የታይላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሾልኮ በወጣ የስልክ ንግግር ምክንያት ታገዱ

የታይላንድ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ከቀድሞ የካምቦዲያ መሪ ሃን ሴን ጋር ያደረጉት የስልክ ንግግር ሾልኮ መውጣቱን ተከትሎ ሥልጣን እንዲለቁ ጫና የበዛባቸውን የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ፓኤቶንግታርን ሺናዋትራን አገደ። በዚህ የስልክ ንግግር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሯ “አጎቴ” ሲሉ ለጠሩት የቀድሞ የካምቦዲያ መሪ ጋር የሀገራቸውን የጦር አዛዥ ሲተቹ ይሰማል። ይህም በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን ከኃላፊነታቸውም እንዲወርዱ ፊርማዎች ተሰባስበዋል።

በታይላንድ ለሁለት አስርት ዓመታት ፖለቲካውን በበላይነት የተቆጣጠሩት ሺናዋትራ ጎሳ አባል የሆኑት ፓኤቶንግታር፣ የሥልጣን ዘመናቸው ሳይጠናቀቅ ከኃላፊነት እንዲነሱ የተደረጉ ሶስተኛዋ ፖለቲከኛ ይሆናሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሯ የሚመሩት ጥምር መንግሥት ቁልፍ የወግ አጥባቂ ፓርቲ ከሁለት ሳምንት መውጣቱን ተከትሎ በጥቂት አብላጫ ለመምራት እየተንገታገተ ይገኛል።

የአገሪቱ ሐረገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከሥልጣን እንዲነሱ 7 ለ2 ድምጽ የሰጠ ሲሆን እሳቸውም መከላከያቸውን ለማምጣት 15 ቀናት ይኖራቸዋል። በዚህም ወቅት የሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሱሪያ ጁንግሩንግሩዋንግኪት ተጠባባቂ መሪ ሆነው የሚያገለግሉ ይሆናል። ፓኤቶንግታር ከሥልጣን የሚነሱ ከሆነ ከነሐሴ ወዲህ ከፌው ታይ ፓርቲ የተወገዱ ሁለተኛዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብሏል።

ከእሳቸው በፊት የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ስሬታ ታቪሲን በእስር ላይ የነበሩትን የቀድሞ ጠበቃ በካቢኔያቸው በመሾማቸው ከሥልጣን እንዲነሱ ተደርገዋል። ከዚህ ቀደም ከሥልጣን እንዲወገዱ የተደረጉት ታክሲን ሺናዋትራ ልጅ የሆኑት ፓኤቶንግታር ከቀናት በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቃለ መሐላ አደረጉ። የ38 ዓመቷ ጠቅላይ ሚኒስትር በሀገሪቷ ታሪክ ሥልጣን የተቆናጠጡ በዕድሜ ትንሽዋ እንዲሁም ከአክስቷ ይንግሉክ ሺናዋትራ በኋላ ሁለተኛዋ ሴት ናቸው። የሀገሪቱን የደከመ ምጣኔ ኃብት ለማነቃቃት እየታገሉ ያሉት መሪዋ ተቀባይነታቸው እየወረደ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሾልኮ የወጣው የስልክ ንግግራቸውን በተመለከተ ይቅርታ ቢጠይቁም ሰሞኑን በድንበር ድርድር ምክንያት የተነሱ ውዝግቦች ጋር በተያያዘ “የድርድር ቴክኒክ” ነው ሲሉ ተከላክለዋል። ነገር ግን የወግ አጥባቂ የፓርላማ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሯ ለካምቦዲያ ተንበርክከዋል እንዲሁም የሀገሯን ጦር ዝቅ በማድረግ ከሰዋቸዋል። የሀገሪቱን መንግሥት ከጀርባ ሆነው ያሽከረክሩታል የሚባሉት አባቷ በፖለቲካው ውስጥ የገቡትን እሰጣ ገባ ጋር እየታገሉ ባሉበት ወቅት ነው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተላለፈው።

አባትየው ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ለደቡብ ኮሪያ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የታይላንድን ንጉሳዊ ሥርዓት ተሳድበዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል። የፍርድ ሂደቱም ማክሰኞ ዕለት ተጀምሯል። ከ15 ዓመታት ግዞት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2023 ወደ ታይላንድ የተመለሱት አወዛጋቢው የፖለቲካ መሪ በሀገሪቱ አፋኝ በሚባለው ‘ሌሴ ማጀስቲ’ ሕግ ክስ ከተመሰረተባቸው ታዋቂ ሰዎች መካከል ዋነኛው መሆናቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You