ቆም ብለን እናስብ፣ እናሰላስል፣ ‘ለምን? ‘ እንበል_ ‘እኮ ለምን?!’ እንነጋገር፣ መነጋገር ብቻ ነው የዴሞክራሲ መምጫው። ለአመታት ከተፈፀመብን ግፍ አንፃር የወያኔዎች አባት የሆነው ስብሀት ነጋና መሠሎቹ ከእስር መፈታት ሁላችንም ላይ ቁጣን፣ ኀዘንን ፣ ተካድን የሚል ስሜትን አጭሮብናል ፤ አበሳጭቶናልም። በሕዝቦች መካከልም እጅግ ከፍተኛ ቁጣ አስነስቷል።
ይህም ቢሆን ግን ለምን እንደዚህ ሆነ? ይህ በመሆኑ ምን እናጣለን? ምንስ እናገኛለን? እነሱ በመታሰራቸው አገራችን ምን ትጠቀም ነበር? አሁን የሚመጣባት ችግር ምንድን ነው? ብለን እንጠይቅ።
ቆም ብለን እናስብ፤ እናሰላስል፤ ያን ጊዜ የችግሮች መፍቻ ቁልፍ ሁሉ እጃችን ላይ ይገባል። ቁልፉ እጃችን ላይ ከመግባቱም በላይ ደግሞ በዚህ ሦስት አመት ውስጥ እንደ አገርና ሕዝብ የገነባነውን አንድነት ከመፈረካከስ ልንታደገው እንችላለን።
አዎ በሆነው ነገር ተቆጥተናል፣ ተከፍተናል ብዙ ነገሮች የተበላሹና መስመር የሳቱም ዓይነት ስሜት በሁላችንም ውስጥ ተሰንቅሯል። ነገር ግን እያሰማን ያለነው ተቃውሞ መስመር ሊይዝ ይገባል። በሌላ በኩል ደግሞ እዚህ እስከምንደርስ ድረስ ያገኘናቸው ድሎች እንዴት መጡ? ከምን መጡ? የሚለውንም ማጤን ይገባል? አልያ ግን ልፋታችን ሁሉ በዜሮ ይጣፋና ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።
በሌላ በኩልም ከዚህ ቀደም በሠራነው ሥራ በፈጸምነው ጀብዱ ሕወሓትን ደጀን አድርገው ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሱ ኃይሎችን ድባቅ መምታት የተቻለው ምናልባትም ከምን ጊዜውም በላይ የተጠናከረው አንድነታችን የፈጠረው አቅም ነው።
አንድነት በሰራዊቱ߹ በልዩ ኃይሉ߹ በሚሊሻው߹ በመንግሥት አመራሩ߹ በሕዝቡ መካከልም አለ። ይህ ደግሞ እስከ አሁን ለደረስንበት ደረጃ እንድንበቃ ከማድረጉም በላይ ወደ ከፋ ደረጃ ላለመግባታችን ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል።
ኢትዮጵያን ለማዳከም ለማሽመድመድ እኛንም አንድነታችንን ለመሸርሸር የሚፈልጉ ኃይሎች ይህንን ቁልፍ በማወቃቸው አሁንም እኛን የሚያባሉበትን ሴራ በመጎንጎን ላይ ናቸው፤ እስከ ዛሬ እንደዚህ ዓይነት ክፍተት አልፈጠርንላቸውም ፤ ነገር ግን አሁን ከሕወሓት አመራሮች ከእስር መለቀቅ ጋር በተያያዘ በሕዝቡ ውስጥ የተቀጣጠለ ቁጣ ይህንን ክፍተት እንዳይፈጥርላቸው መጠንቀቅ ግን ወቅቱ የሚጠይቀው በሳል አካሄድ ይመስለኛል።
አዎ ብዙ የበደሉን አገርና ሕዝብን ችግር ውስጥ የጣሉ ሥራቸው ከመዘግነን አልፎ እውነት ሰይጣን እንኳን እንደዚህ ሊያደርግ ይችላል እንዴ? ሊያስብሉ የሚችሉ ዘግናኝ ተግባራትን በመፈጸም እንደ አገር እንድንዋረድ ብዙዎች ለችግር እንዲጋለጡ አገረ መንግሥቱም ዘርፈ ብዙ ውጥንቅጥ ውስጥ እንዲገባ ካደረጉ በኋላ አሁን ላይ ከእስር ተፈቱ መባሉ ሆድ የሚያስበስ ለምን የሚል ጥያቄ እንዲነሳ የሚያደርግ ነው። ነገር ግን ሰከን ቆም ብሎ ማሰብ ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ውስጥ ከመግባት ያድነናል።
በዚህ ሰዓት መፈታት ነበረባቸው ወይ? ብለው የጠየቁ ብዙ ናቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ስለ ሁኔታው ሊያስረዱ የሄዱበትን መንገድ ብዙ ዜጋ ያልወደደውም፤ ይህ እንግዲህ በሕዝብና በአገር ላይ ከደረሰው ጉዳት ያላገገመን ከመሆናችን ጋር በተያያዘ የሚጠበቅና ከግምት ውስጥ የሚገባ ነው።
በሌላ በኩልም ሕዝቡ ካሳለፈው መከራ እያሳለፈ ካለው አስቸጋሪ ጊዜ እንዲሁም ያሉ ስጋቶች ካለመቀረፋቸው ጋር ተያይዞ የሰዎቹ ከእስር መፈታት የሕዝቡን አንድነት ሊሸረሽረው ይችላል፤ ነገር ግን በተቻለ መጠን እስከ አሁን የታየው ቁጣ ከመጠን በላይ ገዝፎ ወጥቶ አንድነታችን ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር አንድነታችንንም እንዳይሸረሽረው ጥንቃቄ ማድረግ ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው።
ከፋፋዮቻችን ሊያዳክሙን የሚችሉት እኛን መከፋፈል ሲችሉ ነው፤ ስለዚህ እኛ ደግሞ ለከፋፋዮቻችን ተከፋፍለን ራሳችንን ለማስበላት ምቹ ሁኔታ መፍጠር የለብንም።
ተቃውሟችንን መቼ በምን ደረጃ ማድረግ እንዳለብን በትክክል ማወቅ አለብን። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ኅብረተሰቡ በእነዚህ ሰዎች መፈታት ተቃውሞውን ገልጿል፤ በመግለጽ ላይም ነው፤ ይህ የሚጠበቅና መሆን ያለበት ነገር ከመሆኑም በላይ የሚያስከትለውም አደጋ በግሌ አይታየኝም፤ ነገር ግን ይህ ተቃውሟችንና ልዩነታችን ተለጥጦ ሄዶ ለመከፋፈላችን ምክንያት እንዳይሆን ማድረግ ያስፈልጋል።
እንደ እኔ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት ያለን አማራጭ አንድ በከፋፋዮቻችን እኩይ ሥራ ተጠምደን መከፋፈልና በእነሱ መበላት፤ አልያ ደግሞ ያለንን ቅሬታ እንዲሁም ብሶታችንን ዋጥ አድርገን ቀጣዩን ጊዜ ለማሳመር አንድነታችንን ማጽናት ናቸው ።
ከዚህ ውጪ ያለ ሦስተኛ መንገድ ለእኔ አልታየኝም። በመሆኑም አሁን የሆነብንን ነገር ለጊዜው ወደጎን አድርገን መነሳትና ትልቁን ስዕል ይዘን ወደፊት መቀጠሉ ሳያዋጣ አይቀርም።
በመሆኑም እንደ ዜጋ አሁን እየተሠራ ያለው ሥራ የእኛን የተጠናከረ አንድነት ለመናድ ያለመ መሆኑን በቅጡ ተረድተን በተቻለ መጠን የምናደርገውንም የምንሰራውንም የምንቃወምበትንም መንገድ በልኩና በልኩ ብቻ ማድረግ መቻል አለብን። አሁን ያለነው ጦርነት ላይ ነው፤ ጦርነቱ ደግሞ በራሱ ይዟቸው የሚመጡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እጅግ ብዙ ናቸው።
በመሆኑም እነዚህን ለመቀልበስ አንድነታችን እጅግ ወሳኝና አስፈላጊ ነው።
የወደሙ መሠረተ ልማቶች በቦታቸው መመለስ። የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው መግባት መቻል አለባቸው፤ ዛሬ ላይ ይህንን በአንድነት ተረባርበን መስራት ካልቻልን ነገ ላይ እነሱም ሌላ የችግር የተቃውሞ ምንጭ የመሆን ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው።
ይህ እንዳይሆን በአንድ እጃችን የወደመብንን መልሰን እየገነባን፤ በሌላ እጃችን ደግሞ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው አንድነታችንን ሸርሽረው ሊያዳክሙን ለሚፈልጉ ኃይላት ዕድል ባለመስጠት ነገሮች በልክ እንዲሄዱ ማድረጉ ደግሞ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅም ነው።
መተቸት መቃወም የራሱ የሆኑ ጥሩ ጎኖች እንዳሉት አስማማለሁ፤ ነገር ግን አገራችንን አኩርፈን የጀመርናቸውን የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሥራዎችን መተው በውስጥም በውጭም ሊካሄዱ የነበሩ «የበቃ» የተቃውሞ ሰልፎች እንዲሰረዙ ማድረግ ግን ተገቢ አይደለም። በክስተቱ ሁላችንም ላይ ጥሩ ስሜት አልተፈጠረም ነገር ግን ኢትዮጵያ የሚለውን ትልቁን ስዕል ማሰብ ግን ከሁላችንም የሚጠበቅ የውዴታ ግዴታችን ነው።
አሁን ላይ እኔ እንደሚሰማኝ ኢትዮጵያ አንድነቷን በመመለስ አሸናፊ ሆናለች። ይህ ሲሆን ደግሞ የውስጥና የውጭ ጥላቶቿን ከማሳፈር ጀምሮ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮቿ ላይ የተጋረጡባትን ችግሮች ሁሉ ተሸጋግራ አሸናፊነቷን ታጸናለች። ለዚህ ደግሞ ምንም ጥርጥር የለም።
ያሸነፍንበትን አንድነታችን ሳይሸራረፍ እንዲቀጥል ሁላችንም መትጋት ይኖርብናል። ከፋፋይና አገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሀሳቦች ወደ ጎን በመተው፤ መንግሥትም የትኞቹ ችግር ቅድሚያ መፈታት አለባቸው ብሎ በመለየት በመምከር ችግሮቹን ከሥራቸው ለመፍታት መሥራት ይኖርበታል።
ይህም ከገባንበት ውስብስብ ችግር መውጫ መንገድ መሆኑን በመረዳት ስለ ኢትዮጵያ ህልውና ብሎ መሥራትንም ያካትታል።
ወቅታዊ ባልሆነ አጀንዳ መጠለፍ፣ ብልጣብልጥነት፤ ስግብግብነት ፤ አድርባይነት ፤ ግትርነት መከራችንን ከማርዘም ውጪ ፋይዳ የላቸውም። ከምንም በላይ መንግሥት ኅብረተሰቡ የመረጃ ብዥታ ተፈጥሮበታል ብሎ ሲያምን ዝርዝር መረጃዎችን በመሰጠት ማስገንዘብና ማጥራት ትልቁ የቤት ሥራው መሆኑንም ማወቅ ይኖርበታል።
የመረጃ ክፍተት እስካሁን የፈጠረው ችግር ከአሁን በኋላም እንዲዘልቅ ማድረግ አደጋው ብዙ ነው። አበቃሁ።
በእምነት
አዲስ ዘመን ጥር 10/2014