አስናቀ ፀጋዬ
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ እንሆ አንድ አመት ተቆጠረ።ቫይረሱ ወደ ሀገሪቱ መግባቱ እንደታወቀ በሰፊው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል።በተለይ ደግሞ ቫይረሱ አደጉ በተባሉ አገራት በሚኖሩ ዜጎች ላይ ያስከተለው ሞት፤ ይበልጥ ሽብር እንዲፈጥር አድርጎታል።
ህዝቡ ቫይረሱን በእጅጉ በመፍራቱና አስቀድሞ እንደጭራቅ በመሳሉ ልክ ወደ ሀገር ውስጥ እንደገባ የሚፈልጋቸውን ምግብ ነክና ሌሎች ሸቀጦችን ሸምቶ ወደቤቱ ገባ። አስገዳጅ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ በስተቀር ወደ ስራ ገበታው ላለመሄድም ወሰነ። ወደ ስራ ገበታው የሚሄደውም ያለው ማስክ ገዝቶ የሌለው ደግሞ ጨርቅም ቢሆን ሰፍቶ አፍና አፍንጫው ላይ ማድረግ ጀመረ።
መንግስትም ቫይረሱ ወደ ሀገር ውስጥ እንደገባ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አወጀ።በሃላፊነት ቦታ ላይ ካሉትና በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ከሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞች ውጪ ሌሎቹ በቤታቸው ሆነው ስራዎቻቸውን እንዲያከናውኑ ቀጭን ትእዛዝ አስተላለፈ።አንዳንድ መስሪያ ቤቶችም ለሰራተኞቻቸው የትራንስፖርት ሰርቪስ እስከመመደብ ደረሱ።
የአውቶብስና የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችም ሰው የመጫን አቅማቸውን በግማሽ እንዲቀንሱ ተደረገ።ሁሉም የእምነት ተቋማትም ህዝባቸው ከዚህ መቅሰፍት እንዲጠበቅ ፀሎት ምህላ አደረጉ።በግለሰብ ደረጃም ስለቫይረሱ አንዱ የሌላው አስተማሪ ሆነ።ጤና ሚንስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም የቫይረሱን መከሰት ተከትሎ ህብረተሰቡ ከበሽታው እንዲጠበቅ የክልከላ መመርያዎችንና ህጎችን አወጡ።
በመጀመሪያ አካባቢ ህዝቡ ራሱን ከቫይረሱ ለመከላከል ሲያደርግ የነበረው ጥንቃቄም አጀብ አስባለ።የጤና ሚንስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያወጣቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎችንም ሳይሰለች መተግበሩን ቀጠለ። የጤና ሚንስቴርም በየግዜው በቫይረሱ የሚያዙና የሚያገግሙ ሰዎችን ቁጥር ሪፖርት ማድረጉን አላቋረጠም። የሀገሪቱ የመመርመር አቅም ከግምት ውስጥ ገብቶ በቀን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም አንድ፣ ሁለት እና ሶስት እያለ ገሰገሰ።ህዝቡም የጤና ሚንስቴር የሚያወጣውን ሪፖርት አብሮ መቁጠሩን ቀጠለ።
የጤና ሚንስቴር ለተወሰኑ ወራቶች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ብቻ እያሳወቀ ከቆየ በኋላ የሟቾችን ቁጥርን መናገር ሲጀምር ህዝቡ ይበልጥ መሸበር ጀመረ። አንድ ሁለትና ሶስት ሰዎችም በቫይረሱ ምክንያት መሞት ጀመሩ።ቀስ እያለም በቀን የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ሰባት፣ ስምንት፣ ዘጠኝና አስር ደረሰ። አሁንም ግን ህዝቡ ራሱን ከቫይረሱ ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት አልቀነሰም።
ቫይረሱ ከተከሰተ ከአራትና አምስት ወራት በኋላ ሰዎች ሸምተው ወደ ቤታቸው ይዘውት የገቡት ምግብና ሸቀጥ አለቀ።የቀን ስራ ሰርተው የእለት ጉርሳቸውን የሚያገኙ ዜጎችም ችግር ውስጥ ገቡ።ሌሎች የግል ስራዎችን የሚያከናውኑ ሰዎችና ድርጅቶችም ቫይረሱ በፈጠረባቸው ጫና ባዷቸውን ቀሩ።ሲኒማ ቤቶች፣ ፋብሪካዎች፣ ስፖርታዊ ውድድሮችና ሌሎችም የስራ ዘርፎች በቫይረሱ ሳቢያ ክፉኛ ተጎዱ።
ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ይመስላል መንግስት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን አነሳ። ታክሲዎችና አውቶብሶችም በወንበር ልክ ሰዎች እንዲጭኑ አዘዘ። የመንግስት ሰራተኞችም በቤታቸው ሆነው የሚሰሩት ስራ ቀርቶ በቢሮ እንዲሆን ታዘዘ። አንዳንድ መስሪያ ቤቶችም ለሰራተኞቻቸው መድበውት የነበረውን የትራንስፖርት ሰርቪስ አገልግሎት አቋረጡ። አብዛኛዎቹ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ከአስፈላጊ ጥንቃቄ ጋር ወደነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ በመንግስት በኩል ውሳኔ ተሰጠባቸው።የሰዎች እንቅስቃሴም ወደነበረበት ሁኔታ ተመለሰ።
ከዚህ በኋላ የጤና ሚንስቴር በቀን የሚያደርገውን የኮቪድ 19 ምርመራ መጠን የቀነሰ ቢሆንም በየእለቱ በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ሪፖርት ማድረጉን ግን አላቋረጠም።በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም አሻቀበ።
ገና ቫይረሱ ወደ ሀገሪቱ እንደገባ ከቤቱ ለመውጣት ሲፈራ የነበረውና የተያዙና የሞቱ ሰዎችን በቤቱ ሆኖ ሲቆጥር የነበረው ሰውም ወደ አደባባይ ከወጣ በኋላ ቫይረሱ ስለመኖሩም እየረሳ መጣ።ከጎኑ ሰው ሲሞት አስካላየ ድረስ የበሽታውን አደገኛነት ለማረጋገጥም ተሳነው።አፍና አፉንጫን ድብን አድርጎ ሸፍኖ ሲንቀሳቀስ የነበረውም ያለማስክ መተንፈሱን ተያያዘው።በየአደባባዩ የእጅ መታጠቢያዎችን አይቶ የማያልፈው አስር ግዜ መታጠቡ ሰለቸው።
በጤና ሚንስቴርና በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወጡ አስገዳጅ መመሪያዎችና ህጎችም በግለሰቦችም በመንግስትም መጣስ ጀመሩ። ግለሰቦች የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተው እንዳሻቸው ሲንቀሳቀሱ፤ መንግስትም በርካታ ሰዎችን የሚያሳትፉ ስብሰባዎችን በጠባብ አዳራሽ ውስጥ ሲያካሂዱ መመሪያውም ሆነ ህጉ አልከለከላቸውም።
በግለሰብ ደረጃም ሆነ በመንግስት በኩል ሲታይ የነበረው ቸልተኝነትም ዛሬ ላይ የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አድርጎታል።በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን አግሎ የማቆያ ቦታዎችም በሰዎች ተሞልተዋል።አዳዲስና ነባር የህክምና ቦታዎችም በፅኑ ህሙማን ተጨናንቀዋል። አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያዎችም በህሙማን ሙሉ በሙሉ ተይዘዋል።ለዚህ ስራ የተመደቡ የጤና ባለሞያዎችም ስራ በዝቶባቸዋል።በየቀኑ በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም በከፍተኛ ደረጃ አሻቅቧል።
የጤና ሚንስቴር በሚያወጣቸው መረጃዎች መሰረትም ባልተለመደ ሁኔታ በቫይረሱ ምክንያት በቀን የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ አሻቅቧል።በአንድ ሳምንት ብቻ ከአስር ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎችም በቫይረሱ ተይዘዋል።በአንድ ቀን ብቻ ከሁለት ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎችም የቫይረሱ ሰለባ ሆነዋል። ከተመረመሩ አንድ መቶ ሰዎች ውስጥ ቢያንስ ሃያአምስቱ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለም እየተነገረ ነው። አሁን አሁን ደግሞ የቫይረሱ ስርጭት በክልሎችም ከፍ እያለ በመምጣቱ ችግሩ አሳሳቢ ሆኗል።
መንግስት በቅርቡ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን መከተብ ቢጀምርም ክትባቱ ወደ ሀገር ውስጥ ስለገባ ብቻ የህብረተሰቡ መዘናጋት በእጥፍ ጨምሯል። ይህን ክትባት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ማዳረስ እንደማይቻል ደግሞ የማይታበል ሀቅ ነው።
ከዚህ አኳያ ዜጎች ቆም ብለው የሚያስቡበትና ወደራሳቸው መመለስ ያለባቸው ግዜ አሁን ነው።ቀደም ሲል ራሳቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል ሲያደርጉት የነበረውን ጥንቃቄ አሁንም አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። የአንዱ መጠንቀቅ ለሌላው መድሃኒት ነውና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ራሱን ከበሽታው ለመከላከል የመከላከያ መንገዶችን በየቀኑ ያለመሰልቸት ሊተገብር ይገባል። በዋናነት ደግሞ በጤና ሚንስቴርና በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወጡ መመሪዎችንና ህጎችን ማክበር ይኖርበታል።
ቀጣዩ ግዜ ምርጫ ከመሆኑ አኳያ ህዝቡን የሚያሳትፉ በርካታ የምርጫ ቅስቀሳዎች ስለሚደረጉ መንግስትም በሀላፊነት ስሜት መመሪያዎቹና ህጎቹ ተግባራዊ እንዲሆኑ ቁርጠኛ አቋም ሊኖረው ይገባል።ራሱም ጭምር የሚያካሂዳቸውን ስብሰባዎችና ሌሎች ህዝብን የሚያሰባስቡ ጉዳዮችን መቀነስ ይኖርበታል።
የጤና ሚንስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ያወጧቸው መመሪያዎችና ህጎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ በመንግስት ላይ ግፊት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።መንግስትን ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተባበረ መንፈስ ሃላፊነቱን መወጣት የሚችል ከሆነም ዛሬን በመሻገር ነገን መመልከት ይቻላል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2013