታ ከባሕር የመገናኘትና ወደብ የማግኘት ፍላጎት እንዳላት የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም (ዶ/ር) ይህን የምናሳካው በሰላማዊ መንገድ ነው ማለታቸው ይታወሳል። ይህም ከሌሎች ሀገሮች ጋር በሚደረግ ውይይትና ስምምነት በሰጥቶ መቀበል እንደሆነም አመላክተዋል።

የሚያስደንቀው ደግሞ አንዳንድ የባሕር በር የሌላቸው ሀገሮች ለብሔራዊ ኩራትና ለፀጥታ ስጋት መፍትሄ የባሕር ኃይል መሥርተዋል። ፓራጉዋይ በፓራጉዋይ እና በፓራና ወንዞች፣ ሰርቢያ በዳኑብ እና ሩዋንዳ በኪቩ ሐይቅ የባሕር ኃያል አሰልጥነዋል። ቦሊቪያ አምስት ሺህ የባሕር ኃይል ሰርጓጆች በቲቲካካ ሐይቅ የባሕር ንግድ ለሚፈጠር ተግዳሮት አሰልጥናለች። በኢትዮጵያም የባሕር ኃይል ምሥረታና የስልጠና እንቅስቃሴዎች እየታዩ እንደሆነ ይታወቃል።

ኃያላን ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ወታደራዊ ጣቢያዎች አሏቸው። ይህም ወሳኙን የንግድና የኢነርጂ መተላለፊያ (ኮሪዶር) ማለትም የቀይ ባሕር እና የባቢኤል መንደብ ሰርጥን የመቆጣጠር ፍላጎት ነው። ግብጽ ደግሞ ከቀይ ባሕር ተጎራባች ሀገራት ውጭ ማንም በቀይ ባሕር አይገለገልም በሚል ከቀይ ባሕር ተዋሳኞች ጋር እየተገናኘች ግርግር ለመፍጠር እየጣረች ነው።

ግብፅ ከቀይ ባሕር አዋሳኝ ሀገሮች ጋር እየተገናኘች የቀይ ባሕር ወሰን የሌላቸው ሀገራትን ተሳትፎ ‹እንደማትቀበል› ስትገልጽ ነበር። በተጨማሪም ቀይ ባሕርን መጠበቅና ማስተዳደር በዋናነት የባሕሩ ድንበር ተጋሪ ሀገራት ተግባር እንዲሆን ለማሳሰብ የሞከረችው፤ ኢትዮጵያ የዓባይን ጉዳይ ስለጨረሰች ወደ ቀይ ባሕር ትመጣና ትቀናቀነኛለች በሚል ስጋት ነው። ግን ብዙ ሀገራት በኢትዮጵያ አፍንጫ ሥር በሚገኙ ወደቦች የባሕር ኃይል መሥርተው ሲገለገሉ ምነው ዝም አለች?

ቀይ ባሕር ከዓለም እጅግ በጣም ወሳኝ የንግድ መስመር አንዱ ነው። ወደ 15 በመቶ ገደማ የሚሆነው የዓለም ንግድ የሚስተናገድበት ቦታ ነው። ኢትዮጵያ በቀጣናው ከሚገኙ የባሕር ዳርቻ ካሉ ሀገሮች ይበልጥ ብዙ የሰው ኃይል አላት። ያላትን የሰው ካፒታል ወደ ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ላይ ማዋል ይቻል ነበር። በተጨማሪም የባቢኤል መንደብ ሰርጥ ስትራቴጂያዊ ወሳኝ ቦታ እየሆነ ነው። ግን ብዙ ሀገራት በኢትዮጵያ አፍንጫ ሥር በሚገኙ ወደቦች የባሕር ኃይል መሥርተው ሲገለገሉ ምነው ግብጽ ዝምታን መረጠች?

ቀጣናው ከፍተኛ አለመረጋጋት ያለበት፣ እንደ ሶማሊያ እና ሱዳን ያሉ በግጭት የተዘፈቁ ሀገራት የሚያካትት እንዲሁም አብዛኞቹ ነዋሪዎች በከፍተኛ ድህነት ያሉበት ነው። አካባቢው በተናጠል ባላንጣ የሆኑ ሀገሮች ያለማቋረጥ የሚፈራረቁበትም ነው። የኅብረት አጋሮች በቅጽበት ባላንጣዎች የሚሆኑበት በመሆኑ፤ ይህ ተለዋዋጭ አካባቢ፤ በሁሉም ጎረቤት ሀገሮች መካከል፤ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ተሳትፎ፣ ቀጣናዊ ትስስር እና ሁለንተናዊ ትብብር የሚፈልግ ነው።

የዓለም ባንክ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በዓለም ካሉ 12 እጅግ ድሃ ሀገሮች መካከል ዘጠኙ በአፍሪካ ያሉ የባሕር በር የሌላቸው ሀገሮች ናቸው። እነዚህ ሀገሮች በአጠቃላይ፤ የባሕር በር ካላቸው ሀገሮች ጋር ሲነፃፀሩ በከፍተኛ ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ ናቸው። ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዳይኖራቸው፣ ከፍተኛ የፖለቲካ ተጽዕኖ እንዳይፈጥሩ የተረጋጋ ማኅበራዊ መዋቅር እንዳይፈጥሩ ያደርጋቸዋል።

ይህም የባሕር በር የሌላቸው ሀገሮች የንግድ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የባሕር ዳርቻ ካላቸው ጎረቤት ሀገሮቻቸው የኢኮኖሚ ጥገኞች ሆነው ይቀራሉ። ከ90 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ መተላለፊያ ጅቡቲ ነው። ለዚህም በዓመት ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ታወጣለች።

ኢትዮጵያ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄደውን የሕዝብ ቁጥሯ እና የኤክስፖርት ንግድ ለማሳካት የባሕር መዳረሻ መሻቷ ግድ ነው። ከላይ እንደገለጽነው ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦችን ለመጠቀም አማራጭ እየፈለገች ነው። ለዚህም ተስፋ አመንጪና ፋና ፈንጣቂ ጅምሮች እየታዩ ነው። እነዚህ ቢተገበሩ አማራጭ ወደቦች እንዲኖረን ሁነኛ ሚና ይጫወታሉ። ለኬንያ፣ ለሶማሊያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ወደቦች ቅርብ የሆኑ የኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ ከተሞች ያድጋሉ፣ ነዋሪዎችም ጭምር ይጠቀማሉ።

ኬንያ የላሙ ወደብን በኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ሱዳን ለማገናኘት መንገድ ሠርታ ጨርሳለች። መንገዱ ከኢትዮጵያ ሲገናኝ፤ ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ በኩል ተሽከርካሪዎችዋ ወደ ኬንያ ላሙ ወደብ ስለሚመላለሱ ኢትዮጵያ ‹‹በአንድ ወንጭፍ ሁለት ወፍ›› እንደሚባለው አትራፊ ትሆናለች። ለደቡብ ሱዳን ታስቦ በተዘረጋው መንገድ የኢትዮጵያ የደቡብ ከተሞች ለላሙ ወደብ አቅራቢያ ስለሆኑ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

ከኬንያው ላሙ ወደብም በኢትዮጵያ በኩል ደቡብ ሱዳን ለማድረስ የሚደረገው እንቅስቃሴ ለከተሞች ዕድገትና ለንግድ እንቅስቃሴ መስፋፋት አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ኢትዮጵያም በወደቡ ለመገልገል ምቹ ይሆንላታል። ኢትዮጵያን ከጐረቤት ሀገሮች ጋር የሚያስተሳስሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችም አሉ።

ኢትዮጵያ ምርቃት ብቻ የሚቀረውን የዓባይ ግድብ አጀንዳን ጨርሳለች። በቀጣይ አማራጭ ወደቦች ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት መጠናከር አለበት። የአክራሪዎችና ዘራፊዎች እንቅስቃሴ በሚታይበት ቀይ ባሕር ላይ የኢትዮጵያ ወደብ እና ባሕር ኃይል ቢኖር ለባሕሩ ተዋሳኝ ሀገሮች የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ረገድ ሚና እንደሚኖራት እሙን ነው። ወደፊት አቅማችንን አጠናክረን ቦይ ቀደን ቀይ ባሕርን አዋሳኝ አድርገን ወደብ ከፍተን ብንገለገል፤ ሌሎች አማራጮችንም ብንጠቀም ወጪው ‹‹ጥጃ ጠባ ሆድ ገባ›› ዓይነት ይሆንልናል።

በኃይለማርያም ወንድሙ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You