ዲፕሎማት እና የታሪክ ምሁሩ

ስለኢትዮጵያ ቀደምት ታሪኮች ሲጠቀስ የእኝህን ምሁር ስም መጥቀስ የተለመደ ነው። በብዙ የታሪክ ድርሳናት ውስጥ የእርሳቸው መጻሕፍት ምንጭ ተደርገው ይጠቀሳሉ። ‹‹ከንግሥት ሳባ እስከ ዓድዋ›› ከሚለው መጽሐፋቸው ጀምሮ የኢትዮጵያን የጥንት፣ የመካከለኛው ዘመን እና ዘመናዊ ታሪኮችን አስተዋውቀዋል። ‹‹ወዳጄ ልቤ›› በሚለው መጽሐፋቸው በብዙዎች ዘንድ ይታወቃሉ።

በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ አምዳችን ከ86 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም 9 ቀን 1931 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴን እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት ግን እንደተለመደው በዚህ ሳምንት የተከናወኑ ሌሎች ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ የታሪክ ክስተቶችን እናስታውስ።

ከ129 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም የዓድዋ ጦርነት የክተት ዘመቻ አዋጅ ታወጀ። ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የውጫሌን ውል እንደማይቀበሉና ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ከወራሪ ጠላት እንዲከላከሉ የሚያሳስብ ታሪካዊ አዋጅ ተናገሩ። መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም የታወጀው አዋጅ የሚከተለው ነበር።

‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ ሀገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፤ እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም፤ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። አሁን ግን ሀገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚያስለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፤ እኔም ያገሬን ከብት ማለቅና የሰውን መድከም ዐይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት ሀገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፤ ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ! ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለሚስትህና ለሃይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ! ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ! አልተውህም! ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም! ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ!››

ከ46 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም 7 ቀን 1971 ዓ.ም የግብጽ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሜናኽም ቤጊን በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ሸምጋይነት፤ ከ12 ቀናት የምሥጢር ድርድር በኋላ፤ ‹‹የካምፕ ዴቪድ ስምምነት››ን ተፈራረሙ። ‹‹የካምፕ ዴቪድ ስምምነት›› የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካን የለወጠ ክስተት ነበር። የአረቡ ዓለም መሪ ተደርጋ ትቆጠር የነበረችው ግብጽ ስምምነቱን መፈረሟ በከሃዲነት አስፈርጇት ለ10 ዓመታት ከአረብ ሊግ አባልነት ታገደች። ከዚህ በተጨማሪም ስምምነቱ፣ የስምምነቱ ፈራሚ የሆኑት ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት እንዲገደሉ ምክንያት ሆነ።

አሁን በዝርዝር ወደምናየው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ታሪክ እንመለስ።

ገና በሕፃንነታቸው ያሳዩት የትምህርት ፍላጎት፤ የነበራቸው የአዕምሮ ብሩህነት ሊቃውንት መምህሮቻቸውን አስደንቆ ከመምህሮቻቸው የተሰጡትን ስማቸውን እንዲሸልሟቸው ያስደረጉ የቀለም ቀንድ ናቸው። በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከነበሩት የወቅቱ የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ምሁራን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ተመስክሮላቸዋል። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ።

ኅሩይ የተወለደው በ1871 ዓ.ም ሸዋ፣ መርሐ ቤቴ አውራጃ፣ በታች ቤት ወረዳ፣ ረመሸት ቀበሌ፣ ደን አቦ ገዳም በተባለ ሥፍራ ነው። ወላጆቹ ያወጡለት ስም ገብረመስቀል ነበር። ገብረ መስቀል እንጦጦ ራጉኤል ደብር መጥቶ የመጻሕፍትን ትርጓሜ ከደብሩ ሊቃውንት በሚማርበት ወቅት ወልደጊዮርጊስ የተባሉት መምህሩ ‹‹ጎንደር በነበርኩ ጊዜ መምህሬ ስለሚወዱኝ ‹ኅሩይ› እያሉ ይጠሩኝ ነበር። ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ግን በዚህ ስም እየተጠራሁኝ አይደለም። አንተ የቀለም ቀንድ ስለሆንክና በምግባርህም የተወደድክ ስለሆንክ ‹ኅሩይ› የተባለውን ስሜን ትጠራበት ዘንድ ሸልሜሃለሁ›› አሉት፤ እርሱም ስሙን በደስታ ተቀበለ።

አባቱ ትምህርት ባለመማራቸው ምክንያት ስድብ ደርሶባቸው ያውቅ ነበርና በእርሳቸው የደረሰው በልጃቸው ላይ እንዳይደርስ ሲሉ ኅሩይን ከልጀነቱ ጀምሮ ትምህርት ላይ እንዲያተኩር አደረጉ። ኅሩይም በተወለደበትና በሌሎች ቦታዎችም በመዘዋወር የንባብ፣ የዜማና የድጓ ትምህርቶችን ከዘመኑ ሊቃውንት ተምሯል።

ኅሩይ በእንጦጦ ራጉኤል ደብር የመጽሐፍ ትርጓሜን በሚገባ ተምሮ አጠናቋል። በቀሰመው ትምህርትም በአስተርጓሚነት አገልግሏል። በባሕላዊው ትምህርት የተሟላ እርካታ ማግኘት ያልቻለው ኅሩይ፣ አዲስ አበባ ስዊድን ሚሽን ትምህርት ቤት ገብቶ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተምሯል። ከእንግሊዝኛ ቋንቋ በተጨማሪ አረብኛ ቋንቋ ለመማር ጥረት ቢያደርግም ‹‹ኅሩይ ሰለመ›› የሚል አሉባልታ ስለሰማ ለጊዜው ትምህርቱን ለማቆም ተገዷል። በኋላም ከፈረንሳያውያን ሐኪሞች ፈረንሳይኛ ቋንቋን መማር ችሏል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰነድ ላይ ሰፍሮ እንደሚገኘው፤ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ከ1910 እስከ 1914 ዓ.ም ድረስ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው አገልግለዋል። ከንቲባ ከመሆናቸው አስቀድሞ የከተማዋ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሰርተዋል። በከንቲባነት የአገልግሎት ዘመናቸውም ቀደም ሲል በተለያዩ የአስተዳደር ስያሜዎች ይጠራ የነበረውን የከተማውን አስተዳደር ‹‹ማዘጋጃ ቤት›› ብለው በመሰየም እስካሁን ድረስ የዘለቀ ቋሚ ስያሜ ሰጥተውታል። ብላቴን ጌታ ኅሩይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደራዊ መዋቅር መልክ እንዲይዝ እንዲሁም በከተማዋ የመሰረተ ልማት ተግባራት እንዲከናወኑ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል።

በዓለም መንግሥታት ማህበር የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መልዕክተኛ ቡድን አባል ነበሩ፤ አልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን የልዑክ ቡድናቸውን እየመሩ በአውሮፓ ጉብኝት ሲያደርጉ ብላቴን ጌታ ኅሩይም የቡድኑ አባል ሆነው የአውሮፓን ከተሞች ጎብኝተዋል። ይህም የአውሮፓውያንን ባሕል እንዲመለከቱና የወቅቱን የአውሮፓን ስልጣኔና አጠቃላይ ሁኔታም እንዲታዘቡ እድል ፈጥሮላቸዋል።

የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ብላቴን ጌታ ኅሩይ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ። ለአጭር ጊዜ ቢሆንም ብላቴን ጌታ ኅሩይ በጃፓን የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት አምባሳደር ሆነው ሰርተዋል። በጃፓን የነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያም በቴክኖሎጂ ታግዛ እንደጃፓን ጠንካራና ዘመናዊ እንድትሆን የሚያነሳሳ ምኞት ፈጥሮባቸው ነበር።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ‹‹ኢትዮጵያንና ጃፓንን ብዙ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ፤ ስለሆነም ኢትዮጵያ ለዘመናዊነት የጃፓንን አርዓያ ብትከተል ጥሩ ውጤት ታገኝበታለች›› ብለው ከሚያምኑትና ‹‹ጃፓናይዘርስ/ Japanisers›› ተብለው ከሚታወቁት የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ኢትዮጵያውያን ተፅዕኖ ፈጣሪ ምሁራን መካከል አንዱ ነበሩ። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ኢትዮጵያና ጃፓን ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ዘውዳዊ የአስተዳደር ሥርዓት ባለቤት እንዲሁም የምዕራባውያንን ተፅዕኖ ተቋቁመው የኖሩ በመሆናቸው አንዳቸው ለሌላቸው አርዓያ የሚሆኑባቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ በጽኑ ያምኑ ነበር። ይህን እሳቤያቸውንም ‹‹ማኅደረ ብርሃን ሐገረ ጃፓን›› በተሰኘው ስራቸው በዝርዝር አብራርተውታል።

ከማይጨው ጦርነት በኋላ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የዲፕሎማሲ ትግል ለማድረግ ወደ ውጭ በተሰደዱበት ወቅት ብላቴን ጌታ ኅሩይም ከኢትዮጵያ ወጡ። ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ፋሺስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ስለፈጸመችው የግፍ ወረራ ጄኔቫ ላይ ለዓለም መንግሥታት ማህበር ሲያስረዱ ኅሩይ ከጎናቸው ነበሩ።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ከመንግሥታዊ ኃላፊነቶቻቸው ባሻገር በደራሲነታቸውም ይታወቃሉ። በርካታ የታሪክ፣ የጉዞ ማስታወሻ፣ የሃይማኖት፣ የልብወለድ፣ የግጥምና የጠቅላላ ዕውቀትን ጨምሮ ከ16 በላይ መጽሐፍትን አበርክተዋል። ከሥራዎቻቸው መካከል ‹‹ወዳጄ ልቤ›› የሚባለው መጽሐፍ በብዙዎች ዘንድ ታዋቂነትንና ተወዳጅነትን አትርፎላቸዋል።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ እንግሊዝን፣ አሜሪካን፣ ቻይናን፣ ፈረንሳይን፣ ኢጣሊያን፣ ግብጽንና ሌሎች ሀገራትን ጎብኝተዋል። የሀገራቸውን ወደኋላ መቅረት ከአውሮፓውያኑ ዘመናዊነት አንፃር ባስተዋሉ ቁጥር ቁጭታቸውን ባገኙት አጋጣሚ ይገልጹ ነበር። በአንድ አጋጣሚ ኢጣሊያን ሲጎበኙ በኢንዱስትሪው አማካኝነት የሚከናወነውን ድንቅ ሥራ ተመልክተው በመደነቅ ተከታዩን ሃሳብ አስፍረው ነበር።

‹‹ለሀገራችን ለኢትዮጵያ የልብስና የእርሻ መኪና የግድ ያስፈልጋል። ኑሯችን ሁሉ ሸማ ለብሰን ነው እንጂ እንደ አውሮፓዎች የበግ ጠጉርና ሐር ዘወትር አንለብስምና ሀገራችን ጥጥ ለማብቀል የተመቸ ነውና ስለዚህ የሸማ መኪና ያስፈልገናል። ምግባችንም እህል ነው እንጂ እንደ አውሮፓዎች ሥጋና ዓሣ አትክልት ሁልጊዜ አናገኝምና ሀገራችንም አሳምሮ እህል ያበቅላልና ስለዚህ የእርሻ መኪና ያስፈልገናል። ይህንንም አስቀድሞ መንግሥት ገዝቶ ፋብሪካውን ቢያቆም መኳንንቱና ያገር ባለፀጎች ሁሉ እንደ ኩባንያ ገንዘብ እያዋጡ አንድ አንድ መኪና እየገዙ ፋብሪካ ያቆሙ ነበር። ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ያገኙበት ነበር ››

በሌላ በኩል ብላቴን ጌታ ኅሩይ ዓለማዊ ችግርን ለመፍታት ዕጣፋንታ ላይ ተስፋ ማድረግ እንደማይገባና ፈጣሪም የሰጠንን ጸጋ የገጠሙንን ችግሮች ለመፍታት ማዋል ሲሳነን እንደሆነ በሚከተለው መልኩ ገልጸዋል።

‹‹እግዚአብሔር ይጠብቀኛል ብሎ ቤት ሳይሠሩ፣ አጥር ሳያጥሩ፣ እህል ሳይዘሩ መንደር ለመንደር ሲዞሩ ቢሞቱ እግዚአብሔርን መፈታተን ነው። ንጉሥም እግዚአብሔር ይጠብቀኛል ብሎ ጋሻ ጦሩን፣ ሰይፉን፣ መድፉንና ጠመንጃውን ሳያዘጋጅ ቢቀመጥ ድንገት ጠላት መጥቶ እርሱን ገድሎ መንግሥቱን ቢወስድበት እግዚአብሔርን መፈታተን ነው። ጉልበታችሁን ተማምናችሁ እግዚአብሔርን አትርሱ››

ለንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የቅርብ አማካሪ በመሆን የሃይማኖትና የአስተዳደር ሕግጋትን እየተረጎሙና የአርትኦት ሥራዎቻቸውን እያጠናቀቁ እንዲወጡ ያደረጉት ታላቁ ዲፕሎማትና ደራሲ ብላቴን ጌታ ኀሩይ ወልደሥላሴ እንግሊዝ ውስጥ በስደት ላይ ሳሉ፣ መስከረም ዘጠኝ ቀን 1931 ዓ.ም አርፈው ሥርዓተ ቀብራቸው በዚያው እንዲፈፀም ተደረገ። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያውያን ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ምድር ከተባረረ በኋላም በ1940 ዓ.ም አስክሬናቸው ካረፈበት ቦታ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በመንበረ ፀባኦት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል እንዲያርፍ በክብር ተድርጓል። በስደት ላይ የነበሩት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ እንግሊዝ በነበረው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ሥርዓተ ቀብር ላይ የሚከተለውን ንግግር አድርገው ነበር።

‹‹አሁን የአዳምን ልጆች ወግ ሲቀበል የምታዩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በሀገራችን ሥርዓት በመልካም አያያዝ ያደገ ከኢትዮጵያም ከፍ ካሉት ሊቃውንት የሚቆጠር ነው። ብልሃቱንና ትጋቱንም ለመልካም ሥራ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ስላደረጋቸው በመንግሥታችን ሥራ ለመመረጥና ወደ ታላቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለመድረስ በቃ። በየጊዜው የጻፋቸው ከፍተኛ ባህሪውን የሚገልጹ መጻሕፍት፤ ይልቁንም በቤተ-ክህነትና በታሪክ እውቀት በዓለም ሊቃውንት ዘንድ የታወቀና የተከበረ አደረጉት። ለምታውቁት ሰው ከታሪኩ ከዚህ የበለጠ ልነግራችሁ የሚያስፈለግ አልመሰለኝም። በአጭሩ ከጠባዩ ትልቅነት የሚሰማኝን ለመናገር ሳስብ ጊዜውን ሁሉ ቁም ነገር በመሥራት ማሳለፉ፤ ከራሱ ይልቅ የተቸገሩትን ለመርዳት መጣሩ፤ እውነትን፣ ፍርድንም ማክበሩና በሀገር ፍቅር መቃጠሉ ትዝ ይሉኛል።

አገልጋዬና ወዳጄ ኅሩይ! በተቻለህ ስለሀገርህ ሥራህን በሚገባ ፈጽመህ በምትሰናበትበት ጊዜ ታላቅ ነህ ሳልልህ ብቀር ሥራዎችህ ቀድመውኝ ይናገራሉ። በክፉ አድራጊዎች የሚገፋ የዓለምን ፀጥታ የሚያናውጥ ነፋስ ምንም ቢያንገላታህና በታላቅ ፈተና ላይ ቢጥልህም ሊያሸንፍ አልቻለም። ታላቅና ቸር በሆነው ጌታ በተመደበው ሕግ ግን መታዘዝ ግድ ሆነብህ። ይህም ለእያንዳንዳችን የሚደርሰን ዕድል ነው። አንተም እስከ መጨረሻ ከታገልክ በኋላ ዛሬ ደከመህ፣ አንቀላፋህም። በሥጋ ብትለየንም ስምህና ሥራህ በመካከላችን ይኖራሉ።

ኅሩይ፣ እግዚአብሔር ሲያስበን አጥንቶችህና መንፈስህ የሚሰፍሩበትን ቦታ እስኪያዩና ከአባቶችህ እስኪቀላቀሉ ድረስ በእንግድነት በመጣህበት በዚህ ሥፍራ በሰላም ዕረፍ።»

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ከወይዘሮ ሐመረ እሸቴ ጋር ጋብቻ መስርተው ስድስት ልጆችን አፍርተዋል፤ ብዙ የልጅ ልጆችንም ለማየት በቅተዋል። የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ጋር በመተባበር ጳጉሜን ሁለት ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ የአራት ቀደምት ደራሲያንን ምስል የያዙ ቴምብሮች አስመርቆ ገበያ ላይ ሲያውል ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ምስላቸው በቴምብር ላይ ከታተሙላቸው ደራሲያን መካከል አንዱ ነበሩ። ጉለሌ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚም ያስገነባውን የስነ ጥበባት ማዕከል በስማቸው እንዲጠራ አድርጓል። የሕይወት ታሪካቸው ‹‹የብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደ ሥላሴ ታሪክ 1871 – 1931 ዓ.ም›› በሚል ርዕስ በኤመሪተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተዘጋጅቶ ታትሟል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You