በማሊ ዋና ከተማ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ታጣቂ ቡድኖች በዚህ ሳምንት በፈጸሟቸው ጥቃቶች 70 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ፡፡ ላለፉት አስርተ ዓመታት በተደጋጋሚ በሚከሰቱ የሽብር ጥቃቶች ጉዳት እያስተናገደች የምትገኘው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በዚህ ሳምንትም መጠኑ ከፍ ያለ ጥቃት ደርሶባታል፡፡
በዋና ከተማዋ ባማኮ ተፈጽሟል የተባለው ጥቃት የፖሊስ ማሠልጠኛ ተቋም እና የሀገሪቱ አየር መንገድ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ታጣቂ ቡድኖቹ ይህን ጥቃት የፈጸሙት በማዕከላዊ የሀገሪቷ ክፍል ጭምር የትኛውንም አይነት የሽብር ተልዕኮ ማሳካት እንደሚችሉ ለማሳየት ነው ተብሏል፡፡
የሀገሪቱን መንግሥት በመፈንቅለ መንግሥት አስወግዶ እየመራ የሚገኘው ወታደራዊው አስተዳደር በማሊ የሚገኘው የጸጥታ እና ደህንነት ጉዳይ እየተሻሻለ እንደሚገኝ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡ ወታደራዊ አስተዳደሩ የፈረንሳይ እና የአሜሪካ ወታደሮችን ከሀገር እንዲወጡ ካደረገ በኋላ ፊቱን ወደ ሩስያ አዙሯል፡፡
ሽብርተኞችን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የሩስያ ቅጥር ወታደር ቡድን ዋግነር ባሳለፍነው ሀምሌ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወታደሮቹ በማሊ እንደተገደሉበት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ከሰሞኑ የተከሰተውን ጥቃት ተከትሎ አስተዳደሩ የሟቾችን ቁጥር ይፋ ባያደርግም ሮይተርስ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች አገኘሁት ባለው መረጃ ወደ 70 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን ዘግቧል፡፡
በጥቃቱ ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ጉዳት የደረሰባቸው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች በሆስፒታል የህክምና ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የማሊ ጋዜጦች በበኩላቸው በጥቃቱ የተገደሉ 50 የፖሊስ ሠልጣኞች ሥርዓተ ቀብር አርብ እለት መፈጸሙን ዘግበዋል፡፡
የማሊ ወታደራዊ አስተዳደር ከታጣቂዎች እና ሽብርተኞች ጋር በገባበት ውግያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ ሚሊዮኖች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን አል ዐይን ዘግቧል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም