የደቡብ ኮሪያ ፍርድ ቤት ክብደት በመጨመር የግዴታ የውትድርና ሥልጠና ለማምለጥ ሞክሯል ያለውን ግለሰብ ጥፋተኛ ሲል ወሰነበት። የደቡብ ኮሪያ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የ26 ዓመቱ ግለሰብ የአካል ብቃት መለኪያ ጊዜው ሲደርስ ያገኘውን ጠራርጎ በመብላት ክብደት ጨምሯል ሲል የሴዑል ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ብሎታል።
ሰውዬው ክብደቱ ከመጠን በላይ በመሆኑ ምክንያት ከውትድርና ውጭ በሆኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሲያገለግል ቆይቷል። ግለሰቡ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የአንድ ዓመት ቅጣት ተላልፎበታል። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሌላ ጥፋት አጥፍቶ ከተገኘ እስር ሊጠብቀው ይችላል ማለት ነው።
በቀን የሚመገበውን ምግብ መጠን እጥፍ በማድረግ ክብደቱን እንዲጨምር የመከረው ጓደኛው ደግሞ የስድስት ወራት ቅጣት ተፈርዶበታል ሲል ኮሪያን ሔራልድ ዘግቧል። ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ እና አካላዊ መሥራት የሚችል ኮሪያዊያን በመከላከያ ሠራዊት ለ18 ወራት የማገልገል ግዴታ አለባቸው።
ግለሰቡ መጀመሪያ ለወታደራዊ ሥልጠና ሲመዘገብ አካላዊ ብቃቱ ለሥልጠናው ብቁ የሚያደርገው ነበር። ነገር ግን ባለፈው ዓመት ለመጨረሻ ፈተና በተጠራ ጊዜ ክብደቱ 102 ኪሎ ግራም ደርሶ ስለነበር ነው ከሥልጠናው የታገደው። ደቡብ ኮሪያ በየትኛውም ጊዜ ከሰሜን ኮሪያ ጥቃት ሊቃጣብኝ ይችላል በማለት ነው ዜጎች የግዳጅ ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ የምታደርገው።
ቢሆንም በኦሊምፒክ ሜዳሊያ ያመጡ፤ ሙዚቀኞች እና ሌሎች ሀገራቸውን ያስጠሩ ኮሪያዊያን ሥልጠናው ሊያልፋቸው ይችላል። ደቡብ ኮሪያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ ባለቤቷ ሰሜን ኮሪያ የሚመጣን አደጋ ለመከላከል በሚል በተለያዩ ጊዜያት የጋራ ወታደራዊ ሥልጠናዎች ያደርጋሉ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም