ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ መልካም ባህሎች ባለቤት ናት። ከነዚህ መልካም ባህሎቻችን ውስጥ ‹እንብላ› የሚለው አንዱ ነው።እርግጠኛ ነኝ በእያንዳንዱ የህይወት እንቅስቃሴያችን ውስጥ ይሄን ቃል ሰምተነዋል። በተለይ የቀደሙት አባቶቻችን በዚህ ታላቅ ባህል ውስጥ ያለፉ ናቸው።
በነገራችን ላይ አሁን በእኔና በእናንተ ዘመን አብሮ መብላት እንደ ነውር ታየ እንጂ፣ ድሮ አብሮ መብላት የኢትዮጵያዊነትና የአብሮነት ማሳያ ነው። ይህን ይህን ስንመለከት ድሮነታችን ውስጥ ብዙ መልካም እሴቶች አሉን። አሁን ላይ ሀበሻነት በገባቸው አንዳንድ ሰዎች ካልሆነ በስተቀር አብዛኞቻችን ይሄን ቃል አንጠቀመም። በዛ ፈንታ ለብቻ መብላትን፣ በር ዘግቶ ለብቻ መኖርን ባጠቃላይ ጉርብትናን አብሮነትን ጠልተን ግለኝነትን የመረጥንበት ክፉ ጊዜ ላይ ነን።
ለዚህ እኮ ነው በብዙ ነገራችን አየከስረን ያለነው። ለዚህ እኮ ነው መድረስ ከሚገባን ጫፍ ያልደረስነው። የራሳችን የሆነን ድንቅ ባህል ትተን የምንገነባው ታላቅ ሀገርና ህዝብ የለም።ከሁሉ በፊት ወደ ራሳችን ወደ ጥንቱ የአባቶቻችን ስርዓት መመለስ አለብን። አሁን ራሳችንን ትተን ምኑንም በማናውቀው በፈረንጅ አጉል ባህል የተወሰድን ብዙዎች ነን።
በነገራችን ላይ ብቻ መኖር፣ ብቻ መብላት ባጠቃላይ ግለኝነት የፈረንጅ አጉልነት ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን እንዲህ አይነት አፍራሽ ባህል የለንም። ከትናንት እስከዛሬ አባቶቻችን በአንድነት ተጉዘው የመጡ ናቸው። እኛም የነሱ ልጆች በአባቶቻችን ስርዐት መኖር አለብን።
ታላቅነት መነሻውም መድረሻውም ሀገርና ህዝብ ነው። እኔ ግን እላለሁ በዚች ሀገር ላይ የአባቶቻችን ስርዐት መመለስ አለበት።ድሮነት ከነወዙ…ዛሬነትን ይውረስ። ዛሬ በሁሉ ነገሩ ከትናንት የተሻለ እንደሆነ አውቃለሁ፤ በአንዳንድ ማህበራዊ እሴቶቻችን ላይ ግን እያከሰረን ይገኛል። በዚች ሀገር ላይ ከዛሬ ይልቅ ትናንት የሚናፍቀን ብዙዎች ነን።ምርጧ ኢትዮጵያ..ከዛሬ ይልቅ በትናንት ማህጸን ውስጥ ናት…እስካሁን አልተወለደችም። ወይ አዋላጅ የለም ወይ የሚያምጥ ጠፍቷል።
ኢትዮጵያን ሳናውቃት ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ትርጉም የለውም። እውቀት ማለት ራስን ማወቅ የራስ የሆነን ነገር መጠበቅ እንጂ የራስን እየተው በሌሎች ባህልና ስርዐት መሳብ አይደለም።
እስኪ አስቡት..አብሮ እንደ መብላት አብሮ እንደመኖር ምን መልካም ባህል አለ? አብሮነት እኮ ሀይል ነው። አብሮነት እኮ ስልጣኔ ነው።በኑሯችን ውስጥ፣ በትዳራችን ውስጥ፣ በንግግርና በእያንዳንዱ እንቅስቃሴአችን ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን ይዘን መሆን አለበት።
ስንት ልናስቀራቸው የሚገቡ ለሀገርና ወገን ችግር የሆኑ መጥፎ ባህሎች እያሉን የአንድነታችንን ፋና ወጊ ለማስቀረት ስንሞክር አይገርምም? መጀመሪያ ከማይጠቅመን ዘረኝነት እንውጣ።መጀመሪያ ድሮነትን በልባችን ውስጥ እናትም። ዘመናዊነት እየመሰለን ከተውነው ኢትዮጵያዊነት እንመለስ።እንብላ በየትኛውም ሀገር የሌለ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ባህል ነው።
አንድ ጊዜ አንድ ካፌ ቁጭ ብዬ መጽሀፍ አነባለሁ….አጠገቤ ጸጉሩን ያንጨፈረረ ጆሮው ላይ ሎቲ የሰካ አንድ ደንደሳም ጎረምሳ ተቀምጧል…አይኖቹን ስልኩ ላይ አፍጦ የሆነ ነገር ይጎረጉራል። ከእሱ አጠገብ ደግሞ ከዘራቸውን ወንበር ላይ ያስደገፉ ባለ ነጭ ጸጉር አዛውንት ተቀምጠዋል። ወዲያው በአንዲት ፈገግተኛ አስተናጋጅ ተይዞ የሽማግሌው ምሳ መጣ።ምሳው ጠረጴዛ ላይ ከማረፉ ከሽማግሌው አፍ አንድ ቃል ወጣ…ምን ይመስላችኋል? ‹እንብላ ልጆቼ የሚል ነበር፡፡
ከማነበው መጽሀፍ ላይ ቀና ብዬ አየኋቸው…በነጫጭ የሽፋል ጸጉር የተከበቡ አይኖቻቸው ወርውረው አንዴ እኔን አንዴ ወጠምሻውን እያዩ አገኘኋቸው።ምላሽ እየጠበቁ እንደሆነ ስለገባኝ…
‹አመሰግናለሁ አባቴ› ስል የድርሻዬን ተወጣሁ፡፡
ወጣቱ ወጠምሻ አይኖቹን ከሞባይሉ ላይ ሳይነቅል ‹ይሄ ነገር ዛሬም አልቀረም እንዴ ፋዘር? ሲል ጠየቀ፡፡
‹ምኑ?››ሲሉ ያልገባቸው ሽማግሌ መልሰው ጠየቁ፡፡
‹እንብላ የሚለው ነገር? አሁንም አላያቸውም አይኑ፣ ልቡ፣ ቀልቡ፣ መንፈሱ ሁሉ ሞባይሉ ላይ ነበር፡፡
የትዝብት ሳቅ ሳቅ ብለው ‹የአሁኑ ትውልድ ጥሩ ነገር አታውቁም። ለልጆቻችሁ ምን እንደምታወርሷቸው እግዜር ይወቀው። እንብላ እኮ የኢትዮጵያዊነት ቀለም ነው። ከትናንት ዛሬ የደረስንው አብረን እየበላን አብረን እየጠጣን ነው።
ጣሊያንን ያሸነፍነው፣ በኡጋዴንና በአንባላጌ በካራማራም ድል ያገኘንው አብረን ስለበላን ነው። አብሮ መብላት አብሮ መሆን ነው።አብሮ መብላት ወንድማማችነት ነው። ዛሬ ላይ በብዙ ነገራችን ተለያይተን የቆምነው የድሮ መልካም ባህሎቻችንን ስለተውን ነው። አንተም እኔን አባትህን ጎንህ አስቀምጠህ ከሞባይልህ ጋር የምትጫወተው ኢትዮጵያዊነትን ስላላወክ ነው። ከመጣሁ ጀምሮ አንዴም አላየኸኝም። ይሄን ሁሉ ወሬ ሳወራህ እንኳን ቀና ብለህ ቀይ ልሁን ጥቁር አላስተዋልከኝም።እንብላን ብታውቅ ታየኝ ነበር።
ወጣቱ አሁን አያቸው….የተቀየመ ያዘነ ሽማግሌ ፊት ተጋረጠበት፡፡
‹በአዛውንቶች ልብ ውስጥ ያለችውን ጥንታዊቷን ኢትዮጵያ ፈልጋት። እርሷን ስታውቅ አሁንህን ትጠላዋለህ..ድሮነት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ትረዳለህ። እርሷ ለእኔም ለአንተም ለሁላችንም የጋራ እውነት ናት። ሲሉ ተናግረው እጃቸውን ወደ ምግቡ ዘረጉ።
መጽሀፌን ዘግቼ ከራሴ ጋራ ግብ ግብ ገጠምኩ። የሽማግሌው እውነት ውስጤ ዘልቆ ተሰማኝ። ከተናገሩት ውስጥ አንድም ውሸት የለም። እውነት በዛ ቀን ላይ እዛ ቦታ ከእሳቸው ጎን በመቀመጤ ደስ አለኝ። ኢትዮጵያን እንካ ብለው የሰጡኝ ነበር የመሰለኝ…ደግሞም ሰጥተውኝ። እንደሳቸው እውነት የነገረኝ ሰው የለም። በዙሪያዬ ያሉ ብዙ ሰዎች የውሸት ተረት እየፈጠሩ ኢትዮጵያዊነትን የሚያረክሱና የሚያቆሽሹ እንደሆኑ አውቃለሁ፤ እርሳቸው ግን ልዩ ነበሩ። በተቀመጥኩበት ራሴን እንዲህ አልኩት…አንተ እኮ ራስህን ብታውቅ፣ ኢትዮጵያዊነት ምን እንደሆነ ብትረዳ የአለም አይኖች ማረፊያ ነበርክ። በታላቅ ሀይል ተሞልቼ ከወንበሬ ተነሳሁ…ስነሳ ከእንግዲህ በአዛውንቶች ልብ ውስጥ ያለችውን እውነተኛይቱን ኢትዮጵያ ፈልጌ ላገኝ ለራሴ ቃል በመግባት ነበር። ቸር ሰንብቱ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2013