ህልምን የመከተል ውጤት- የወጣት ሥራ ፈጣሪዋ ስኬት

ነገዋን ብርሃን ለማድረግ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ትታትራለች። እይታዋን ከፊቷ የሚታያት ብሩህ ቀን ላይ አድርጋ ተስፋ መቁረጥን ‹‹ዞር በል!›› ብላዋለች። ምክንያቱን ነገን በስኬት እንድትፈካ ዛሬን ተስፋ ማድረግ የግድ ይላታል። ለዚህ ደግሞ ጠንክራ መሥራት እንዳለባት ታውቃለች።

በልጅነቷ በእግሯ ላይ በገጠማት አደጋ የአካል ጉዳት አጋጥሟት ነበር። በህክምና ቀዶ ጥገና ብታደርግም አሁንም ረጅም መንገድ ስትራመድ የህመም ስሜቱ አብሯት ዘልቋል። በዚህ ፈተና ግን አልተሰበረችም፤ የአካል ጉዳቷ የአዕምሮ ስብራት ሳይሆንባት፤ የ”ይቻላል” መንፈስ በልቧ ተጭሮ ይበልጥ አጠነከራት እንጂ ተስፋ አላስቆረጣትም። ፈተና ከሚያጠነክራቸው እንጂ ከሚሰብራቸው ወገን አይደለችም።

ትናንት በተስፋ መነፅር አሻግራ ወዳየችው ታላቁ መዳረሻዋ ለመድረስ ዋናውን መንገድ አግኝታ ጉዞ ጀምራለች። የራሴ የምትለውን ሥራ ከመሥራትም ባለፈ፤ በተወሰነ ደረጃ ሌሎችን ቀጥራ ታሰራለች። ለዚህ ያበቃት ወደኋላ ከሚጎትታት እኩይ ሃሳብ ይልቅ ተስፋና ጥንካሬን የሚያጎናጽፋትን የመበርታት እሳቤ መርጣለች። ለዚህ ነው የዝግጅት ክፍላችን የዛሬው የሴቶች ገጽ እንግዳ ሊያደርጋት የወደደው።

ወጣት ብርሃን ቀነአ ትባላለች፤ የተለያዩ የቆዳ ቦርሳዎች፣ ጫማዎች እና ሌሎች በቆዳ የሚሰሩ እቃዎችን ታመርታለች። የተወለደችው ወሊሶ አካባቢ ቢሆንም፤ በአዲስ አበባ ከተማ ከዘመዶቿ ቤት ነው ያደገችው። የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰደች ቢሆንም፤ እንዳለመታደል ሆኖ ዩኒቨርሲቲ ሊያስገባት የሚችል ውጤት አላመጣችም። በዚህ ምክንያት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ገብታ መማር የግድ አላት። በዙሪያዋ ያሉ ሰዎች ሌሎች የትምህርት ዓይነቶችን ብትማር የተሻለ እንደሚሆን ቢመክሯትም የልቧን ፍላጎት ለማስቀደም ግን አላመነታችም።

“የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ምኒልክ ትምህርት ቤት ነበር የተማርኩት። እንዳጋጣሚ ሆኖ የማትሪክ ውጤት አልመጣልኝም›› የምትለው ወጣት ብርሃን፤ ወዲያው ቴክኒክና ሙያ ገብታ ለመማር እንደወሰነች ትናገራለች። ነገር ግን ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቱ በቆዳ ዘርፍ እንደሚያስተምር አታውቅም ነበር። ለምዝገባ ስትሄድ የስልጠና ዓይነቶችን አሳይተው ሲያስመርጧት ግን ሥልጠናው መኖሩን ተረዳች። በቆዳ ዘርፍ ለመማር ብትመርጥም መምህራኑ ግን ውጤቷ ጥሩ ስለነበረ ማኔጅመንት፣ አካውንቲንግና ሌሎች የትምህርት ዓይነቶች እንድትመርጥ ስለፈለጉ ምክር ሰጧት። ነገር ግን እሷ የቤተሰቦቿን ሃሳብ ነበር ለመቀበል የፈለገችው። በቆዳ የሙያው ዘርፍ እንድትማር የሰጧትን ሃሳብ ተቀብላ ለመቀጥል ወሰነች።

የሥራ ፈጣሪዋ ወጣት ብርሃን በቴክኒክና ሙያ በደረጃ አራት በቀን ፕሮግራም እየተማረች በማታ ፕሮግራም ደግሞ አካውንቲንግ በዲፕሎማ አጠናቀቀች። ከሙያ በተጨማሪ አካውንቲንግ መማሯ በንግድ ሥራዋ ላይ የሂሳብ ሥራዎችን በራሷ እንድትሰራ እንደረዳት ትናገራለች።

ወደ ሥራው እንዴት እንደገባች የምትናገረው ወጣት ብርሃን፤ ተመርቃ ከወጣች በኋላ ተቀጥራ መሥራት ብትጀምርም የምታገኘው ደመወዝ ዝቅተኛ ስለነበር ግራ መጋባት ውስጥ ነበረች። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ነበር በግሏ ለመሥራት የወሰነችው።

“የሥራውን ሂደት ጀመርኩና ለመንግሥት አካላት የመሥሪያ ቦታ እንዲሰጠኝ ጥያቄ አቀረብኩኝ›› በማለት እንዴት ወደ ሥራው እንደገባች የምትናገረው ወጣት ብርሃን፤ ጥያቄዋ በተማረችበት የትምህርት ዘርፍ ለመሥራት እንደነበር ተናገራለች። የተግባር ፈተናውን አልፋ ስለነበርና የትምህርት ውጤቷም ጥሩ በመሆኑ ጥያቄዋ ተቀባይነት እንዳገኘ ትናገራለች። እነሱ ከተቀበሏት በኋላ ለማሽን መግዣ፣ የቆዳ መቁረጫ እና የቆዳ ጥሬ እቃ ለመግዛት ገንዘብ ስላጠራት ቀጥታ ወደ ሥራው ለመግባት ጊዜ ወስዶባት ነበር።

ምንም እንኳን የመሥሪያ እቃዎችን ለመግዛት የገንዘብ ችግር ቢገጥማትም፤ ለተስፋ መቁረጥ ምክንያት እንዲሆናት አልፈቀደችም። ገንዘብ ለማግኘት የአበዳሪ ተቋማትን በር ማንኳኳት ጀመረች። እነሱም ፊት ሳይነሷት የሚያስፈልጋትን ብር ሰጥተዋት አስፈላጊ እቃዎችን መግዛት ቻለች።

“ብድር የሰጠኝ ተቋም መንግሥታዊም ስለነበር እና እኔም ቦታውን ተቀብዬ አጠቃላይ ሂደቱን አጠናቀቄ ስለነበረ፤ የገንዘብ ብድሩን አልከለከሉኝም። ብሩን ተቀብዬ የተወሰኑ ማሽኖች ብገዛም ወደ ሥራው በደንብ ልገባ የቻልኩት በ2016 ዓ.ም ነው” ትላለች ስለ ሁኔታዋ በዝርዝር ስታስረዳ። ሙሉ እቃውን ለማሟላትም በተጨማሪነት ተቀጥራ ሥራ እንደጀመረች ትናገራለች።

ተቀጥራ ትሰራበት የነበረው ጫማ እና ቦርሳ አምራች ድርጅት ነበር። ከዛ በምታገኘው ገንዘብ የማሽን እዳዋን ትከፍላለች፣ በተጨማሪም የንግድ ፈቃድ አውጥታ ስለነበር ግብርም ትከፍላለች። አንዳንዴ ከምትሰራበት ቦታ ሥራዋን ጨርሳ ስትወጣ ወደ ራሷ መሥሪያ ቦታዋ በመምጣት የኪስ ቦርሳዎችን ትሰራ እንደነበር ትናገራለች።

“ወደ ቆዳ ምርት ውጤቶች ማምረት እንድገባ የተማርኩት ትምህርት በደንብ ጠቅሞኛል ብዬ አስባለሁ። ወደ ትምህርቱ ከመግባቴ በፊት በሀገራችን ጫማና ቦርሳ ይሰራል ብዬ አላስብም ነበር። ወደ ትምህርቱ ከገባሁ በኋላ ግንዛቤውን ሳገኝ እኔም መሥራት እችላለሁ የሚለው ሞራል መጣ። ተቀጥሬ መሥራቴ ደግሞ ሙያውን ለማዳበር የበለጠ ጠቅሞኛል” ስትል ትገልጻለች።

“ሥራውን ሥሰራ አንዳንድ ተግዳሮቶች ይገጠሙኛል” የምትለው ሥራ ፈጣሪዋ፤ ለምሳሌ አንድ ቦርሳ ሰው ላይ ብመለከት ለመሥራት ብፈልግ ቀጥታ እሱን መውሰድ አልችልም ዲዛይኑን ቀይሬ አዲስ ፈጠራ ጨምሬ ነው የምሠራው። ተመሳሳይ ብሠራ ገበያ ማጨናነቅ ነው የሚሆነው እንጂ ምርቱ አይሄድልኝም። ስለዚህ አዲስ ፈጠራ ደግሞ ጊዜ ወስዶ ማሰብ ስለሚፈልግ ትንሽ ያስቸግራል። ” ትላለች።

“አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን ለማግኘት ማህበራዊ ሚዲያዎችን እከታተላለሁ፤ እዛ ላይ ያየሁትን በምን መልኩ ማሻሻል እንዳለብኝ አስቤ እሰራለሁ። ሌላው ደግሞ ከዚህ በፊት እኔ የሰራሁትን ሥራ እመለከትና ፎቶ አነሳለሁ ከዛን ቁጭ ብዬ ምን መጨመር እና መቀነስ እንዳለበት አስብና አዲስ ነገር ለመፍጠር እሞክራለሁ። ” ስትል ትገልጻለች።

“መሥሪያ ቦታ ያለን ቢሆንም በልማት ምክንያት ውስጥ ለውስጥ መንገዶች ስለፈረሱ ምርቶቹን ደርድሮ ለማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው። መሽቶ ወደቤት ስንመለስ እቃዎቹን አንስተን ነው የምንሄደው። ቆዳ በባህሪው ደግሞ መጨማደድ አይፈልግም፤ አንድ ቦታ ተሰቅሎ አቧራውን ማራገፍ ብቻ ስለሚፈልግ ተሰብስቦ አንድ ቦታ ሲቀመጥ ይጨማደዳል” ትላለች።

የቆዳን ባህሪ አውቀው አመስግነው የሚገዙ እንዳሉ ሁሉ ‹‹ዋጋው ውድ ነው›› የሚሉም አይጠፉም የምትለው ወጣት ብርሃን፤ ገበያ ላይ ቆዳ ከመወደዱ ጋር ተያይዞ ደንበኛው የሚፈልገው ዋጋ እና እቃዎቹ የሚቀርቡበት ዋጋ ተመጣጣኝ አለመሆን ሌላኛው ተግዳሮት መሆኑን ታነሳለች።

“ወደ ሥራው ከመግባቴ በፊት ኮሌጅ ያስተማረኝ መምህሬን አማክሬው ነበርና፤ ክፍለ ከተማዬ ባለበት ለመሥራት ባመለክት የተሻለ እንደሚሆን እና ማሽን ለመግዛትም ብድር በቀላሉ ማግኘት እንደምችል መክሮኛል። ሌላው ቆዳ እና ሌሎች ግብዓቶች የት እንደሚገኙ በአካባቢዬ ላይ የሚሰሩ ሰዎችን አጠያይቄ መርካቶ መሆኑን ነገሩኝ። ከዚህ በፊት ተቀጥሬ የምሰራበት አሰሪዬም ቦታውን ወስዶ አሳይቶኛል። ” ትላለች።

ወደ ቆዳ ምርቶች ስትገባ “ግን ይሄን ነገር ትችይዋለሽ?” በማለት የሚጠይቁና ነገሮችን በጥርጣሬ ዓይን እንድትመለከት የሚገፋፉ ሃሳቦች ይቀርቡላት እንደነበሩ በማንሳት፤ ነገር ግን እራስን አሳምኖ ጨክኖ ከተገባበት የማይቻል ነገር አለመኖሩን ትጠቁማለች።

“እውነት ለመናገር እችላለሁ ብሎ እራስን ማሳመን ከተቻለ የማይቻል ነገር የለም። ከማህበረሰቡ የሚነገረውን ሁሉንም ሃሳብ ከተቀበልን ከባድ ነው። ነገር ግን ለራስ ሊጠቅም የሚችለውን ሃሳብ መርጦ መውሰድ ከተቻለ የሚጠቅም ሃሳብም አይጠፋም። ” ስትል ትናገራለች።

አሁን ላይ ከመሥሪያ ቦታዋ በተጨማሪ፤ የተለያዩ ባዛሮች ሲዘጋጁ ምርቶቿን ለእይታና ሽያጭ ታቀርባለች። ተቀጥራ ከመሥራት ወደ መቅጠር በመሻገር ሁለት ሠራተኞችን አንድ በቋሚነት፣ አንድ ደግሞ በጊዚያዊነት ቀጥራ ታሰራለች። የገበያው ተቀባይነት መልካም የሚባል መሆኑን በመግለጽ፤ ምርቶቿን ለጅምላ ነጋዴዎች ታቀርባለች። የበለጠ ግን ባዛሮች ሲዘጋጁ ምርቶቿን በማቅረብ ተጠቃሚ መሆኗን ታስረዳለች።

ብርሃን ሥትሰራ ድካም የሌለባት ነው የሚመስለው፤ ደከመኝ እንቅልፌ መጣ ሳትል በምሽት ቦርሳም ሆነ ጫማ ሥትሰራ ነው የምትቆየው። በተለይ ደግሞ የተሰጣት ትእዛዝ ካለ ደንበኞቿን ላለማስከፋት ሌሊቱን ሙሉ ሥትሰራ ነው የምታድረው። ጠዋት ተነስታ ወደ ሱቅ ትወስዳለች። ምክንያቱም ለተሻለ ነገዋ መንገድ ከፋቹ ሥራና ሥራ ብቻ እንደሆነ ገብቷታል።

ቀጣይ እቅዷ ከዚህ የበለጠ በመሥራት አሁን የምትሠራበትን ቦታ በማስፋፋት፤ አሁን ቀጥራ ከምታሠራቸው ሠራተኞች በተጨማሪ፤ ሌሎች ሠራተኞችን በመቅጠር ምርት በስፋት አምርታ ወደ ውጭ ሀገራት የቆዳ ምርቶችን የመላክ ፍላጎት እንዳላት ታስረዳለች።

“ይህንን ህልሜን ለማሳካት ቦታ እና ገንዘብ በጣም አስፈላጊ ናቸው። በዚህ ረገድ አበዳሪ ተቋማት ብድር ማቅረብ ቢችሉ መልካም ነው። ሌላው ነገር ደግሞ ደንበኞችን ማግኘት ወሳኝ ነገር ነው። ምክንያቱ ምርቱ ከተመረተ በኋላ የሚገዛ ደንበኛ በስፋት ካለ ማደግ የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም” ትላለች።

ምርቶቿን ለማስተዋወቅ ባዛሮች ላይ ከማቅረብ ባለፈ፤ አንዳንድ ሥልጠናዎች ሲዘጋጁ ራሷን ለማስተዋወቅ መንገዶችን የምታገኝ ሲሆን፤ አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በተወሰነ መልኩ ለመጠቀም ትጥራለች።

እንደ ወጣት ብርሃን ሃሳብ ወደ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ገብቶ መማር በጣም ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም የእጅ ሙያ መማር ያስችላል። ይህ ደግሞ ሙያው ከራስ ጋር ለዘላለም የሚቀር የትም ብሄዱ ከራስ ጋር የሚቆይ ነው።

ይህ ሁሉ ነገር ሊሆን የሚችለው የግል ጥረት የበለጠ ሲኖር ነው። የማህበረሰቡን አንዳንድ አሉታዊ ሃሳብ በመስማት ተስፋ መቁረጥ ካለ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ የራስ አዕምሮ የሚለውን በማዳመጥ የማህበረሰቡን ሃሳብ ደግሞ መርጦ የተሻለውን መውሰድ አስፈላጊ ነው።

አብዛኞቻችን ሌሎች ስለመከሩን ብቻ የማንፈልገውን ትምህርት ነው የምንማረው። ከዚህ ይልቅ ውስጣችን የሚፈልገውን እንወቀው በዛ ለመቀጠል እንሞክር። ምክንያቱ አንድ ሰው ወዶት የሚማረው ትምህርት ሲሆን፤ በሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ለመልፋት አይቸገርም። ሁሉም በተማሩበት ትምህርት በደንብ ቢሰሩ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ትናገራለች።

እንደ ወጣት ብርሃን ገለፃ ኢትዮጵያ የእንስሳት ቆዳ በመላክ ታዋቂ ብትሆንም፤ እሴት ጨምሮ የቆዳ ምርቶችን በመላክ ረገድ ብዙም አልተሰራም። አሁን አሁን በተደረጉ ማሻሻያዎች ለውጦች እየታዩ ቢሆንም ገና ብዙ መስራትን ይጠይቃል። የተወሰኑ ምርቶች እየተላኩ ነው ያለው። እናም በዚህ ዘርፍ መሥራት ከተቻለ ከራስ አልፎ ሀገርንም ለመጥቀም እድል አለው።

ወጣት ብርሃን የግል ሥራ ስትጀምር ባጋጠማት ፈተና አልተንበረከከችም። ውጣ ውረዱ ሥራውን ትታ ተቀጣሪነትን እንድትመርጥ አላስገደዳትም። ይልቁኑ ፈተናዎቹን ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይራቸዋለች። “እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ሲጠነክሩ ለምን ይህን ያህል አለፋለሁ የሚል ሃሳብ ይመጣል። ነገር ግን ከጎኔ አይዞሽ ይሄን ብትሰሪ ይሄ ይሆናል እያሉ የሚያበረታታ አይጠፉም። የእነሱን ማበረታቻ ቃል ስሰማ ደግሞ እበረታለሁ”ትላለች። ላጋጠማት ሁኔታ የሰጠችውን መፍትሔ እያብራራች።

ወጣት ብርሃን የእርሷ መለወጥ ሌሎች ዜጎችንም፣ ሀገርንም እንደሚጠቅም ታምናለች። በዚህ ምክንያት አሁን ካለችበት በተሻለ መሥራትን ትሻለች።

ከመንግሥትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ማሽን ለመግዛት ብድር ቢመቻችላት፤ ከምንም በላይ ደግሞ ምርቶቿን የምትሸጥበት ቦታ ብታገኝ ከዚህም በተሻለ ውጤታማ እንደምትሆን ታምናለች። ይህንን ጥያቄዋን መንግሥት ምላሽ እንዲሰጣትም ትጠይቃለች።

በመጨረሻም አሁን ላይ ምርቶችን ወደ ክፍለ ሀገር ለመውስድ በአንዳንድ ቦታዎች የሚከሰቱ የጸጥታ መደፍረስ ተግዳሮት በመሆናቸውና ለሁሉም ነገር ሰላም አስፈላጊ በመሆኑ ለሀገሯ ሰላምን እየተመኘች፤ በመጨረሻም ሥራዋን በምትሠራበት ወቅት በሃሳብም ሆነ በጉልበት ለደገፏት ምስጋናዋን አቅርባለች።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You