
አካል ጉዳተኛ በመሆኑ እንደ ልብ ለመንቀሳቀስና በእግሩ ብዙ ቦታዎች ለመጓዝ አይችልም። ሌሎች አካል ጉዳተኞች ዊልቸር ሲጠቀሙ ቢመለከትም ለመግዛት አቅሙ አልነበረውም። ይህን ተከትሎ የዕለት ተዕለት ኑሮውን ለመግፋት ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ የግድ የሰዎች እገዛ ያስፈልገው ነበር።
ይሁንና ሁልጊዜም በሰዎች ድጋፍ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እየሰለቸውና ዘወትር የሰዎችን ፊት ማየትና እንዲያግዙት መለመን እየታከተው መጣ። ቀን ቀንን እየተካ ሲሔድ አካል ጉዳተኝነት እጆቹን ከሥራ፣ አእምሮውን በጥልቅ ከማሰብና ከማሰላሰል አልገደበውም። የነበረው አንድና አንድ አማራጭ የራሱን ችግር በራሱ መፍታት ነበር።
እጆቹን ለሥራ አነሳሳ። በአካባቢው በቀላሉ የሚያገኛቸውን ብረታ ብረቶችን በመጠቀም በአእምሮው ሲያሰላስል ቆየ። አካል ጉዳተኝነቱ ብሩህ አእምሮና እጆቹን ተጠቅሞ እሱ እና ሌሎች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች ለመሥራት ምክንያት ሆነው። ለእሱ ችግሮች መፍትሔ ለማግኘት ባደረገው ጥረት፤ ለብዙዎች መትረፍ አስቻለው።
ወጣት ከማል አብዱራህማን ይባላል። አካል ጉዳተኛነቱ ሳይገድበው ከሦስት በላይ የፈጠራ ሥራዎችን ሠርቷል። በምዕራብ አርሲ ገደብ አሳሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የብየዳ ሙያ ሠልጣኝ ነው። ያለሰዎች ድጋፍ እንደልቡ ሊያንቀሳቅሰው የሚችል ዊልቸር እንዲኖረው ስለፈለገ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ቀጠለ።
አካል ጉዳተኝነት የአእምሮ ጉዳተኛነት እንዳልሆነ በጽኑ የሚያምነው ከማል፤ ለመሥራት ሲነሳ መጀመሪያ ዊልቸሩ ምን ዓይነት ቅርጽ ሊኖረው እንደሚችል አስቦ፤ በንድፈ ሃሳብ ዲዛይን አወጣ። የሚሠራባቸውን ግብዓቶች በቀላሉ በአካባቢው አገኘ። ወጣት ከማል የተለያዩ እንቅፋቶች ቢያጋጥሙትም ላጋጠመው ችግር መፍትሔ ለማፈላለግ የሚያደርገውን ጥረት አላቋረጠም።
የብየዳ ሥራውንና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎች እንዲሠሩለት የሌሎች ሰዎች እርዳታና ድጋፍ ጠየቀ። የሰዎች እገዛ ታክሎበት ዊልቸር የመሥራት ጥረቱ ፍሬ አፍርቶ፣ ህልሙን ወደ ተግባር ቀይሮ፣ ይመኘው የነበረውን ዊልቸር መሥራት ቻለ። ዊልቸር የመሥራት ሃሳቡ እውን ሆነለት። እጁን ያፍታታበትን የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራ የሆነውን ዊልቸር ለራሱ ይገለገልበት ጀመር።
ዊልቸሩ ያለሰዎች ድጋፍ እንደፈለገው የዕለት ተዕለት ተግባሩን ለማከናወን በራሱ ለመንቀሳቀስ አስቻለው። ወደ ትምህርት ቤትም ሆነ ሌሎች ቦታዎች መሄድ ቀላል ሆነለት። ቀደም ሲል ጀምሮ ከትምህርቱ ጎን ለጎን የዕለት ጉርስ ፍለጋ የሚሠራው ሥራ የነበረው ከማል፤ በራሱ ሥራው ቦታው ድረስ በመሄድ መሥራት ጀመረ። ይሁንና ዊልቸሩ እንደፈለገው ያለ ሰው እርዳታ መንቀሳቀስ ቢያስችለውም፤ ሥራውን ለመሥራት ወደ ገበያ የሚወስዳቸውን ቁሳቁሶች ለማጓጓዝ የሰዎች እርዳታ መጠየቅ ግድ ሆነበት።
ለእዚህ ችግር መፍትሔ ለማመንጨት ያልዘገየው አእምሮውን ተጠቅሞ፤ በዊልቸሩ ላይ ቁሳቁሶች መጫን የሚችልበት ተጨማሪ ሳጥን ሠራ። ሳጥኑንም ቁሳቁሶችን ለማስቀመጫ ብቻ ሳይሆን ገበያ ሄዶ አንዳንድ ነገሮችን መሸጫ አደረገው። ዊልቸር በመሥራት የፈጠራ እጆቹን ያፍታታው ከማል፤ በእዚህ የፈጠራ ሥራ ሳያቆም የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች አከታትሎ ለመሥራት በቃ።
ከዊልቸሩ ቀጥሎ በሚኖርበት አካባቢ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ጋሪዎች መሆናቸውን በማየት ወደ ባጃጅ ለመቀየር በማሰብ ዲዛይኑን በአእምሮ ሳለ። የራሱን ፈጠራ ተጠቅሞ ባለሁለት እግር ሞተር ሳይክል በመግዛት፤ በአካባቢው የሚገኙ ብረታ ብረቶችን ቆራርጦ በመጠቀም ሦስት ሰዎች የሚጭን ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) መሥራት ቻለ። ይህም የበለጠ ሥራውን ለማቀላጠፍ አስቻለው።
ይህ ፈጠራው ወጣት ከማል ልምድ እያካበተ የፈጠራ ሥራውን እያሳደገ እንዲመጣ ምቹ ሁኔታ ሁኔታ እንደፈጠረለት ይናገራል። እነዚህ የፈጠራ ሥራዎቹን የተመለከቱ የአካባቢው ሰዎች እያበረታቱት ለእነርሱም እንዲሠራላቸው ይጠይቁት ጀመር።
በተለይ ከዊልቸሩ ቀጥሎ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪውን ከሠራ በኋላ፤ ብዙዎች እንዲሠራላቸው ጥያቄ በማቅረባቸው ሦስት ዊልቸሮችንና አንድ ባጃጅ ሠርቶ መሸጡን ይገልጻል። የሠራቸውን ሦስት ዊልቸሮች ስድስት ሺ፣ ሰባት ሺ እና ስምንት ሺ ብር መሸጡንም ይናገራል። ወጣት ከማል እንደሚገልጸው፤ ሁለተኛ የፈጠራ ሥራው የሆነውን ሦስት ሰዎች የሚጭነውን ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ደግሞ ብዙ ወጪ የነበራቸው ግብዓቶችን በመጠቀሙ 80ሺ ብር ሸጠ።
ወጣት ከማል፤ በተጨማሪ አካባቢው ላይ ላሉ የመግዛት አቅም ለሌላቸው አካል ጉዳተኞች አቅማቸውን ባገናዘበ በተመጣጣኝ ዋጋ ዊልቸሮችን ሠርቶ መስጠቱን ይገልጻል። የሚሠራቸው የፈጠራ ሥራዎች ሰዎች እየተጠቀሙበት የገቢ ምንጭ እየሆኑት መምጣቱ ትልቅ ሞራልና ጉልበት እንደሆነው የሚናገረው ከማል፤ የፈጠራ ሥራዎቹን ይበልጥ ሊያሻሽል የሚችልበት እውቀትና ክህሎት እንዲኖረው የሚያደርግ መልካም አጋጣሚ ገጥሞት በገደብ አሳሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የመግባት እድል ተመቻቸለት። በኮሌጅ ቆይታውም የብየዳ ሙያ ተምሮ እውቀት ገብይቶ ልምድ አካበተ።
ኮሌጅ ከገባው በኋላ በእውቀት የታገዙ ብዙ የፈጠራ ሥራዎች መሥራት ቻለ። በ2015 ዓ.ም ከዞኑ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ በተዘጋጁ ውድድሮች አንደኛ በመውጣቱ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ባዘጋጀው “በኢትዮ ክህሎት ውድድር” መሳተፍ መቻሉን ይናገራል።
ወጣት ከማል ወደ ማበልጸጊያ ማዕከሉ ከገባ በኋላ በተሰጡት የተለያዩ ሥልጠናዎችና ድጋፎች የተሻለ እውቀትና ልምድ ማግኘቱን ጠቅሶ፤ ቀደም ሲል ከሠራቸው ሁለት የፈጠራ ሥራዎች ላቅ ያለ ደረጃውን የጠበቀ አራት ሰዎች መጫን የሚችል ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ(ባጃጅ) መሥራቱን ይናገራል። ይህም በክህሎት ባንክ ውስጥ እንደሚገኝ ያመላክታል።
“አካሌ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ ምንም ስላልሆነ የፈለግኩትን ያሰብኩትን ነገር መሥራት እችላለሁ፤ ሠርቼም እንደምችል አሳይቻለሁ። በቀጣይም ሥራዎቼን ከበፊቱ ከፍ አድርጌ ለመሥራት እፈልጋለሁ። ” የሚለው ከማል፤ በዘንድሮ ዓመትም ሞተር ሳይክል ወደ ሦስት እግር ተሽከርካሪ በመቀየር ቀድሞ ከሠራው ፈጠራ በተለየ መልኩ የጭነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ ሠርቷል።
የፈጠራ ሥራዎችን በየጊዜው እያሳደገ የመጣው ከማል፤ የጭነት አገልግሎት የሚሰጥ ባለሦስት ተሽከርካሪ ባጃጅ ሠርቶ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባዘጋጀው 4ኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር ማቅረብ ችሏል። ይህን ባለሦስት እግር የጭነት ተሽከርካሪ ለመሥራት ግብዓቶች ከሰበሰበ በኋላ የአንድ ወር ጊዜ ብቻ ፈጅቷል የሚለው ወጣት የፈጠራ ባለሙያ፤ ተሽከርካሪው እንደሌሎች ሞተር ሳይክሎች ሁለት ጎማ ያለው ሳይሆን ሦስት ጎማ እንዲኖረው አድርጎ መሥራቱን ይገልጻል።
ተሽከርካሪው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፤ ማርሹም ሆነ ፍሬኑ እጅ ላይ ተደርጎ መሥራቱ አካል ጉዳተኞች እንደልባቸው እንዲያሽከረክሩ ያስችላቸዋል። ተሽከርካሪውን ራሱንና ሌሎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርጎ የሠራው ቢሆንም፤ ሌሎችም ሰዎች ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አመላክቷል።
ወጣት ከማል እንዳብራራው፤ ተሽከርካሪው የተለያዩ የወዳደቁ ቁሳቁሶች በመጠቀም የተሠራ ነው። በቤንዚል የሚሠራ ሲሆን፤ በአንድ ሊትር ቤንዚል ሰላሳ ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ ይችላል። ለጭነት አገልግሎት እንዲውል ተደርጎ የተሠራ በመሆኑና በአንድ ጊዜ አራት ኩንታል የመጫን አቅም ስላለው ጭነቱ በዝናብ እንዳይበሰብስ የሚያደርግ መከላከያ ጥላ ተሠርቶለታል።
የጭነት ተሽከርካሪውን ለመሥራት በአካባቢው ላይ የሚገኙ ቁሳቁሶች ይጠቀም እንጂ፤ ተሽከርካሪውን ለመሥራት የሚያስፈልጉ የገዛቸው ግብዓቶች መኖራቸው ያመለክታል። የራሱን ስልክ ሳይቀር በመሸጥና አቅሙ የፈቀደውን ያህል ገንዘብ ያወጣበት መሆኑን ይናገራል። በተጨማሪም ኮሌጁ የገንዘብና የማሽነሪ ድጋፍ እንዳደረገለት በመጥቀስ፤ ይህን ተሽከርካሪ ሠርቶ ለማጠናቀቅ 170ሺ ብር ወጪ አድርጌያለሁ ሲል ይገልጻል።
በአሁኑ ወቅት ባጃጁን ጥቅም ላይ አውሎ የጭነት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጾ፤ አካል ጉዳተኞችም ሆኑ ሌሎች እንዲሠራላቸው የሚፈልጉ ሰዎች ጥያቄ ሲያቀርቡ ሠርቶ መስጠት የሚያስችል አቅም እንዳለው አመላክቷል። አካል ጉዳተኛ ቢሆንም ቀደም ሲል ጀምሮ በፍጹም ሰዎችን ማስቸገር እንደማይፈልግ እና ሌሎችን ማገዝ እንደሚሻ የሚገልጸው ከማል፤ የፈጠራ ሥራዎችን ለራሱ በሚመች መልኩ መሥራቱ ለራሱ ብቻ ለመገልገል አስቦ የሠራው ሳይሆን ሌሎች አካል ጉዳተኞችም እንዲገለገሉበት ያስብ እንደነበር ይናገራል።
ይህም ራሱን ችሎ ለመሥራት እንደልቡ ተንቀሳቅሶ ሥራውን ለማከናወን እንደረዳውና ብዙ ነገሮችን በቀላሉ እንዲያከናውን እንዳስቻለው ይገልጻል። ተሽከርካሪውን አካል ጉዳተኞች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ሰው ሊጠቀምበት የሚችል መሆኑን አስታውቋል።
ሦስት ለአካል ጉዳተኞችም ሆነ ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎች ሲሠራ ነገሮች አልጋ በአልጋ እንዳልነበሩ የሚናገረው ከማል፤ እነዚህን የፈጠራ ሥራዎች የሠራው በቀላሉ በአካባቢው ላይ ከሚገኙ ቁሳቁሶች ቢሆንም፤ እያንዳንዳቸውን የፈጠራ ሥራዎች ሲ“ራ ብዙ እንቅፋት አጋጥመውት እንደነበር ያስታውሳል። አካል ጉዳተኛ መሆኑ ደግሞ በራሱ ማከናወን የማይችላቸውን ነገሮች ሰዎች እንዲያደርጉለት ሲጠይቅ ብዙ ችግሮች አጋጥመውት እንደነበር ያስታውሳል።
“አካል ጉዳተኛ ብሆንም መሥራት እችላለሁ ብዬ ማመን ብቻ ሳይሆን፤ ከሁሉ በላይ የራሴን ችግር ለመፍታት ከራሴ የቀረበ የለም። የሚል ጽኑ እምነት መያዜ ጠቅሞኛል። ” የሚለው ከማል፤ ላጋጠመው ችግር መፍትሔ ለመስጠት ባደረገው ጥረት ውጤታማ ሆኖ አሁን ለደረሰበት ደረጃ መብቃቱን ይገልጻል።
በሌላ በኩል በአካባቢው ላሉ ወጣቶች አርአያ መሆን የሚችል እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ የሚገልጹለትና ሞራል እየሰጡ እያበረታቱት እንደሆነ ገልጾ፤ የአካባቢው ማህበረሰብ የሚሠራውን እያየ የሚያበረታታው መሆኑን ገልጻል፤ እንዳይደክም እንዲሁም ብዙ የፈጠራ ሥራዎች እንዲሠራ ብርታት እንደሆነውም ይናገራል።
በፈጠራ ሥራዎች የኅብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ሥራዎች እንደሚሠራ ገልጾ፤ በአሁኑ ወቅት የሠራቸው የፈጠራ ሥራዎች ለራሱም ሆነ ለሌሎች ሰዎች እንዲገለገሉበት እያደረገ እንደሚገኝ ይናገራል።
ከማል እንደሚለው፤ ወደፊትም የሠራቸውን የፈጠራ ሥራዎች ያሉባቸውን ክፍተቶች በማሻሻል ምርጥ እንዲሆኑ ያደርጋል። ሌሎች አዳዲስ የኅብረተሰቡን ችግር መፍትሔ የሚሰጡ የፈጠራ ሥራዎችንም ለመሥራት አቅዷል። በተለይ አካል ጉዳተኞችን የሚጠቅሙ የፈጠራ ሥራዎች ለመሥራት አላማ አድርጎ ብዙ ሥራዎች የመሥራት ሃሳብ አለው።
አካል ጉዳተኞች ሞተር ሳይክል ወደ ባጃጅ በመቀየር እሱ የሠራውን ዓይነት ተሽከርካሪዎች በቀላሉ መሥራት እንዲችሉ ሥልጠናዎች ለመስጠት ማቀዱን የሚገልጸው ከማል፤ ይህም ለብዙዎች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚያስችል አመላክቷል። በተጨማሪም ማንኛውም ሰው ሊጠቀምበት የሚችል በመሆኑ፤ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን የራሱን ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል።
የፈጠራ ሥራ ሃሳብ ለራስ ችግር መፍትሔ ከመፈለግ ይጀምራል የሚለው ከማል፤ ከእሱ ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻለው ላጋጠመው ችግር መፍትሔ ፍለጋ ያደረገው ጥረት ከራሱ አልፎ ብዙዎችን መጥቀም እንደቻለ ያብራራል።
ከማል፤ ወጣቱ ፈጠራዎችን ከመፍጠር ምንም ሊገድበው እንደማይችል በማመን ውስጡ ያለውን ነገር ለማውጣት ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባ ይናገራል። የሚያጋጥሙ ብዙ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ያለመታከትና መሰልቸት በጥበብ ማለፍ ያስፈልጋል ሲል ይመክራል።
በወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም