
በጥንታዊዋ የጎንደር ከተማ የሚገኘው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቷ ከሚገኙ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ነው። ዩኒቨርሲቲው ከተመሠረተ 70 ዓመታት፣ ማስተማሪያ ሆስፒታሉ 100 ዓመታትን በማስቆጠር ከፍተኛ ሀገራዊ ፋይዳዎችን አበርክቷል።
በእነዚህ ረጅም ዓመታት ጉዞው ከ100ሺ በላይ ምሩቃንን ለሀገር ያበረከተ ሲሆን የአካባቢው የጤና አገልግሎት ሽፋን በመስጠትና ተማሪዎችን በዕውቀት በማስታጠቅ መተኪያ የሌለው ሚና ተጫውቷል።
ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት 12 የምርምር ማዕከላትን አቋቁሟል። 22 ግቢዎችና 11 ኮሌጆች ያሉት አንጋፋ ተቋም ሲሆን 89 የቅድመ መደበኛ ፣ 300 የሁለተኛ ዲግሪ፣ የሦስተኛ ዲግሪና የድህረ ዶክተራል ዲግሪ ፕሮግራሞች ከ40ሺ በላይ ተማሪዎች እያስተማረ ይገኛል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ ተልዕኮውን እየተወጣ የሚገኘው የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን የምርምር ፕሮጀክቶች በመሥራትም ጭምር ነው። በ2017 በጀት ዓመትም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው 22 የምርምር ፕሮጀክቶችን አስመርቋል።
በአሁኑ ሰዓት መደበኛ የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል። 89 የቅድመ መደበኛ እና 300 የሁለተኛ ዲግሪ፣ ሦስተኛ ዲግሪና ድህረ ዶክተራል ዲግሪ ፕሮግራሞችን ይዞ ከ40ሺ በላይ ተማሪዎች እያስተማረ ይገኛል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሚታወቅባቸው የትምህርት ዘርፎች ውስጥ ቀዳሚው የጤና ዘርፍ ነው። አብዛኞቹም ምርምሮች የሚካሄዱት ከዚሁ ዘርፍ ጋር በተያያዘ ነው። አብዛኞቹም ፕሮጀክቶች የሚነደፉት የጤና ዘርፉን ለማዘመን ነው። ፕሮጀክቶቹ አብዛኛዎቹ ሆስፒታል ላይ የሚገኙ እንደመሆናቸው የሆስፒታሉን አገልግሎት፣ የሆስፒታሉን የጤና ትምህርትና የሆስፒታል የመቀበል አቅም ከመጨመር አኳያ የሚኖራቸው ፋይዳ ብዙ ነው።
የጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አራት የሚደርሱ የካንሰር የጨረር ሕክምና ማዕከላት የነበሩት ሲሆን ሰሞኑን አምስተኛውን ማዕከል ከፍቶ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል። የዚህ ማዕከል መከፈት በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ለአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ክልሎችም (ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ትግራይና ሱዳን) ሳይቀር አገልግሎት የሚሰጥ ነው። ጎንደር የምትታወቅበት ታሪኳ የበለጠ እንዲጎላና የሕክምና ማዕከል እንድትሆን በማድረግ የሕክምና ቱሪዝምን የሚያስፋፋ ነው።
የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከሉም እንዲሁ ለበርካታ ዜጎች አገልግሎት የሚሰጥ ነው። ቀደም ሲል ኦክስጂን ከአዲስ አበባ ወይም ከባሕርዳር ነበር ሲመጣ የቆየው። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ኦክስጂን በወቅቱ ማምጣት ከባድ ፈተናዎች ያሉት በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው የኦክስጂን ማዕከላትን እያስፋፋ ይገኛል። ይህን በማድረጉም ዩኒቨርሲቲው ከራሱ አልፎ ለአካባቢው ላሉ ሆስፒታሎች ጭምር ማከፋፈል ችሏል። ከታካሚዎች ውስጥ 90 በመቶ ያህሉ ታካሚ ኦክስጂን የሚፈልግ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት መስጠቱ ብዙዎችን ከጭንቀት ገላግሏል። በአሁኑ ወቅትም በሲሊንደር ከቦታ ቦታ ማድረሱ እንዳለ ሆኖ ኦክስጂን ከማምረቻው በመስመር ወደ ታካሚ እንዲደርስ ተደርጓል።
የሰው ሠራሽ አካል ማምረቻ ማዕከሉም ለብዙዎች እፎይታ የሰጠ ነው። በጦርነት፣ በመኪና አደጋ፣ በተለያዩ ጉዳቶች ምክንያት የአካል ጉዳት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ የተለያዩ ምርምሮችን በማድረግ ላይ ይገኛል። የሚሠሩት የምርምር ሥራዎች ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ ክትትል ይደረግባቸዋል።
ዛሬ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአዲስ ጎዳና ላይ ይገኛል። ራስ ገዝ ለመሆን እና የበለጠ በጥናት እና በምርምሩ ላይ የጎላ አስተዋፅዖ ለማበርከት ዝግጅቱን አጠናቋል። በዚህ ረገድ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀዳሚ ሆኖ ራስ ገዝ የመሆን አቅም አላቸው ተብለው ዘጠኝ የሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ተለይተዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ነው። ራስ ገዝነት ዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ የአስተዳደር ነፃነት የሚያጎናጽፍ ተልዕኮዎቻችን ላይ ትኩረት አድርጎ ጥራት ያለው መማር ማስተማር፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ ምርምር ለመስጠት የሚያስችለው ነው።
ከዚህ ረገድ ባለፉት አራት ዓመታት ዩኒቨርሲቲውን ሰፊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ራስገዝ ለመሆን የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። ከ40 በላይ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች፣ ተዘጋጅተዋል። ሀብት ለመፍጠር የሚያስችሉ የገቢ ተቋማት ተፈጥረዋል። በተለይ ከ2013 ጀምሮ ከመማር ማስተማሩና ከምርምሩ ጋር እየተሳሰሩ በአንድ በኩል ገቢ እየፈጠሩ ነው። በሌላ በኩል መማማሪያና ምርምር መሥሪያም እየሆኑ ይገኛሉ።
በተጨማሪም ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ያሉ ገቢ የሚገኝባቸው ተቋማት ተፈጥረዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ሞዴል ፋርማሲ ነው። በእዚህ ፋርማሲ የጤና ባለሙያዎች ይሳተፉባቸዋል። ለአካባቢው ጥራት ያለው መድኃኒት ማቅረብ ተችሏል። የሥራ ዕድልም ተፈጥሯል። ጥራት ያለው መድኃኒት በማቅረብ የገበያ ማረጋጋት ሥራም እየተሠራ ነው።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (አይሲቲ)ና የምሕንድስና ማማከር አገልግሎት ይሰጣል። እነዚህም መምህራንና በቀጥታ ተያያዥ የሆኑ ትምህርት ክፍሎች ይሳተፋሉ። ትምህርታቸው አብረው እየተገበሩ ሙያቸውን እያዳበሩ ለመማር ማስተማሩም የመመራመር አቅም እየጨመሩ ነው።
ሌሎች የእንጨትና ብረታብረት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የማተሚያ ቤት፣ የሲኦሲ ማዕከል እና ሌሎች 10 በላይ የሆኑ ዘርፎች አሉት። ስለሆነም አቅምን ከመፍጠር አኳያ ሰፊ ሥራዎችም እየተሠሩ ነው።
ዩኒቨርሲቲው የሰው ኃይል ለማብቃት የአጭርና የረጅም ጊዜ ሥልጠናዎችን በመስጠት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ መጠን ከረጅም ጊዜ አኳያ ሁሉም መምህራን የሦስተኛ ዲግሪ እንዲኖራቸው ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች በትንሹ ተባባሪ ፕሮፌሰርና ከዚያ በላይ የሆኑ መምህራንን መያዝ ስለሚኖርባቸው ይህንኑ ለማሟላት ለሥልጠና ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። በአሁኑ ወቅት ከ700 በላይ መምህራን በሀገር ውስጥና በውጪ በተለያዩ ሀገራት ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን እየሠሩ ይገኛሉ። ከመምህራኑ ባሻገርም የአካባቢው ማኅበረሰብ ሰፊ የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ማኅበረሰብ በሩን ክፍት አድርጓል።
ከዚህ ባሻገር አጫጭር የሥራ ላይ ሥልጠናዎችን በትኩረት ይሰጣል። በተለይ ተተኪ አመራር ለማፍራት ‹የፖስት ግራጅዌት ኤንድ ሊደርሽፕ ዲፕሎማ› በሚል ሠራተኞችን በመመልመል የአንድ ዓመት ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል። ሌሎች አጫጭር ልዩ ሥልጠናዎችንም ለሴት መምህራን ይሰጣል።
ለወጣት ተመራማሪዎች ልዩ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ። ተሞክሮ ያላቸው ታዋቂ ስኬታማ ሰዎችንም በማምጣት ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ሥልጠና በመስጠት ዕውቀት እንዲገበይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው ባስገነባው ድረገጽ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ እጅግ ዘርፈ ብዙ ሰዎች ይሠራሉ። በትምህርት ለክልሉና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የትምህርት ዕድል በመስጠትና የአካባቢውን ትምህርት ቤቶችን የማጠናከር ሥራ ይሠራል።
ዩኒቨርሲቲው ሞዴል ትምህርት ቤት ያለው ሲሆን ከኬጂ ጀምሮ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርት ይሰጣል። ይህም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ልጆች የሚማሩበት ነው። ይሁን እንጂ ለአካባቢው ትምህርት ቤቶች እንደሞዴል ሆኖ ስታንዳርዱን ጠብቆ በማስተማር የጥራት ተምሳሌት መሆን የቻለ ነው። ሌሎች የአካባቢው ትምህርት ቤቶች ይህንን አርዓያ ተከትለው እንዲሠሩም ምሳሌ ሆኖ እያገለገለ ነው።
በጤናው በተመሳሳይ ሰፋፊ ሥራዎች ናቸው የሚሠሩት። በሆስፒታል ውስጥ ከሚሰጡ አገልግሎቶች በተጨማሪ የጤና ባለሙያዎቻችን ከቦታ ወደ ቦታ እየተንቀሳቀሱ የሚሰጡት አገልግሎት በጣም ሰፊ ነው። ለምሳሌ የዓይን ሞራ ግርዶሽን ለማከም በሁሉም አካባቢዎች ከቦታ ወደ ቦታ በመንቀሳቀስ አገልግሎቱን ለበርካቶች ተደራሽ መሆን ችለዋል።
በግብርና ዘርፍም የግብርና መካናይዜሽን እንዲተዋወቅ በማድረግ ትራክተሮችና፣ ኮምባይነሮች ተገዝተዋል። በተለይ በምሥራቅ ደንቢያ አካባቢ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ የተሠራው ሥራ አርሶ አደሩን ከተለምዶ አሠራር እንዲወጣ የሚያስተምሩና ግብርና መካናይዜሽን ላይ ባለሀብት እንዲገባበት የሚያደርጉ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል።
በተጨማሪም በአትክልትና ፍራፍሬም በአካባቢው የማይታወቁ የማምጣትና የማላመድና አርሶ አደሩን ማሠልጠንና በሥራው እንዲሠማራና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። የግብርና ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ሥራም ተሠርቷል። በተለይ ሩዝ ምርት በደንብ ዘሩን ተደራሽ በማድረግ በደንብ ተደርጓል።
ስማርቲ ሲቲን በመፍጠር ረገድ ጎንደር ከተማ ዘመናዊ ከተማ ለማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን አዲስ አበባ ጨምሮ የሌሎች ከተሞችን ተሞክሮ በመውሰድ እየተተገበረ ነው። በኮሪዶር ልማቱ የጎንደር ከተማ ዲዛይን በዩኒቨርሲቲው ነው የተሠራው። 15 የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን ከዲዛይን እስከ ክትትል እየተሠሩ ናቸው።
በአጠቃላይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከማኅበረሰብ አገልግሎት ጋር ያለው ትስስር ከፍተኛ ነው። ከጤና፤ ከግብርና ከትምህርት በተጓዳኝ በሕግ ዘርፍ በጎንደርና በአካባቢው 18 የሚሆኑ ነፃ የሕግ ማዕከላት አሉ።
ጠበቃ ገዝተው መከራከር ለማይችሉ ወገኖች የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት መምህራንና ተማሪዎች ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ይሰጣሉ። ይህም በአንድ በኩል ተማሪዎች በሙያቸው የተግባር ትምህርት የሚያገኙበት ነው። በሌላ በኩል በተለይ ሴቶች፣ ሕጻናትና አረጋውያንን የመሳሰሉ ጠበቃ ማቆም ለማይችሉ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል።
እኛም በዚህ ለሕዝብና ሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ ዐሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች እንዲሁም ስመጥር ታሪክ ያላቸውን የሀገራችንን ተቋማት ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት የባለውለታዎቻችን ዓምድ የአንጋፋውን የትምህርት ተቋም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ታሪክ በማውሳት ለተቋሙ መመሥረት አስተዋፅዖ የነበራቸውን ሁሉ አመሰገንን ሰላም!
ይህንን ፅሑፍ ለማዘጋጀት የዩኒቨርሲቲውን ጨምሮ የተለያዩ ድረገጾችን ተጠቅመናል!
በእስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም