ያልተወሳው የጥበብ ሰው

“በሉ እንጂ በሉ እንጂ…”ን ላቀነቀነችው አበበች ደራራ፤ ምን እንበል? ብለን ብንጠይቅ በወደድን ነበር። ነገር ግን ለማለቱ ቃላቶቹ ያጥሩናል። እንዲህ ላስባላት ድንቅ ሰው ግን በቃላቱ እጥረት መካከልም እያሳሳብንም ቢሆን ላልተወሳው እናውሳለት። ሠርቶ ሠርቶ ያልተወሳው አሳዬ ዘገየ…ጥላሁን ገሠሠ በህይወት ኖሮ እስቲ ጥቂት በልለት ቢሉት፤ ከአበበች ደራራ ጆሮ ጠጋ ብለው እንዲያው ስለ እርሱ ቢጠይቋት፣ ማርታ ሀይሉንም ቢሆን ቀርበው አሳዬን በመልካም እንማው ያሏት እንደሆን… ሁሉም እንዴት ባሉ ወለላ ቃላት እያሽሞነሞኑ እንደ ማር ከአንደበታቸው ጠብ! ጠብ! እያደረጉ ባጣፈጡለት ነበር።

ማርን የሚሰጠው አበባዋን የቀሰመ ንብ ነውና ከእርሱ ጥበብ ውብ የሆነውን ያገኙ ሁሉ ስለ እሱ አጣፍጠው መናገራቸው የማይቀር ነበር። በሀገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ አይጠበቡ ተጠበው ጥዑም የሙዚቃ እንኮይ ካረገፉልን የሙዚቃ ግጥምና ዜማ ደራሲያን አንደኛውና ከግንባር ከተሰለፉት መካከል አሳዬ ዘገየ አለበት። ከ47 ዓመታት በላይ በሙዚቃ ዓለም ውስጥ ሰንብቶ ዛሬም አልተለየም። በቁጥር ከሰፈሩት 3 መቶ ያህል የግጥምና ዜማ ሥራዎችን አድሏል።

ነገሩ መች ግጥምና ዜማ ብቻ ሆነና ብዙዎች ጆሯቸውን ቀጥ አድርገው እስኪያቆሙለት ድረስ በክራርና በኪቦርድ አጨዋወቱ ሸክፎ ይዟቸዋል። ወንበር ስቦ ከኪቦርዱ ላይ ያሉትን ባለ ነጫጭና ጥቋቁር ቁልፎችን መነካካት ሲጀምር ገና ጆሮ እንደቆመ ልብ ያስፈንድቃል። የክራሩ ጅማቶች ለመናዘር ግርፉን የሚጠብቁ እንኳን አይመስሉም። የክብሪት እሳት እንዳገኘው ሰንደል እየጨሱ ቡልል! ማለት ብቻ።

አሳዬ ዘገየን ያበቀለች የጎጃሟ የወርቅ አፈር ግሽ ዓባይ ናት። በተንጣለለው የጣና ሀይቅ፣ በሚያረሰርሰው የዓባይ ወንዝ ለምልሞ ያሸተውን የጥበብ አዝመራ እያሸና እየጠረጠረ የበላባት መነሻ ሀረጉ ናት። ከጎጃም ምድር አልፎ በመላው ሀገሪቱ የኪነጥ ጥበብ በተለይም ደግሞ የሙዚቃ ደጀን የሆኑትን ሲያመርት የነበረውን “የጎጃም ግሽ ዓባይ የባህል ኪነት” ቡድንን አቋቁመው ለወግ ማዕረግ ካደረሱት አባላት መካከል አሳዬ ግንባር ቀደሙ ነው። ኪነትን ቡድኑን ከመሠረቱት በኋላ በጎጃም ክፍለ ሀገር ከነበሩት ሰባት የኪነት ቡድኖች ጋር ተፎካካሪ በማድረግ በየዓመቱ ሲያካሂዱት በነበረው ውድድር ላይ ጎልቶ እንዲታይ አድርገውታል። የግሽ ዓባይ ፍሬ የሆነው አሳዬም ኋላ በ1970ዎቹ አጋማሽ ላይ ውድድሩን በዳኝነት ሲመራ ነበር።

በትውልድ ቀዬው ውስጥ ሆኖ ድንቅ ችሎታውን እያጎመራ በየመድረኮቹ ላይ ከልብ ከሚጨበጨብላቸው አንዱ ሆነ። ከዚያ እየቀጠለ ግን በመሀል ሾልኮ ውስጣዊ የሙዚቃ ጓዙን በመሸከፍ አዲስ አበባ ገባ። ብዙዎች ዛሬ ላይ ሆነው የትናንቱን አሳዬን ሲያስታውሱ በምናባዊ ምስል ድቅን ከሚልባቸው ስፍራዎች አንዱ ከሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ጀርባ የነበረው “ግራር” የምሽት ክበብ ነው። ጸሐይ ጠልቃ ጀንበር ስታዘቀዝቅ ወደዚህ ቤት የሚገሰግሰው ኮቴ ብዙ ነው። ሲሮጥ የመጣ ተጋፍቶ ቦታ ይዞ ከሚጠባበቃቸው ነገሮች አንዱ አሳዬ ከነሙዚቃ መሳሪያው መድረክ በድምጽ እያዜመ ሲጫወት መመልከት ነው። ጸጉሩን አጎፍሮ፣ በቄንጥ አለባበሱ ሽክ ብሎ ቦግ እልም እያለ ከሚያሸበርቀው የመድረክ መብራት ፊት ሲቆም ብቻውን ደስ የሚያሰኝ ነገር አለው። የሙዚቃ መሳሪያውን በአንገቱ እንዳነገተ ገረፍ! ገረፍ! እያደረገ ጭንቅላቱን ወዝወዝ፣ ወገቡን እንቅጥቅጥ! እግሮቹን ፍትግትግ! ሽክርር! ሲያደርጋቸው ከአለባበሱ ጋር የተመለከተው፤ ቁርጥ ማይክል ጃክሰንን ይሉታል።

ድምጹም ቢሆን ጣዕሙ የከረሜላ ነው። በድምጽ እያቀነቀነ የሙዚቃ መሳሪያዎቹን ራሱ ሲጫወታቸው መመልከት፤ አንድ ሰው ሳይሆን ለብቻው አንድ ሙሉ ባንድ ነው ያስብላል። ጥፍጥ ብሎ ከሚደመጠው ክራሩ ጀምሮ ከባህላዊ ቢሉ ከዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ጋር ያለው ቁርኝት የሚለይ ነው። እኔ ባለክራር አሊያም ኪቦርዲስት ነኝ ብሎ ራሱን ከየትኛው ጋር አይገድበውም። ምን ይሁን ምን ከተመለከተው የሙዚቃ መሳሪያ ሁሉ ጠጋ ብሎ በፍቅር ማውጋቱን አይተውም። መሀላቸው ቆሞ በመሀላ ያስተሳሰራቸው ማንና እንዴት እንደሆነ ራሱም በውል ባያውቀውም ከመሳሪያዎቹ ጋር ያለው የማይፈርስ ግንኙነት ግን አስደናቂ ነው። የሚፈልጋቸውን ያህል ፈልገው፣ የሚወዳቸውን ያህል የሚወዱት መሆኑ አይጠረጠርም። የያዛት ማሲንቆ ማጫወቻዋን ጠጋ አድርጎ ሊገዘግዛት ባለ ቅጽበት ፀሐይን የሚያስንቅ የፈገግታ ጥርሷን ወከክ አድርጋ ትስቅለታለች። አርሞኒካዋማ እንደ ጉብል ልጃገረድ ስትሽኮረመም ከእርሱ አልፎ አጠገብ ያለውን ልብ ሁሉ ታቀልጣለች። አኮርዲዮኑ ከሰውነቱ ደገፍ ሲል ገና በግርማ ሞገስ ከሚንቆረቆረው ድምጽ ሰፈፍ! እያለ ለጆሮ ምቾትን ለልብ እርካታን ያወርዳል። ሲደባብሳቸው እየቦረቁ ከሪትሙ ጋር አብረው ከአምባሰል እስከ ባቲ የሚነጥሩት ነጫጮቹና ጥቋቁር ሻርፖቹ የኪቦርድ ቁልፎች በስምንቱም ኦክታቮች ሽብሻቦ ይጀምራሉ። የዋሽንቱ ዜማም እንኳን ሰው አዕዋፋትን ከሰማይ የሚጠራ ነው። ከሁሉም በላይ ግን፤ በነካካት ቁጥር አጸፋዊ የስሜት ንዝረት የምታከታትለዋ ክራሩ…ጅማቷ ከደም ስሩ ላይ የተመዘዘች እስክትመስል ራሱም በስሜት ይነሆልልባታል። ሲቀርቡትና ሲቀርባቸው ሁሌም እንደዚህ ነው።

ታላቁ ሰው ከታላላቆቹ ማጀት ውስጥ አሰናድቶ የሰጣቸው እጅግ በርካቶች ናቸው። ከእነዚህም መካከል ጥቂቱን ጠቃቅሰን ስናልፍ የምናገኘው አንድም የክብር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠን ነው። ከጊዜያት በአንደኛው ጊዜ፤ አሳዬ አንድ ግጥምና ዜማ ሠራ። መቼም ደስ ይለዋል ሲል በልቡ እየተፍነከነከ ይዞት ወደ ጥላሁን ገሠሠ ገሰገሰ። ከጥላሁን ዘንድ እንደደረሰም የሠራለትን ሙዚቃ በኩራት አቀረበለት። ጥላሁን ሙዚቃውን አደመጠውና “አይ…” አለ። አልመስልህ ስላለው ይቅርብኝ ሲል ግጥምና ዜማውን መለሰው። ለአሳዬ ያልጠበቀው ምላሽ ነበር። ፊቱን መልሶም ወደ ተሾመ ወልዴ በማቅናት የሠራውን ሥራ አስደመጠው። ተሾመ ግን ሙዚቃው ደስ የሚል ስሜት ስለሰጠው ሊሠራው ቆርጦ ተነሳ። ሙዚቃውም እንዲህ የሚለው ነበር…

“መጀመሪያ ማወቅ መተዋወቅ

ቀስ ብሎ በፍቅር መሳሳቅ

ሲይዝ አይታወቅ ልብ ሲሰርቅ

እንዲህ ያደርጋል ፍቅር ወይ ፍቅር”

በዚህ ሙዚቃ የጥላሁን ገሠሠ ፍራቻ እንዳሰበው ሳይሆን ቀርቶ የተሾመ ቤት መታ። ከተሠራ በኋላ ምን ተወደደ ብቻ አይሉት፤ ገጠር ከተማውን ከጫፍ ጫፍ አዳርሷል ፈንደቅደቅ ተባለበት። ይህን ጊዜ ጥላሁን ምን እንደተሰማው ባይሰማም አሳዬ ለጥላሁን ገሠሠ የሰጠውን “ጉብል” የተሰኘውን ሌላኛውን ሙዚቃ ግን ከድምጸ ስርቅርቁ አንደበት ሰምተነዋል። ተሾመ ግን ከአጃቢ መካከል ከነበሩት ከበዛወርቅ አስፋውና ብፅአት ጋር ደመቅመቅ ብሎ ታየበት። በርከት ያሉ ጣዕመ ዜማዎች ባለቤት የሆነው ተሾመ ወልዴ በዚህኛው ግን ከመታወቁም በላይ የዝናን እርካብ የረገጠበት ነበር። ያልተወሳውን ሰው የሚያወሳው ድንቅ የሙዚቃ አልበም ከድምጻዊቷ ማርታ ሀይሉ ጋር ይተሳሰራል።

“ከረሜላዬ”ንና አዲስ አበባ ሆና የአስመራውን ሸጋ የምትናፍቅበት “ሀብ አስመራ”ን አካቶ በወጣው የማርታ ሀይሉ የመጀመሪያ አልበም ውስጥ አስሩንም ሙዚቃዎች ጥንቅቅ አድርጎ የቀመመላት አሳዬ ዘገየ ነው። ሙዚቃን በጆሮ ብቻ ሳይሆን በልብም ጭምር የሚያደምጡ የሙዚቃ አፍቃሪያን ሙሉ አልበሙን ከአንጀታቸው ይወዱታል። “ሸበል ዓለም”፣ “ብራ ነው ብራ ነው” በማለት “ና ጋሜ” ሲሉ “ርሀቤን ጥማቴን” በእርካታ ለወጡት የሚያሰኙ ናቸው። ሌላኛው የአበበች ደራራ “በሉ እንጂ” ደግሞ ለአሳዬ በሉለት እንጂ እያለ አስቁሞ የሚያስጨበጭብለት ሥራ ነው። ከዕለታት በአንዱ ቀን ላይ አሳዬና ወዳጆቹ ብርጭቆ ጨብጠው ሲዝናኑ ነበር… በጣቶቹ አንቆ ጎንጨት ሊያደርግባት ወደ አፉ ካስጠጋት ብርጭቆ ውስጥ “በሉ እንጂ በሉ እንጂ” እያለ ሽብልቅልቅ! ከሚለው ጥልቅ ባህር ውስጥ ብቅ ጥልቅ የምትል አንዲት አሳ የተመለከተ መሰለው። ድንገት ከምናቡ ላይ ቅጭል! ያለችውን የዜማ አሳ ሳትሰምጥበት በፊት ቶሎ ብሎ በመንጠቆው ደጋገማት። ያጠመዳትን ዘሜ እየተከተለም እዚያው ቁጭ ብሎ ግጥሟንም ይጽፋት ጀመረ። አብረውት ላሉት ሲያሰማቸው እጅግ ጥፍጥ ያለ ጅምር እንጎቻ ነበር። አጣፍጦ ያዘጋጃትን የአሳ ጥብስ በእንጎቻዋ ጠቅልሎ የሚያጎርሰውን ድምጻዊ ፍለጋ ወጣ። ከሃሳቡ የመጣችለት ጸሀይ እንዳለ ነበረች። በቀጥታ ወደ ብሔራዊ ቲያትር አቀና።

ሙዚቃውን ሊሰጣት በተዘጋጀበት ሰዓት ግን ተወዛዋዡ የነበረችው ፋንትሽ በቀለ ስትናጎራጉረው ድንገት ሰማት። የሰማው ድምጽ ለጸሀይ የመስጠቱን ሃሳብ አስለወጠው። “በቃ አንቺ ነሽ የምትዘፍኚው” አላት። ፋንትሽ ከዚህ ቀደም መወዛወዙን እንጂ ድምጻዊነቱን ሞክራውም ስለማታውቅ “እንዴት ብሎ ማን ይፈቅድልኛል…” ስትል ፍላጎቷ ውስጥ ጥርጣሬ ገባ። ሙዚቃውን የሠራሁት እኔ ነኝና ወስኛለሁ ሲል ቁርጥ አድርጎ ነገራት። ፋንትሽም ለመጀመሪያ ጊዜዋ መድረክ ላይ ወጥታ “በሉ እንጂን” አቀነቀነች። ግሩም አድርጋ በማቅረብ ሙዚቃውም እርሷም ከመወደዳቸውም የድምጻዊነትን ጎህ የቀደደላት ሥራ ነበር። በመድረኩ የኮራባት አሳዬም በሌላ ጊዜ ሌላ ሙዚቃ ሠራላት። በሉ እንጂንም ተቀብሎ ለአበበች ደራራ አልበም ካሰናዳቸው ሌሎች ሥራዎቹ ጋር ቀላቀለው። አበበች ደራራም በሉ እንጂን ሌላ ከፍታ ላይ አድርሳው ከስሟ ቀጥሎ መታወቂያዋ እስከመሆን ደረሰ። መታወቂያ በመሥራት አበበች ብቸኛው አይደለችም። ስዩም ዘውዴን ስናስበው ቀድሞ ብልጭ! የሚልልን “ጠጋ በይኝ ጠጋ”ን የተሸከመው ሳዱላዬ ነው። “ሰው አለኝ” የተሰኘው ለስለስ ያለ ነፋሻማ ሙዚቃም ከጣዕመ ዜማው ጋር ሀና ሸንቁጤን እንድንወዳት ያስገድደናል። ፋንትሽ በቀለ “አንተ ልጅ ወድጄህ ነው” ከምትለዋ ልብ አቅላጭ ሙዚቃ ጋር ያወጣችውን አልበም የሠሩት አሳዬና ንዋይ ደበበ ነበሩ። በዚህ አልበም ውስጥ ያዋጣው ከግማሽ በላይ የሆነ የጥበብ ድርሻ አለው። ሀመልማል አባተን ጨምሮ በወርቃማው ዘመን ነበሩ ከምንላቸው ጋር የአሳዬን ስም ማንሳት እንጀምረው ይሆናል እንጂ አንጨርሰውም።

አሳዬ በሀገር ውስጥ ዝነኝነቱ እየበረታበት፣ ከፍ ከፍ እያለ መብረር በጀመረበት ጊዜ ከሀገር የመውጣት ሃሳብ አቃጭሎበት መሹለኪያዋን ቀዳዳ ፍለጋ ወደ ጎረቤት ኬንያ ገባ። ጥቂት ከዚያ ከቆየ በኋላም የካናዳውን ነገር አመቻችቶ ለስደት እብስ አለ። ወደ ካናዳ የሚገባበትን መንገድና ጥበቡን ሲመክር ሲያስጠናው የነበረው ሰው ደግሞ አንጋፋው ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ ነበር። ዳሩ ለካናዳው ብቻም ሳይሆን በሙዚቃ ህይወቱም ብርሃን ከጨለማ ለይቶ በመልካም የሚጓዝበትን ስንቅ ያሰነቀው መሪውም ጭምር ነው። አሳዬ ካናዳ ደርሶ ከተቀበለው ሰውና ካረፈበት ቤት ውስጥ አንድ እውቅና መልህቅ የሆነ ዓለም አቀፍ አቀንቃኝ ወጥቶበታል። ያን ጊዜ የተቀበለው ሰው የዝነኛው አቤል ተስፋዬ( ዘ ዊኬንድ) አባት ሲሆን፤ ከአመት በላይ ከቤታቸው ኖሯል። አቤል ተስፋዬ ጊታሩን ይዞ የሙዚቃን ዱካና አሻራ ሲፈልግ ያን ጊዜ አሳዬ አጠገቡ ነበር። እጁን ይዞ በመምህርነት ባይገራውም ትንሹ አቤል አሳዬን እየተመለከተ የቀሳሰመው ዕውቀትና ጥበብ የለም ለማለት ግን አይቻልም።

ወደ ካናዳ ሲገባ ዘለግ ቢል ለዓመት እንጂ ከዚያ በላይ የመኖር እቅድ አልነበረውም። ነገር ግን እንደዋዛ 2 ዓመታት ሞሉት። አሁንም ነገ ዛሬ ሲል፣ ሲያስብ ሲያሰላስል ድንገት በትዳር ገመደ ተጠለፈ። እያለም ከካናዳ ወደ አሜሪካ ገባ። አሁንም ልቡ ሳይረግጥ ልጅ መጣ። የራሱንም ዘመናዊ የምሽት ቤት ከፈተ። ከዚያ በኋላ ግን ሥራ ያውጣህ ሲል የመምጣት ሃሳቡን ተወት አድርጎ ዲሲ ሙዚቃን ከዚያው አጥብቆ ያዘ። በአሜሪካን ዲሲ ከተማ ውስጥ “ደመራ” የተሰኘ ባንድ ውስጥ ከብዙ ታላላቅ ሙዚቀኞች ጋር አብረው መሥራት ጀመረ። ከአሰፉ ደባልቄ፣ አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ቴዲ ማክ እና ከሌሎችም ጋር በተለያዩ ጊዜያት አብሮ ሠርቷል። በዲሲ በነበረው ቆይታው ብቻ ከ150 በላይ ዝግጅቶች ላይ አሻራውን አኑሯል። በወቅቱ በዋናነት ያቀርቡ የነበረው ለነጮቹ በመሆኑ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በአሜሪካ ውስጥ እንዲታወቅ ቀላል የማይባል ሚና ተጫውቷል። በዚህ ላይ ደግሞ አሳዬ በየዝግጅቶች የኢትዮጵያን የባህል ሙዚቃዎች በተጫወተ ቁጥር የሚታየው ሙዚቃውን ከሚመስሉ የባህል አልባሳት ጋር ነው። ሙዚቃውን ብቻ ሳይሆን ባህልን በማስተዋወቅ ምስጉን ነው።

አሳዬ በሙዚቃ ህይወቱ ሙዚቃን ከመሥራት ጎን ለጎን የሚነገርለት ሁለት አዳዲስ ነገሮች አሉት። የመጀመሪያው በቆዳ ተወጥሮ ሲሠራ የነበረው የክራር ክር ወደ ዘመናዊ አውታር በመቀየር ከጊታር ድምጸት ጋር በመቀየጥ ልዩ የዜማ ጦማር ለማምጣት በተደረገ ፈጠራ ውስጥ ስሙ ይነሳል። ሁለተኛው ደግሞ መድረክ ላይ ነው። በመድረክ የሙዚቃ ዝግጅቶች ላይ ቀደም ሲል የሚታወቀውና የተለመደው አንድ ድምጻዊ መድረክ ከወጣ በኋላ አንዲት ሙዚቃ አቀንቅኖ መውረድ ነበር። አሳዬ ይህን ልምድ በመለወጥ አንድ ድምጻዊ የተዘጋጃቸውን ልዩ ልዩ ሙዚቃዎችን አከታትሎና ቀጣጥሎ መጫወት እንዲችል አደረገ። በተመሳሳይ የሪትም ምት የሚገኙ የተለያዩ ሙዚቃዎችን ቀላቅሎ መጫወቱ የበለጠ የማዝናናት አቅም ስላለው ተወደደ በዚያው ልማድ ሆኖ ቀጠለ። ብዙ ጊዜ እንደምንለው ሁሉ የኛ የጥበብ ተቀባዮች ሠሪን ያለማውሳት ልምድም እንደጦፈ ነው። በመጥፎ አባዜው ላይ የብዙ የጥበብ ሰዎች ከሀገር ወጥቶ፣ ከሕዝብ ርቆ መኖር ደግሞ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ነው። ከሀገር እንደወጣ ረዥም ዓመታትን ከዚያው ለከተመው አሳዬም እጣ ፈንታው ይሄው ሆኗል።

ያልታወሰውን የሙዚቃ ፈርጥ ስናስታውስ ብዙ የህይወትና የኑሮ ውጣውረዶች ላይ ሲያዳልጠው ሲንሸራተት፣ ሲወድቅ ሲነሳ ዛሬም ድረስ አለ። ልቡ ተሰብሮ በጣሙን የተጎዳበትን ጊዜ ብንጠይቀው ኖሮ 2012ዓ.ም እንደሚጠቅስልን እሙን ነው። የዛሬ አራት ዓመታት ገደማ እጅግ የሚሳሳለት የ22 ዓመት ወንድ ልጁ በድንገት ሞቶ ተገኘ። ድንገቴ የሞት አውሎ ንፋስ ልጁን የነጠቀበት አስከፊ ጊዜው ነበር። ህይወት መዝገቧ ተገልጦ አያልቅምና ግን አሁን ደህና ነው…በሙዚቃ ጉዞው 50 ዓመታትን ደፍኖ ልዩዋን የኢዮቤልዩ ኒሻን ለማጥለቅ የቀረው ሁለት ዓመታት ብቻ ናቸው። እንደገና ሌላ ትውስታ…

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You