ራስወርቅ ሙሉጌታ
ክፍል ሁለት
ባለፈው ሳምንት እትማችን የማህበራዊ ልማትና አመራር ባለሙያ ከሆኑትና በቲቪ ዘጠኝ የክሊፍ ሞቲቬሽን ወይም አፋፍ ለመድረስ ዝግጅት አዘጋጅና አቅራቢ አቶ ዘላለም ይትባረክ ጋር በነበረን ቆይታ ትኩረት ማጣትን በተመለከተ ያጠናቀርነውን የመጀመሪያ ክፍል ማቅረባችን ይታወሳል። ለዛሬም ሁለተኛውንና የመጨረሻውን ክፍል እነሆ። ትኩረት በመስጠት በኩል ያሉብንን ክፍተቶች ለማስወገድ በቅድሚያ ትኩረት እንድናጣ የሚያደርጉን መሰረታዊ ምክንያቶች እንዲሁም መገለጫ መንገዶቹን ልንለይ ይገባል። በዚህም መሰረት፤
ትኩረት እንድናጣ የሚያደርጉን መሰረታዊ ምክንያቶች፤
1. ፍርሃት፣ ጥርጣሬ፣ ስጋት፣ ጭንቀትና ጉጉት።
2. መረጃ ማግበስበስ።
3. ስራዎቻችንን ቅደም ተከተል ማስያዝ አለመቻል።
4. የሚረብሹንን ነገሮች ማስወገድ ወይም መቀነስ አለመቻል።
ትኩረት ማጣት የሚገለጽባቸው ሁኔታዎች፣
1. ጀምሮ አለመጨረስ፣ ሁሉ አማረሽነት መሆን፤
2. ወላዋይነት ወይም አቋም ማጣት፣ መጽናት አለመቻል ወይም የያዘነውን አለማክበር
3. ጥራት የለሽ ስራ መስራት፣ ግዴለሽነትና ጥድፊያ እንዲሁም የስሉችነት መስተዋል
4. መኪና እያሽከረከሩ መልዕክት በመላላክ ለአደጋ መዳረግ፤ በተለይ የትራፊክ አደጋ፣ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በሰሜን አሜሪካ 25 በመቶ የተሽከርካሪ አደጋ የሚከሰተው መኪና እያሽከረከሩ መልዕክት ከመላላክ ጋር በተያያዘ ነው። በዚሁ አገር በዓመት 1.6 ሚሊዮን አደጋዎች ይከሰታሉ፤ 330 ሺህ ሰዎች አካል ጉዳተኛ ሲሆኑ በየቀኑ 11 ወጣቶች ይሞታሉ። በተያያዘም መኪና እየነዱ ቴክስት የሚያደርግ ሰው በስካር ሆኖ ከሚያሽከረክር ሰው ይልቅ 6 እጥፍ ለአደጋ ይጋለጣል። እንዲሁም መኪና ማሽከርከር ቴክስት ማድረግ ለ5 ሴኮንድ አይንን ጨፍኖ እንደማሽከርከር እንደሆነ ጥናቶች ይናገራሉ።
ትኩረት ለማድረግ የሚረዱን ብልሃቶች፤
1. ራስን መለየት፡-
መለየት* (ሲጠብቅ) ብቻ ከሆነ ከውጭ ካለው ከአካባቢ ሲሆን ከራስ መለየት* (ሲላላ) ሲሆን ግን ከውጭ በተጨማሪ ከውስጥ ከስሜትና ካልፈለግነው ሃሳብም ጭምር ይሆናል። ውጭንም ሆነ ውስጥን ዝም በማስባል የሚያስፈልገን ላይ ብቻ ማተኮር እንደማለት ነው። ይህም አዕምሮን ካልተፈለገ ሃሳብ ነጻ በማድረግ፣ ሃሳብን በትኩረታችን ላይ ማድረግ መቻል፣ ተመስጦን ያካትታል።
2. መምረጥ መቻል፡-
ዶክተር ዘመኑ ማሞ “ትኩረት” በሚለው መጽሐፉ ላይ እንዳሰፈረው “በአሁኑ ጊዜ አንድን ዓለም አቀፍ ተነባቢነት ያለውን ጋዜጣ አንብበን የምናገኛቸው መረጃዎች ብዛት ከመቶ ዓመታት በፊት አንድ ሰው በአንድ ዓመት ከሚያገኛቸው መረጃዎች ይበልጣል።” ስለዚህ መረጃን ከመረጃ እንዴት መምረጥ እንደሚኖርብን ልናውቅ ይገባል።
የሚያስፈልገን፣ የወደድነውን ወይም የፈቀድነውን ሆነን መኖር የሚያስችለን በትኩረት ውስጥ መምረጥ ስንችል ነው። በእውቀት፣ በተሞክሮና በምክንያት ውስጥ መምረጥ የምንችል ከሆነ የመረጃ አይነትና ብዛት አያስጎመዠንም፣ አይነዳንም። ምክንያቱም ለመምረጥም የሚያስችል ትኩረት ስለምናገኝ እና በመምረጥ ውስጥ ደግሞ የትኩረት ጊዜ ስለምናገኝ ነው። ስለዚህ ግዴታዎቻችን እና ውዴታዎቻችን መምረጥ መቻል ይኖርብናል።
ስንመርጥ የመጣው ሁሉ አይነዳንም፤ ይህም ማለት ከሁኔታ በላይ መሆን እንደማለት ነው። ልክ እንደንስር ከደመና በላይ በመሆን ዝናቡን ሲያሳልፍ ሌሎች አእዋፋት ግን ዝናብን ለማለፍ ይጠለላሉ። ደግሞም ካልመረጥን መረጃ-መር፣ ስሜት-መር እና ቁስ-መር እንሆናለን። ህይወት ደግሞ የሁለትዮሽ ምርጫ ናትና መምረጥ ከቻልን እየመረጥን፣ ካልቻልን ደግሞ እየተመረጠልን እንኖራልን እንደማለት ነው። እናም ድህነትም ሆነ ብልጽግና፤ ምቾትም ሆነ ጉስቅልና የመረጥነው እንጂ ይዘነው ያልተፈጠርነው ስለሚሆን ቢል ጌት “ደሃ ሆኖ መወለድ ሳይሆን ደሃ ሆኖ መሞት ነው ሃጢያቱ!” እንዳለው ማለት ይሆናል።
እንዲሁም ከመማር ማስተማር ሂደት አንጻር ስንመለከተውም የተማሪዎችን ውጤታማነት ከሚዋጉ ተጠቃሽ እንቅፋቶች መካከል ዋነኛው ትኩረት መስጠት አለመቻል ወይም የትኩረት መበታተን ሆኖ እናገኘዋለን። ብዙ ግዜ እንደሚስተዋለው አንዳንድ ተማሪዎች ትምህርት ቤት መማሪያ ክፍል ተቀምጠው ትኩረት ማድረግ ስለማይችሉ በሀሳብና በስሜት ሌላ ቦታ ሆነው ይገኛሉ።
በዚህ ግዜ የሚሰጥ ትምህርትን ቢሰሙትም ቢያዩትም ትኩረት ስለማያደርጉ የሚያውቁትም የሚያስታውሱትም ነገር አይኖራቸውም። በመሆኑም በዚህ ረገድ የትምህርት ቤቶችና የመምህራኖች ሚና ሊሆን የሚገባው ትኩረት እንዲያደርጉ ከማነቃቃት ባለፈ ስለ ትኩረት የቡድን ውይይት ተማሪዎቻቸው እንዲያደርጉ ማለማመድ ይሆናል። እንደ አጠቃላይም ትኩረት በማድረግ ወደ ዓላማችን መገስገስ ስለምንችል ትኩረት በእያንዳንዷ እንቅስቃሴያችን ትኩረት ስለማድረግ እያሰብንና እየተገበርን ልንሄድ ይገባል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2013