አዲስ ዘመን ድሮ

ስለትናንትን ሲነገር እንደ አዲስ ዘመን ያለ የታሪክ ማጣቀሻና ታሪክን ሰንዶ ለትውልድ አውራሽ አይገኝምና ታሪክ ነጋሪውን ካደመጡ ወጉ እልፍ ነው። “አዲስ አበባ ያብባል ገና” ይላልናም ከ1964ዓ.ም ገደማ ከታየው የማበብ ሰበዝ ለአብነት አንዱን ያሳየናል። በሌላ በኩል ደግሞ መቀሌን በጨረፍታ ምስል ያስቃኘናል። ከፓርላማው አዳራሽ ውስጥ የሆነው ነገርም ምን ነካቸው ሊያስብለን ነው። እጥር ምጥን ካሉት የጳውሎስ ኞኞ ደብዳቤዎች መካከልም ለራሱ ከተጻፉት ሁለቱን እናስታውሳለን።

አዲስ አበባ ያብባል ገና

የአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ጥቂት ዓመቶች ውስጥ ከፍ ያለ የዘመናዊነት መሻሻል አድርጋለች። ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት አዲስ አበባ ከተማን ያየ ሰው ዛሬ እንደገና ተመልሶ ሲመለከት በተደረጉት ከፍተኛ የእድገት ለውጦች በጣም ይደነቃል። በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመቶች ውስጥ ያሳየችው የመሻሻል ለውጥ የሚደነቅ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ በየጊዜው ለሚደረገው የልማት እንቅስቃሴ የአዲስ አበባ ከተማ ዓይነተኛ ምስክር ነች።

ከተማይቱ የተቆረቆረች ጊዜና ከዚያም በኋላ ያደረገችው እድገት የጊዜውን እንጂ ዘመናዊውን ፕላን ያልተከተለ ስለነበረ ዛሬ ማዘጋጃ ቤቱ ባሉት በቂ የተማሩ ሰዎች ከተማይቱ ወደ አዲስ ዘመናዊ ይዞታ ተለውጣለች።

በመንገድ ረገድም በየቀበሌው አዳዲስ መንገዶች በየጊዜው በመከፈታቸው የከተማይቱን መልክ ለውጠውታል።

ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት በከተማይቱ የነበሩት መኪናዎች 20 ሺህ ሲሆኑ ዛሬ ግን ወደ 50 ሺህ ደርሰዋል። ለምሳሌ ያህል የቸርችል ጎዳናን በዘመናዊ ሁኔታ ለማሠራትና ለማስፋፋት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሲደረግበት፤ አዲስ ለሚሠሩት የመስፍን ሐረር መንገድና ለቄራ መንገድ በጠቅላላው ከሁለት ሚሊዮን ተኩል ያላነሰ ወጪ ተመድቧል።

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 14 ቀን 1964ዓ.ም)

መቀሌ ውብና ታሪካዊት ሰሜናዊ ከተማ ናት

የትግሬ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው መቀሌ ወለል ባለ ሜዳ ላይ እየተስፋፋች የምትሔድ መዲና ስትሆን በስተ ምሥራቅ ደቡብ በኩል የእንዳ ኢየሱስ ተራራ በኃይለኛ አውሎ ነፋስ ይከልላታል። ዙሪያውን በተራራ ባለመከበቧ ከተማዋ ነፋሻ ናት።

የአብርሃ ሕንጻ በብዙዎቹ እንደሚጠራው ታላቁ የከተማው ሆቴል በመሆን “የመቀሌ ሒልተን” የሚል ስም ተሰጥቷታል።

የትግሬ ሕዝብ ባሕላዊ ለውጥን በቀላሉ የሚቀበል አይመስልም። ብዙ ዘመናዊያን በሚታዩበት በመቀሌ ከተማ እንኳ ሴቶች በጥንታዊ የፀጉር ሥራ ማለት ሹርባ ተውበው ከዚያ ከሚያምረው ፀጉራቸው ላይ ቀጭን ኩታቸውን ጣል አርገው ይሔዳሉ። ወንዶችም ብዙዎቹ ጥንታዊውን ግማሽ ተፈሪ ሱሪ ቅድ ታጥቀው ሲታዩ፤ የዘመኑን አለባበስ ተቀብለናል የሚሉትም ካማረው ሱፍ ላይ ኩታ ደርበው ይታያሉ።

ሆኖም እንደኔ ላለ ከአዲስ አበባ የዘመናዊ ሥልጣኔ ደቀ መዝሙር ነኝ ብላ የምታምን ወጣት አጭር ልብስ ለብሳ ብትንሸራሸር የተቃውሞ ድምጽ የሚያሰማ የለም። ምናልባት የመቀሌ ከተማ ሰዎች የራሳቸውን የአለባበስ ባሕል እንደሚጠብቁ ሁሉ ሁሉም በየፊናው እንደፈለገው ይሁን የሚል ፍልስፍና ይከተሉ ይሆን?

( አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 1964ዓ.ም)

ከፓርላማ

የሕግ መምሪያ ምክር ቤት በየሳምንቱ እንደተለመደው ሁሉ ትናንት ከአማካሪዎች በቀረቡት የሕዝብ ጉዳዮች ለመነጋገር ተሰባስቦ ሳለ፤ በአንዱ አባልና በሰብሳቢው ፕሬዚዳንት መካከል በአንዳንድ ጉዳይ ላይ በተፈጠረው ክርክርና አለመግባባት ምክንያት በፀጥታ ሊሠራ ስላልቻለ፤ የዕለቱ ጉባኤ ተበትኗል።

ምክር ቤቱ እንዲነጋገርባቸው ሃሳብ ካቀረቡት አባሎች አንዱ በሆኑት በተከበሩ አቶ ዘውዴ በዳዳ የደቡብ አዲስ አበባ ሕዝብ እንደራሴና በዕለቱ ሰብሳቢ ፕሬዚዳንት መካከል በምክር ቤቱ ውስጥ በተፈጠረው አለመግባባትና ክርክር፤ የዕለቱ ስብሰባ የተበተነ መሆኑን ሰብሳቢው ፕሬዚዳንት የተከበሩ አቶ ተክሊት መኮንን አስታውቀዋል።

በተከበሩት አቶ ዘውዴ በዳዳና በሰብሳቢው ፕሬዚዳንት መካከል አለመግባባት የተፈጠረው፤ ፕሬዚዳንቱ የሰጡትን ውሳኔ አማካሪው ጉባኤው ካልወሰነ በቀር የፕሬዚዳንቱን ትእዛዝ አልቀበልም በማለታቸው ነው። ሆኖም በዚሁ ምክንያት ምክር ቤቱ ውስጥ ፀጥታ በመታጣቱና ጉባኤውን ለመምራት ስላልተቻለ፤ የዕለቱ ስብሰባ እንዲበተን የተደረገ መሆኑ ታውቋል።

(አዲስ ዘመን ሰኔ 18 ቀን 1964ዓ.ም)

አንድ ጥያቄ አለኝ

-ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ

*ስምህን እንጂ መልክህን የማያውቅ ብዙ ነው። ስለዚህ አጠገባቸው መሆንህን ሳያውቁ ስላንተ

አንሥተው ሲያሙህና ሲያመሰግኑህ አጋጥሞህ ያውቃል?

ከፈለው አርጋው

-ብዙ ጊዜ ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ “ና ጳውሎስን እናሳይህ” እያሉ ሲያንከራትቱኝ የሚያድሩ አሉ። አንዳንዱም የአደባደቡን ሁኔታ እንዲህ አድርጌ ደበደብሁት እያለ ለኔው ለራሴ አጫውቶኛል። እንዲህ ዓይነቱን ባወራው ብዙ ዓምድ ይፈጃል። ብዙ ወሽካቶች አሉ።

*ሚያዝያ 24 ቀን በወጣው ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ላይ አቶ ኑሬ በፈቃዱ የተባሉ የማዘጋጃ ቤት ሠራተኛ ስለደመ መራራ ቴያትር በሰጠኸው ትችት የሰጡትን መልስ አንብቤአለሁ። አንተ በአማርኛ እንደጻፍከው በአማርኛ በሚወጡት ጋዜጦች ቢጽፉ ምን ይጎድላቸው ነበር? ምናልባት ኢትዮጵያዊ ሆነው አማርኛ የማይችሉ ከሆነ፤ ያንተን ትችት አንብበው እንዴት ለመረዳት ቻሉ? ወይስ የማያውቁት ሀገር ከሚናፍቋቸው ሰዎች አንዱ ሆነው? አስተያየትህን እጠብቃለሁ።

አብደላ መሐመድ(ከጎንደር)

-ግራ ለማጋባት ነው። ስለኔ አርቲክል ምንም ነገር የማያውቁት ፈረንጆች የምን ሕልም ነው ብለው እንዲሉ ካልሆነ በስተቀር ምናለ የኔን ያነበቡ ጥፋቴን እንዲያውቁልኝ ለአነበቡት ቢጻፍ? ግን ጽሑፉ የማይረባ መሆኑን ያወቅሁት “ያንባቢን ጊዜ አባከንክ” ተብዬ መወቀሴን ሳይ ነው። ምክንያቱም የኔ ጽሑፍ ጊዜ ማባከን ሳይሆን ብዙ ትምህርት የነበረበት ነውና ነው። ብዙ ነገሮች የተፈለሰፈበትን ጊዜና የፈልሳፊውንም ስም ይነገር ነበርና ነው።

(አዲስ ዘመን ሰኔ 24 ቀን 1964ዓ.ም)

 

 

ሙሉጌታ ብርሃኑ

 

 

አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You