ንግድ ዓይነተ ብዙ ነው። በችርቻሮ አነስተኛ ሸቀጦችን በመሸት የተጀመረ ንግድ ዳብሮ ወደ ጅምላ ከፍ ይላል። በሂደት ወደ አስመጪና ላኪነት ይሻገራል። ከዚህ በላይ ከጎመራ ሌላ አምራች ያመረተውን ከማከፋፈል ወደማምረት ያድጋል። የቧንቧ እቃዎችን በማምረት የሚታወቀው ሞሪንጋ ፋርምስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅትም ዕድገቱ እንደዚያው ነው። ከድርጅቱ ሥያሜ በላይ የንግድ ሥያሜያቸው የሆነው በአማን ጎልቶ ይታወቃል። ድርጅቱ የተመሠረተው የቧንቧ እቃዎችን ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ነበር።
ድርጅቱ ከ13 ዓመታት በላይ በንግዱ ዓለም ቆይቷል። ዋነኛ መታወቂያው ወደ ሀገር ማስገባት ነበር። ደብረብረሃን በሚገኘው ፋብሪካቸው እያመረቱ ወደ አምራቾች ጎራ ከተቀላቀሉ አንድ ዓመት ተቆጠረ። አሁን የተለያየ ዓይነት ቧንቧዎችንና ፊቲንጎችን ያመርታሉ። በዘርፉ የማማከርና የባለሙያ ሥልጠና፣ የተዘጋ መስመር መክፈትና መሰል አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰይፉ ታደሰ፤ ከዚህ ቀደም ብዙ የውጭ ምንዛሬ አውጥተው ከውጭ ያስገቡ እንደነበር በማንሳት፤ በሀገር ውስጥ ማምረት በመጀመራቸው ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ይገልጻሉ።
ቴክኖሎጂውን ከውጭ በማምጣት በሀገር ልጆች በአነሰ ወጪ ማምረት በመቻላቸው የምርቱ ተጠቃሚዎችም በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶቹን ማግኘት ችለዋል ይላሉ። ምርቶቹ ወደ ሀገር በሚገቡበት ጊዜ ከነበራቸው ዋጋ እስከ 50 በመቶ በሚደርስ ቅናሽ ለሸማቾች ማቅረብ መቻላቸውን የሚገልፁት ሥራ አስኪያጁ፤ አስቀድመው በሸማቾች ዘንድ ድርጅታቸው ጥራት ያላቸውን እቃዎች ወደ ሀገር በማስገባት ጥሩ ሥም በመያዙ የራሳቸውን ምርት ሲያመርቱ የገበያ ችግር እንዳላጋጠማቸው ይገልፃሉ።
ሥራ አስኪያጁ እንደሚናገሩት፤ ማምረት ሲጀምሩ በሂደት ወደ ሀገር የሚያስገቧቸው እቃዎች መጠንና ዓይነት ቀንሰዋል። አሁን እጃቸው ላይ የቀሩ የተወሰኑ ምርቶችን ሸጠው ማጠናቀቅ እንጂ ድርጅቱ ከውጭ ያስገባቸው የነበሩ ምርቶች በሙሉ በሀገር ውስጥ በተመረቱ ምርቶች ተተክተዋል።
ሌላኛው ድርጅት ኤች ኬ ቢዚነስ ግሩፕ ይሰኛል። ይህ ድርጅት ደግሞ ‹‹ችግር ብልሀትን ይወልዳል›› እንዲሉ፤ ችግሩ ወደ አምራችነት አሸጋግሮታል። ድርጅቱ የተመሰረተው በኮንስትራክሽን ድርጅትነት ነው። እንደማንኛውም የኮንስትራክሽን ድርጅት የተለያዩ ግንባታዎችን ያከናውናል። ኮንትራክተር ሆነው በሚሠሩበት ወቅት ለተለያዩ ግንባታዎች ጥቅም ላይ የሚውለው የፕለይውድ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና አክሳሪ እየሆነባቸው ሄደ። ትርፍ እንደሚያገኙ አስበው እና እንደሚያዋጣቸው ገምተው ተጫርተው ያገኙትን ሥራ ገበያ ላይ ላሉት ፎርምዎርክ የሚያወጡት ዋጋ አዋጭ ሆኖ አላገኙትም። ለዚህም የተሻለ አማራጭ ለማግኘት መፍትሄ ፍለጋ ተሰማሩ።
የድርጅቱ የኮንስትራክሽን ኃላፊ ኢንጅነር ማዕረግ አብረሃ፤ ድርጅቱ ለፎርምወርክ ጥቅም ላይ የሚያውለው ፕለይውድ የተሰኘ ከእንጨት የሚሠራ የኮንስትራክሽን ግብአት መኖሩን ይናገራሉ። አምራች ከመሆናቸው በፊት በዋናነት መፍትሄ ፍለጋ እንዲያማትሩ ያስገደዳቸውም ይኸው ፕለይውድ መሆኑን ያብራራሉ። በህንጻም ሆነ በተለያዩ ግንባታዎች ላይ የኮንክሪት ሙሌት ይከናወናል። የተሞላው ኮንክሪት ድጋፍ የሚሆነው ፎርምወርክ ይፈልጋል። ሙሌቱ ቀኑ ሲደርስና ሲፈርስ ፎርምወርኩ ተነስቶ ለሌላ ሙሌት ድጋፍነት ይዘጋጃል። ግብአቱ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ሳይውል በውሃና በመሰል ሁኔታዎች የሚበላሽ በመሆኑና ከዋጋም ውድነት የተነሳ እሱን የሚተካ ምርት ለማምረት ማሰብ ጀመሩ።
በሌሎች ሀገራት ፎርምወርኩን ከፕላስቲክ በማምረት በአነስተኛ ዋጋ እንደሚጠቀሙ ኢንጅነር ማዕረግ ተረዱ። በዚህም በፒፒ ማቴሪያል (ፖሮክሎሪን ፕላስቲክ ማቴሪያል) በመጠቀም ፕላይውድን የሚተካ ኤች ኬ ፕላስቲክ ፎርምዎርክን ወደ ማምረት ተሸጋገሩ። እንደ ኢንጅነር ማዕረግ ማብራሪያ፤ የድርጅቱ ምርት ከ50 ጊዜ በላይ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ መዋል እና በሚስማር መመታት የሚችል፣ በግራይንደር በተፈለገው ቅርጽ መቆረጥ የሚችል፣ በውሃ የማይበላሽ፣ በክብደት ቀላል የሆነና መልሶ ጥቅም ላይ የሚውል ነው። ከአካባቢ ብክለት ነጻ የሆነና ለማንኛውም የኮንስትራሽን ግንባታ የሚያገለግል የፎርምዎርክ ምርት ሲሆን፤ በድርጅቱ ለኪሳራ መዳረግ የተነሳ የተጀመረው የተኪ ምርት ሃሳብ አሁን ዳብሮ የድርጅቱን ፍላጎት በመሸፈን ለሌሎች ድርጅቶችም አማራጭ ወደ መሆን ተሻግረዋል።
ገበያ ላይ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው አዲስ ነገር የመሞከር ፍራቻ ትንሽ ፈትኗቸው እንደነበር የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ አሁን ያለውን ገበያ አመርቂ በማለት ይገልፁታል። ለዚህ እማኝ ይሆኑ ዘንድ የእነሱን ምርት እየተጠቀሙ የሚገኙ የመንግሥትና የግል ድርጅቶችን ሥም በመጥራት እየተጠቀሙት መሆኑን ጠቅሰዋል። በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠትና ምርቱ ከተሸጠ በኋላ፤ ክትትል በማድረግ ችግሮች ሲያጋጥሙ እየፈቱ በመሄዳቸው ምርታቸው ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በደንብ መተዋወቁንና ጥሩ ገበያ መኖሩን ያነሳሉ።
ድርጅቱ ሥራ ሲጀምር ጥሬ እቃውን ከውጪ አስገብቶ ወደምርት የገባ መሆኑን ይናገራሉ። የምርቱ ባህሪ መልሶ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል በመሆኑ፤ ምርቱን ከድርጅቱ ገዝተው የተጠቀሙና ከአሁን በኋላ አያስፈልግም የሚሉ አምራቾች የገዙበትን 20 በመቶ ክፍያ በመፈጸም ምርቱን ይሰበሰባሉ። የተሰበሰበው ምርት ተፈጭቶ ለድርጅቱ ጥሬ እቃ የሚሆን በመሆኑ ድርጅቱ አሁን ከውጭ ምንም አይነት ጥሬ እቃ እያስገባ አለመሆኑን ይገልፃሉ።
ሌላኛው ድርጅት ደግሞ ወደ ንግዱ ገብቶ የደረሰበትን ችግር ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ የንግዱን ዓለም ከመቀላቀሉ በፊት ያየውን ጉድለት ለመሙላት በማሰብ የተቋቋመ ነው። ድርጅቱ ቤቶን ሞዴል ሜከርስ ይሰኛል። ድርጅቱ ኢንቲሪየር ዲዛይንና ፊኒሽንግ ቢሠራም የድርጅቱ ዋና መታወቂያ ሞዴል መሥራት ነው። ከድርጅቱ መስራቾች አንዱ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አርክቴክት በረከት ብርሃኑ፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ሊገነባ የታሰበውን የሚያሳይ የተገነባ ሞዴል መኖሩ ጠቃሚ ነው ይላል። በተለይ ለሪልስቴቶች ለሽያጭ የሚያግዝ ሲሆን፤ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችም ሕዝብ ላይ ተነሳሽነት ለመፍጠርና ፕሮጀክቶች ምን ይመስላሉ? የሚለውን ለማስረዳት ይጠቅማል። በዚህም ከህዳሴ ግድብ ጀምሮ ለትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችና ለበርካ ሪልስቴቶች ሞዴል መሥራታቸውን ጠቅሰዋል።
ሞዴል አሁን ላይ ተፈላጊነቱ መጨመሩን የሚናገሩት አርክቴክቱ፤ ዘመኑን የዋጁ ግብአቶችን እንደሚጠቀሙ በማንሳት፤ ለአብነት የ3ዲ ፕሪንቲንግ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ በማዋል እየሠሩ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ ቀደም ሞዴሎች በውጭ ሀገራት ይሰሩ የነበሩና የማሠራት አማራጭ ያላቸው ድርጅቶች በድርጅታቸው እያሠሩ በመሆኑ የውጭ ምንዛሬን ማስቀረት ተችሏል ይላሉ።
ድርጅታቸው የሚገነባውን የሞዴል ጥቅም ሲያስረዱ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ሰዎች ያላዩትን ነገር አምነው ለመግዛት ይቸግራቸው ነበር። ሃሳቡን ይዘው ወደ ገበያ የወጡት ሰዎች ያሰቡትን በተወሰነ ሞዴል መሬት ይዞ የሚወጣበትን ሁኔታ በሞዴል ሲያዩ ‹‹ማየት ማመን ነው›› እንደሚባለው፤ ሰዎች ቤት ለመግዛት አይተው መረዳት ምርጫቸው ነው። በተመሳሳይ መልኩ ለሀገራዊ ፕሮጀክቶች መቃናት ስለፕሮጀክቶቹ በደንብ መረዳት የማይፈልግ የለም። ያኔ የሞዴል ሚና ከፍተኛ ይሆናል።
‹‹ዘርፉ በደንብ ገበያ ያለውና እያደገ ያለ ዘርፍ ነው። ››የሚሉት አርክቴክት በረከት፤ ቀድመው ዘርፉን በመቀላቀላቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ድርጅቱ የሦስት ዓመት እድሜ ብቻ ቢኖረውም በዚህ አጭር ጊዜ ብዙ ማሳካታቸውን ተናግረዋል።
ከላይ የተጠቀሱት ሦስት ድርጅቶችን ያገኘናቸው ባሳለፍነው ሳምንት በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዶ በነበረው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ሲምፖዚየም እና ኤግዚቪሽን መድረክ ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው በቀረቡበት ወቅት ነው። በመድረኩ ሌሎችም በርካታ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተሳታፊ ነበሩ። በመድረኩ ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው ከቀረቡ ድርጅቶች ውስጥ ሌላኛው ትኩረታችንን የሳበው ድርጅት ሮሜል ሆልዲንግ ድርጅት ይሰኛል። ድርጅቱ የተለያዩ ላይት ፊክሰሮችን በሀገር ውስጥ ያመርታል። እንዲሁም ምርቱን ወደ ሀገር ያስገባል። ማብሪያ ማጥፊያዎችና ሶኬቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ያመርታል። ድርጅቱ ቡናን ወደ ውጭ ይልካል። ሌሎች አምራች ድርጅቶች ላይም ባለድርሻ ነው። በዋናነት ትኩረታችንን የሳበው ከቻይና ድርጅት ጋር በትብብር በሚሠራው ሥራ ነው።
በሀገር ውስጥ የማይገኙ የተለያዩ ምርቶችን ለማምጣት የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ወደ ቻይና መሄዳቸው የተለመደ ነው። ችግሩ በቻይና ተመሳሳይ ምርት የሚያመርቱ በርካታ ፋብሪካዎች አሉ። የሚፈልጉትን ምርት ለማግኘት ማንን ማናገር አለባቸው? የሚለው ማወቅ በቂ ልምድ ለሌለው ነጋዴ ራስ ምታት ነው። በሮሜል ሆልዲንግ ድርጅት ውስጥ የሶርሲንግ ዲፓርትመንት ኃላፊ አርክቴክት ሮቤል አበበ “በቻይና አንድ ምርት አንድ ከተማ ሙሉ ሊመረት ይችላል። ሁሉም ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ ናቸው ማለት አይቻልም፤ ለመለየት አስቸጋሪ ነው።” ሲሉ ይገልጻሉ።
ቻይና ሄዶ እቃ መግዛት ከባድ መሆኑን ሲያስረዱ፤ ትርፍ ፍለጋ የሄዱ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ከምርቶቹ የሚፈልጉትንና የሚያስፈልጋቸውን እንዴት ይመርጣሉ? የሚመርጡት እቃ ለእነሱ የሚሆን ነው? ተገቢውን መስፈርት ማሟላቱን እንዴት ያውቃሉ? እቃውንስ እንዴት ያመጣሉ? የሚለውም ሌላ ጣጣ ነው ይላሉ። እነዚህን ሁኔታዎች ለማቅለል ድርጅቱ ከቻይናው ጆንግሻን ጃምቦ ቴክኖሎጂ ጋር በጥምረት እየሠራ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
“በሀገራችን አርክቴክቶችና ኢንቲሪየር ዲዛይኖች (የውስጥ ስነውበት) ይበጃል የሚሉትን ዲዛይን ያወጣሉ፤ ሆኖም ጥቅም ላይ ስለሚውለው ግብዓት መስፈርት ቻይኖቹ ወይም የጣልያን ባለሙያዎች ይሥሩት ይባል ነበር።” ይላሉ። ይሁንና አሁን ድርጅታቸው በሀገር ውስጥ ተገቢውን መስፈርት የሚያወጡ ባለሙያዎችን በማሰልጠንና ከቻይናው ድርጅት ጋር በመሆን ክፍተቱን እየሞላ መሆኑን ይናገራሉ። እነሱ በሀገር ውስጥ የቻይናው ድርጅት ወኪል ሲሆኑ፤ የሀገር ውስጥ ነጋዴዎችን ከድርጅቱ ጋር እንደሚያገናኙ ያብራራሉ።
የቻይናው ድርጅት ጥራት መመርመሪያ መሳሪያዎች እንዲሁም ባለሙያዎች አሉት። ምርቱ ከተመረጠ በኋላ የጉዞ ሂደቱን የሚያቀላጥፉ ባለሙያዎችም አሉት። እንደአርክቴክት ሮቤል ገለፃ፤የተለያዩ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች የተለያዩ ምርቶችን ገዝተው ምርቱን ካስገቡ በኋላ ጥቅም ላይ ሲያውሉት ከሃሳባቸው የሚለያይበት ሁኔታ አለ። በተጨማሪ ገበያ ላይ ምርቶች በየጊዜው ይቀያየራሉ ያሉት አርክቴክቱ፤ ያሉ አማራጮችን በዘርፉ በቅርበት የሌለ ሰው አያውቃቸውም ብለዋል።
በተጨማሪ አስመጪው በራሱ ቢያመጣ ከእሱ ፍላጎት ጋር የማይሄዱና ፋሽን ያለፈባቸው የመሆን እድላቸው ሰፊ መሆኑን በመጠቆም፤ የእነሱ ባለሙያዎች በየጊዜው የሚወጡ ምርቶችን ይከታተላሉ። ስለዚህ በቀላሉ ገበያውን የሚያማክል የምርት ሃሳብ ያቀርባሉ። ይህንን ተከትሎ እቃ የሚያመጡ ሰዎች ለፍላጎታቸው የሚበጁ ትክክለኛ እቃ እንዲያመጡ እያገዙ መሆኑን ያመለክታሉ።
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ሲምፖዚየም እና ኤግዚቪሽን መድረክ ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው የቀረቡት አብዛኞቹ አምራቾች ከውጭ ዕቃዎችን የሚያስገቡ ነጋዴዎች ሲሆኑ፤ ብዙሃኖቹ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች መተካታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው። በሌላ በኩል ነጋዴዎች እንዳይጉላሉ እና ለተጨማሪ ወጪ እንዳይዳረጉ የሚሠሩትንም በማበረታታት በቀጣይም አስመጪዎች እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሠጥተው መሥራት ቢችሉ መልካም ነው እንላለን። ሠላም!
በቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም