ለምለም መንግሥቱ
ከተሞች ህይወት የሚኖራቸው ለሰዎች የመኖሪያ ቤት፣ መዝናኛና የሥራ ቦታ አሟልተው በቅርጽም ሆነ በይዘታቸው የመሠረታቸው እና የሚኖሩባቸው ማህበረሰብ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ነፀብራቅ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የኢፌዴሪ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የከተማ ልማት ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ዘርፍ በ2009ዓ.ም ስለከተሞች ልማት ባካሄደው ጥናት ላይ የተገኘው መረጃ እንደጠቆመው፤ ከተሞች እንደማንኛውም ሕይወት ያለው ፍጡር የሚያልፏቸው የጉዞ ሂደቶች ይመሰረታሉ (ይወለዳሉ)። ያድጋሉ፤ ያረጃሉ፤ ይሞታሉ። ነገር ግን ህይወት ካላቸው የሚለዩበት ባህሪ አላቸው። ከተሞች ዕድገታቸው ሙሉ ለሙሉ ወደ እርጅና ሳይለወጥ እራሳቸውን እያደሱ ለማደግ ያላቸው ዕድል ይጠቀሳል። ይሁን እንጂ ዕድገታቸው በሥርአት ካልተመራ ሞተው እስከመጨረሻው ይጠፋሉ።
በዓለም ላይ ለነዋሪዎች መኖሪያና ለሥራ ምቹ ባልሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የከተማ ነዋሪዎች ድርሻ 31.6 በመቶ ሲሆን፣ ይህ አሀዝ እንደሚያመለክተው በበለፀጉ ሀገራት ስድስት በመቶ፣ በታዳጊ ሀገራት 43 በመቶ፣ ከሰሀራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ 71.9 በመቶ ነው። የኢትዮጵያ የከተሞች እርጅና የሚገኝበት ደረጃ ከሰሃራ በታች በሚገኙ ሀገራት ካለው የከፋ ነው። በመሆኑም በመልሶ ማልማት ከተሞችን የማሻሻልና ወደ ዘመናዊ ኢኮኖሚ መዋቅር የማሸጋገር እርምጃ አስፈላጊነት ሆኖ ይገኛል። እንዲህ ያለ እርምጃ የከተሞች የወደፊት ቁልፍ የልማት አጀንዳ ተደርጎም ይወሰዳል።
ከተማ መልሶ የማልማትና የማዘመን እንቅስቃሴ እንደ አንድ የከተማ ልማት አጀንዳ ተይዞ ራሱን የቻለ ፕሮግራም ተቀርጾለት መተግበር ከተጀመረ እኤአ ከ1930 ጀምሮ በተለያየ ቅርጽ፣ ይዘትና የትኩረት መስክ የከተማ ማደስ ሥራ በተለያየ ሀገራት ሲተገበር መቆየቱን ያስታወሰው መረጃው፤ በኢትዮጵያ የከተማ ማደስ ልማት አጀንዳ የመንግሥትን ትኩረት በመሳቡ በተለይም በትላልቅ ከተሞች ተቋማዊ ምላሽ ማግኘት መጀመሩንና በዚህ ረገድም ከሁሉም የክልል ከተሞች አዲስ አበባ ከተማ ተጠቃሽ እንደሆነች አመልክቷል።
በኢትዮጵያ ነባር ከተሞችን መልሶ ማልማትን ጨምሮ አዳዲስና እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ መኖራቸው የግንባታ ዘርፉ ከፍተኛ የሆነ ግብአት እንዲጠቀም እንዳደረገውና ይህም ለግብአት አቅርቦት እጥረት እንደ አንድ ምክንያት ይነሳል። ምንም እንኳን በምክንያትነት ቢጠቀስም ብቻውን በቂ ምክንያት ነው ብሎ መቀበል እንደማይቻል አንዳንዶች ይገልጻሉ። የታቀደው ግንባታና የግብአት አቅርቦቱ ተጣጥመው ባለመከናወናቸው በግንባታ መጓተቶች ላይ ችግር ማስከተሉ ነው የሚነገረው። በብዙ የግብአት አቅርቦቶች ችግሮች እየተነሱ ቢሆንም በቅርቡ ትልቅ ችግር ሆኖ ምሬት ያስከተለው የሲሚንቶ ግብአት አቅርቦት ከሁሉም የከፋ ሆኖ ተገኝቷል። ምንም እንኳን ከሰሞኑ የሲሚንቶ ዋጋ መውረዱ ችግሩን ረገብ ያደረገው ቢሆንም። ዘላቂ መፍትሄ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ግን አይቻልም። አሁንም የግብአት እጥረት የዋጋ መዋዠቅ ቀጥሏል።
ምንም እንኳን የግብአት አቅርቦቱ ሰው ሰራሽና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እንደሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎችና መንግሥትም በተደጋጋሚ የገለጸው ቢሆንም ችግሩ እየቆየም ቢሆን ወደ ኋላ እየተመለሰ ተግዳሮት ሲሆን ይስተዋላል። ለመሆኑ በአማራጭ የግብአት አቅርቦት ችግሩን ማቃለል የሚቻልበት ዕድል ይኖር ይሆን? ሁሉንም የግንባታ አይነት በተመሳሳይ ግብአት ማከናወንስ ግድ ነው? እነዚህን ጥያቄዎች በዘርፉ ለሚገኙ የተለያዩ ባለሙያዎች አቅርበን የሚከተለውን ሀሳባቸውን አካፍለውናል።
በቅድሚያ ሀሳባቸውን ያካፈሉኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር ግንባታና ከተማ ልማት ተቋም መምህር ኢንጂነር ዶክተር ጥበቡ አሰፋ ናቸው። በሌላው ዓለም አማራጭ የግንባታ ግብአት የሚውሉ አማራጭ ቴክኖሎጂ መኖሩን ይገልጻሉ። እርሳቸው እንዳሉት ህንፃውን ሊያቀሉ ወይንም ክብደቱን ሊቀንሱ የሚችሉ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም ጀምሮ በአሁኑ ጊዜ ዓለም ግሪን ቴክኖሎጂ ወደሚባለው ተፈጥሯዊ በሆኑ ግብአቶች ወደ መጠቀም በማዘንበል ላይ ነው። ይህ ዘዴ ከፍተኛ የኃይል አጠቃቀምን በመቀነስ ለሰው ልጅ ጤና ተስማሚ የሆኑ ግንባታዎች እንዲከናወኑ የሚያግዝ ሲሆን፣ የሲሚንቶ ማጣበቂያን ከመጠቀም በፀሐይ ኃይል በማድረቅ፣ ድንጋዩን በብሎኬት ቅርጽ በመቁረጥ እርስ በርሱ በማጣበቅ ዘዴ ጠጠር፣ አሸዋና ሲሚንቶ ግብአት የሚፈልገውን ብሎኬት ማስቀረት የሚያስችል ነው። በቤት ግንባታ ብዙ ግብአት የሚወስደው ግድግዳ በመሆኑ እንዲህ ያለው ዘዴ ይመከራል። በኢትዮጵያም ቢሆን አክሱምና ላሊበላ አብያተክርስቲያናት ሲገነቡ ጥቅም ላይ የዋለውን ሀገር በቀል የግንባታ ዘዴ ማንሳት እንደሚቻልና ይህንን በማጥናት ለዚህ ዘመን ግንባታ እንዲውል ማድረግም ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ይመክራሉ።
በሌላው ዓለም ከወረቀትና ከሌሎችም ቀላል ግብአቶች ለግንባታ የሚውሉ ግብአቶች መጠቀም እየተለመደ ነው። በኢትዮጵያም ቢያንስ ለአነስተኛ ግንባታ የሚውል ሀገር በቀል ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሲሚንቶን ማጣበቂያ መተካት የሚቻልበት ዘዴ ወይንም ቴክኖሎጂ ለማላመድም ሆነ የግንባታ ኢንዱስትሪው እንዲቀየር ከተፈለገ በየጊዜው በዘርፉ ምርምር ማካሄድና በምርምር እንዲደገፍ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ ኢንጂነር ዶክተር ጥበቡ። አብዛኛውን ግብአት አፈር በማድረግ በትንሽ ሲሚንቶ በመጠቀም የሲሚንቶ ግብአቱን መቀነስ የሚቻልበት ዕድል መኖሩንም ለአብነት ጠቅሰዋል።
‹‹በአሁኑ ጊዜ ከገጠር ወደ ከተማ የመፍለስ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በመሆኑም አዳዲስ የህንፃ ግንባታዎች መኖራቸው ደግሞ ግድ ነው። አንድ ከተማ ከተማ አድርጎ ለማቆየት የኃይል፣ የግብአት፣ የቁሳቁስ፣ የምግብ፣ የውሃ ፍሰት ሳይቋረጥ መኖር አለበት›› የሚሉት ኢንጂነር ዶክተር ጥበቡ እንደገለጹት፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በኢትዮጵያ አማራጭ የግብአት ቴክኖሎጂዎች ከሲሚንቶ ግብአት ውጭ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም። በምርምር የታገዘ አለመሆኑ አንዱ ክፍተት ነው።
ሌላው ተጠቃሚው ገበያው ካቀረበለት ውጭ ሌላ የግብአት አማራጭ የመጠቀም ዕድል የለውም። ግብአቱ የተለመደና የተመሰከረለት ነው ብሎ ስለሚያምንም ጭምር ያለውን ለመጠቀም ይገደዳል።
ምንም እንኳን የቴክኖሎጂ አማራጭ መኖሩ አስፈላጊ እንደሆነ ቢታመንም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የቴክኖሎጂ አማራጭ ለመጠቀም የሚያስገድድ ሁኔታ እንደሌለም መምህሩ ይናገራሉ። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ምርቱን ለማምረት የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ለመለየት የህይወት ዑደት ትንተና ማካሄድ ያስፈልጋል። ምርቱን ለማምረት ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ ከጎደለ ማምረት አይቻልም። እጥረት ይፈጠራል። ከሚያስፈልጉ ግብአቶች አንዱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ነው። አምራች ኢንዱስትሪዎቹ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ የሚፈለገውን ያህል ሲሚንቶ ማምረት እንዳልቻሉ ቅሬታ ሲያቀርቡ ይሰማል። የኤሌክትሪክ ኃይልን ተክቶ የሚሰራ የድንጋይ ከሰል ሀብት በአማራ ክልል ወሎ ውጫሌ ይስማንጉሥ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ክምችት ይገኛል። ጣሊያን ኢትዮጵያን ወርሮ በኃይል በያዘበት ወቅት ከዚህ አካባቢ የድንጋይ ከሰል በማውጣት ገበያ ላይ በማዋል ይጠቀም እንደነበርም መምህሩ ያስታውሳሉ።
ሌላው ለእጥረቱ መንስኤ ናቸው ያሏቸው በማምረትና ምርቱን በማከፋፈል ላይ የተሰማሩት የተወሰኑ ኩባንያዎች ብቻ መሆናቸው ነው። አቅሙና ፍላጎቱ ካላቸው ግለሰቦች ጀምሮ በማምረትና በማከፋፈሉ ላይ በማሳተፍ በተወሰነ አካል እጅ ላይ ያለውን በማውጣት መፍትሄ መስጠት ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።
በመንገድና በህንፃ የግንባታ ዘርፍ ከመሰማራታቸው በተጨማሪ በማማከር ሥራ ላይ ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት ዠቅአለ፤ በህንድና የመን ያለውን አማራጭ የግብአት ቴክኖሎጂ ከጭቃና ቃጫ የሚሰራ መኖሩን በማስታወስ፣ የሲሚንቶ ግብአትን የሚተኩ ብዙ አማራጭ ቴክኖሎጂዎች መኖራቸውን ይገልጻሉ።
እንደርሳቸው ማብራሪያ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ሲውሉ ተያያዥ የሆኑ ነገሮችም አብሮ ታሳቢ ማድረግ ይገባል። ለአብነትም ለነፋስ፣ ለመሬት መንቀጥቀጥና ተያያዥ ለሆኑ ችግሮች እንዳይጋለጡ አብሮ የሚታሰቡ ሥራዎች ሲሆኑ፣ እንዲህ ያሉ ቴክኖሎጂዎች ደግሞ በዋጋ ውድና የውጭ ምንዛሪ ይጠይቃሉ። ነገር ግን አቅርቦታቸው የሚፈለገውን ያህል አይሆንም። ይሄንንም በምሳሌ ሲያስረዱ ውስጥ ለውስጥ መንገድ ሥራ የሚውለው ኮብል ስቶን ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት በአንድ መኪና ተጭኖ የሚቀርበው ድንጋይ ዋጋ ሶስት መቶ ብር ነበር። ጥቅሙ እየጨመረ ሲመጣ ግን ዋጋው ወደ አንድ ሺህ ብር ከፍ ብሎ ለአስፓልት ሥራ ከሚወጣው ወጪ እኩል ሆነ። አቅርቦቱ በቂ መሆኑ ሳይረጋገጥ አማራጭ ለመጠቀም መሞከር ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። የሲሚንቶ ግን ከቴክኖሎጂዎቹ በዋጋ ርካሽ በመሆኑ ነው በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው። ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲዎች አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን በተመለከተ ጥናት ተካሂዷል። አማራጭ ቴክኖሎጂን መጠቀምም ክፋት የለውም። ግን የግብአት አቅርቦቱ አስተማማኝ ባለመሆኑና ግብአቱ በብዛት በውጭ ምንዛሪ ከውጭ ሀገር የሚገባ በመሆኑ ሲሚንቶን መጠቀሙ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ መፍትሄ ብለው የጠቆሙት ሲሚንቶን በብዛትና በጥራት በማምረት እጥረቱን ወይንም ክፍተቱን መቀነስ ብቻ ነው።
‹‹ከአካባቢ የአየር ጠባይ ጋር ተስማሚ የሆነ የግንባታ ሥራ እንዲከናወን በሚል በአንድ ወቅት ከዲዛይን ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንድ የሚሰራ ሥራ እንደነበር አስታውሳለሁ። በዲዛይን የግንባታ ግብአትን መቀነስ የሚቻልበት ዕድል ይኖራል። ይህ ካልሆነ በስተቀር እስከማውቀው ድረስ በሀገር ውስጥ የግብአት ችግር አለ ተብሎ ወደሌላ አማራጭ ሊወስደን የሚችል ነገር የለም።›› የሚሉት በንግድ ሚኒስቴር የብረታ ብረትና ኬሚካል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዱጋሳ ዱንፋ ናቸው። ከሲሚንቶ ግብአት ውጭ ሌላ አማራጭ ይኑር ብለው እንደማይመክሩ ይገልጻሉ።
እንደ አቶ ዱጋሳ ማብራሪያ ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የግንባታ ሥራ ለማከናወንም ለግብአቱ ማዘጋጃ የሚውለው የኃይል ምንጭ ጋዝ በመሆኑ በአብዛኛው ካርቦን የሚስብ በመሆኑ ተጽዕኖ አለው። በአሁኑ ጊዜ ግን በድንጋይ ከሰል የመጠቀም ሁኔታ በመጀመሩ የአካባቢ ተጽዕኖውን መቀነስ የሚቻልበት ዕድል እየተፈጠረ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ የሚነሱ ተጽዕኖዎች የሲሚንቶ ግብአትን በሌላ አማራጭ ወደ መተካት የሚያስኬድ አይደሉም።
በቂ የሆነ ግብአት አለ በሚል ብቻ አማራጭ ቴክኖሎጂ አያስፈልግም የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል ወይ? ለሚለው ጥያቄ አቶ ዱጋሳ በሰጡት ምላሽ፤ በእርሳቸው እምነት ችግር ነው ብሎ ለመነሳት እንኳን ጥናት ያስፈልጋል። ጥናት ለማድረግ ደግሞ ጥያቄ መኖር አለበት። ሌላው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ሲደረግ ሌላ አቅርቦት ይፈልጋል። በአካባቢ ላይም ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
በዘርፉ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ስላለው ፍላጎት ለአቶ ዱጋሳ ጥያቄ አንስቼላቸው ‹‹በዘርፉ ለመሰማራት የገንዘብ አቅም ይጠይቃል። ቶሎ ትርፋማ ለመሆን ጊዜ ስለሚወስድም በፍጥነት ትርፍ በሚያስገኙ ነገሮች ላይ ለመሰማራት ያለውን ያህል ፍላጎት አለ ለማለት አያስደፍርም። ዋጋ በሚያስከፍል ነገር ላይ ሰው አይበረታታም። በዘርፉም የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚፈለገውን ያህል አለመሆኑም ሌላው ክፍተት ነው›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። መንግሥት ግን ዘርፉን ለማበረታታት የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱንና አሁንም መቀጠሉን ተናግረዋል። በአሁኑ ጊዜም በኦሮሚያ ወደ ሶስት ቦታዎች አዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ዝግጅት ማድረጋቸውን፣ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካም ተጨማሪ ፋብሪካ ለመክፈት ከዚህ ቀደም ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ቅድመ ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን፤ በኮቪድ-19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታና በተለያየ ምክንያት ሥራቸው ተቋርጦ የነበሩ ፋብሪካዎችም ወደ ስራ መግባት መጀመራቸውን አስረድተዋል። በከፊል ይሰሩ የነበሩ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ባለሙያዎችንና አመራሮችን ያካተተ ቡድን ተዋቅሮ አስፈላጊውን የድጋፍና ክትትል ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደሀገር አማራጭ የሚያስፈልግበት ደረጃ ላይ ባይደረስም በአካባቢ ተጽዕኖም ይሁን፣ የሚነሳው የተለያየ ሀሳብ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ያሳያል። የዘርፉ ምሁራንም ምርምርና ጥናት በማድረግ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በማሳየት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2013