ባለፈው ዓመት ከደቡብ ኮሪያ ወደ ሰሜን ኮሪያ በሕገ ወጥ መንገድ አቋርጦ በመግባት የአንድ ዓመት እስር ተፈርዶበት የነበረው የአሜሪካ ወታደር ከእስር ተለቀቀ። ትሬቪስ ኪንግ የተባለው ወታደር ወደ ሰሜን ኮሪያ ከሸሸ በኋላ ወደ አሜሪካ እንዲመለስ ተደርጎ ነበር። ትሬቪስ በጦር ክህደት እና የጦር መኮንን ላይ ጥቃት በማድረስ ክስ የተመሠረተበት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ነው።
ሆኖም የቁም እስሩን ጊዜ በማጠናቀቁ እና በዚህ ጊዜ ባሳየው መልካም ሥነ ምግባር ምክንያት የ24 ዓመቱ ኪንግ ነጻ እንዲወጣ መደረጉን ጠበቆቹ ተናግረዋል። ኪንግ አርብ ዕለት በቴክሳስ ፎርት ብሊስ በተካሄደው ችሎት ከተመሠረቱበት 14 ወታደራዊ ክሶች መካከል በአምስቱ ጥፋተኛ መሆኑን ያመነ ሲሆን ሌሎቹ ውድቅ ተደርገዋል።
በችሎቱ ላይ ኪንግ ለጦሩ ዳኛ ሌተናንት ኮሎኔል ሪክ ማቴው፣ የአሜሪካን ጦር ጥሎ ለመውጣት የወሰነው “በሥራው ባለመርካቱ” እንደሆነ እና ወደ ሰሜን ኮሪያ ከመሸሹ አንድ ዓመት በፊት ጥሎ ለመውጣት ሲያስብ እንደነበር ተናግሯል። በችሎቱ ተገኝተው እንደዘገቡት ጋዜጠኞች ከሆነም “ከአሜሪካ ጦር መውጣት እና አለመመለስ እፈልግ ነበር” ብሏል ኪንግ።
ከዚህም በተጨማሪ ምንም እንኳን ችሎት ለመቅረብ እና ክሶቹን ለመረዳት ብቁ ቢሆንም የአዕምሮ ጤና ችግር እንዳለበት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። የኪንግ ጠበቃ ፍራንክሊን ሮሰንብላት በመግለጫቸው እንዳሉት ደንበኛቸው ለተፈጠረው ክስተት ሙሉ ኃላፊነቱን መውሰዱን ገልጸው፣ ኪንግ የልጅነት አስተዳደጉ፣ ወንጀል በሚፈፀምበት አካባቢ ማደጉ እና የአዕምሮ ጤና ችግርን ጨምሮ በሕይወቱ ከባድ ፈተናዎች እንደገጠሙት አውስተዋል።
“እነዚህ ችግሮችም በጦሩ ውስጥ ያለውን ፈተና እንዳይቋቋም አድርገውታል” ብለዋል ጠበቃ ሮሰንብላት። ኪንግ የአሜሪካ ጦር ሠራዊትን የተቀላቀለው በአውሮፓውያኑ 2021 ሲሆን ደቡብ ኮሪያ ያለው ካምፕ ውስጥ ነበር። ወደ ሰሜን ኮሪያ የተሻገረውም ከባድ ጥበቃ በሚደረግለት እና በሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ መካከል ባለ ነጻ ቀጣና በምትገኘው ፓንሙንጆም መንደር ጎብኚዎችን በመቀላቀል በሕገ ወጥ መንገድ ነው።
ኪንግ ቀደም ብሎ ሁለት ሰዎችን በመሳደብ እና የፖሊስ መኪናን በመምታት ወንጀል በደቡብ ኮሪያ እስር ቤት ወደ ሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ ታስሮ ተለቅቋል ። በወቅቱ የአሜሪካ ባለሥልጣናት፣ በተደረገ “ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት” ከሁለት ወራት እስር በኋላ መለቀቁንና በደቡብ ኮሪያ ወደሚገኘው የአሜሪካ አየር ኃይል ሰፈር በአውሮፕላን መወሰዱን አስታውቀዋል። ከዚያም እአአ መስከረም 28 /2023 ወደ ቴክሳስ ተወስዷል ሲል የዘገባው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም