አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ጦርነትን እንደ ትልቅ የሰላም ምንጭ ስትጠቀመው ቆይታለች። ያለፉትንም ሆነ የቅርብ ጊዜ የጦርነት ትዝታዎቻችንን መለስ ብለን ብንቃኝ አገራችን ያተረፈችው አንዳች ነገር እንደሌለ እንደርስበታለን።
እያንዳንዱ አገራዊ ጉዳያችን ለጦርነት በር ከፋች ከመሆኑም በላይ የመፍትሄ ሃሳቦችን መለስ ብለን እንዳናይ ያደረገም ነበር። ልዩነቶቻችን ሁሉ ወደ መገፋፋትና ወደ ጦርነት የሚወስዱን ናቸው። ከትናንት እስከ ዛሬ እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል እሳቤ ለንክሻና ለመለያየት ተዳርገናል።
ሃሳብን በሃሳብ ማሸነፍ ተስኖን፣ ልዩነትን በጋራ እውነት መርታት አቅቶን ቅራኔዎቻችንን ሁሉ በአፈ ሙዝ ለመፍታት ስንውተረተር ዓመታት አስቆጥረናል ። ከሰሞኑ የሰማንው አገራዊ ምክክር ግን ይሄን አዳፋ ታሪካችንን የሚቀይር ነው ብዬ በጽኑ አምናለው። እንደ አገርም ሆነ እንደ ዜጋ የዚህ አገራዊ ምክክር ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ ነው ብዬ አላስብም።
በአለመግባባቶችና በተለያዩ ልዩነቶች አገራችን ውጥንቅጧ በወጣበት በዚህ ሰዓት ይሄ የምክክር ጉባኤ እንደ አገር እውቅና አግኝቶ መቋቋሙ አገራችንን ወደ ፊት የሚያራምድ ድንቅ ተግባር ነው ብዬ ነው የምወስደው። ያለፉ ታሪኮቻችንን መለስ ብለን ብናጤን ለመለያየታችን አንድ ሺ ምክንያት እናገኝ ይሆናል እነዛ ተቃርኖዎቻችንን ወደ አንድነት ለማምጣት በጋራ ሃሳብ ስንወያይ ግን አንታይም። ለውይይትና ለምክክር ክፍት የሆነ ባህልና ልማድ ቢኖረን ኖሮ በጦርነትና ባለመግባባት ያባከናቸው መልካም እድሎቻችን ዛሬ ፍሬ ባፈሩ ነበር እላለው።
ለጦርነት ቅርብ የሆነ ሥነ ልቦና ያለን ሕዝቦች ነን። ምንም ነገር በሃይል ለማድረግ እንጂ በንግግር ለመግባባት ሆነን የኖርነው ጊዜ እምብዛም ነው። ከትናንት እስከዛሬ ልዩነትን እንደ ትልቅ ክፍተት በመጠቀም ለጦርነት ስንዳረግ ቆይተናል። ሰላም በጦርነት መጥቶ አያውቅም፣ የሰላም መገኛ ስፍራው መነጋገር ብቻ ነው።
ይሄ አገራዊ ምክክር ለአገራችን ተስፋ ይዞ እንደመጣ አምናለሁ። በጦርነትና በመገፋፋት የዳበረ ጡንቻችንንም ያለዝብልናለ ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ። እንደ ዜጋ ከጦርነት አርቀን ማየት ይኖርብናል። በቀሪ ጊዜአችን የውይይትን በረከት መቋደስ ቀጣይ እጣ ፈንታችን እንዲሆን በጋራ መስራት ይጠበቅብናል።
ከፊታችን ላለው አገራዊ መነቃቃት ሰላም ሊያመጡ የሚችሉ ማናቸውንም አማራጮች ማየቱ መልካም ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው። ማየት ከቻልን በአገራዊ ምክክሩ ብዙ ነገር እናተርፋለን። ትውልድ እንቀርጽበታለን፣ ሰላም እናመጣበታለን፣ ያለፈ ታሪካችንን እናድስበታለን።
ወደ ፊት ለመሄድ በምናደርገው ጎዞ ላይ ሃይል ሆኖ የሚያራምደንም ነው። በዚም በዛም የተደቀኑብንን ችግሮች እያጠራን እንድንሄድ በብርቱ የሚያግዘንም ይሆናል። አገር ልዩነትን አቻችሎ በሚያስታርቅ የጋራ ሃሳብ መቀረጽ አለባት። ዓለም ላይ አንድ አይነት አስተሳሰብ ያላቸው አገራት የሉም።
እንደ መልካችን አመለካከታችንም የዛኑ ያክል የተራራቀ ነው። ግን ደግሞ በልዩነት ውስጥ መግባባት ይቻላል። እኛ ያቃተን በልዩነት ውስጥ መግባባት ነው። ባለመስማማት ውስጥ ያለውን መስማማት እስካሁን ድረስ አልደረስንበትም።
ብዙ ነገሮቻችን ዋጋ ያጡት ለዚህ ነው። በየትኛውም መስፈርት ቢለካ አገር የጋራ ሃሳብ ያስፈልጋታል። የጋራ ሃሳብ የሚመጣው ደግሞ ከብዙ ልዩነቶች ውስጥ ነው። ዓላማቸውን አገርና ማሕበረሰብ ካደረጉ ብዙ ልዩነቶች ወደ አንድ እውነት የማይመጡበት ምንም ምክንያት የለም። እኛን እያስቸገረን ያለው ሁሉም በራሱ ሃሳብ እኔ ልክ ነኝ ብሎ መቆሙ ነው።
በዚህ አመለካከት ደግሞ ለዘመናት ዋጋ ስንከፍልበት ኖረናል። አሁን በጋራ ምክክር የጋራችንን ኢትዮጵያ የምንፈጥርበት ነው። በዚህ አገራዊ ምክክር ላይ መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ ሳይሆኑ፣ ታዋቂ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም የመሳተፍ ነጻነት አለን። አገር የግለሰቦች አመለካከት ጥርቅም ናት።
አገራችንን ከገጠሟት የሰላም ጠንቆች ለመታደግ በዚህ አገራዊ ምክክር ላይ በመሳተፍ የድርሻችንን ማዋጣት እንችላለን። አገራዊ ምክክሩ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ዓላማው አገር በተሻለ መሰረት ላይ ማዋቀር ነው። ሰላምን መሰረት ያደረገ ሁሉን አቀፍ አአገራዊ መግባባትን መፍጠር ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን ስለሰላም ከከፈልናቸው ዋጋዎች አንጻር የሰላም ዋጋው ምን ያክል እንደሆነ በደንብ እናውቃለን። ባለፉት ዓመታት ውስጥ በሰላም እጦት የከፈልናቸውን መስዋዕቶች እናውቃለን። በሰላማዊ ድርድር ሰላማዊ አገር መፍጠር እንደሚቻል ዛሬ ስለገባን በግሌ አዝናለው። ቀላል ነገሮችን ባለማድረግ አገራችንን ለብዙ ችግሮች ስንዳርጋት ኖረናል።
በመመካከርና መግባባት ለአገራችን ውለታ መዋል እየቻልን ይሄን ባለማድረጋችን በግሌ እቆጫለው። አሁንም አልረፈደም… ቀጣይ የምትፈጠረውን አገራችንን የሰላም መንደር ለማድረግ ሁሉ ነገር እጃችን ላይ ነው። እኔ ሥልጣኔን የምለካው ቀላል ነገሮችን ለከባድ ነገር መጠቀም ስንችል ነው። እውቀትን ለበጎ ነገር መጠቀም ስንችል ነው።
ባለመነጋገር ብዙ ነገር አጥተናል ይሄ ደግሞ የሥልጣኔአችንን ክፍተት፣ የኋላ ቀርነታችንን ስፋት ያሳየ ሆኖ አግኝቼዋለው። ዋናው ነገር ከትናንት መማራችን ነው፣ ዋናው ነገር ዋጋ ካስከፈሉን ስህተቶቻችን መታረሙ ነው… ይሄ አገራዊ ምክክር በዚህ ሰዓት አገር ለመፍጠር ትክክለኛ ውሳኔ ከመሆኑም በላይ ለአገራችን የበኩላችንን ሃሳብ እንድናዋጣ መልካም እድል የፈጠረም ነው። ለአገራችን ውለታ መዋል አለብን… ውለታ የምንውለው ደግሞ ልዩነትን ወደ ጎን ብሎ ሊያግባቡን በሚችሉ ነገሮች ላይ ውጤት ስናመጣ ነው።
በቀላል ነገር ዋጋ መክፈል የለብንም። የትናንት ድርሳኖቻችንን ማገላበጥ ብንችል ብዙ መከራዎቻችን በትንሽ ነገር የተፈጠሩ ሆነው እናገኛቸዋለን። ያጣናቸው ብዙ ነገሮች ቆም ብሎ በማሰብ የሚስተካከሉ ነበሩ። ግን ያንን ማድረግ አልቻልንም። ስሜታዊነት ዋጋ አስከፍሎን ቆይቷል። ከስሜታዊነት መውጣት አለብን… በማሰብና በማሰላሰል ወደ ፊት መሄድ ያዋጣናል። ኢትዮጵያ መከራ ይበቃታል… ሕዝባችን ስቃይ ይበቃዋል።
አሁን የመግባባት ዘመን ይሁን። ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን ብለን በአስታራቂ ሃሳብ አገርና ትውልድ የምንፈጥርበት የንጋት ጊዜ ይሁን። ኢትዮጵያ አገራችን አፍ ቢኖራት እንዲህ የምትለን ይመስለኛል ‹እስከ መች ነው የምትገሉኝ… የኔ ሞት መች ነው የሚያበቃው? እስከ መች ነው የምታሰቃዩኝ… የእኔ ስቃይ መች ነው የሚያበቃው? እንዴት ስለ አንድ እናታችሁ ስለ እኔ ስትሉ መግባባት ያቅታችኋል?› የምትለን ይመስለኛል።
እውነት ነው አገራችን በትንንሽ ነገሮች ስትሰቃይ ኖራለች። ከጥንት እስከዛሬ ለጦርነት ምክንያት በማይሆኑ ጉዳዮች ሰላሟን አጥታ ከርማለች። በዚህ ሀገራዊ ምክክር መንግሥት ኢትዮጵያን ከስቃይ ለመታደግ ትክክለኛ ውሳኔ እንደወሰነ ይሰማኛል።
ምክክር ያስፈልገናል… ሁሉንም የማሕበረሰብ ክፍል ያሳተፈ ውይይት ግድ ይለናል። ከፌዴራል ጀምሮ ክልሎችንና ወረዳዎችን ያማከለ የአብሮነት ሃሳብ ያሻናል።
ያለፉ ስቃዮቻችን የሚረሱት፣ ያለፉ መከራዎቻችን የሚዘነጉን ዛሬ ላይ ሁሉን አቀፍ ምክክር አድርገን ሁሉን አቀፍ ሰላም ስናመጣ ብቻ ነው። ይሄን እድል መጠቀም አለብን… የመሳሪያ ድምጽ የማይሰማባትን ኢትዮጵያ፣ በሃሳብ ልዩነት መከራ የማይደርስበትን ማሕበረሰብ መፍጠር መቻል በዚህ ምክክር የምናተርፈው አገራዊ ትርፍ ነው እላለሁ።
የአገር ትርፍ በምንም የሚለካ አይደለም። የአገር ትርፍ በሕዝቦቿ ሰላም የሚለካ ነው። የአገር ትርፍ በትውልዷ መረጋጋት የሚመዘን ነው።
እስከ ዛሬ አትርፈን አናውቅም…ትልቅ አገርና ትልቅ ሕዝብ ይዘን እንደከሰርን ነው። ላለመግባባት ምክንያት እየፈጠርን በዘመነ ዓለም ውስጥ እኛ ጦርና ጎራዴ ስንሰብቅ ነበር። የትውልዱ ክስረት በዚህ አገራዊ ምክክር መካስ ይኖርበታል።
አገራችን ያጣቻቸውን የሰላም እድሎች በዚህ ብሄራዊ መግባባት መመለስ አለባት እላለሁ። ትናንትና በልዩነታችን ጎራ በመፍጠር አገር ስንጎዳ ኖረናል። ለትውልዱ ሳንበጅ በመሰለን እየተነዳን ብዙ ስህተቶችን ፈጽመናል።
አሁን ደግሞ በሌላ ጎዳና ላይ ነን… አገርን መሰረት ባደረገ የምክክር ጎዳና ላይ። በነዚህ እድሎች ተጠቅመን አገራችንን ጦርነት አልባ የሰላም ምድር ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል።
በዚህ የለውጥና የሰላም ሃሳብ ላይ አስታራቂ ሃሳብ በማዋጣት ሕዝባችን ያጣውን ልንሰጠው ይገባል። ያለፉት ዓመታት ምን ይዘውልን እንደመጡ እናውቃለን፣ እነዛን ስህተቶች ዛሬ ላይ ባለመድገም ለትውልዱ ውለታ ልንውልለት ይገባል። በዚህ አገር አቀፉ የምክክር መድረክ ቀጣይ የምትፈጠረውን ኢትዮጵያ፣ ቀጣይ የሚፈጠረውን ትውልድ ለሁላችንም ያስፈልጉናል።
ልዩነቶቹን በሰላማዊ መንገድ የሚፈታ መንግሥት እንሻለን። ቅራኔዎቹን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ እልባት የሚያመጣ ትውልድ ያስፈልገናል። ማሕበረሰባችን ተነጋግሮ መስማማትን ባህል ሊያደርግ ይገባል። ዘመኑ ከልብ የመግባባት ነው። ጦርና ጎራዴ ጊዜ አልፎባቸዋል።
ጦርነት ለዚህ ዘመን የሚመጥን አይደለም። ራሳችንን ለእርቅና ለተግባቦት ካዘጋጀን የማንፈታው ምንም አይነት ችግር አይኖርም ። የእስካሁኑ ችግራችንም ራስ ወዳድነታችን የፈጠረው እንጂ የመፍትሄ ሃሳብ አጥተን የተፈጠረ አይደለም። አሁን ላይ በአራቱም አቅጣጫ ውይይት የሚፈልጉ አገራዊ አጀንዳዎች አሉ።
እኛን የሚጠብቁ፣ የእኛን ምክክርና ውይይት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች በዙሪያችን አሉ። አነዚህ ችግሮች መፍትሄአቸው አንድና አንድ ውይይት ነው።
በውይይት ስንዘምን፣ ለተሻለ ሃሳብ ቅድሚያ ስንሰጥ ለጦርነቶች የከፈልነው ዋጋ ያስቆጨናል። የበላይነት የችግሮቻችን ሁሉ ሁነኛ መፍትህ መሳሪያን የምንም ነገር መፍትሄ ማድረጋችን የሚያበቃበት ጊዜ ይመጣል። ለዚህ ደግሞ ልዩነቶቻችንን የሚያጠቡ፣ ተቃርኖዎቻችንን የሚያለዝቡ ውይይቶች እዚም እዛም ያስፈልጉናል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 18/2014