የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄድ ነው፤ የመጀመሪያው በኅብረቱ ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ በጥር ወይም በየካቲት ወር ላይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የወቅቱ የኅብረቱ ሊቀመንበር በሆነችው አገር አስተናጋጅነት የሚካሄድ ነው።
በአፍሪካ ኅብረት መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ደግሞ የአሁኑ ጉባኤ አዘጋጅ የኅብረቱ መሥራችና መቀመጫ ኢትዮጵያ ናት፤ ጉባኤውም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ይህ ጉባኤ አፍሪካውያን ወደ ቤታቸው የሚሰበሰቡበት፤ ሁላችንም በጉጉት የምንጠብቀው በተለይም በዚህ ወቅት ለኢትዮጵያ ብሎም ለከተማችን አዲስ አበባ ልዩ ትርጉም ያለው ስለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ገጥሟት ከነበረው ውስጣዊና ውጫዊ የህልውና ትግል አንፃር ጉባኤው ለኢትዮጵያ የመልካምና የአሸናፊነት ማብሰርያ ደወልም ነው፡፡
ባደረግነው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት፤ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንም ከጎናችን መሆናቸውን ጉባኤው እንዲካሄድ በመወሰን አሳይተዋል፤ ለአገራችን ያላቸውን አክብሮትና ወዳጅነትም አረጋግጠዋል፡፡
ጉባኤው ኢትዮጵያ ሰላም አይደለችም በሚል ሲካሄድባት የቆየውን ፕሮፓጋንዳ እርቃኑን የሚያስቀር፤ አገሪቱ ሰላም ከመሆን አልፋ እንግዶችን ተቀብላ የምታስተናግድበት ሰላምና ልብ ያላት መሆኑን በተጨባጭ ለመላው ዓለም የምታሳይበት እንደሆነም ይታመናል።
«ታዋቂ» የሚባሉ የመገናኛ ብዙኃን ሳይቀር አገሪቱን ሰላም አልባ አድርገው ለማቅረብ በከፍተኛ ደረጃ ሲያካሂዱት የነበረው ዘመቻን በማጋለጥ፤ እውነትም ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም በራሷ ማረጋገጥ የምትችል አገር መሆኗን፤ ከተማዋ አዲስ አበባም ከምንጊዜውም በላይ ሰላማዊና ውብ እንደወትሮውም የአፍሪካውያን መዲና ሆና መቀጠል የሚያስችል ብቃት ያላት መሆኑን ለማረጋገጥም ጭምር ጉባኤው ወሳኝ ነው፡፡
ይህ በብዙ መልኩ የአገራችንን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ለማሳወቅ ከፍ ያለ ትርጉም ያለው ጉባኤ ስኬታማ እንዲሆን መላው ሕዝባችን በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ ሕዝብ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡
ይህን ኃላፊነት ለመወጣት፤ ይህንን ታሪካዊ ጉባኤ በደመቀና ባማረ መልኩ ተካሂዶ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል አዲስ አባባ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ስለማድረጓ በየጎዳናውና በአደባባዮች ላይ ያለው ትዕይንት እንዲሁም የሆቴሎቻችን ዝግጅት ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
ይህ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ከአህጉራዊ የሰላምና የጸጥታ ጉዳዮች እስከ አጀንዳ 2063 አፈጻጸም ድረስ ያሉ በርካታ ጉዳዮች ለውይይት የሚቀርቡበት፤ የጋራ መግባባትና መስማማት የሚደረስበት አቅጣጫዎች እቅዶች የሚቀርቡበት፤ እንደ አህጉር አንድ በምንሆንባቸውና መሆን ባሉብን ጉዳዮች ላይ በጋራ የምንመክርበት ነው።
የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ላለፉት ጥቂት ዓመታት የፊት ለፊት ስብሰባ እንዳላደረገ ይታወሳል፤ ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ በአንዳንድ ወገኖች ከፍ ያለ ጫና ሲካሄድ መቆየቱም ይታወቃል።
በተለይም በጁንታው ቡድን ላይ የተወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ያስከፋቸው አካላት ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አሳምኖ ጉባኤው በተለመደው መንገድ አገራችን ላይ እንዲካሄድ እልህ አስጨራሽ ትግሎችም ተደርገዋል።
እዚህ ላይ ስለ አገሬ ያገባኛል በማለት ትግሉን ያካሄዱ የሥራ ኃላፊዎች ዜጎች እንዲሁም አንዳንድ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ከእውነት ጋር በማበራቸው ምስጋና ይገባቸዋል።
ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በተለያዩ እርከኖች ውስጥ የሚገኙ በውጭ ግንኙነት ዘርፍ በሥራ ላይ ያሉ ወገኖች ባደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እነሆ 35ተኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በመዲናችን በመዲናቸው ሊካሄድ ቀናት ቀርተውታል። በዚህ አጋጣሚም አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ በመረዳት፣ ለኢትዮጵያውያንም ወገንተኝነታቸውን በማሳየት ጭምር ወደ ከተማዋ እየገቡ ነው።
ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነው። ብዙ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነት፣ ሉዓላዊነትና ሰላም የምታደርገውንና ስታደርግ የኖረችውን ተጋድሎ በሚገባ ያውቃሉ፤ ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውም የሚያስገኝላቸውን ጥቅም በቅጡ ይገነዘባሉ፤ ኢትዮጵያ ሰላም አይደለችም ጉባኤውንም በሌላ አገር ማድረግ አለብን ሲባል አይ ኢትዮጵያ በራሷ መንገድ ሰላሟን አረጋግጣለች ጉባኤውም በአካል በአዲስ አበባ ከተማ ነው በሚል መወሰናቸውም የዚሁ እውነት ማሳያ ነው።
ይህንን እውነታ ለመቀልበስ ጠላቶቻችን ሰፊ ዘመቻ ውስጥ ቢቆዩም፤ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ከእኛ ጋር መቆማቸው የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ሲያጠለሹ የነበሩ ኃይሎች ያፈሩበት፤ በአንጻሩ እኛና እኛን ያሉ ሁሉ ከፍ ያሉበት ነው፤ ወደፊትም ይኸው እውነታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በወንድሞቻችን ያለን መታመን ከፍ ያለ ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን የውስጥና የውጭ ፈተናዎቻችንን ሁሉ አልፈን ጉባኤውን ማስተናገዳችን አዲስ አበባ የተረጋጋች፣ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴና ሌሎችም የሥራ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱባት መዲና መሆኗን ለማስመስከር ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ በርካታ እንግዶች ስለሚመጡ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው።
መንግሥት ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ነው፤ እኛ ኢትዮጵያውያንም ጨዋነትና እንግዳን የማስተናገድ ልምዳችንን ተጠቅመን አፍሪካዊ ወንድም እህቶቻችን ወደመዲናችን ሲመጡ የማይረሱት ትዝታ ይዘው በሚሄዱበት መልኩ ማስተናገድ፤ ከሁሉም በላይ እኛን ብለው ለመጡ እንግዶቻችን ፍጹም ኢትዮጵያዊ በሆነ እንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በፍቅር ልብ ጎንበስ ብለን መቀበል አለብን እላለሁ። አበቃሁ፡፡
በዕምነት
አዲስ ዘመን ጥር 24/2014