ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከወራት በኋላ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ያካሂዳል፡፡ ዓለም አቀፉን ኮሚቴ ባለፉት ስምንት ዓመታት የመሩት የፕሬዚዳንት ቶማስ ባህ የሥልጣን ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ ኮሚቴውን የሚመራ አዲስ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ እጩዎች ከወዲሁ ራሳቸውን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
እአአ ከ2013 አንስቶ በሁለት የሥልጣን ዘመን ኮሚቴውን የመሩት የ 70 ዓመቱ ባህ በኮሚቴው አዲስ ፕሬዚዳንት እንደሚያስፈልግና ከዚህ በላይ የሥልጣን ጊዜያቸውን ማራዘም አስፈላጊ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሠረት በቀጣዩ የካቲት ወር 2017 ዓ/ም ምርጫው የኦሊምፒክ መነሻ በሆነችው ግሪክ የሚከናወን ይሆናል፡፡
ቀጣዩ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ለመሆንም 7 እጩዎች በምርጫው የመወዳደር ፍላጎታቸውን አሳይተዋል፡፡ ከእነዚህ እጩዎች መካከል ሁለቱ የቀድሞ የኦሊምፒክ ቻምፒዮናዎች ሲሆኑ፣ የመመረጥ ከፍተኛ እድል ይኖራቸዋል ተብሎ በልዩነት የስፖርት ቤተሰቡን ትኩረት ስበዋል፡፡ የተቀሩት እጩዎች ደግሞ የመካከለኛው ምስራቅ የዮርዳኖስ ልዑል ፈይሰል አል ሁሴን፣ ፈረንሳዊው የዓለም ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዴቪድ ላፓርቲየንት፣ ስፔናዊ ሁዋን አንቶኒዮ ሳማራንች፣ ስዊድናዊ ባለሀብት ዮሃን ኢሊያሽ እንዲሁም ጃፓናዊው የዓለም ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሞሪናሪ ዋታናቤን ናቸው፡፡
100 ዓመታትን በተሻገረው የዘመናዊው ኦሊምፒክ ታሪክ አንዲትም ሴት ፕሬዚዳንት ተመርጣ አታውቅም፡፡ በዚህ ምርጫ ብቸኛዋ ሴት ክርስቲ ኮቨንትሪ አፍሪካን በመወከል የቀረበች ሲሆን፤ ምናልባትም ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት እጩዎች መካከል አንዷ ነች፡፡ ከዚህ ቀደም ኮሚቴውን በፕሬዚዳንትነት ካገለገሉት መካከል 8 የሚሆኑት ከአህጉረ አውሮፓ የተገኙ ሲሆኑ፤ ከአሜሪካ አንድ ሰው በብቸኝነት መርጧል፡፡ ከወራት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ሊያሸንፉ አሊያም ለተፎካካሪዎቻቸው ፈተና ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ከሚጠበቁት እጩዎች መካከል ቀዳሚው አውሮፓዊው የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ ናቸው፡፡
በምርጫው አሸናፊ ይሆናሉ በሚል የተገመቱት ሁለቱ እጩዎች ከሚኖራቸው የምረጡኝ ዘመቻ ፉክክር ባለፈ ሁለቱም ኦሊምፒክን በተወዳዳሪነት የሚያውቁትና የመድረኩን ታላቅነት ያጣጣሙ የቀድሞ አትሌቶች መሆናቸው ያመሳስላቸዋል፡፡ ትኩረት ሳቢዋና ነጭ የቆዳ ቀለም ያላት ዚምባቡዌያዊቷ ክሪስቲ እአአ በ1983 የተወለደች ሲሆን፤ በውሃ ዋና ሀገሯን በኦሊምፒክ መድረክ ማስጠራት የቻለች ብርቱ ስፖርተኛ ናት፡፡ እአአ በ2000 ኦሊምፒክ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ብትሆንም በመድረኩ ሀገሯን በመወከል እስከ ግማሽ ፍጻሜ በመጓዝ ቀዳሚዋ ዚምባቡዌያዊት ናት፡፡
በ2004 እና 2008 የአቴንስ እና ቤጂንግ ኦሊምፒኮች ላይም ሁለት ሁለት የወርቅና ብር ሜዳሊያዎችን አስመዝግባለች፡፡ በአህጉርና ዓለም አቀፍ ቻምፒዮናዎች በመሳተፍም በርካታ ሜዳሊያዎችን ማጥለቅ የቻለች ምርጥ ዋናተኛ ብቻም ሳትሆን በአፍሪካም ተወዳዳሪ ያልተገኘላት ብርቱ አትሌት ናት፡፡ እአአ ከ2017 አንስቶ ወደ ስፖርት አመራርነት የተሸጋገረችው የቀድሞዋ ዋናተኛ በዚምቧቡዌ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም በወጣቶች፣ ስፖርት፣ አርትና መዝናኛ ሚኒስትር ሆና እያገለገለች ትገኛለች፡፡ የ41 ዓመቷ ኮቨንትሪ ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ አባልነት የተመረጠች ሲሆን፤ በዓለም አቀፉ የስፖርት አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ውስጥም በአባልነት አገልግላለች፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንቱ ሰባስቲያን ኮ በበኩላቸው እአአ ከ2020 አንስቶ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንትነት እአአ ከ2015 ጀምሮ ለሦስት የሥልጣን ዘመን ያገለገሉት እኚህ ሰው እአአ በ2027 የሥልጣን ዘመናቸው የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንትነት ለመመረጥ የእድሜ ገደቡ ከ70 ዓመት በታች በመሆኑ ጊዜያቸውን ላለማባከን የፈለጉ ይመስላል፡፡ የ68 ዓመቱ ኮ የአትሌቲክስ የሥልጣን ጊዜያቸውን ሲያጠናቅቁ ወደሌላኛው ተቋም በመዞር መሪነታቸውን የማጠናከር ፍላጎት አላቸው፡፡ በመሆኑም እንዳለፉት ፕሬዚዳንት ለ8 ዓመታትም ባይሆን ለ4 ዓመት የማገልገል ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ዘገባዎች ያመላክታሉ፡፡
ከጊዜ ጋር ውድድር የገጠሙት ሰባስቲያን ኮ እአአ በ1956 የተወለዱ ሲሆን፤ ሀገራቸው እንግሊዝን ወክለው በ1980 ኦሊምፒክ በ1 ሺ500 ሜትር የወርቅ በ800 ሜትር ደግሞ የብር ሜዳሊያዎችን ሲያጠልቁ፤ እአአ በ1984 ኦሊምፒክም በተመሳሳይ ርቀቶች ተመሳሳይ ሜዳሊያዎችን ማስመዝገብ የቻሉ አትሌት ነበሩ፡፡ እአአ በ1990ዎቹ መጀመሪያ በተደጋጋሚ በሚገጥማቸው ጉዳት ምክንያት ከአትሌቲክስ ተወዳዳሪነት ራሳቸውን ሲያርቁ ፊታቸውን ወደ ፖለቲካው በማዞር ለዓመታት ቆይተዋል፡፡ ይሁንና ሀገራቸው እአአ የ2012 ኦሊምፒክ አዘጋጅ መሆኗን ተከትሎ በአመራርነት በድጋሚ ስፖርቱን በመቀላቀል አሁን ካሉበት ሊደርሱ ችለዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም