በናይጄሪያ ዋና ከተማ አቢጃን አስተናጋጅነት ለሁለተኛ ጊዜ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የአፍሪካ ጦር ኃይሎች (ሚሊታሪ) ስፖርት ፌስቲቫል ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባለች። ሃምሳ አለቃ ወርቅውሃ ጌታቸው ሜዳሊያውን ያጠለቀች አትሌት ነች። በውድድሩ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ የጦር ኃይሎች እየተሳተፉ ሲሆን ኢትዮጵያ በመቻል ስፖርት ክለብ አማካኝነት ተወክላለች።
ውድድሩ ከኅዳር 11 ጀምሮ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ናይጄሪያ እየተካሄደ ሲሆን፣ በዋና ከተማዋ አቢጃን የሚገኘው ሞሾድ አብዮላ ናሽናል ስታድየም ፉክክሮችን እያስተናገደ ይገኛል። ኢትዮጵያ በመቻል ስፖርት ክለብ በመወከል ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን የቻለች ሲሆን እስከ ትናንት ከሰዓት አራት ሜዳሊዎችን ሰብስባለች። በአትሌቲክስ ስፖርት እየተሳተፈ የሚገኘው መቻል፣ በአትሌት ሃምሳ አለቃ ወርቅውሃ ጌታቸው አማካኝነት የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አሳክቷል።
አትሌት ሃምሳ አለቃ ወርቅውሃ ጌታቸው በ 5 ሺ ሜትር ውድድር አሸናፊ የሆነችው በውድድሩ ጠንካራ ፉክክር በማድረግና በጥሩ ብቃት ተፎካካሪዎችን በመርታት ነው። ሌላኛዋ አትሌት ሃምሳ አለቃ አያልፍም ዳኛቸው በዚሁ ውድድር የብር ሜዳሊያ ማሳካት ችላለች።
በተጨማሪም በሜዳ ተግባራት የአትሌቲክስ ውድድሮች የተሳተፉ ሁለት አትሌቶች ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን አስመዝግበዋል። በሴቶች ርዝመት ዝላይ ምክትል አስር አለቃ በፀሎት ዓለማየሁ የብር ሜዳሊያ ስታስመዘግብ፣ በተመሳሳይ በዲስከስ ውርወራ አስር አለቃ ዙርጋ ኡስማን የብር ሜዳሊያ አጥልቃለች። መቻል ስፖርት ክለብ እስከ አሁን በተሳተፈበት አትሌቲክስ ውድድር አንድ የወርቅ እና ሦስት የብር ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ችሏል።
መቻል ስፖርት ክለብ በውድድሩ በአትሌቲክስ ስፖርት እየተሳተፈ የሚገኝ ሲሆን በአጭር ርቀት፣ መካከለኛ ርቀት፣ በሜዳ ተግባራት፣ በረጅም ርቀትና በማራቶን ውድድር እንደሚፎካከር ታውቋል። ክለቡ ለውድድሩ በሀገር ውስጥ ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ፣ አትሌቶችንና አሠልጣኞችን ጨምሮ አርባ የሚደርሱ ልዑካን ቡድን አባላትን አካቶ ወደ ስፍራው አንዳቀና ለማወቅ ተችሏል።
የአፍሪካ ጦር ኃይሎች (ሚሊታሪ) ስፖርታዊ ውድድር በርካታ ስፖርቶችን በማካተት ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በተወጣጡ ሚሊታሪ አትሌቶች መካከል የሚካሄድ ውድድር ነው። የመጀመሪያው የአፍሪካ ሚሊታሪ ስፖርት ውድድር እአአ በ2002 ከዓለም አቀፉ ሚሊታሪ ካውንስልና ከአፍሪካ ሚሊታሪ ስፖርት ተቋም ጋር በትብብር በኬንያ ናይሮቢ አስተናጋጅነት ተካሂዷል። በመጀመሪያው የሚሊታሪ ስፖርት ውድድር 32 ሀገራት የተሳተፉ ሲሆን አራቱ በታዛቢነት ቀርበውም ነበር። አፍሪካ የሚሊታሪ ስፖርት ውድድርን በተለያዩ ስፖርቶች በማሰናዳት የመጀመሪያዋ አሕጉር እንደመሆንዋ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ተካሂዶ የነበረውን ውድድር በርካታ ታዋቂ የፖለቲካና የስፖርት ሰዎች እንደተከታተሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የውድድሩ ዓላማ በአሕጉሪቱ ለሚገኙ የሚሊተሪ ስፖርተኞች የውድድር ዕድል መፍጠር ሲሆን፣ አትሌቲክስን ጨምሮ፣ በቅርጫት ኳስ፣ ቦክስ፣ እግር ኳስ፣ ጎልፍ፣ እጅ ኳስ፣ ጁዶ፣ ውኃ ዋና፣ ቴኳንዶ፣ መረብ ኳስና በሌሎች ስፖርቶች ይከናወናል።
በናይጄሪያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ስፖርት ፌስቲቫል ኢትዮጵያን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ25 የአፍሪካ አገራት የተወጣጡ 1 ሺህ 625 ስፖርተኞች በ 19 የስፖርት ዓይነቶች ተሳታፊ መሆናቸውም ተገልጿል። የስፖርት ፌስቲቫሉ ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን በመጪው ቅዳሜ ፍጻሜውን ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ፌስቲቫሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በኬንያ አስተናጋጅነት ከተካሄደ ከ20 ዓመታት በኋላ በድጋሚ መካሄድ ችሏል።
ውድድሩ በአፍሪካ ውስጥ ለሚገኙ የሚሊታሪ ቡድኖች ያላቸውን ተሰጥዖ ለማሳየት ዕድል እንደሚፈጥር የታመነበት ሲሆን መድረኩ ለስፖርተኞቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመፎካከርና ከተቀሩት የአፍሪካ ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተጠቁሟል። በተጨማሪም በጦር ኃይሉ ውስጥ የአካል ብቃት እና የስፖርት እድገትን ከማጠናከርም በላይ ውድድሩ የአፍሪካ ሀገራትን የግዛት ወሰን ለመጠበቅ በሚደረገው ሥራ ክልላዊ ትብብር እና ውሕደትን ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል።
በዘንድሮው የጦር ኃይሎች (ሚሊታሪ) ጨዋታዎች አልጄሪያ፣ ካሜሩን፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ እና አስተናጋጇ ናይጄሪያ ከተሳታፊ ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም