አቅርቦትን በማስፋትና ህገወጥነትን በመቆጣጠር የኑሮ ውድነትን የማረጋጋት ስራ

ዓለም አቀፋዊና አገራዊ በሆኑ በርካታ ምክንያቶች የተነሳ በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት የሸማቹን አቅም በእጅጉ እየተፈታተነው ይገኛል። መንግሥት ይህን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት የተለያዩ መንገዶችን ቀይሶ መስራቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ለእዚህም የኑሮ ውድነቱን ሊያረግቡ የሚችሉ የተለያዩ አማራጮች መንገዶችን እየተጠቀመ ነው።

በተለይም በበዓላት ወቅት ካለው ከፍተኛ የሸቀጦች ፍላጎት ጋር ተያይዞ የምርት እጥረት እንዳይከሰት እንዲሁም ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት እንዳይፈጠር ለማድረግ ገበያን የማረጋጋት ሥራውን አጠናክሯል። በአሁኑ ወቅትም መጣሁ መጣሁ ከሚለው የአዲስ ዓመት በዓል አስቀድሞ የበዓል ገበያውን ለማረጋጋት እየሰራ ነው። ለእዚህም የምርት እጥረት እንዳይከሰትና ህገወጥነትን ለመቆጣጠር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

ሰሞኑን የበዓል ገበያው እንደሚደራ ይታወቃል። ለዚህም በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ከነሐሴ 27 ቀን 2015 ጀምሮ እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ የሚቆይ የባዛር ገበያ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲኖር አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል። ቢሮው ገበያው እንደሚኖር ከመግለጽ ባለፈ የምርት እጥረት እንዳይከሰት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሠራ ስለመሆኑም ነው ያስታወቀው።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንም እንዲሁ በመላው ኢትጵያውያን ዘንድ በድምቀት የሚከበረውን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ የዋጋ ንረት እንዳይከሰትና በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ አብረው እየሠሩ መሆናቸውን በቅርቡ በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ተቋማቱ በመግለጫው እንደጠቀሱትም፤ ከበዓሉ ጋር በማያያዝ አንዳንድ ወገኖች ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉና የኑሮ ውድነቱ ይበልጥ እንዳይባበስ፤ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ለማድረግ ይሰራሉ፤ የገበያ ቁጥጥርና ክትትልም ያደርጋሉ።

ለእዚህም የቅድመ ዝግጅት ተግባሮች መከናወናቸውን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተሻለ በልሁ አስታውቀዋል። ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ በአገሪቱ የኑሮ ውድነት ስለመኖሩ መንግሥት ይገነዘባል፤ የኑሮ ውድነቱ መነሻ ምክንያቶች ውስጣዊና ውጫዊ ናቸው። ለዘመን መለወጫ በዓል የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይገጥም በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

ሚኒስትር ዴኤታው ውስጣዊ ምክንያቶች ተብለው በዋናነት ከተለዩት መካከል ካለው ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ጋር ተያይዞ የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን አንዱ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ያለውን ምርት ለማቅረብም በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር እንቅፋት መፍጠሩን ጠቁመዋል። ይህም ሸቀጦችን በተፈለገው ጊዜና መጠን ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር ምቹ ሁኔታ እንዳይኖር ማድረጉን ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም በተወሰኑ ክልሎች በነበረው የኬላ መዘጋት ምርትን ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር አስቻይ ሁኔታ እንዳልነበር አስታውሰው፣ ይህም የምርት እጥረት እንዲከሰት አርጎ እንደነበር ገልጸዋል። ይህን ችግር መቆጣጠር መቻሉን ነው የገለጹት።

ዓለም አቀፉ ሁኔታም ለኑሮ ውድነቱ መንስኤ መሆኑን ያነሱት አቶ ተሻለ፤ ለአብነትም የዩክሬንና የሩስያ ጦርነት በምርቶች ዋጋ ላይ ጭማሪ ማስከተሉን አመልክተዋል። ኢትዮጵያ የምግብ ሸቀጦችን ጨምሮ በርካታ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ከውጭ የምታስገባ መሆኑ የኑሮ ውድነቱን ዓለማቀፋዊ ጫናም ያለው እንዳረገው ተናግረዋል። እንደ ስኳር፣ ዘይት፣ ሩዝ፣ የህጻናት ወተትና የመሳሰሉት ከውጭ ተገዝተው የሚገቡ በመሆናቸው የዋጋ ንረቱ ዓለማቀፋዊ ግሽበትን በማስከተል የኑሮ ውድነቱን ከፍ እንዲል አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አቶ ተሻለ እንደተናገሩት፤ መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለመከላከልና ገበያውን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። በተለይም ባለፉት ሶስት ወራት በበላይ አመራር የሚመራ ሥራ ለማከናወን ተሞክሯል። ከእነዚህም መካከል የሰንበት ገበያ አንዱ ሲሆን፤ ይህም በየከተሞቹ ተግባራዊ ተደርጎ ሸማቹ በቀጥታ ምርቶችን ከአምራቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዲችል ተደርጓል።

የሰንበት ገበያ በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያለውን ርዝመት ማሳጠር ማስቻሉን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በዚህም አላስፈላጊ የሆኑና ምንም እሴት ሳይጨምሩ ትርፍ ይሰበስቡ የነበሩ አካላትን ከንግድ ሰንሰለት ውስጥ ማስወጣት ተችሏል ብለዋል። በተለይም በእህል ንግድ፣ በቁም እንስሳትና በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ላይ ድለላን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ማስቀረት የተቻለበት ነበር ሲሉ ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ተሻለ ገለጻ፤ ህገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የሚያስችል ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል። በዚህም ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 395 ሺህ በሚጠጉ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ገበያውን ማረጋጋትና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን መቆጣጠር ተችሏል።

መጪው የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ በሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል። በአገሪቱ ካሉት ከተሞች በዋናነት ከፍተኛ ፍላጎትና ብዙ ሸማች ያለው አዲስ አበባ ከተማ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ለዚሁ ገበያ የሚመጥን ምርት ለማቅረብ እየተሰራ ነው ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ 170 በሚጠጉ የእሁድ ገበያዎች ለበዓሉ አስፈላጊ የተባሉ የምርት አይነቶችን በስፋት ለማቅረብ ከህብረት ሥራ ዩኒየኖች ጋር እየተሠራ መሆኑንም ነው አቶ ተሻለ የተናገሩት። ከሕብረት ሥራ ማሕበራቱ ጋር ኮንትራት በመፈራረም ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ እንደ ሽንኩርት፣ የቁም እንስሳትና ሌሎች የምርት አይነቶችን ለተጠቃሚው ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል። በተለይም በከተማ የተደራጁ የሸማች ሕብረት ሥራ ማሕበራት የገንዘብ እጥረት እንዳያጋጥማቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብቻ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ብድር በማመቻቸት ምርቶቹን እንዲያቀርቡ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ሲሉም ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ ስድስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር የብድር አቅርቦት በማድረግ ምርቶች በስፋት እንዲቀርቡ ተደርጓል። ሌሎችም ክልሎች እንደየአቅማቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ብድር በማቅረብ የፋይናንስ እጥረት እንዳይጋጥምና ምርቶችን በበቂ መጠንና በወቅቱ ማቅረብ እንዲቻል ተሰርቷል።

በመንግሥት ደረጃ ዘይትን በተመለከተ ሰፊ አቅርቦት መኖሩን አቶ ተሻለ ጠቅሰው፤ አሁን ገበያ ላይ ካለው ዋጋ በላይ ዋጋው ሊያሻቅብ የሚችልበት ምንም ዕድል እንደሌለው ነው የገለጹት። ስለሆነም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት በሌለው ሁኔታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንደማይኖር ተናግረው፣ በህገወጥ መንገድ የሚፈጠር የዋጋ ጭማሪ ካጋጠመም ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ተገቢው የሆነ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድም አስገንዝበዋል።

የኑሮ ውድነቱን ለመከላከል ዘላቂው መፍትሔ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሆነ የገለጹት አቶ ተሻለ፤ በአሁኑ ወቅት በክልሎች ጭምር ተግባራዊ እየሆነ ያለው የሌማት ትሩፋት ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል። ለአብነትም በአሁኑ ወቅት ከሶማሌ ክልል የሽንኩርት ምርት እየገባ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ ከተማም የሌማት ትሩፋትን ዕውን ለማድረግ በተደረገው ጥረት በሚሊዮኖች የሚቆጠር እንቁላል ማምረት ተችሏል። ይህ ደግሞ ገበያውን ማረጋጋት እንደሚቻል መሰረት ሆኗል። እንቁላል ከአስር ብር በታች ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል። ዶሮ፣ በግና ፍየልም እንዲሁ ለማቅረብ የአዲስ አበባ መስተዳደርና ክልሎች ዝግጅት አድርገዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ገበያን ለማረጋጋት የሚሠራው ሥራ እንዳይደናቀፍ በየቦታው ግብረኃይል መቋቋሙን የጠቀሱት አቶ ተሻለ፤ ከፌዴራል እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅር ወረዳ ድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል። በተለይም የፖለቲካው አመራሩ እዚህ ላይ ጠንካራ ሥራ መሥራት ግዴታው እንደሆነ በመጥቀስ፤ የፖለቲካ አመራሩ ህብረተሰቡን መታደግ የሚችልበትን የመጨረሻ አቅም ተጠቅሞ እንዲሠራ አቅጣጫ በመስጠት በተቀናጀ መንገድ እየተሠራ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ከዚህ አልፎ ዋጋን ለማናር የሚደረግ ጥረት ካለ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል። መሰረታዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት በሌለበት በዓልን ተገን በማድረግ ዋጋን አንራለሁ የሚል ስግብግብ ነጋዴ ሲያጋጥም ማህበረሰቡ ጥቆማ በመስጠት ሊተባበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የምርት እጥረት ባለበት ጤናማ የሆነ የንግድ ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ እንደማይቻል ገልጸው፣ የንግድ ሥርዓት በውድድር እንዲመራ ማድረግ ለኑሮ ውድነቱ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሆን አቶ ተሻለ ጠቁመዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ምርት እንደልብ ተመርቶ ወደ ገበያው መግባት አለበት። ይህ ሲሆን አንዱ ነጋዴ ከሌላው ነጋዴ በውድድር ያቀርባል። የግብርና ምርቶች በስፋት ወደ ገበያው ሲገቡ ተመጣጣኝ ዋጋ ይፈጠራል። በተመሳሳይ አቅርቦት ሲያጥር ውድነቱ በዛ ልክ ይቀጥላል። ስለዚህ ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማምጣት የምርት አቅርቦትን ማስፋት የግድ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንም በአሉን አስመልክቶ በሸቀጦች አቅርቦት በኩል ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉን የኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቀጸላ ሸዋረጋ አስታውቀዋል። በዓል ሲመጣ የሸማቹ ፍላጎት እንደሚጨምር ጠቅሰው፣ የንግዱ ማህበረሰብ ደግሞ ይህንኑ ፍላጎት ተገን በማድረግ የሚያደርገውን የዋጋ ንረት ለመከላከል እንዲሁም ህብረተሰቡን ካልተፈለገ የዋጋ ንረት ለመታደግ ኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ለአዲስ ዓመት በዓል የፓልም ዘይት በከፍተኛ መጠን ለአዲስ አበባ እንዲሁም ለክልል ከተሞች በቀድሞ ዋጋ እንዲከፋፈል እየተሰራጨ ነው። ዘይቱ በበቂ መጠን የገባ ሲሆን፤ በኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት በኩል እየተሰራጨ ይገኛል። ዋጋውም አዲስ አበባ ላይ ባለ ሶስት ሊትሩ 324 ብር፣ ባለ አምስት ሊትሩ 526 ብር እና ባለ 20 ሊትሩ 2064 ብር እየተሸጠ ነው። የዘይቱ አቅርቦት እስከ መስቀል በዓል ድረስ ያለ እጥረትና የዋጋ ጭማሪ የሚቀጥል ይሆናል።

ለክልሎችም እንዲሁ የዘይት ምርትን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ ሸቀጦች በስፋት እየቀረቡ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ቀጸላ፤ በየክልሉ ምን ያህል መጠን ተደራሽ መሆን እንዳለበት ተደልድሎ እየተሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል።

ከምግብ ሸቀጣሸቀጦች በተጨማሪ ከአዲስ ዓመት ጋር ተያይዞ የሚቀርበው ሸቀጥ የትምህርት ቁሳቁስ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ከትምህርት ቁሳቁስ መካከልም አንዱ የሆነውን ደብተር ለሕብረተሰቡ ለማቅረብ ዝግጅቱ መጠናቀቁን አቶ ቀጸላ ይገልጻሉ።

ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው ኮርፖሬሽን ደብተር ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት ደብተር ገበያ ላይ በከፍተኛ ዋጋ እየተሸጠ ይገኛል ያሉት አቶ ቀጸላ፣ በዚህም ህብረተሰቡ እየተቸገረ መሆኑን መንግሥት መገንዘቡን ገልጸዋል። ይህን ችግር ለመፍታትም ደብተር ከቻይና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በእርግጥ ችግሩ በዓለም ካለው የወረቀት ዋጋ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። ስለዚህም ለኑሮ ወድነቱ አባባሽ ምክንያት ነውና መንግስት ይህን ችግር ለመፍታት አስቀድሞ እየሰራ ይገኛል። ጥራቱን የጠበቀ ደብተርም ከቻይና እንዲገባ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ምርቱ እየተጓጓዘ ነው። በቅርቡ ገበያ ውስጥ እንደሚገባ ይደረጋል። ደብተሩ ከኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት ጋር በመነጋጋር በቅርቡ እንደሚደርስና በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ይቀርባል።

በሌሎች ሸቀጦች ላይም በቂ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፤ በዓሉን አስመልክቶ የሚኖር ምንም አይነት ጭማሪ አለመኖሩን አስረድተዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን    ረቡዕ ጳጉሜን ቀን 1 2015 ዓ.ም

Recommended For You