የዲ ኤች ኤል የጭነት አውሮፕላን በሊዩቲኒያ ተከስክሶ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ በሦስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል። ቦይንግ 737-400 የጭነት አውሮፕላኑ ከጀርመን ሌፕዚሽ ከተማ ተነስቶ በሉቱኒያ ዋና ከተማ ወደሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ሲቃረብ ነው በአቅራቢያው በሚገኝ አንድ ቤት ላይ ተከስክሶ አደጋው የደረሰው።
የሀገሪቱ ባለሥልጣናት የአደጋው መንስኤ እስካሁን አለመታወቁን ገልጸዋል። በተከሰከሰበት ቤት ዙሪያ ያሉ መሠረተ ልማቶች በእሳት የተጎዱ ቢሆንም፤ በአካባቢው ያሉ ሰዎችን ማትረፍ መቻሉን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ በኋላ በእሳት የተያያዘ ሲሆን አንድ የበረራ ቡድኑ አባል ሕይወቱ ማለፉን የሊዩቲኒያ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ሲኤንኤን ዘግቧል። አብራሪውን ጨምሮ ሶስት የበረራ ቡድኑ አባላትም ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጿል። ከጀርመኗ ላይፕዚሽ የተነሳው የጭነት አውሮፕላን የተከሰከሰበት መንስኤ እየተጣራ መሆኑንም የሊዩቲኒያ የብሄራዊ አደጋ አስተዳደር ኃላፊው ቪልማንታስ ቪልካውካስ ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ ከመከስከሱ አስቀድሞ ፍንዳታ እንደገጠመው የሚያመላክቱ ጉዳዮች እስካሁን ሪፖርት አለመደረጋቸውንም ነው ለሀገሪቱ ብሔራዊ የዜና አገልግሎት ኤልአርቲ የገለጹት። በአውሮፕላኑ ከተገጨው መኖሪያ ቤት ውስጥ 12 ሰዎችን ለማስወጣት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ርብርብ ማድረጋቸው ተሰምቷል። የቪሊኒየስ አውሮፕላን ማረፊያ የእሳት አደጋ ሠራተኞች በእሳት የተያያዘው አውሮፕላን ሙሉ በሙሉ እንዳይወድም ጥረት እያደረጉ ነው ተብሏል።
አደጋው በቪሊኒየስ ኤርፖርት የበርካታ አውሮፕላኖች የመነሻ ሰዓት እንዲጓተት ማድረጉ ቢገለጽም የአውሮፕላን ማረፊያው ቃል አቀባይ ግን ሁሉም በረራዎች በተያዘላቸው ሰዓትት ቀጥለዋል ሲል አል ዐይን ገልጿል።
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም